Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 05 January 2013 10:36

“የጅብ እርሻ ነገር ሳያድግ በቡቃያው”

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

“ሕዝቦች የስልጣን ባለቤቶች ናቸው፡፡ የምርጫው ውጤትም በእጃቸው ላይ ነው፡፡ እናም ሁላችንም የምርጫ ካርድ እንውሰድ፡፡ ምርጫው ሰላማዊ፣ ነጻና ፍትሐዊ እንዲሆን የበኩላችንን ጥረት እናድርግ፡፡ ምርጫ ዘጠና ሰባት ያሳየንን የሕዝብ ጉልበት በተግባር ላይ እናውለው፡፡ አሁንም ከተደራጀንና በነቂስ ለምርጫ ከወጣን----ማሸነፍ በእጃችን ያለ አማራጭ መሆኑን አንዘንጋ---”
ከሙሼ ሰሙ (የኢዴፓ ፕሬዚደንት)
በአንድ ወቅት ወደ ሰሜን ሸዋ ለቅስቀሳ ከተላከው የቅንጅት አመራር ቡድን ጋር ተመድቤ ቅስቀሳውን ካጠናቀቅን በኋላ፣ ከአካባቢው አርሶ አደሮች ጋር የመወያየት እድል ገጥሞኝ ነበር፡፡ በቅስቀሳው እጅግ ደስተኛ የነበሩት አርሶ አደሮችን ማንን ትመርጣላችሁ ለሚለው ጥያቄ የሰጡኝ መልስ “ቅንጅትን” የሚል ነበር፡፡

ቅንጅትን በመምረጣቸው ቅንጅት መንግስት ከሆነ እንደማያሳፍራቸው አብራርቼ ምስጋናዬን ሳልጨርስ አንዱ አርሶአደር፡- “ይስሙኝ ጌታው-- ለኛ የመንግስት ለውጥ የምንሻው ለውጥ ፍለጋ አይደለም። ለውጥ ከአምላክ ብቻ መሆኑ ከገባን ውሎ አድሯል። ለዚህ ከቅንጅት የምንጠብቀው አንዳችም ለውጥ የለም፡፡ ጉዳያችን ያለው ከወዲህ ነው፡፡ ይሰሙኛል ጌታው” አሉኝ በድጋሚ፡፡ “አሮጌው መንግስት ወድቆ አዲሱ ሲተካ እንኳን ስልጣኑ መሬቱም ፈጥኖ አይረጋለትም፡፡ ታድያ አዲሱ መንግስት ጊዜ ፈጅቶ ርብራቡን አደላድሎ፣ እርካቡን ቆንጥጦ መግረፍ እስኪጀምር እንዲያው ቢያንስ ለሶስት አራት ዓመት ያህል ፋታ ስለምናገኝ ነው፡፡ ምን በላችሁ፣ ምን ጠጣችሁ፣ ድረስ ወጉ አይቀርብንም፡፡ እንዳው በተስፋ እንጠግባለን፡፡ ልጆቻችን በሰላም ቀያቸው ገብተው ይወጣሉ፡፡ ግብሩም አይጎዳንም፡፡ ስራም አንፈታም፡፡ ከብቱም ሰዉም መቅኖ አያጣም” አሉኝ፡፡
በጊዜው ጉዳዩን ያለ አርምሞ በሳቅ በፈገግታ እንደዘበት አልፌዋለሁ፡፡ ስምንት ዓመት መሆኑ ነው እንግዲህ፣ በጊዜ ሂደት ግን አርሶ አደሮቹ ከገሃዱ ዓለም የተማሩት እውነታ ዛሬ ፍንትው ብሎ እየታየ ነው፡፡ ከኢህአዴግ ሃያ አንድ ዓመት የስልጣን ዘመን በኋላ፣ ዛሬም ስለኑሮ ውድነት፣ ስለትራንስፖርት ችግር፣ ስለመብት ጥሰትና ስለጋዜጠኞች መታፈን፤ በግዳጅ የኢህአዴግ አባል ስለመሆን፣ ስለአስከፊ ሙስናና በስልጣን መባለግ፣ ስለአስተዳደራዊ በደል፤ በአጠቃላይ ስለ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ እያሰላሰልን እንድንኖር መገደዳችን የታሪካችን አስከፊ ገጽታ ነው፡፡ ስለመልካም ነገሮቻችን ለመወያየት እንችል ዘንድ ኢህአዴግ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ችግሮቻችንን አቅም በፈቀደ ፈትቶ ወይም ለአማራጭ ፖለቲካ ተገቢውን እውቅና ሰጥቶ ቢሆን ኖሮ የፍጥጫ ፖለቲካ ተረት መሆኑ አይቀሬ ነበር። እንዳለመታደል ሆኖ ግን ይህ ሳይሆን ቀረ፡፡ እሱም ሳያንስ ልዩነቶቻችን እንደተጠበቁ ሆነው፣ በዜጎች ገንቢና መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ለመነጋገር ክፍት የነበሩ ዝንባሌዎች እንዲሁም መልስ በሌለበትም ቢሆን ለመደማመጥ የነበረው እድል ተቀለበሰ፡፡ እንዲያ ባይሆንማ ኖሮ በመልካም ፋይዳዎቻችን ላይ መነጋገር ጭርሱኑ ቀርቶ፣ በችግሮቻችን ላይ ብቻ እንድናተኩር ባልተገደድን ነበር፡፡
