Saturday, 29 December 2012 09:10

“ትንሽ ግንኙነት!”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(0 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ይኸው ሌሎች በዓላት ደረሱ…እንኳን ለዋዜማው አደረሳችሁማ!
ስሙኝማ…በዓልን በተመለከተ ምን ይመስልሀል በሉኝ፣ የሚመስለኝማ እዚህ አገር በዓል…አለ አይደል…ልክ እንደ ሰመመን መስጫ (አኔስቴዚያ) አይነት ነገር ይመስለኛል፡፡ ‘ፔይን’ ምናምን ትረሳለቻ! መንፈቅ ሙሉ “ኽረ ልናልቅ ነው፣ ኑሮ ከበደ… ምናምን” ስንል እንቆይና በዓል ሲደርስ ምን አለፋችሁ፣ የሆነ ቢል ጌትስ ምናምን ነገር ያደርገናል፡ ለዕለታዊ ሆድ ማበባያ አልገኝ ሲል የከረመው ገንዘብ ለበዓል ሰሞን ከየት እንደሚመጣ አይገርማችሁም!

“አቦ በዚች ሰሞን እንኳን ትንሽ ፈገግ እንበል፣ አትነጅሰን…” ልባል ስለምችል እንኳን ለዋዜማ ደረሳችሁልኝማ!
እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ይቺን ስሙኝማ፡፡ እዚቹ የጉድ ከተማ እየሆነች ያለችው አዲስ አበባ ውስጥ ነው። (ስሙኝማ…መቼስ ለምን ይዋሻል፣ አዲስ አበባ የማላውቃት ከተማ እየሆነችብኝ ነው። በቃ ልክ ሠላሳ ዓመት ውጪ የከረመ ዳያስፖራ አለ አይደል?…እንደዛ ማለቴ ነው።)
እናላችሁ…ሰውየው የአእምሮ በሽተኛ ነው፡፡ እናም ምግብ በሚያገኝበት ጊዜ በፌስታል ይዞ ሄዶ የሆነ ሥጋ ቤት አጠገብ ሆኖ ነው የሚበላው፡፡ በልቶ ከጨረሰ በኋላ ወደ ‘ቀይ መብራት’ ሰፈር ይሄድላችኋል። ታዲያ… በሴቶቹ በራፎች እያለፈ በእጁ ሽልንግ ከፍ አድርጎ ይዞ ምን እያለ ይጮሀል መሰላችሁ… “ትንሽ ግንኙነት!” “ትንሽ ግንኙነት!” እያለ ይጮሀል፡፡ በሌላ አነጋገር የያዘው ሽልንግ ብቻ ስለሆነ “የአቅሜን ያህል ሰርቪስ ስጡኝ ማለቱ ነው፡፡ ቢያንስ፣ ቢያንስ አቅሙ የት ድረስ እንደሆነ ያውቃል ማለት ነው፡፡
ከግለሰብ እስከ አገር ብዙዎቻችን የተቸገርነው አቅማችንን አናውቅ ብለን ነው!
የምር እኮ …በተለይ ዘንድሮ እዚህ አገር “ትንሽ ግንኙነት!” የሚል አቅምን ያገናዘበ ነገር ከመናገርና ከመሥራት የሚከለክሉን “ጨሰ! አቧራው ጨሰ!” ነገሮች እየበዙ ነው፡፡ “ከአፍሪካ የመጀመሪያ…” “ከምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ…” ምናምን እየተባለ ጨው ባላነሰው ነገር ውስጥ ሁሉ ሌላ አይነት ‘ጨው’ እየተሞጀረና ነገሮች እየኮመጠጡ አቅማችንን እንዳናውቅ እየሆንን ነው። ከየት የመጣ ባህል እንደሆነ አንድዬ ይወቀው!
