Saturday, 29 December 2012 09:55

“Emergency contraceptive... ጥቅሙና ጉዳቱ...”

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(19 votes)

“... እኔን የሚገርመኝ አንድ ነገር አለ፡፡ ዘመን ተለወጠ ወይንም ተሸሻለ ሲባል በተለይም በሰዎች ባህርይ መስፈርቱ ምንድነው ?ለሚለው ምላሽ አላገኘሁም፡፡ በሙያዬ ፋርማሲስት ወይንም መድሀኒት ሻጭ ነኝ፡፡ እናም ተረኛ ሆኜ በምሰራበት ወቅት የማገኛቸው መድሀኒት ገዢዎች የተለያዩ እንደመሆናቸው ይህን ጽሁፍ ለመጻፍ ያነሳሳኝ በአንድ አቅጣጫ የተመለከትኩት ትዝብት ነው፡፡ እንግዲህ እኔ ልክ ነው ወይንስ አይደለም ብዬ ልታዘብ እንጂ ተጠቃሚዎቹ ወይንም ሌሎች ባለሙያዎች የሚሰጡትን ምላሽ አላውቅም፡፡

1/ ብዙ ጊዜ ወንዶች ለወሲብ መነቃቃት የሚጠቀሙበትን መድሀኒት ለመግዛት ሴቶቹ ሲጠይቁ ለምንድን ፈለግሽው? ይሔ እኮ ለወንዶች በሐኪም ትእዛዝ የሚሰጥ መድሀኒት ነው ብዬ ስጠይቅ የማገኘው መልስ አይ ...እሱ እኮ ስላልተመቸው ነው እንጂ በሐኪም ታዞለት የሚጠቀምበት ነው የሚል ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ለመከራከር ብዙ የማይመች ነገር አለ፡፡ ያው...እንደሚታወቀው የገበያ ጉዳይ ስላለ ጥያቄ ስናበዛ የማይወዱ ሰዎች አብረውን ስለሚገኙ ዝም ብለን እንሸጣለን፡፡ በእርግጥ ከሕይወት ጋር በተያያዘ በቀጥታ ያለሀኪም ትእዛዝ የሚሸጡትን መድሀኒቶች አይመለከትም፡፡ ነገር ግን ይሔኛውም ቢሆን የሚያስከትለው የጤና ችግር እንደተጠቃዎቹ የሚለያይ ስለሆነ ጥንቃቄ ሊደረግበት የሚገባ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ 
2/ ሌላው ነገር ደግሞ የአፋጣኝ የእርግዝና መከላከያ ዘዴ ነው፡፡ አፋጣኝ የእርግዝና መከላከያን ሴት ወጣቶች በተደጋጋሚ ሲገበዩ ይስተዋላሉ፡፡ በተደጋጋሚ ሲባልም በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ከአራትና አምስት ጊዜ በላይ ነው ፡፡ ለመምከር ሲሞከርም የፈለግሁትን ለመሸጥ እንጂ ማን ሐኪም አደረገህ የሚል ስሜት ያለው መልስ ይሰነዘራል፡፡
በአጠቃላይም እኔ ለመግለጽ የፈለግሁት በስልጣኔ ስም እንደዚህ ያሉ አደገኛ እንቅስቃሴዎች ምን ያህል ጎጂ መሆናቸውን በሚገባ ማስተማር ከሁሉም ይጠበቃል ባይ ነኝ፡፡ በተለይም ሴት ወጣቶቹ በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ መመርመርና መምከር የባለሙያዎች ተግባር ይመስለኛል”
ይሁን ከፍያለው ከናዝሬት
ከላይ ያነበባችሁት በመድሀኒት መሸጥ ስራ ላይ የተሰማሩ የአንድ ባለሙያን አስተያየት ነው፡፡ ባለሙያው በሰጡት ሀሳብ መሰረት የአፋጣኝ ወይንም Emergency contraceptive ወሊድ መከላከያው አገልግሎት ከሚሰጥባቸው መካከል የጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታልን ጎብኝተናል፡፡ በዚያም ሜዲካል ዳይሬክተሩን ዶ/ር ደረጀ አለማየሁን አነጋግረናል፡፡ ዶ/ር ደረጀ አለማየሁ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት ናቸው፡፡
