Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 29 December 2012 09:38

የመንገድ ዳር ሰዓሊው

Written by 
Rate this item
(2 votes)

“በውስጥህ ያለውን ሃሳብ ሳል የሚልህ የለም”
ፒያሳ ከሚገኘው አፍሪካዊያን መፃሕፍት መደብር ወደ ዶሮ ማነቂያ ልኳንዳ ቤቶች ሲያቀኑ ዳገቱን ከመጨረስዎ በፊት በቀኝ በኩል ሲታጠፉ፣ ወደ ሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት የሚያደርስ የኮረኮንች መንገድ ያገኛሉ፡፡ በቅያሱ ካሉ ቤቶች በአንዱ ደጅ ላይ አንድ ወጣት ዘወትር ሸራ ወጥሮ በሥዕል ሥራ ተጠምዶ ይታያል፡፡ ሥዕሉ፣ አሳሳሉና ሁለመናው በመንደሩ የሚያልፉ ሰዎችን ቀልብ የሚስብ ነገር አለው፡፡ ጋዜጠኛ ብርሃኑ ሰሙ ከወጣቱ ሰዓሊ ሚሊዮን ታደሰ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ስለህይወቱ፣ ስላሳለፈው ውጣ ውረድ፣ ስለ ሙያውና አመለካከቱ ጠይቆት ምላሽ ሰጥቶታል፡፡

