Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 29 December 2012 08:46

ከማይመጥነው ሰው ጋር የሚካኤል ማህበር ጠጣ፤ ተራውን ሳያጠጣ ሞተ!

Written by 
Rate this item
(0 votes)

(ቴኾን ሰብ ምኬር ሰጨም፤ ቴያሰጭም ወጣም ሞተም) የእነሞር ምሣሌያዊ አነጋገር
ቻይናዎች ሁሌም የሚተርቱት አንድ አፈ-ታሪክ አላቸው፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን ሱንግ በተባለ የቻይና ቀበሌ ውስጥ ይኖር የነበረ አንድ ገበሬ ሞፈር - ቀንበሩን ሰቅሎ፣ በሬዎቹን ፈትቶ፣ ማሳው ዳር ቁጭ ብሎ ብዙ ሰዓት ያሳልፋል፡፡ በአገሩ የታወቀው አንድ ፈላስፋ ደግሞ የዚህ ገበሬ ነገር ገርሞታል፡፡ ምክንያቱም በዚህ ማሳ አካባቢ ባለፈ ባገደመ ቁጥር ገበሬው እግሩን አጣምሮ እንደተቀመጠ ስለሚያየው ነው፡፡
አንድ ጠዋት ያ ገበሬ እማሳው ዳር እንደተቀመጠ ያ ፈላስፋ ይመጣና፤
“አቶ ገበሬ ደህና አድረሃል?” ይልና የእግዜር ሰላምታ ያቀርባል፡፡