ኢሶግ፡ Emergency contraceptive አፋጥኝ የእርግዝና መከላከያ ለምን አገልግሎት ይውላል?
ዶ/ር፡ አፋጣኝ የእርግዝና መከላከያ ማለት ከእርግዝና መከላከያ ወይንም ለቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ከሚሰጡ መድሀኒቶች መካከል ነው፡፡ ይህ መድሀኒት የሚሰጠው የግብረስጋ ግንኙነት ከተፈጸመ በሁዋላ እርግዝና እንዳይከሰት ለማድረግ ነው፡፡ ሴቶች ምንም ጥንቃቄ ሳያደርጉ በግዳጅም ይሁን በፈቃደኝነት ከወንድ ጋር ሲገኛኙ ያልፈለጉት እርግዝና እንዳይከሰት የሚሰጥ መከላከያ ነው፡፡ ይህ የእርግዝና መከላከያ ዘዴ በጋንዲ ሆስፒታል የሚሰጥ ሲሆን የሚሰጣቸው ሰዎችም በተለይም ተገዶ መደፈር የደረሰባቸው ወይንም የኮንዶም መበጠስ እንዳጋጠማቸው ሲገልጹ ነው እንጂ እንደመደበኛው የእርግዝና መቆጣጠሪያ የሚሰጥ አይደለም፡፡
ኢሶግ፡ የጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል ይህንን መከላከያ የሚሰጠው እንደህክምና ነው ወይንስ እንደ አገልግሎት?
ዶ/ር፡ ይህ መድሀኒት የሚሰጠው እንደአገልግሎት እንጂ እንደህክምና አይደለም፡፡ መድሀኒቱ በሆስፒታሉ የተለያዩ ክፍሎች ማለትም በቤተሰብ እቅድ ክፍል ፣በድንገተኛ ክፍል ፣በኤችአይቪ ክፍል ፣ተገድዶ መደፈር የደረሰባቸው በሚታከሙበት ክፍል ይገኛል፡፡ ስለዚህ ይህ አገልግሎት የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት አንዱ ዘርፍ ነው፡፡
ኢሶግ፡ ተጠቃሚዎች ወደሆስፒታል ሲመጡ በምን አይነት የመግባቢያ ዘዴ ይስተናገዳሉ?
ዶ/ር፡ ሆስፒታሉ በአገር ደረጃ ልዩ የሆነ ክፍል አለው። ይህም ክፍል የኃይል ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶችና ሕጻናት ፍትሕና እንክብካቤ ማእከል ሲሆን እነዚህ የኃይል ጥቃት የደረሰባቸው በቀጥታ በመምጣት ሪፖርት ያደርጋሉ ፡፡ በእርግጥ አንዳዶች ክፍሉ መኖሩን ስለማያውቁ ወደፖሊስ በመሄድ ያመለክቱና ወደእኛጋ ይላካሉ፡፡ ጥቃቱ ከተፈጸመ ወይንም ግንኙነት ካደረጉ ከ72/ ሰአት ወይንም ከአምስት ቀን በፊት ከሆነ እና እድሜያቸው በመውለጃ የእድሜ ክልል ውስጥ ከሆነ መከላከያውን እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡ ከአምስት ቀን ወይንም ከ72/ ሰአት በላይ ከሆነ ግን መከላከያው አቅሙ ስለሚደክምና ጥቅም ስለማይሰጥ አይሰጥም?
ኢሶግ፡ የአፋጣኝ ወሊድ መከላከያ መድሀኒት ለመውሰድ መስፈርቱ ምንድነው?ሰአቱስ?
ዶ/ር፡ የወሊድ መከላከያውን ለመስጠት መሟላት ያለባቸው ነገሮች አሉ፡፡
1/ በድንገተኛ ሁኔታ ወይንም በሓይል ጥቃት መደፈራቸውን መግለጽ