ከትምህርት ታሪክህ እንጀምር … 
8ተኛ ክፍል ደርሼ የሚኒስትሪ ፈተና ሳልወስድ ነው ትምህርቴን ያቋረጥኩት፡፡ በብሔራዊ ቤተመንግሥት፣ በራስ አበበ አረጋይና በብርሃን ኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች እየተማርኩ እስከ ስምንተኛ ክፍል ደርሼአለሁ። የመማር ፍላጎት ነበረኝ፤ በትምህርቴም ጎበዝ ነበርኩ፡፡ በተፈጥሮዬ ኃይለኛ ስለነበርኩ ከሌላው ጋር ለመጋጨትና ለመደባደብ እፈጥን ነበር፡፡ እንዳለመታደል ደግሞ የትምህርት ቤት መምህራኖቼ ፀባዬን እንዲሻሻል ከማድረግ ይልቅ በክፍል ውስጥ በተማሪው መሐል እያቆሙ የዱርዬና መጥፎ ልጅ ምሳሌ እንደሆንኩ ማሳያ ሲያደርጉኝ ኃይለኝነቴ እየባሰበት መጣ፡፡ በዚህ ምክንያት ትምህርቴን አቋረጥኩ፡፡ በግልም በቡድንም መደባደብ የየዕለቱ ሥራዬ ሆነ፡፡ እስር ቤትም ሌላው መኖሪያ ቤቴ እስከመሆን ደርሶ ነበር፡፡
ትውልድህ የትና መቼ ነው?
በዚሁ በዶሮ ማነቂያ መንደር በ1974 ዓ.ም ነው የተወለድኩት፡፡ ወላጆቼ በሕይወት የሉም፡፡ አንዲት እህት አለችኝ፤ ትዳር መሥርታ በሲኤምሲ አካባቢ ትኖራለች፡፡ እኔ ብቻዬን እዚህ እኖራለሁ፡፡
ሥዕል ከመጀመርህ በፊት ምን ትሰራ ነበር?
ምንም ሥራ አልነበረኝም፡፡ ታሪኬ በሙሉ በፀብና በተደባዳቢነት የተሞላ ነበር፡፡ ትምህርት ቤት እያለሁ ከእኔ በላይ የሚያጠፉ ልጆች ነበሩ፡፡ የምሳ ዕቃ፣ መጽሐፍ፣ ደብተርና እስክሪብቶ የሚሰርቁ ነበሩ። እኔ ግን ተደባዳቢ ስለነበርኩ ብቻ ነው የመጥፎ ልጅ ምሳሌና ማሳያ አድርገው ያቀርቡኝ የነበረው። መምህራኑ እንደዚያ ማድረጋቸው አመፀኝነቴንና ኃይለኝነቴን አባብሶታል፡፡ ለምን አየኸኝ ወይም ሳትገላምጠኝ ገላምጠኸኛል ብዬ መደባደብ ነበር ዋናው ሥራዬ፡፡ አሁን ያንን መለስ ብዬ ሳስበው ሁሉ ያስገርመኛል፡፡
ሥዕል መሳል መቼ ጀመርክ?
የእኔ ፀባይ በመለወጡ የማይገረም የለም፡፡ ለመለወጤ ግን ሰው አይደለም አስተዋጽኦ ያደረገልኝ። እግዚአብሔር ነው የረዳኝ፡፡ ችግር አስተምሮኛል። ስትቸገር ብዙ ነገር የማወቅ ዕድልህ ይሰፋል፡፡ ሥዕል የጀመርኩት ተምሬ ሳይሆን በእግዚአብሔር እርዳታ ነው፡፡ ስጀምር በእርሳስና በእስክሪቢቶ ነበር የምስለው። አሁን በቀለም ሁሉ እጠቀማለሁ። ሥዕል ፀባይና አመለካከቴን ከመለወጡም ባሻገር መዝናኛዬም፣ ኑሮዬም ሕይወቴም ሆኗል፡፡
በልጅነትህ ምን ዝንባሌ ነበረህ?
የእንጨት ሥራና ሥዕል እወድ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ግን ያ ዝንባሌዬ ገብቶት በትምህርትና በልምድ እንዳሳድገው የሚያግዘኝ አላገኘሁም፡፡ ጥሩ መምህራን ባገኝ ትልቅ ቦታ እደርስ ነበር፡፡ መምህራን አንተ ምን አለህ ሳይሆን እኔ የምሰጥህን ተቀበል ነው የሚሉህ፡፡ እኔ ደግሞ አመፀኝነቴና ኃይለኝነቴ የመነጨው መታዘዝ ካለመፈለጌ ጋር በተያያዘ ነው የሚመስለኝ፡፡ አሁን ሥዕል የምሰራው ማንንም ሳልከተልና ሳያዙኝ ውስጤ የሚነግረኝን ተከትዬ ነው፡፡ አሁን ሥዕል ልማር ብዬ አንዱ ትምህርት ቤት ብሔድ አንድ ቁስ አስቀምጠውልኝ ያንን ሳል ብለው ይፈትኑኛል፡፡ ባይሳካልኝ ይጥሉኛል፡፡ በውስጥህ ያለውን ሀሳብ ሳል የሚልህ የለም፡፡ ያንተ ፍላጎትና የአስተማሪዎችህ ፍላጎት ይለያያል፡፡
ስለ ቀለማት ትርጉም፣ ስለ ምጣኔ፣ ስለ መስመሮች … መማሩ የተሻለ ግንዛቤ ያስገኛል ብለህ አታምንም?
ትምህርት ቤት የሥሉን ብሩሽ እንዴት መያዝ እንዳለብህ ያስተምርሀል፡፡ እኔ ስለ ብሩሽ አያያዝ አልጨነቅም፡፡ ያንተን ፍላጎት አይቶ በነፃነት የሚለቅህ የለም፡፡ እኔ ነፍሴ በነገረኝ መልኩ ነው የምሰራው። ተጨንቄ አልስልም፡፡ ከማንም ጋር መወዳደርም አልፈልግም፡፡
የሌሎችን ሥዕል ታያለህ? ያንተንስ ሥራ ያዩ ምን ይላሉ?