“ደህና እግዚሃር ይመስገን፡፡ አንተስ ደህና አድረሃል አያ ፈላስፋ፡፡” 
“እኔ ደህና አድሬአለሁ፡፡ ሆኖም ያንተ ነገር ለተወሰነ ሰዓት ሲያሳስበኝ እንቅልፍ አጥቼ ነበር”
“የእኔ ነገር ምኑ አሳሰበህ?”
“ሰሞኑን ሳይህ ሥራ ፈትተህ፣ እግርህንም እጅህንም አጣምረህ ትቀመጣለህ፡፡ እንደወትሮው በሬዎችህን ጠምደህ ባለማየቴ ምን ቸግሮት ይሆን? ብዬ ተጨንቄ ነው”
“ምንም ችግር ገጥሞኝ አይደለም፡፡ እንዲያው ቀላል የመኖሪያ ዘዴ አግኝቼ ነው፡፡”
“ምን ዓይነት ዘዴ አገኘህ?”
“ታሪኩን ባጭሩ ልንገርህ፡፡
አንድ ቀን እኔ እርሻዬን እያቀላጠፍኩ ሳለሁ፤ አንድ ጥንቸል ስትሮጥ ትመጣለች፡፡ እንደምታየው በማሳዬ መካከል ያ ግንድ አለ፡፡ ጥንቸሏ ተክለፍልፋ መጥታ ከዚያ ከግንድ ጋር ትጋጫለች፡፡ አንገቷ ተቀጭቶ፣ እግሩዋ ተሰብሮ እዚያው ክልትው ብላ ቀረች፡፡ ሞፈር ቀንበሬን ፈትቼ አነሳኋትና ጠብሼ እስክጠግብ በላኋት፡፡ ለቤተሰቤም አበላሁ፡፡ ለካ ይሄም አለ አልኩና ከዚያን ጊዜ ወዲህ እዚህ ቁጭ ብዬ ዛፍ ዛፉን አያለሁ፡፡ ምክንያቱም አንድ ዓመት ሙሉ የእርሻ ሰብል ከመጠበቅ ሌላ ጥንቸል መጥታ እስክትጋጭልኝ መጠበቄ የተሻለ ሆኖ አግኝቼዋለሁ!” አለው፡፡
ፈላስፋውም፤
“ገበሬ ሆይ! ሞኝነትህ ልክ የለውም፡፡ ከእንግዲህ ለቻይና ህዝብ የሞኝነት ምሳሌ የምትሆን አንተ ነህ፡፡ አንድ የቻይና መሪ በአለፉት ነገሥታት የአገዛዝ ስልት የዛሬውን የቻይና ህዝብ ልምራ ቢል እንዳንተ ቁጭ ብሎ ዛፉን ሲመለከት ዋለ ማለት ነው!!” ብሎት ሄደ፡፡
***
ብልህ የጥንቶቹንም ለመከተል አይፈልግም፤ ዘልዓለማዊ ነው የሚባል ደረጃ ለመመደብም ሆነ ለማስቀመጥ አይሻም፡፡ ይልቁንም የራሱን ዘመን መርምሮ ለዚያ የሚያዋጣውን ዘዴ ይዘይዳል፡፡
“የብልህ አመራር ማለት ገዢው የሱ ሰዎች ልክ እሱ ያዘዘውን ያሰቡ እንዲመስላቸው ማድረግ ነው፤” ትላለች የሩሲያዋ ታላቋ ካቴሪን፡፡ ቀጥላም “ይሄን ለማድረግም፤ አንድ እርምጃ ከህዝቡ ፍላጐት መቅደምና ከአልቀበል - ባይነቱ (Resistance) ጋር መላመድ ነው” ትለናለች፡፡ ልብ ያለው ልብ ይበል!
ራመድ ብለን የንግሥቲቱን አካሄድ ስንመረምር ለውጥን ያለጉልበት በዘዴ እንዴት ለማምጣት እችላለሁ? የማለት፤ ጥበባዊ ፍላጐትን የመቀዳጀት ጥያቄን ይሰርጽብናል፡፡ የኛ ዕቅድ፣ መርህ፣ ስትራቴጂ ወዘተ. ከሰማይ በወረደ ኃይልም አይታጠፍም፣ አይቀየርም፣ የምንለውን፤ በልባምነት አውጠንጥነን እንድናይ የሚያግዘን አስተውሎት ነው፡፡
ተቃዋሚዎቻችንን ወይም በግልባጩ ገዢዎችን የምናይበትን ሁኔታ በሁለት ታዋቂ የሰንጠረዥ ጨዋታዎች ምሳሌነት ለማፀኸየት እንሞክር፡፡ አንደኛው፤ ቼዝ ነው፡፡ ሁለተኛው፤ ጐ የሚባለው ጨዋታ ነው (“Chess” and “Go”)፡፡ Go (ጎ) (wei chi በቻይኒኛ) የእስያውያን ታዋቂ የሠንጠረዥ ጨዋታ ነው፡፡
ቼዝ ጨዋታ፤ በጠባብ ሜዳ የምንጫወተው ሠንጠረዥ ነው፡፡ 32 ጠጠሮች አሉት - አለቃና ምንዝር የሆኑ። ከሁለቱም ወገን የሚሠለፉ፡፡ የቼዝ ጨዋታ የጠላትን ወታደርና መኮንኖች ግንባር ለግንባር እየገጠሙ መደምሰስ ነው፡፡
በአንፃሩ በ “ጐ” ጨዋታ፣ ከቼዝ ስድስት ጊዜ በሰፋ ሰፊ ሜዳ በየጐራው 52 ጠጠሮችን በጥቁርና በነጭ አሰልፎ መፋለም ሲሆን፤ ዘዴው እያንዳንዱን ጠላት በመክበብ ከእናት ክፍሉ ለይቶ መጠጊያ ማሳጣት ነው፡፡ ከዚያም እንዲሟሽሽና ሽባ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ በሰፊው ማሰብ፣ ትንሽ ቦታ ሰውቶ፣ ቀስ በቀስ ሰፊ ቦታ መያዝ፤ በመጨረሻም ማሸነፍ ነው፡፡ ሁለቱን ስልቶች ጠንቅቆ ማወቅ ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ሠንጠረዥ እጅግ ጠቃሚ ነው! ቅልጥፍናን ከገዢ መሬት በላይ የማየት ክህሎት ይኑርህ ነው ነገሩ!
እጅ መስጠት የሚጀምረው ከአንጐል ውስጥ ነው፡፡ ስለዚህ አስቀድመህ የባላንጣህን አዕምሮ ክበብ ይላሉ፤ የፖለቲካ ፀሐፍት (Submission starts in the mind and hence encircle the enemy’s brain) ቀስቅስ፣ ግንዛቤ ፍጠር፣ አንቃ ነው፡፡ የማዖን የጦር ዘዴ ለአዕምሮ ጦርነት ማሰብ ድንቅ ነው፡፡
“ጠላት ሲገፋ አፈግፍግ፡፡ ጠላት ካምፕ ውስጥ ሲያርፍ እረፍት - ንሳው፡፡ ጠላት ሲዳከም አጥቃው፡፡ ጠላት ሲያፈገፍግ አንተ ግፋ፡፡” ዘመኑ የአዕምሮ ትግል ወቅት ነውና አዕምሮህን አስላ፡፡ እቅድህን አጥራ፡፡ ስትራቴጂህን በጥንቃቄ ቀንብብ እንደማለት ነው፡፡ ይሄ ሁሉ ሲሆን ግን ከብጤህ፣ ከእኩያህ፣ ከአምሳያህ፣ የፖለቲካ አዕምሮ - ፈርጁ (wavelength) ከአዐምሮ - ፈርጅህ የሚጣጣም የፖለቲካ ባልንጀራ አበጅተህ ወቅቱ በሚፈቅደው ዛፍ ጥላ ሥር ሆነህ፣ ንጋት፣ ቀትርና ጨለማ ለይተህ፣ መጓዝ እንዳለብህ ማወቅ ነው ታላቁ ቁምነገር፡፡ እንዲያው በጥቅም - ቀደም - አካሄድ ለእለት - እንጀራ የተጐዳኘኸውን ወይም ብረት - ድስትና ሸክላ - ድስት ሳትለይ የተወዳጀኸውን ሁሉ የፖለቲካ ወዳጄ ነው ብለህ ከተጓዝክ “ከማይመጥነው ሰው ጋር የሚካኤል ማህበር ጠጣ፤ ተራውን ሳያጠጣ ሞተ” (ቴኾን ሰብ ምኬር ሰጨም፤ ቴያስጭም ወጣም ሞተም) ከመባል አታመልጥም!!

 

Read 8989 times Last modified on Saturday, 29 December 2012 08:54