2/ እርጉዝ አለመሆኑዋ መረጋገጥ አለበት፡፡ ከግንኙነቱ በፊት አስቀድሞውኑ እርግዝና ተከስቶ ከሆነ ምንም ስለማይጠቅም መድሀኒቱ አይሰጥም፡፡ ሴቷ ባልተዘጋጀችበት ወይንም በድንገት በፈጸመችው ግብረስጋ ግንኙነት ምክንያት ከ72/ሰአት በፊት ለሕክምና ከመጣች የእርግዝና ምርመራው ውጤት ኔጌቲቭ ስለሚሆን መድሀኒቱ ይሰጣል፡፡
3/ የወር አበባ አይታ ሌላ የወር አበባ ጊዜ ካለፈ ...ለምሳሌ የወር አበባዋን ካየች ሁለት ወር ያለፋት መሆኑን ከገለጸች አሁንም መድሀኒቱን መስጠት አይቻልም፡፡ የዚህም ምክንያት እርግዝና ተከስቶ ሊሆን ስለሚችል ነው፡፡ በተቻለ መጠን የወር አበባዋ ከአራት ሳምንት ላልበለጠ ጊዜ የቆየ ሲሆን መድሀኒቱ ይሰጣል፡፡
ሰአቱን በሚመለከት በማንኛውም ቀንና ሰአት ለ24/ሰአት አገልግሎቱ የሚሰጥ ስለሆነ ማንኛዋም ተጠቃሚ የኃይል ጥቃት ከተፈጸመባት በአስቸኩዋይ ሪፖርት በማድረግ መከላከያውን መውሰድ ትችላለች፡፡
ኢሶግ፡ አፋጠኝ የወሊድ መከላከያው እንደመደበኛው የወሊድ መከላከያ ማገልገል ይችላልን?
ዶ/ር፡ ይሄ መሰረታዊና ለብዙ ሰዎች መልስ የሚሰጥ ጥያቄ ነው፡፡ አፋጣኝ የወሊድ መከላከያ በምን መንገድ እንደመደበኛው የወሊድ መከላከያ ሊያገለግል የማይችል መድሀኒት ነው፡፡ ይሄ መድሀኒት የተሰራው ግብረስጋ ግንኙነት ከተፈጸመ በሁዋላ እርግዝናን ለመከላከል እንዲያስችል ተብሎ የሆርሞን መጠኑ ከመደበኛዎቹ የሚጨምር ሲሆን እንደመደበኛዎቹ መከላከያዎች ጠንንራ ስላልሆነ አቅም የለውም፡፡ ለምሳሌ አንዲት ሴት ግንኙነቱ ከተፈጸመ ከሁለት ቀን በሁዋላ አፋጣኝ የእርግዝና መከላከያውን ብትወስድ ከ20-30 ኀ ያህል ያላትን የማርገዝ እድል አይሸፍንም፡፡ ይህ መድሀኒት የእርግዝና መከላከል አቅሙ ከ70 ኀ አያልፍም፡፡ መደበኛዎቹ ግን 99.5ኀ ያህል እርግዝናን የመከላከል አቅም ስላላቸው አስተማማኝ ናቸው፡፡ አፋጣኝ እርግዝና መከላከያው ግን ግንኙነቱ እንደተፈጸመ ወዲያውኑ ቢመጡ እንኩዋን ከ80 በመቶ በላይ አይከላከልም፡፡ ይህ መድሀኒት በትክክለኛው መንገድ ካልተወሰደ የወር አበባ መዛባትን ያስከትላል፡፡ የወር አበባ መዛባት የእርግዝና ሁኔታን ለመከታተል የሚያስቸግር ነው፡፡ መድሀኒቱ የሆርሞን መጠኑ ከፍተኛ ስለሆነ ማስመለስ ፣ማቅለሽለሽና ቁርጠት ይኖረዋል፡፡
ኢሶግ፡ አፋጣኝ የእርግዝና መከላከያው የሚያስከትለው ጉዳት ምንድነው?
ዶ/ር፡ Emergency contraceptive › አፋጥኝ የእርግዝና መከላከያ ሊወሰድ የሚገባው በአንድ የወር አበባ ኡደት ከሁለት ጊዜ በላይ መሆን የለበትም፡፡ ከዚያ በላይ የሚወሰድ ከሆነ፡-
የወር አበባ መዛባት ያስከተላል፡፡
የሆድ ቁርጠትና ማቅለሽለሽ ፣ማስመለስ የመሳሰሉት ከባድ ሕመሞች ይገጥማሉ፡፡
በማህጸን ላይ እጢ ቢኖር በመድሀኒቱ ምክንያት ያድጋል፡፡
አልፎ አልፎ የሚፈስ ደም ካላት፣
በጡት ላይ የሚከሰት ችግርን፣
የደም ግፊት ፣የምታጨስ ፣ቫሪኮስ ያለባት ሴት ...በተደጋጋሚ መከላከያውን ብትወስድ የጤና ችግርዋን ያባብሰዋል፡፡
ስለዚህ Emergency contraceptive አፋጥኝ የእርግዝና መከላከያ በአንድ የወር አበባ ወቅት በምንም ምክንያት ከሁለት ጊዜ በላይ መወሰድ የለበትም፡፡

Read 31741 times