የአንዳንድ ሰዓሊያንን ጋለሪ ያየሁበት አጋጣሚ አለ፡፡ የስዕል ጋለሪ ስገባ ቤተክርስቲያን የገባሁ ያህል ነው ደስ የሚለኝ፡፡ እኔም ጋ መጥተው ሥዕሎቼን የሚያዩ አሉ፡፡ አቋሜን አሰራሬንም የሚደግፉልኝ አሉ፡፡ እኔ ቀለም የመግዛት አቅም እንደሌለኝ አይተው በገንዘብ ቢተመን ከሺህ ብር በላይ የሚያወጣ የሥዕል ቀለም የሰጡኝ ሰዓሊያን አሉ፡፡ በዚህ አጋጣሚ ሰዓሊ እስራኤልና ዘላለምን አመሰግናለሁ፡፡ መስራት ትችላለህ በርታ የሚሉኝ አሉ፡፡
ሥዕሎችህን ለሽያጭ ታቀርባለህ? ኤግዚቢሽን ለማሳየትስ ችለሀል? ምን ያህል ሥዕሎችስ አሉህ?
እኔ ባገኘሁት ነገር ላይ ሁሉ እስላለሁ፡፡ በእንጨት፣ በድንጋይ፣ በቆርቆሮ፣ ተወጥሮ በተዘጋጀ ሸራ፣ በቆርቆሮ፣ በካርቶን፣ በአልባሳት፣ በፕላስቲኮች … ባገኘሁት ነገር ላይ ሁሉ እስላለሁ፡፡ ምን ያህል ሥዕሎች እንዳሉኝ ቆጠራ አላደረግሁም፡፡ ሥዕሎቼን የመሸጥ ወይም ኤግዚቢሽን የማሳየት ሀሳቡ አሁን የለኝም። ከትንሽ ጀምሬ ቀስ በቀስ እስከ ቀለም ቅብ ደረጃ እንደደረስኩት ሁሉ በሂደት አሁን ከምገኝበትም ወደ ተሻለ ቦታ እደርሳለሁ የሚል እምነት አለኝ፡፡ እዚያ ላይ ስደርስ ሌሎች መጥተው ሀሳብ የሚለዋወጡበት፣ የሚያነቡበት ጋለሪ ሊኖረኝ ሁሉ ይችላል፡፡
ሥዕሎችህ ላይ ጽሑፍ ትጠቀማለህ፡፡ ምንድነው ምክንያትህ?
ሥዕሎቼን የሚያዩ ጓደኞቼ የሚሰጡት አስተያየት አለ፡፡ አንዱን ሥዕሌን አይተው አስቴር አወቀ በሸራተን ሆቴል ስትዘፍን የነበራትን ገጽታ ይመስላል አሉ። ሌላውን ሥዕል አፄ ምኒልክ ናቸው ሲሉኝ፣ በዚያ አጋጣሚ በሥዕሎቹ ላይ ጽሑፍ የተጠቀምኩበት ሁኔታ አለ፡፡ በሥዕሎቼ ላይ ጽሑፍ የምጠቀምበት ዋናው ምክንያት ግን ከሕብረተሰቡ ጋር ለመነጋገር ነው፡፡ ለምሳሌ “ዛሬ ምን ሰሩ?” የሚል ጽሑፍ ስላለበት ሥዕል ልንገርህ፡፡ ሥዕሉ ሰዎች አሉበት፡፡ ሦስቱም ሰዎች አንዳንድ ቃል ነው የሚናገሩት፡፡ “ዛሬ” የሚለው ሰው አፉ የለም፤ በዛሬ ተሸፍኗል፡፡ “ምን” የሚለው አፉ አለ፡፡ “ሠሩ” የሚለውም በተመሳሳይ መልኩ ቃላቱን ከምስሉ ጋር አገናኝቼ ነው የሰራሁት፡፡ ይህን ሥዕልና ጽሑፍ የሚያይ ሰው ከራሱ ጋር እንዲነጋገር ይጋብዘዋል። ጥሩም ይስራ መጥፎ ከሕሊናው ጋር እንዲነጋገር ያደርገዋል፡፡
ሥዕሎችህን ለሽያጭ ካላቀረብክ በምን ትተዳደራለህ?
ብዙ የችግር ጊዜያትን ስላሳለፍኩና አሁን ለሕሊና ሠላምና እርካታዬ ዋጋና ክብር ስለሰጠሁ፣ ጉንጬን እያለፋ ለሚያደክመኝ ምግብ ብዙ አልጨነቅም፡፡ ሠላምና የአእምሮ እርጋታ ካለህ ሳትበላ ለብዙ ሰዓታት መስራት ትችላለህ፡፡ ሰው የሚበላ ነገር ካላመጣልህ የምግብ ነገር ትዝ ላይልህ ሁሉ ይችላል፡፡ እርቦህ ሆድ ቁርጠት ሲሰማህ ውሃ በመጠጣት ልታስታግሰውና ቀና ልትል ትችላለህ፡፡ በምግብ ብዛት አገጩን ከሚያደክም ሰው በሥራ ብዛት እርቦት ሆድ ቁርጠት የሚያመው ሰው ይሻላል የሚል አቋም አለኝ፡፡ ይህንን አቋምና ፍላጎቴን የተረዱኝ ሰዎች የዕለት ጉርሴን ይችሉኛል። መንግሥትም ሕብረተሰቡም የሚታይና የማይታይ፤ ሊገለጽ የማይችልና የሚችል ጥበቃና ትብብር እያደረጉልን ነው ሁላችንም የምንኖረው የሚል መረዳትም አለኝ፡፡
ሌሎች ከእኔ ምን ይማራሉ ትላለህ?
እኔና ጓደኞቼ በግልና በጋራ እንታወቅበት የነበረው ተደባዳቢነት ምንም ጥቅም እንዳላስገኘልን የሚገባቸውና ከእኛ የተማሩ ብዙ የመንደሩ ልጆች አሉ። ይህንን ሳይ ትውልዱን የሚጎዳ አንድ ነገር መቆሙ ያስደስተኛል፡፡ ዶሮ ማነቂያን በመሰለ ብዙ ዝብርቅርቅ ሕይወት ባለበት መንደር ውስጥ ራሴን ገዝቼ በሰላምና በእርጋታ ሥዕል መስራት መቻሌ፣ ወደፊት ምንም ያህል ከባድ ችግር ቢገጥመኝ መወጣት እንደምችል እያስተማረኝ ነው፡፡ ከእኔም ሕይወትና ሥራ ብዙዎች እየተማሩ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ በየዕለቱ በመንደሩ የሚያልፉ ተማሪዎች “ዛሬስ ምን አዲስ ነገር ሠርቷል?” በሚል ጥያቄ በመኖሪያ ቤቴ ደጅ መሰባሰባቸው በራሱ አስደሳች ነገር ነው፡፡ በጥቅሉ ለሌሎች የጥሩ ነገር ምሳሌ ለመሆን እየጣርኩ ነው፡፡

Read 5371 times Last modified on Saturday, 29 December 2012 10:00