ዛሬም በፍጥጫ ፖለቲካ ውስጥ ሆነን ለተቃውሞ ትኩረት የመስጠታችን ምስጢር፣ በኢህአዴግ እንደምንታማው ለተቃውሞ የተለየ ፍቅር ስላለን አይደለም፡፡ መብቶቻችንና ጥቅሞቻችን ከሕገ መንግስት አንቀጽነት ወጥተው በተግባር መረጋገጥ ስላልቻሉና ሃገራዊ ፋይዳችንና አንድነታችን በየእለቱ ፈታኝ ጥያቄ ውስጥ እየገባ በመዳከሩ እንደሆነ ኢህአዴግ ጠንቅቆ እንደሚያውቅ እገነዘባለሁ፡፡
የማያቋርጥ ውትወታችንና የተቃውሟችን ምስጢር ግን ጥያቄዎቻችንና ፍላጎቶቻችን በተግባር አለመሟላታቸው ብቻ አይደለም፡፡ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥያቄዎቻችን በቁርጠኝነት መንፈስ ቢጤኑ ያላቸው ሃገራዊ ፋይዳ እየታወቀ፣ በኢህአዴግ በኩል መፍትሔ የማያሻቸው ተራ ነገር ተደርገው መወሰዳቸው ጭምር ነው፡፡ ይህን በቅጡ ለሚያጤን ኢትዮጵያዊ፣ ኢህአዴግ ወደደም ጠላም ቁርጠኝነቱና የአሳታፊነት በሩ ይበልጥ እየሰፋ ሄዶ ወደ ምሉዕነት ካልገሰገሰ፤ የእርግማንና የማጥላላት ፖለቲካው በመቻቻልና እውቅና በመስጠት እንዲሁም በመከባበር እስካልተተካ ድረስ ለሚቀጥሉት በርካታ ዓመታትም ቢሆን የተቃዋሚዎች ታሪክ ድህነትን፣ የኑሮ ውድነትን፣ ስራ አጥነትነትን፣ የመብት ጥሰትንና ማህበራዊ ቀውስን መታገልና ማራገብ ሆኖ እንደሚቀር ጥርጣሬ የለኝም፡፡ ይህ ደግሞ የገንቢ ፖለቲካ መለኪያም ሆነ መልካም አስተዳደር የሚፈጥረው ትሩፋት መገለጫ እንደማይሆን አምናለሁ፡፡
ለምን ይሄ ይሆናል ? ከሃያ አንድ ዓመት ሕገ መንግስታዊ ስርዓት በኋላ፣ ዛሬም መብቶቻችን ቁልቁል እየተደፈቁና በኢህአዴግ ወቅታዊ ፍላጎት ይሁንታ ልክ እየተሰፈሩ የሚሰጡበት ጊዜ ላይ እንገኛለን፡፡ ዛሬም መጎልመስ ያቃተው በነጻነት የማሰብና ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ ጥያቄ ከበርካታ መሸራረፍ በኋላ፣ በጸረ ሽብርተኝነት ሕጉ አማካኝነት ቀለበት ውስጥ እንደወደቀ ይገኛል፡፡ የሃገራችን ኢኮኖሚ ልማትን እንጂ ዜጎችን ማማከል ባለመቻሉ ሁላችንንም በእኩልነት ማገልግል ተስኖታል፡፡ ሕገ-መንግስታችን ዜጎች ሁሉ እኩል ናቸው ቢልም በብዙሃኑ ድሃና በሕገ ወጥ መንገድ በከበሩ ጥቂት ሃብታሞች መካከል ያለው የኑሮ ልዩነት ሊቀራረብ በማይችልበት ደረጃ በእጅጉ ተራርቋል፡፡ “ኢኮኖሚያችን በሁለት ዲጅት ቢያድግም” የኑሮ ውድነቱና የገቢ ልዩነታችን ሰማይ ነክቷል፡፡ ሃገር በመዋጮ ይለማ ይመስል፤ ማብቂያ የሌለው የመዋጮ ጥያቄ፣ ከኪስ ብርበራ ባልተናነሰ ሁኔታ እየተፈታተነን ይገኛል፡፡ ሰፋፊ የመሰረተ ልማት ግንባታዎቻችን ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸው ይልቅ ፖለቲካዊ ይዘታቸው ስለሚጎላ ችግሮቻችንን ከስረ-መሰረቱ መቅረፍ አልቻሉም፡፡ የትራንስፖርት ችግር ጊዜያዊ መፍትሔን በመሻት ላይ ያተኮረ በመሆኑ ዘላቂ መፍትሄ መስጠት ስላልተቻለ ዛሬም ውጣ ውረዱና እንግልቱ ተስፋ አስቆራጭ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ “ቢፒአርና ካይዘን” ወይም ሌሎች መሰል የማኔጅመንት አሰራሮች ተዘረጉ ቢባልም፣ አስተዳደራዊ ፍትሕና መሰረታዊ አገልግሎቶችን ማግኘት ከባድ ዋጋ የሚያስከፈል ፈተና ነው፡፡ ፀረ-ሙስና ቢቋቋምም ሙስና የበርካታ ባለስልጣኖቻችንና ባለሟሎቻቸው የኑሮ መደጎሚያና የኢንቨስትመንት ማስፋፊያ መስክ ሆኗል፡፡ ጉቦ የኑሮአችን አካል ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ አዲስ ጥሪት መቋጠርም ሆነ ባፈራነው ጥሪት መተማመን ከንቱ ምኞት ነው፡፡ በገንዘባችን የገዛነውና ከዘመናት ጀምሮ ከቤተሰቦቻችን የወረስነው መሬትና የመኖርያ ቤት “ለህዝብ ጥቅም” በሚል ሶሻሊስታዊ መፈክር በሕግ ተነጥቀናል፡፡
ከተሞክሮአችን ስንነሳ፣ ኢህአዴግ ዘመናት ለቆጠሩና ቀስፈው ለያዙን ውስብስብ ችግሮች እራሱን ብቸኛ መፍትሄ ሰጪ ከማድረግ ይልቅ የችግሮቹን ታሪካዊ ዳራ አንጥሮ በማውጣት፣ የችግሩም ሆነ የመፍትሄው ባለቤትነትን የጋራ በማድረግ ልዩነቶችን ማክበርና አማራጮችን መቀበል ቢችል ኖሮ፣ ምንኛ በታደልን ነበር፡፡ እራስን “ሁሉ በኩሉ” አድርጎ በመሳል አማራጭ መፍትሄዎች በተነሱ ቁጥር በተነካሁ ባይነት መንፈስ፣ አላስፈላጊ ትግል ውስጥ መግባት ለውጤትም ሆነ ለለውጥ አያበቃም፡፡ ከውጥረት በሚመነጭ መንፈስ ቁጥር ስፍር የሌላቸውና ምሉዕ ያልሆኑ አቋራጭና ጊዜያዊ መፍትሄዎችን በመደርደር አማራጭ ሃሳቦችን ማጥቃት ለኢህአዴግም ሆነ ለሌላው የሚበጅ አይደለም፡፡ በዜጎች መሐል አላስፈላጊ ውዝግቦችን በመፍጠር ልዩነቶችን እያጎሉ ግጭትን ማካረርም ለልማትና ለእድገት የሚያሻንን ጊዜ ከማባከን ያለፈ ፋዳ የለውም፡፡
ኢህአዴግ ከዚህ ባሕርይው በመነጨም ቀስፈው ለያዙን መሰረታዊ ጥያቄዎች ዛሬም ከሃያ አንድ ዓመታት የስልጣን ዘመን በኋላ የሚሰጠን መልስ “ጥሩ እየሰራን ስለሆነ ተስፋ አድርጉና ታገሱን” የሚል ነው። ከምኞት በመለስ መፍትሄውን መዋጥ የሚተናነቀን ትዕግስታችን ዳቦ፣ ትራንስፖርትና የስራ እድል ሊሆን የሚችልበት ተአምራዊ አጋጣሚ ስለሌለ ብቻ ነው። ለዘመናት የዘለቀው የኢትዮጵያ ችግር በኢህአዴግ ጉልበትና አቅም ብቻ የሚፈታበት ዕድል ቢኖር ኖር መታገሱ ባልከፋ ነበር፡፡ ክፋቱ ግን ይሄ እውን ሊሆን የሚችልበት እድል ፈፅሞ እንደሌለ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡
ለችግሮቻችን በጋራ መፍትሔ የመሻት ዕድሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ መጥበቡን ቀጥሏል፡፡ በዚህ ላይ ኢህአዴግ ትዕግስታችን እንዲቀጥል የሚፈልገው ለተጨማሪ አርባና ሃምሳ ዓመታት ወይም ከዛም በላይ መሆኑ ደግሞ ይበልጥ አሳሳቢው ጉዳይ ነው፡፡ በኢህአዴግ “የልማት ጎዳና” ሃያ አንድ ዓመታትን አሳልፈናል፡፡ ይህ እንግዲህ የአንድ ጎረምሳ እድሜ ነው፡፡ በዚህ የኤሊ ጉዞ ውስጥ እየዳህን ስርነቅል ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ለውጥ መጠበቃችን ሳያንስ፣ ሌላ አርባና ሃምሳ ዓመታት ሊጨመርብን መታቀዱ ጭካኔ የተሞላበት በደል ነው፡፡ ለመሆኑ ተስፋ የምናደርገውና አሁንም ኢህአዴግን በተስፋ የምንጠብቀው ለምን ይሆን? ምሬታችን የምር ስላልገባው ወይስ ለአብዮታዊ ዴሞክራሲ የማይተናነቅ መፍትሔ እስኪያገኝ ድረስ? ያለተቀናቃኝ ለዘመናት በስልጣን ላይ መዝለቁ እስኪረጋገጥለት ወይስ አንዳች ተዓምራዊ ሃይል መፍትሄ በራዕይ እስኪያሳየው ድረስ? ይሄንንም በቅጡ ብናውቀው እኮ በጠበቅን ነበር፡፡
ሆኖም ምንም ሳንጨብጥ በባዶ ተስፋ ልንጠብቅ የማንችልበት በርካታ ተጨባጭ ምክንያቶች አሉን፡፡ አልሰማንም እንጂ የኑሮ ውድነቱን መሸከም አቅቶናል፤ የዋጋ ንረቱ መፈናፈኛ አሳጥቶናል፤ ምሳ በልተን እራት መድገም ካቃተን ሰንብተናል እያልን ነው፡፡ የኢህአዴግ ካድሬዎችና ቃል አቀባዮቹ ግን “የምን የኑሮ ውድነት፤ የምን የዋጋ ንረት- ቁርጥ ቤት፣ ክትፎ ቤትና ድራፍት ቤት ተጨናንቆ እያየነው!” ትሉናላችሁ፡፡ የኑሮ ውድነት አለ የሚሉት ጭፍኖች ናቸውም እንባላለን፡፡ እኛ ደግሞ ቁርጥ ቤት፣ ክትፎ ቤትና ውስኪ ቤት የሚያጨናንቁት የናንተ ሙሰኞች እንጂ እኛን አይመለከትንም ባይ ነን፡፡ በአሁኑ ወቅት የሚከፈለን ደሞዝ በአማካይ አንድ ሺሕ አምስት መቶ ብር ነው፡፡ የቤት ኪራይ አንድ ሺህ ብር፤ ምሳ በቀን አርባ ብር፣ በወር አንድ ሺህ ሁለት መቶ ብር ነው፡፡ መዋጮና ቤተሰብን፣ እንዲሁም ለጤናና ለክፉ ቀን የሚቆጠበውን ጨምሩበት፡፡ እንዴት ተደርጎ ይሆን ውስኪና ክትፎ ቤቶትን የምናጨናንቀው? ፅድቁ ቀርቶብኝ በቅጡ በኮነነኝ ይሏል ይሄ ነው፡፡
ይህ እንግዲህ ከተማ ውስጥ ያለው ችግር ነው፡፡ ወደ ገጠር ሲገባ ደግሞ የባሰ መሆኑ አሌ አይባልም፡፡ ዛሬም የማይካደው ሐቅ ቢኖር በሚሊዮኖች የሚቆጠሩትን አርሶ አደሮች ሕይወት በየዓመቱ በልማት ጀግናነት የሚሸለሙት ጥቂት አርሶ አደሮች እንደማይወክሉት ነው፡፡ በአንጻራዊነትም ቢሆን የተሻለ ደሞዝ ተከፋይ የሆነውን ከተሜ እንኳን የሚያንገዳግደው የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት፣ በአርሶ አደሩ ሕይወት ላይ ምን ያህል አዳጋች ፈተና እንደሚጋርጥበት ለመገመት አንዳችም ፍልስፍና አያሻውም፡፡
የስልጣን ዘመን ባልተገደበበት ሁኔታ በተገደበ አቅምና ዝግጁነት ውስጥ ሆኖ ለዘመናት መዝለቅ የሚሻ መንግስት፤ ዓይነተኛ ስራው በስታቲስቲክ ላይ የሚመሰረት የመረጃ ርብርብና የአዕምሮ ጥቅጠቃ ነው፡፡ የተመዘገበው እድገት የዜጎችን መሰረታዊ ችግር የፈታ ነው ወይ የሚለው ጥያቄ እንዲነሳ አይፈለገም። ዋናው ጉዳይ በስንት ፐርሰንት አድገናል የሚለው ብቻ ነው፡፡ የሚፈጠረው የስራ እድል ዘለቄታዊና አስተማማኝ፤ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው የተረጋገጠ ነው ወይ የሚለውም እንዲነሳ የሚሻ የለም፡፡ እድገቱ ኢኮኖሚያዊ ክፍትትን ይሞላል አይሞላም