Saturday, 29 December 2012 09:10

እሥረኛው የጃንሆይ ቤተሰብ በዓለም በቃኝ ወሕኒ ቤት

Written by  ባየህ ኃይሉ ተሰማ bayehailu@gmail.com
Rate this item
(2 votes)

ሕዝባዊ አብዮት የተቀጣጠለባቸው አገሮች ታሪክ እንደሚያሳየው ቀዳሚው የአብዮቱ ግብ፣ ግፍና ጭቆናን ማስወገድ ብቻ ሳይሆን የኢፍትሐዊነት አርማ ተደርጐ የሚቆጠረውን መሪ ከመንበረ ሥልጣን ማባረርም ጭምር ነው፡፡ ይህ እርምጃ በፈረንሳይ አገር በንጉሥ ሉዊ 16ኛ እና በሩስያ ደግሞ በዛር ኒኮላስ ዳግማዊ ላይ በከፋ መልኩ ተከስቶ በነገሥታቱና ቤተሰባቸው ላይ አብዮታዊ ሰይፍ እንዲያርፍበት ምክንያት ሆኗል፡፡በየካቲት 1966 ዓ.ም በኢትዮጵያ የተነሳው ሕዝባዊ አብዮት፤ በስተኋላ በብልጣ ብልጥ ወታደራዊ መኮንኖች ተጠልፎ አገሪቱን ወደ ግድያ መድረክነትና ወደ ግዙፍ እሥር ቤትነት ከመቀየሩ በፊት፣ የነበረው ዓላማ በአገሪቱ ግፍና ጭቆናን በማስወገድ ማህበራዊ ፍትሕ እንዲሰፍን የሚጠይቅ ነበር፡፡

ዘውዳዊ ሥርዓትን አስወግዶ ስልጣን መያዙን መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም በይፋ ያወጀው የደርግ ወታደራዊ ጁንታም፣ በዚሁ እለት ንጉሠ ነገሥቱን ከቤተ መንግሥታቸው ይዞ አራተኛ ክፍለ ጦር በተባለው የወታደር ሰፈር እንዲታሰሩ በማድረግ፣ እስከ ጊዜ ሞታቸው ድረስ ለአንድ አመት ያህል አቆይቷቸዋል፡፡
ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ንጉሳዊ ቤተሰቡ በጃንሆይ ልጅ በልዕልት ተናኘወርቅ ኃይለሥላሴ መኖሪያ ቤት ውስጥ በቁም እስር እንዲጠበቁ የተደረገ ሲሆን ከነዚህ መካከል አረጋውያን፣ ሴቶች እና ሕፃናት ይገኙበት ነበር፡፡ ደርጉ የጃንሆይ ቤተሰቦች በቁም እስር የሚጠበቁት ምክንያት “ሰፊው ሕዝብ በግብታዊነት ተነሳስቶ የበቀል እርምጃ እንዳይወስድባቸው ነው” በማለት ለውጪ ተመልካቾች ገልፆ ነበር፡፡
ሕዳር 14 ቀን 1967 ዓ.ም “ስልሳዎቹ” ተብለው ከሚታወቁት ከዘውድ መንግሥት ባለስልጣናት ጋር የተሰውት፣ የኢትዮጵያ የባህር ኃይል ጠቅላይ አዛዥና የጃንሆይ የልጅ ልጅ፣ ሪል አድሚራል እስክንድር ደስታ በደርግ የተገደሉ የመጀመሪያው የጃንሆይ ቤተሰብ አባል ናቸው፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ በነሐሴ 1967 ዓ.ም ያረፉት ግድያ ተፈፅሞባቸው ከሆነ ደግሞ ጃንሆይ በደርግ የተገደሉ ሁለተኛው የንጉሳዊ ቤተሰብ አባል ናቸው ማለት ነው፡፡
ደርግ በመስከረም ወር 1968 ዓ.ም በቁም እሥር የሚገኙትን ንጉሳዊ ቤተሰቦች በአዲስ አበባ ወህኒ ቤት ውስጥ የእድሜ ልክ ፍርደኞች ከሚታሰሩበትና ዓለም በቃኝ ከተባለው ክልል ውስጥ በማዘዋወር አያያዛቸውም በእሥረኛ ደንብ እንዲሆን መወሰኑ ታወቀ፡፡ ከእነዚህ የንጉሳዊ ቤተሰብ እሥረኞች ውስጥ የሚበዙት ሴቶች የነበሩ ሲሆን ወጣት ወንዶችም ይገኙበት ነበር፡፡
