Print this page
Saturday, 05 January 2013 10:27

በአራት ኪሎ ዩኒቨርስቲ በተቀሰቀሰ ብጥብጥ ተማሪዎች ተጎድተዋል

Written by  ሰላም ገረመው
Rate this item
(1 Vote)

የኦሮሞ ብሔር ተወላጆችን የሚነቅፍ ፅሁፍ በግድግዳ ላይ ተፅፎ ተገኝቷል
ፖሊስ መንስኤውን እያጣራሁ ነው ብሏል
ባለፈው ረቡዕ በአራት ኪሎ ዩኒቨርስቲ የወንዶች ዶርም ግድግዳ ላይ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆችን የሚነቅፍ ፅሁፍ ተፅፏል በሚል በተቀሰቀሰ ብጥብጥ፣ በበርካታ ተማሪዎች ላይ ጉዳት እንደደረሰ ምንጮች ተናገሩ፡፡ ፖሊስ የብጥብጡን መንስኤ እያጣራሁ ነው ብሏል፡፡ ምንጮች እንደገለፁት፤ በወንዶች ዶርም ግድግዳ ላይ የተፃፈውን የኦሮሞ ብሔር ተወላጆችን የሚነቅፍ ፅሁፍ ቀድሞ ያየው ተማሪ ለግቢው ፖሊስ ያመለከተ ሲሆን ፖሊሱም የተፃፈውን ፅሁፉ ወዲያው ያጠፋው ቢሆንም ፅሑፉ በሌላ ቦታ ላይም በመገኘቱ፣ ለብጥብጥ መነሻ ሆኗል ተብሏል፡፡

የብሔረሰቡ ተወላጆች የሆኑ ተማሪዎች ረቡዕ ማምሻውን “መብታችን ይከበር” በማለት ሌሎች ተማሪዎችን ከዶርም እንዲወጡ ሲቀሰቅሱ እንደነበረ  ምንጮች ጠቁመው፤ ወዲያው ፌደራል ፖሊስ ወደ ዩኒቨርስቲው በመግባት ነገሩን ለማረጋጋት የሞከር ሲሆን  ሀያ የሚሆኑ ተማሪዎችን “ለማነጋገር” በሚል ከግቢ ይዟቸው እንደወጣ ገልፀዋል፡፡ በነጋታው ጠዋት ላይ ግን ነገሩ እንደአዲስ መቀስቀሱን ተማሪዎች ይናገራሉ፡፡ በግቢው ውስጥ ተማሪዎች እርስ በእርስ በጀመሩት የድንጋይ ውርወራም በርካቶች እንደተፈነከቱ እንዲሁም ከፍተኛ 
ጉዳት የደረሰባቸው እንዳሉ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ምንጮች እንደሚሉት በጩቤ የተወጉ ተማሪዎች በአምቡላንስ ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል፡፡ ሐሙስ እለት የአራት ኪሎ አስፋልት በድንጋዮች ተሞልቶ የነበረ ሲሆን አካባቢው ጭንብል ባጠለቁ አድማ በታኝ ፖሊሶች ተከብቦ ነበር፡፡ አምቡላንሶችም ከዩኒቨርሲቲው ግቢ ሲወጡ ታይተዋል፡፡ ፖሊስ በብጥብጡ ተሳትፈዋል ያላቸውን ተማሪዎች በመኪና ጭኖ የወሰደ ሲሆን ሌሎች ተማሪዎችንም ከግቢው በማስወጣት ዩኒቨርሲቲው እንደተዘጋ ታውቋል፡፡  የብጥብጡን መነሻ መርምሮ እንዳልጨረሰ የጠቆመው ፖሊስ፤ አንዳንድ ተማሪዎች በግድግዳው ላይ የተፃፈ የኦሮሞ ብሄረሰብን የሚያንቋሽሽ ፅሁፍ ነው ሲሉ ሌሎች ደግሞ የዩኒቨርስቲው የፈተና ውጤት አሰጣጥ ለብጥብጡ መንስኤ ነው ብለው እንደሚናገሩ ገልጿል፡፡ በብጥብጡ የተጐዱ ተማሪዎች ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውን ፖሊስ ጠቁሞ፤ አንድም የሞተ ተማሪ አለመኖሩን አስታውቋል፡፡

Read 5063 times