የሚለውም አይፈተሽም፡፡ “ስራ እየሰራሁ ነው” በሚል ተስፋ የተሞላና በምርጫ የሃይል አሰላለፍ ላይ ተፅዕኖ የሚያሳርፍ “ሕዝባዊ መንፈስ” መፈጠሩን ማረጋገጥ ብቻ በቂ ነው፡፡ ኢኮኖሚያዊ ተመላሽ የሌለውና ጊዜያዊ ችግርን የሚቀርፍ መፍትሄ የቱንም ያህል የዜጎችን አቅም ይበርብር እንጂ በመፍትሄነት ልዩ ትኩረት ይሰጠዋል። ፖሊሲን ለለውጥ አመቻችቶ በመቅረጽ ፖሊሲው በሚፈጥረው የስራ እድል አማካኝነት ተጨማሪ የስራ እድልን የሚፈጥር እቅድን ከመንደፍ ይልቅ ከአንዱ ሃብት ላይ ወይም የእለት ገቢ ላይ ቀንሶ የሌላውን ኑሮ ማካካሻ ማድረግ አማራጭ ሆኖ ይታያል፡፡ ይህ ሁሉ ሳያንስ ሰጭና ከልካይ የሆነ ልማታዊ መንግስት ግዙፍነቱ በሚፈጥርበት ቀርፋፋነት፣ ልክ የሌለው ቀዳዳና ክፍተት እየታገዘ ብክነት፣ ዝርክርክነት፣ ሙስና፣ አልፎ ተርፎ የሃላፊነትና የተጠያቂነት መላላት ሲጨመርበት ጉዞው ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡ ያኔ በበር የገባ የስምንት ዓመት ልማት በመስኮት መሽሎኩ አያጠራጥርም፡፡
የሕግ የበላይነትና አስተዳደራዊ ፍትሕ ወይም መልካም አስተዳደር በሕገ መንግስቱ ውስጥ የተረጋገጡ መሰረታዊ መብቶች ናቸው፡፡ እነዚህ መብቶች ዜጎች የእርስ በርስ ግንኙነታችንን በሰላማዊ መንገድ መምራት እንድንችል ሁኔታዎችን በማመቻቸት፣ ፍትሕንና መልካም አስተዳደርን በማስፈን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነታችንን ማረጋገጥ መቻላቸው አንዱና መሰረታዊ ፋይዳቸው ነው። ከዚህ የሚልቀውና ዓይነተኛ ፋይዳቸው ግን የሕግ የበላይነትና አስተዳደራዊ ፍትሕን በማስፈን፣ የታጠቀ ሃይል የሚያዝ መንግስት ዜጎች ላይ ሊያደርስ ከሚችለው ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥቃትና ተጽእኖ ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ መከላከልና መጠበቅ ነው፡፡
በዴሞክራሲያዊ አስተዳደር በገፉ ሃገራት ዜጎች የስልጣን ምንጭና የስርዓት ባለቤት ናቸው፡፡ ከዚህ እምነት በመነጨም መንግስት ስልጣን የሚያገኘው በሕግ ለተወሰኑ ዓመታት በውክልና ነው፡፡ በውክልና በሚያገኘው ስልጣን አማካኝነት ለዜጎች፣ ለሃገርና ለስርዓቱ ጥበቃ ያደርጋል፡፡ ከስርዓቱ ጋር የማይጋጩ ፖሊሲዎችን በመቅረጽ የዜጎችን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተግዳሮቶች ያቃልላል፡፡ ዜጎችን ከውስጣዊና ውጫዊ ጥቃት ይጠብቃል፡፡ ሉአላዊነታቸውንና ሰላማቸውን ያረጋግጣል፡፡ ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ ለዜጎች ጥቅም ብቻ ዘብ ይቆማል፡፡