ምን መሰላችሁ…ነገርዬው “አያ በሬ ሆይ ሳሩን አየህና ገደሉን ሳታይ…” አይነት እየሆነ ነው፡፡ ችግሩ ምን መሰላችሁ… “በአፍሪካ አንደኛ…” “በዓለም የመጀመሪያው…” አይነት ፉክክር ውስጥ ከገባን…አለ አይደል… ደግሞ እንደገና ‘አድቫንስድ ዲክሸኒሪ’ ላይ ለሌላ ደስ የማይል ቃል ምሳሌ እንዳያደርጉንማ! ለምሳሌ “Fantasy” ለሚለው ቃል የሆኑ ትርጉሞች ከሰጡ በኋላ ለማጠናከሪያ ‘ምሳሌ፣’ ብለው “አሁን የአቢሲንያ ሰዎች ‘አንደኛ ነን’ ‘ቀዳሚ ነን’ እንደሚሉት አይነት…” ምናምን የሚል ነገር ሊፅፉብን ይችላሉ፡፡ ደግሞ በ‘አባሪ’ በዓለም “ውራ” የሆንንባቸው ነገሮች ይደረደሩብናላ! ሳር አይቶ ገደል ያላየው በሬ ነገር ይመጣል፡፡ የምር…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…‘ውራ’ ወይም ‘ለውራ ቅርብ’ የሆንንባቸው ነገሮች ብዛት የኮምፒዩተር እገዛ ካልተጨመረበት በራሳችን ቆጥረን እንችለዋለን! የምር…በአዲስ አበባው አነስተኛ ባቡር ሀዲድ ላይ ቢዘረጉም ቦታ የሚበቃቸው አይመስልኝም፡፡
እናማ…ከግለሰብ እስከ አገር ብዙዎቻችን የተቸገርነው አቅማችንን አናውቅ ብለን ነው!
ስሙኝማ…ምን ይገርምሀል አትሉኝም… አሁን፣ አሁን የሆነች ትንሽ ነገር ካገኘን በዛቹ እንዳለች ከመደሰት ይልቅ… ይሄ የሆነ “ከምናምን አንደኛ…” “ከምናምን የመጀመሪያ…” የሚሏቸውን ነገሮች በባትሪ መፈለግ ከመቼ ጀምሮ የመጣ ልምድ እንደሆነ ግርም ይለኛል፡፡ ከሆነ ነገር አንደኛ የሆንንበት የማይገለጽበት ስብሰባ እየጠፋ ያለ ይመስላል፡፡
ደግሞ እኮ እንዲህ የምንለው መረጃ መያዝ ባልተለመደበት አገር ነው፡፡
እናላችሁ…ሆይ ሆይታ ለማድመቅ፣ አርእስት ለማሳመር፣ እንደ አየሩ ሁኔታ የሚለዋወጥ ‘ፓትሪዮቲዝም’ ለመግለጽ እየተባለ ከሥራው ይልቅ ዲስኩሩ እየበዛ ነው፡፡ “ትንሽ ግንኙነት!” ብሎ በአቅም ከመኖር ይልቅ የቆጡን ልናወርድ ስንል የብብቱ እየወደቀ ነው፡፡
ለምሳሌ ጓደኝነት ይባልና አንዳንዶቻችን የእኔ ቢጤ ቺስታዎች ካለው፣ ከደላውና ጓደኝነትን…አለ አይደል… እንደ ግብር ሰብሳቢ በ‘ወጪ’ ‘ገቢ’ና ‘የተጣራ ትርፍ’ አይነት ነገር ከሚያስብ ጋር በሆነ ምክንያት እንለጠፋለን፡፡ አንድ ሁለት ቀን እዚቹ ከተማ ውስጥ ምርጦቹ በሚተያዩበት ቦታ ብቅ እንልና የዓመት ጥሪታችን ሙልጭ ትላለች፡፡ ከዛ በኋላ የእኛ ጓደኝነት በገንዘብም ሆነ በምንም አይነት ኢንቬስትመንት አዋጪ ስላልሆነ ፋይላችን ይዘጋል፡፡ ይሄኔ “ወይኔ! እንዲሀ ይጫወትብኝ…” አይነት ጨጓራ የሚልጡ ነገሮች ይሰፍሩብናል፡፡ መጀመሪያውኑ “ትንሽ ግንኙነት!” የምትለዋን ባንረሳ ኖሮ ይህ ሁሉ ባልመጣ፡፡
ስሙኝማ…በ‘ቦተሊካ’ም ቢሆን “ትንሽ ግንኙነት!” ማለት የማይችሉ ሰዎች አደባባዩን ይሞሉትና…አለ አይደል… ይኸው ከሉሲ ጀምሮ ልባችን እንደ ደረቀ ነው። (የእሷ ነገር እንዴት ሆነ! ለአሳይለም አፕላይ አደረገች እንዴ!) እናላችሁ…በአስተሳሰብ ለአቅመ ‘ቦተሊካ’ ሳይደርስ ጥልቅ ብሎ እየተገባ እኛው መከረኞቹ ‘ቲራቲር’ ተመልካች ሆነን አርፈነዋል፡፡! “እንዳካሄድ…” “የዛሬ ስብሰባችንን ልዩ የሚያደርገው”፣ “ሰው በላው ስርአት…”፣ “የህዝቡን ጥቅም ያላገናዘበ…” ምናምን ብቻ ማለት ብቻ የ‘ቦተሊከኝ’ነት ‘የሙያ ብቃት ማረጋጋጫ’ አይሆኑማ! ቂ..ቂ…ቂ…
እናላችሁ…በየመሥሪያ ቤቱ “ትንሽ ግንኙነት!” ማለት ያልለመድን ሰዎች ሞቅ፣ ሞቅ ያለውን ወንበር ይዘን ይኸው ነገሮች ሁሉ አስቸጋሪ ሆነዋል፡፡ (በጨርቅና በሸራ ላይ የሚጻፍ መፈክር ትልቅነትና ብዛት የ‘ፐርፎርማንስ’ መለኪያ ሆኗል እንዴ! አሀ…ግራ ገባና! አንዳንድ መሥሪያ ቤት በየሁለት ቀኑ ምናምን ስንሄድ የምናየው አዳዲስ አሠራር ሳይሆን አዳዲስ መፈክር ነዋ! (ዘንድሮ በሲልክ ስክሪን ምናምን ሥራ ያልከበረ መቼም አይከብር!)