እሥረኞቹ ልዑላን የአፄ ኃይለሥላሴ የቅርብ ዘመዶች ከመሆናቸው በስተቀር በዘውድ መንግሥት ውስጥ የያዙት ሥልጣን ወይም ሹመት አልነበረም። ለአንድ ዓመት በቁም እስር ሲቆዩም በወንጀል አልተከሰሱም ወይም ፍርድ አልተፈረደባቸውም፡፡ ከአንድ አመት የቁም እስር በኋላ ደግሞ ይባስ ብሎ ለረጅም ጊዜ ወደሚቆዩበትና የእድሜ ልክ ፍርደኞች ወደሚታሰሩበት የአለም በቃኝ የወህኒ ክልል ውስጥ እንዲዘዋወሩ ተደረገ፡፡
በዓለም በቃኝ ከታሰሩት ንጉሳዊ ቤተሰቦች ውስጥ ልዕልት ተናኘወርቅ ኃይለሥላሴ እና ልጆቻቸው ልዕልት ሰብለ ደስታ፣ ልዕልት አይዳ ደስታ፣ ልዕልት ሒሩት ደስታ፣ ልዕልት ሶፍያ ደስታ እንዲሁም ልዕልት ሳራ ግዛውና ልጆቻቸው ልዑል ወሰንሰገድ መኮንን፣ ልዑል ሚካኤል መኮንን፣ ልዑል በዕደማርያም መኮንን እና ልዕልት ምሕረት መኮንን በተጨማሪም የልዑል አልጋ ወራሽ አስፋ ወሰን የመጀመሪያ ልጅ ልዕልት እጅጋየሁ ይገኙበት ነበር፡፡
ከእስረኞቹ በእድሜ ዝቅተኛው የ17 አመቱ ወጣት ልዑል በዕደማርያም መኮንን ሲሆን ከፍተኛ እድሜ የነበራቸው ደግሞ የ63 አመቷ ልዕልት ተናኘወርቅ ኃይለሥላሴ ነበሩ፡፡ በወህኒ ቤት ደንብ መሰረት ልዑላኑ ወንዶችና ሴቶች በዓለም በቃኝ የታሰሩት ተለያይተው በልዩ ልዩ ክፍሎች ውስጥ ነበር፡፡ የወህኒ ቤቱ ክፍሎች ከድንጋይ የተሰሩና የሚያዡ በመሆናቸው ዘወትር ቅዝቃዜ አይለያቸውም፡፡ ከጥቂት የመመገቢያ ቁሳቁሶች በስተቀር ሌላ መገልገያ እንዳያስገቡ የተከለከሉት እሥረኞች የሚተኙትም በወለሉ ላይ ፍራሽ ብቻ በማንጠፍ ነበር፡፡
ደርጉ የልዑላኑን ቤትና ንብረት የወረሰ በመሆኑ፣ በምትኩ በየወሩ ብር 120 እየቆረጠላቸው ለጥቂት ጊዜ ሲቀበሉ የቆዩ ሲሆን በኋላ ላይ “ይበዛል” ተብሎ ወደ 50 ብር ዝቅ እንዲል ተደርጓል፡፡ እሥረኞቹ ከዘመዶቻቸው በቀን አንድ ጊዜ ምግብ ለመቀበል፣ በሳምንት አንድ ጊዜ አጭር ደብዳቤ ለመፃፍ እንዲሁም ለጥልፍ የሚያገለግሉ ቁሳቁስ ለማስገባት የሚችሉ ቢሆንም ጠያቂ ለማነጋገር የሚፈቀድላቸው ግን በአመት ሁለት ወይም ሦስት ጊዜ ብቻ ነበር፡፡ እሥረኞቹ ንጉሳዊ ቤተሰቦች በጣም በሚያስጨንቅ አካላዊና ሥነ ልቡናዊ ሁኔታ ላይ እንደነበሩ በጊዜው የፖለቲካ እሥረኞችን ሁናቴ እየተከታተለ መንግሥትን ይማፀን የነበረው አለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች አምነስቲ ኢንተርናሽናል በጊዜው ያወጣቸው ተከታታይ ሪፖርቶች ይጠቁማሉ፡፡
የንጉሳዊ ቤተሰቡ ከነበሩባቸው በርካታ ችግሮች አንዱ የመሰረታዊ ሕክምና እጦት ነበር፡፡ ምንም እንኳን በወህኒ ቤቱ ውስጥ የጤና አገልግሎት የሚሰጥ ክሊኒክ የነበረ ቢሆንም፣ የንጉሳዊ ቤተሰቡ ሕክምና ሆነ ተብሎ እንዲዘገይ ይደረግ ነበር፡፡ ስለዚህም በጊዜ ቢደረስበት መፍትሄ ያገኝ የነበረ ቀላል ሕመም እየተባባሰ እሥረኞቹን ለከፋ አደጋ ሲያጋልጣቸው ተስተውሏል፡፡