በዲሞክራሲያዊ ጎዳና ብዙ ርቀት ባልሄዱ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሃገራት ግን የመንግስት ሚና ከዚህ ለየት ያለ ነው፡፡ ዜጎች ባሳለፉት የአፈና ዘመን በተፈጠረባቸው ተጽእኖ ምክንያት መንግስትን፣ ሃገርንና ስርዓትን አደባልቀው ማየታቸው የተለመደ ጉዳይ ነው፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ የሕገ መንግስታዊ ስርዓቱ ፈጣሪ ኢህአዴግ በመሆኑና በሌላ ተቃዋሚ ፓርቲ ሃገሪቱ የመተዳደር እድል ባለማግኘቷ ምክንያት፣ ልዩነቱን ለመረዳት እስከሚያዳግት ድረስ ስርዓት፣ መንግስት፣ ሕዝብና ሃገር የተደበላለቁ ናቸው። በዚህም ምክንያት መንግስት ሲፈተሽ፣ ሲመረመር፣ ሲብጠለጠል፣ ሃገርና ስርዓት ይፈርሳል፤ ብጥብጥ ይነሳል፤ ሁከት ይነግሳል፤ የሚል ስጋት በመንግስታት ዘንድ መነሳቱ የተለመደ ጉዳይ ነው፡፡ ስጋቱ ውሎ አድሮ መብትን በቁጠባ ማቃመስን፣ የመብት ጥያቄዎችን በጥርጣሬና በጎሪጥ ማየትን በማስከተል ለፍጹም የመብት ረገጣና አፈና አቀባብሎ መስጠቱ ግልጽ ነው፡፡ እንደዚህ አይነቱ ድርጊት ቀስ በቀስ ስር እየሰደደ በመጠናከሩ ሕገ መንግስታዊ የመብት ቁጠባው የመንግስት መብት ይሆኗል፡፡ ቀጥሎም ኢህአዴግ የማይነካበት፣ የማይወቀስበትና የማይከሰስበት ማማ ላይ እንዲሰቀል መንስኤ ሆኗል፡፡ ዛሬ ላይ፣ ኢህአዴግ ፍርሃትና የግንዛቤ እጥረት የፈጠሩትን ክፍተቶች ተጠቅሞ መንግስትን፣ ስርዓቱንና ሃገርን ዘለግ ሲልም ሕዝብን ተክቷል፡፡ በአጠቃላይ የኢህአዴግ መሰረታዊ ችግሮቹ የማይፈተሹና ድርጅቱም የማይወቀስ ወይም ተቃውሞ የማይነካው ሆኗል፡፡
የመብት ገፈፋን፣ የመልካም አስተዳዳር እጦትን፣ ኢኮኖሚያዊ ድቀትን፣ ድህነትንና የአስተዳደራዊ ፍትሕ መመናመንን ተከትሎ በመንግስት ላይ የሚነሱ ጥያቄዎችና ተቃውሞዎች ሃገርንና ስርዓትን እንደ መናድ ሙከራ እየተቆጠሩ፣ ጠያቂዎቹን ገና ከጅምሩ በማሸማቀቅ አጀንዳ ማስጣል የተለመደ ጉዳይ ነው። ውስብስብ የሕግ መሰናክሎቹ ሳይታከሉባቸው ዜጎች መብቶቻቸውን፣ ጥቅሞቻቸውን አልፎ ተርፎም ሕይወታቸውን ባላሰቡት ሁኔታና በድንገት ሲነጠቁ በመኖራቸው፣ ዛሬም ኑሮአቸውን የቆቅ አድርገዋል። ከመሞት መሰንበት መፈክራቸው ሆኗል፡፡ ቀላል በማይባሉ ዜጎች ዘንድ ከስራ ከመፈናቀል አቀርቅሮ መኖር፣ እሺ ባይነትና አድርባይነት ዋጋ እንዳላቸው አማራጮች መታሰብ ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡ በራስ ተነሳሽነት በራስ ላይ የሚፈጸም(Self inflicted) ተንበርካኪነትና እሺ ባይነት በበርካታ ዜጎች ዘንድ መስፈኑን ጠንቅቆ የተረዳውና የዜጎች ሃሞት መፍሰሱ የገባው ኢህአዴግም፣ ፍርሃቱንና ሃሞት መፍሰሱን የስልጣን ዘመኑ መደላድል አድርጎ መጠቀሙን ችሎበታል፡፡
መንግስታት በውክልና የተሰጣቸውን ስልጣን በአግባቡ ተጠቅመው፣ የዜጎችን ሁለንተናዊ ጥቅሞች ማረጋገጥ ካልቻሉ ኃላፊነታቸውን በብቃት አልተወጡም ከማለት ውጭ ሌላ ትርጉም ሊሰጠው አይችልም፡፡ ሃላፊነቱን በብቃት መወጣት ያልቻለ መንግስት ደግሞ ኃላፊነቱን በብቃት ሊወጣ ይችላል ተብሎ ለታመነበትና በዴሞክራሲዊ ምርጫ በሕዝብ ይሁንታ ለሚመረጥ አካል ስልጣኑን ማስረከብ አለበት፡፡ ምርጫ በማጭበርበር፣ በማሸማቀቅና በኢኮኖሚያዊ ጥቅም የሕዝብን ድምጽ መግዛት ለዛሬ ያውል ያሳድር ይሆናል እንጂ ለዘለቄታው ግን መፍትሄ ሊሆን አይችልም፡፡
