ከፓርቲው ሀላፊነታቸው የለቀቁትም በህመም ሳይሆን የተሻለ ስራ ለመስራትና ጠንካራ ለውጥ ለማምጣት ከእኛ ይልቅ ወጣቶቹ ይሻላሉ በሚል እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ ምክትላቸው ለነበረው ወጣት ዳንኤል ተፈራ ስልጣናቸውን ሲያስረክቡ ከእሳቸው የበለጠ በመንቀሳቀስ የተሻለ ነገር እንደሚሰራ በማመን እንደሆነም ይናገራሉ - ዶ/ር ኃይሉ፡፡ የፓርቲው ሃላፊነታቸውን ቢለቁም በብሔራዊ ምክር ቤት አባልነታቸው እንደሚቀጥሉ የጠቆሙት ዶ/ር ኃይሉ፤ ከትግል የሚለየኝ ሞት ብቻ ነው ብለዋል፡፡
አንዳንድ ሠዎች ምን እየሠራችሁ ነው እያሉ ይጠይቁናል ያሉት ዶ/ር ሀይሉ፤ የትግሉ ባለቤት ህዝብ ስለሆነ እያንዳንዱ ሰው ምን እየሠራሁ ነው ብሎ እራሱን መጠየቅ አለበት - ብለዋል፡፡
ፓርቲዎች ሃላፊነታቸው ትግሉን ማጠናከርና ማስተባበር እንደሆነ በጠቆምም አሁንም በርካታ ለትግል የሚያነሳሱ ችግሮች ስላሉ ህዝቡ በሠላማዊ ትግል ውስጥ በመሳተፍ ለውጥ እንዲያመጣ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