ለዚህም አይነተኛ ምሳሌ የሚሆኑት ልዕልት እጅጋየሁ አስፋ ወሰን ናቸው፡፡ እኒህ ሴት በወህኒ ቤት በተቆራኛቸው ደዌ ለረጅም ጊዜ ሲሰቃዩ አሳሪዎቻቸው ሕክምና እንዲያገኙ አልፈቀዱላቸውም ነበር፡፡ ህመማቸው ተባብሶ ከፍተኛ ደረጃ ከደረሰ በኋላ ግን በፖሊስ ሆስፒታል ተኝተው እንዲታከሙ ተወሰነ። ሐኪሞች ልዕልቷን ኦፕራሲዮን ቢያደርጉዋቸውም ያደረባቸው ደዌ ለረጅም ጊዜ መፍትሄ ሳያገኝ የቆየ በመሆኑ፣ ጥር 23 ቀን 1970 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡
እሥረኞቹን ያሰቃዩዋቸው የነበሩት ሕመሞች የመነጩት ወይም ሥር ሰደው የተባባሱት ለረጅም ጊዜ ያለ ሕክምና በቆዩበት በዚህ ወህኒ ቤት ውስጥ ነበር። በከባድ ህመም ይሰቃዩ ከነበሩት መካከል ልዕልት ሒሩት ደስታ አንዷ ናቸው፡፡ እኒህ ልዕልት በእሥር ላይ እያሉ ከተከሰተባቸውና ከባድ ደረጃ የደረሰ የቆዳ ካንሰር የተነሳ ኦፕራሲዮን የተደረገላቸው ሲሆን በሕመሙ ሳቢያ የሰውነት ክብደታቸው በአደገኛ ሁኔታ አሽቆልቁሎ እስከ 25 ኪሎ ግራም ደርሶ ነበር፡፡
ሌላዋ የእሥር ቤት ሕመም ሰለባ ደግሞ ልዕልት አይዳ ደስታ የነበሩ ሲሆን ሕመማቸው ደግሞ የማያቋርጥና ብርቱ ራስ ምታት ነበር፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የሰውነታቸው አንዱ ክፍል እዚያው ወሕኒ ቤት ውስጥ ፓራላይዝድ በመሆኑ ከቦታ ወደ ቦታ ለመንቀሳቀስ የሚችሉት በከፍተኛ ችግር ነበር፡፡ የልዑል መኮንን ባለቤት የነበሩት ልዕልት ሣራ ግዛው በበኩላቸው፤ በወሕኒ ቤት በለከፋቸው የሄፒታይተስ በሽታ ክፉኛ ታመው ለረጅም ጊዜ ተሰቃይተዋል፡፡
መሰረታዊ የሕክምና እጦት፣ ከዛሬ ነገ ልንገደል እንችላለን የሚል ብርቱ ስጋት እንዲሁም በውጪ እና እዚያው እሥር ቤት ካሉ ልጆቻቸውና ዘመዶቻቸው ጋር ለመገናኘት አለመቻል፣ ተደራርቦ እሥረኞቹን ለአስከፊ ስነልቡናዊ ስቃይ ዳርጓቸዋል። የደረሰባቸውን የመንፈስ ጭንቀት ለማስታገስም ቤተሰቦቻቸው እንቅልፍ እንዲያስወስድ የሚያደርጉ እና አእምሮን የሚያረጋጉ እንክብሎች እንዲያመጡላቸው በመጠየቅ፣ ያለ ሐኪም ፈቃድ ይወስዱ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡
እነዚህ እሥረኞች ያለ ፍርድ ወደ ወህኒ የተወረወሩ በመሆኑ ለፍርድ እንዲቀርቡ ወይም እንዲለቀቁ፤ እንዲሁም አያያዛቸውም የሕግ እሥረኞች በሚጠበቁበት አግባብ ሆኖ መሰረታዊ ሕክምና ሳይዘገይ እንዲሰጣቸው፤ በማለት አምነስቲ ኢንተርናሽናል ከታሰሩበት ጊዜ ጀምሮ ባለማቋረጥ የደርጉን መንግሥት ሲማፀን ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ ሕክምናን ማዘግየት ወይም መከልከል እንደ መደበኛ ቅጣት ተቆጥሮ፣ እሥረኞቹ እስከ 1980 ዓ.ም ድረስ መሰረታዊ ሕክምናን ተነፍገው ቆይተዋል። ንጉሳዊ ቤተሰቡ ከእሥር እንዲለቀቅ ከዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችና የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ሳያቋርጥ ለደርጉ ይቀርብ የነበረው ተማፅኖ ፍሬ ማሳየት የጀመረው እሥረኞቹ ወደ ወህኒ ከተወረወሩ ከስምንት አመታት በኋላ ነበር፡፡