ኢህአዴግ እንደፖሊሲ አቅጣጫ ይከተለውም አይከተለውም ዜጎች በውስብስብ ችግር መታሰራቸው ሳያንስ፣ መንግስት ከዜጎች ጫንቃ ሊያወርዳቸው በሚገቡ ዘመናዊ ጭቃሹምና ምስለኔዎች መብቶቻቸው እየተረገጡ ከዕለታት በአንዱ ቀን ሊመጣ ይችላል ተብሎ የሚተረክለትን ኢኮኖሚያዊም ሆነ አስተዳደራዊ ለውጥ በትዕግስት ሊጠብቁ አይገደዱም፡፡ በኢኮኖሚያዊም ሆነ በፖለቲካዊ መስፈርት ሊለኩ የሚችሉ ጥቅሞቻቸው ነገ ሳይሆን ከዛሬ ጀምሮ መከበርና መረጋገጥ አለባቸው፡፡ ነገ ሁልጊዜም ሌላ ቀን ነው፡፡ ስልጣን ለዜጎች ፍትሕና ርትዕን በማጎናጸፍ፣ ሁለንተናዊ ጥቅሞቻቸውን የሚያረጋግጥ መሳርያ እንጂ የሹመኞችን ህይወት ማበልጸጊያና የባለሟሎቻቸው መጠቃቀሚያ መሳርያ መሆን የለበትም፡፡
ከላይ ለማየት እንደተሞከረው አምባገነን መንግስታት መብት ለማፈን መሳርያ ከሚያደርጓቸው ስልቶቻቸው መካከል አንዱ ዜጎች የሚያነሷቸውን የመብት ጥያቄዎች ስርዓትን ከመናድ ጋር በማቆራኘት፣ ህዝብን በተጽእኖና በማሸማቀቅ መብቱን የማይጠይቅ፣ አማራጭ የማይሻና መድረሻ የለሽ ጥገኛ አድርገው መግዛት መቻላቸው መሆኑ ጥርጥር ለውም፡፡
ኢህአዴግ “ሕዝባዊ መንግስት” ስለሆንኩ ሕዝቡ “የኔ ነው” የሚል መሰረት የሌለው የተዛባ እምነት አለው፡፡ ሕዝብ ሲል በምን ዓይነት ተጨባጭ ሁኔታ ውስጥ የሚገኝ ሕዝብን ይዞ እየተጓዘ እንደሆነ በቅጡ ለመረዳት የቻለ አይመስልም፡፡ ኢህአዴግ አመነም አላመነም በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው ግን በነጻ መንፈስ ልቡ የተሞላና አንገቱን ቀና አድርጎ የሚራመድ፣ መብቱንና ግዴታውን ጠንቅቆ የሚረዳ፣ የራሱን መብት ለማስከበር የሌሎችን መብት የማይፃረር፣ ሳይሸማቀቅ ለምርጫ ወጥቶ ከአማራጮች ውስጥ ጥቅሙን መሰረት አድርጎ እነእገሌን እመርጣለሁ የሚለውን ዓይነት ሕዝብ እንዳልሆነ ግልጽ ነው፡፡
በግምት ለምርጫ ከደረሱ ሰላሳ ሁለት ሚሊዮን ዜጎች መካከል ስድስት ሚሊዮን አባል አለኝ በሚለው ኢህአዴግ ስሌት መሰረት፣ የዜጎች የነፍስ ወከፍ ትስስር ሲሰላ፤ በየአምስቱ ዜጎች መካከል አንድ የኢህአዴግ አባል እንዳለ ውጤቱ ይነግረናል፡፡ ስድስትም አስርም ሚሊዮን አባል መመልመል የፓርቲዎች መብት ነው የሚሉ በርካታ የዋሆች እንዳሉ እገምታለሁ፡፡ የዋህ ያልኳቸው በሌላ ምክንያት ሳይሆን ያልተረዱት ወይም ሊረዱት የማይፈልጉት ነገር እንዳለ ስለምገምት ነው፡፡ ኢህአዴግ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አባላትን መመልመል የሚችለው ልዩ የምልምላ ሙያ ስላለው አይደለም፡፡ ይልቁንም ቅድም ከጠቀስኳቸው ጉዳዮች በተጨማሪ ሁሉንም የመንግስት መዋቅሮች ጨምሮ መንግስታዊና ሕዝባዊ ተቋማትን የፓርቲ ስራ መዘወርያ ማሽን ስላደረጋቸው መሆኑን ግልጽ ነው፡፡ ይህ እንግዲህ በማንኛውም መስፈርት ጤናማ ምልመላ ሊባል አይችልም፡፡ በእርግጥ እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት ጉዳይ በፓርቲው ፍልስፍናና ፖሊሲዎች ተጠምቀው፤ በአስተሳሰብ ድጋፍ ከኢህአዴግ ጋር የተሰለፉ አባላት ጉዳይ እንደተጠበቀ ቢሆንም፣ ቀላል የማይባሉ አባላቱ ግን ዘለቄታ ላለው ጥቅማቸው ሳይሆን ለእለት ኑሮአቸው ሲሉ በኢህአዴግነት የሚመለመሉ መሆኑን የመልማዮቹና የተመልማዮቹ ልብ በቅጡ እንደሚረዳው በቂ ግንዛቤና ተመክሮ በሁላችንም ዘንድ መኖሩን አልጠራጠርም ፡፡