ስሙኝማ…እኔ አንዳንዴ ሳስበው ምን ይመስለኛል መሰላችሁ… ይሄ “ደፋርና ጭስ መውጫ አያጣም!” የሚለው ተረት ላይ “እንደ አስፈላጊነቱ…” የሚል ነገር ካልተካተተልን አስቸጋሪ የሚሆን ይመስለኛል፡፡
ደግሞላችሁ…በ“ትንሽ ግንኙነት!” ሌላ ትርጉም…አለ አይደል…በየቦታው ነገሮችን ለማስፈጸም “ትንሽ ግንኙነት!” አስፈላጊ እየሆነ ነው፡፡ ልጄ …አለ አይደል…ደረጃ ‘ሀ’ እድል ያላቸው የጂ.ኤም. ወይም ኤክስኪዩቲቭ ሴክሬታሪ “ትንሽ ግንኙነት!” አላቸው፡፡ እነሱ ዘንድ ‘ሁሉ በእጅ፣ ሁሉ በደጅ’ ነው፡፡
(“በሥራ አስኪያጅ ደረጃ የሥራ አስኪያጁ ጸሀፊ…” የሚል ምናመ መ.ፕ. ምናምን የሥራ ደረጃ ይፈጠርልንማ! አሀ…አንዳንዴ ከቢሮው ምንጣፍ በስተቀር — ‘ከሊፕስቲኩ በስተቀር…’ የሚል ልጨምር አልኩና ተውኩት— “ይሄ መሥሪያ ቤት ሁለት ሥራ አስኪያጅ ነው እንዴ ያለው?” እያልን እየተቸገርን ነው፡፡)
እናላችሁ…ደረጃ ‘ለ’ የሆኑት ደግሞ መምሪያ ኃላፊ፣ ክፍል ኃላፊ አይነት “ትንሽ ግንኙነት!” አላቸው፡፡ (እዚህ አካባቢ የሥራ ክፍፍል ብዙም አያስቸገርም፡፡
ልክ ነዋ…‘በመምሪያ ፀሀፊ ደረጃ የመምሪያ ጸሀፊ’ አይነት ነገር “የላይኛውን ያህል” በብዛት አይገጥመንማ!) ደረጃ ‘ሐ’ የሆኑት ደግሞ ክለርኩ፣ ጠቅላላ አገልግሎት፣ ንብረት ክፍል ምናምን አይነት “ትንሽ ግንኙነት!” አላቸው። (ልጄ…የምር ‘ፌቨር’ የሚገኘው እዚህ አካባቢ ነው!)
እናላችሁ…የእኛ ቢጤዎቹ ደግሞ አለን “ትንሽ ግንኙነት!” የለን፣ ምን ‘ግንኙነት’ የለን…እንደፈጠጥን ፈጠን የቀረን! ቂ..ቂ…ቂ… ልክ ነዋ…በእኛ ያልተሳቀ በማን ሊሳቅ ነው! የኢንተርኔቱን ሳይሆን የፊት ለፊቱ ‘ኔትወርኪንግ’፣ ፌስቡክ ምናምን ያልገባን ምስኪኖች! ግፋ ቢል በምንፈልገው መሥሪያ ቤት አካባቢ ያሉ ሲጋራ ሻጮች ወይም ሊስትሮዎችን… “ስማ የዚህን መሥሪያ ቤት ዘቡሌ ካወቅህ እንዲያስገባኝ ተሟሟትልኝ፣ አምስት ብር እበጥስልሀለሁ…” ብንል ነው፡፡ ይቺም እንደ “ትንሽ ግንኙነት!” ከተቆጠረች ማለት ነው፡፡ እናማ…ከግለሰብ እስከ አገር ብዙዎቻችን የተቸገርነው አቅማችንን አናውቅ ብለን ነው!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 5902 times