ደርግ ዘጠነኛውን የአብዮት በዓል አስመልክቶ በጳጉሜ ወር 1975 ዓ.ም ለፖለቲካ እሥረኞች ይቅርታ ሲያደርግ ወጣቷ ልዕልት ምሕረት መኮንን ከንጉሳዊ ቤተሰብ እሥረኞች መካከል ለመለቀቅ የመጀመሪያዋ ሆነች፡፡
የደርግ “አብዮታዊ ምህረት” ሁሉንም እሥረኛ ንጉሳዊ ቤተሰብ ያካተተ ባይሆንም እሥረኞቹ እንዲፈቱ ለሚማፀኑት ዓለም አቀፍ ተቋማት ግን እንደ በጐ እርምጃ ተደርጐ ተወስዷል፡፡ ተቋማቱ ምህረቱን አስመልክተው ለኢትዮጵያ መንግሥት ምስጋናቸውን በማቅረብ ቀሪዎቹ እሥረኛ ንጉሳዊ ቤተሰቦች እንዲለቀቁ የተለመደውን ልመና አቅርበዋል፡፡
ደርግ ለንጉሳዊ እሥረኞቹ ያደረገው ሁለተኛው ምህረት የተከናወነው ከመጀመሪያው ምህረት አምስት አመት ያህል ቆይቶ ሚያዝያ 13 ቀን 1980 ዓ.ም ነበር፡፡ ከአሥራ ሁለት አመት በኋላ ከእሥር የተለቀቁት የ75 አመቷ አዛውንት ልዕልት ተናኘ ወርቅ ኃይለሥላሴ፣ ልዕልት ሰብለ ደስታ፣ ልዕልት ሒሩት ደስታ፣ ልዕልት አይዳ ደስታ፣ ልዕልት ሶፍያ ደስታ እና ልዕልት ሳራ ግዛው ነበሩ፡፡
ደርጉ ለንጉሳዊ ቤተሰብ ሁለተኛውን ምህረት ከሰጠ ከአንድ አመት ከአራት ወራት በኋላ ደግሞ ሦስተኛውንና የመጨረሻውን ምህረት ጳጉሜ 2 ቀን 1981 ዓ.ም አደረገ፡፡ ከ13 አመታት በኋላ የተለቀቁት የንጉሳዊ ቤተሰብ እሥረኞች፣ ወርቃማውን የወጣትነት ጊዜያቸውን በወህኒ ቤት ያቃጠሉት፡- ልዑል በዕደማርያም መኮንን፣ ልዑል ሚካኤል መኮንን እና ልዑል ወሰንሰገድ መኮንን ነበሩ፡፡
ከእነዚህ ታሳሪ የንጉሳዊ ቤተሰብ አባላት ወስጥ አብዛኛዎቹ እድሜያቸው የገፋ ሴቶች በመሆናቸው ቢለቀቁ በደርጉ መንግሥት ላይ የሚያደርሱት አንዳች አደጋ አልነበረም፡፡ ንጉሳዊ ቤተሰቡ የተያዙት ከእሥር ቢወጡ ለመንግሥት አደጋ ያደርሳሉ በሚል ስጋት ሳይሆን በራሳቸው ላይ አደጋ እንዲደርስባቸው ተፈልጐ መሆኑን የታሳሪዎቹን ስብጥር፣ እድሜና አያያዝ በመመልከት በቀላሉ ለመገመት ይቻላል፡፡
መርሆውንና ቃልኪዳኑን ተቀብለው አብረውት ረጅም ርቀት የተጓዙትን የገዛ ጓዶቹን ሳይቀር “አብዮት ልጆቿን ትበላለች” እያለ ያለ ርህራሄ ይጨፈጭፍ በነበረው የደርግ የጭለማ ሥርዓት፤ የጃንሆይ ቤተሰብ ሆኖ ሳይገደሉ ከእሥር ቤት በህይወት መውጣት “ምሕረት” ብቻ ሳይሆን ተአምርም ሊባል የሚችል ነው፡፡
ይህ በአፄ ኃይለሥላሴ የቅርብ ዘመዶች ላይ የደረሰው እሥርና በቤተሰቡ ላይ ያስከተለው ቀውስ፤ በጊዜው ብዙዎች እንደፈሩት ወደ ጅምላ ጭፍጨፋ ሳይሸጋገር በረጅም እሥር ብቻ ማለፉ በአንድ በኩል ቤተሰቡን እድለኛ ሊያሰኘው ይችላል፡፡ በእርግጥ አለመገደል ግን ያለ ፍርድ አንድ ቀንም ቢሆን መታሰርን ትክክል ሊያደርገው አይችልም፡፡

Read 6814 times