ኢትዮጵያ ለዘመናት የነገሰና ስር የሰደደ ድህነት፣ ስራ አጥነትና ማህበራዊ ቀውስ የተንሰራፋባት ሃገር ናት፡፡ ኑሮ ያደቀቃቸው ዜጎች ከመተዳደር ለመገዛት የተመቹ መሆናቸው ዓለም የመሰከረው እውነታ ነው። የስራ እድል፣ ትምህርት፣ የቀበሌ ራሽን፣ የጤና አገልግሎት፣ የመሰረተ ልማት ፍጆታ፣ የመኖርያ ቤት አቅርቦት በገዢው ፓርቲና በመንግስት ችሮታ ስር በተያዙባት ኢትዮጵያ፤ የኢህአዴግ አባል መሆን በተለይ ደግሞ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኘው ማህበረሰብ የመብት ጉዳይ ሳይሆን አማራጭ የሌለው የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ባይሆን ኖሮ በ2002 ምርጫ ኢህአዴግ 99.6 በመቶ ማሸነፍ ባልቻለ ነበር፡፡
ጤናማና ሚዛናዊ በሆነ ዴሞክራሲያዊ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ውስጥ አንጻራዊ ብልጫ ማስመዝገብ ፍትሐዊ ነው፡፡ ዘጠና ዘጠኝ ነጥብ ስድስት በመቶ በምርጫ ማሸነፍ ግን በመድብለ ፓርቲ ስርዓቱ ላይ ትልቅ ችግር መኖሩን ጠቋሚ ነው፡፡ ለንጽጽር ስለማይመች በዴሞክራሲ የበለጸጉት ሃገራትን የምርጫ ውጤት መፈተሹ የማይሞከር ነው፡፡ ይህም ሆኖ በሁለንተናዊ የድል ባለቤትነታቸው የሚተማመኑት ሶሻሊስቶችም ቢሆኑ ብቻቸውን እንደተወዳደሩ እያወቁ፤ የማይደግፋቸው ማህበረሰብ ሊኖር እንደሚችል ቀልባቸው ስለሚነግራቸው የምርጫ ውጤታቸውን ከዘጠና አምስት በመቶ በላይ አያሳድጉም፡፡ ከዚህ አኳያ ኢህአዴግ ለዴሞክራሲው ይቅርና ለቀልቡና ለጥላው እንኳን መታመን ያልቻለ ድርጅት መሆኑን ምርጫ 2002 በቂ ማረጋገጫ ነው፡፡
ሕዝቦች የስልጣን ባለቤቶች ናቸው፡፡ የምርጫው ውጤትም በእጃቸው ላይ ነው፡፡ እናም ሁላችንም የምርጫ ካርድ እንውሰድ፡፡ ምርጫው ሰላማዊ፣ ነጻና ፍትሐዊ እንዲሆን የበኩላችንን ጥረት እናድርግ። ምርጫ ዘጠና ሰባት ያሳየንን የሕዝብ ጉልበት በተግባር ላይ እናውለው፡፡ አሁንም ከተደራጀንና በነቂስ ለምርጫ ከወጣን እንዲሁም በስፋት ከታዘብን ማሸነፍ በእጃችን ያለ አማራጭ መሆኑን አንዘንጋ። የፊታችን ሚያዝያ በሚካሄደው የአካባቢና የአዲስ አበባ ምርጫ በንቃት በመሳተፍ ኢህአዴግን በምርጫ ማሸነፍ ይቻላል - ከአዲስ አበባ መስተዳደር፡፡
ምርጫው ነጻ ሊሆን እንደማይችል ከሂደቱ ከተረዳን፤ መራጮች ያለመምረጥ መብታችንን ተጠቅመን ከምርጫ መታቀብ አስፈላጊ ስልት ነው። ኢህደአዴግን መምረጥ የሚፈልገው ማህበረሰብ ከሃምሳ ፐርሰንት በታች ሊሆን እንደሚችል የምርጫ 2002 እውነታ ያስረዳል፡፡ ከበርካታ ምርጫ የማጭበርበር ድርጊት በኋላም፣ ከ45 ፐርሰንት በላይ የሚሆነው የአዲስ አበባ ነዋሪ ኢህአዴግን አልመረጠም፡፡ በዚህ መንገድ ምርጫው በቂ የህዝብ ይሁንታ ( Vote of confidence) የሌለውና ከሃምሳ ፐርሰንት በታች የሚሆኑ የኢህአዴግ አባላትና ደጋፊዎቹ ውጤት ብቻ መሆኑን ማሳየት ይቻላል፡፡
Read 8407 times