Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Print this page
Saturday, 05 January 2013 10:41

የፕሬዚደንት ግርማ የ60 ዓመት የአገልግሎት ዘመን ይከበራል Featured

Written by 
Rate this item
(3 votes)

በመጪው ዓመት መስከረም ወር መጨረሻ ላይ የሥልጣን ዘመናቸውን የሚያጠናቅቁት የኢፌዲሪ ፕሬዚደንት የተከበሩ ግርማ ወ/ጊዮርጊስ የ89 ዓመት ልደትና የስልሳ ዓመት የስራ ዘመን አገልግሎት በዓል የፊታችን ማክሰኞ ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝና ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እንዲሁም አምባሳደሮችና ታዋቂ ሰዎች በተገኙበት በሸራተን አዲስ እንደሚከበር ተገለፀ፡፡ከአፄ ኃ/ሥላሴ ዘመን ጀምሮ እስካሁን ድረስ በሶስት መንግስታት በተለያዩ የስራ ኃላፊነቶች ላይ እያገለገሉ የቆዩት ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ፤ ‹‹ለሃገር መስራትን የመሰለ ክብር ያለው ነገር የለም›› ይላሉ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ በዛሬው መርካቶ በድሮው ፊታውራሪ ሃብተጊዮርጊስ ሠፈር በታህሳስ 1917 ዓ.ም. የተወለዱት አቶ ግርማ ወ/ጊዮርጊስ፤ በእንግሊዞች ህብረት፣ በአርበኞች ትግልና መስዋዕትነት ጣሊያን ኢትዮጵያን ለቆ ከወጣ በኋላ በብሪትሽ አመራር በተቋቋመውና ብሪቲሽ ሚሊታሪ ሚሽን ቱ ኢትዮጵያ (British Military Mission to Ethiopia) በተባለው መ/ቤት በተራ ወታደርነት በሲግናል መገናኛ ክፍል ውስጥ በአስር አለቃነት ማዕረግ ተቀጥረው መስራት እንደጀመሩ ይናገራሉ፡፡
አውሮፕላን ለማብረር የነበራቸውን ፅኑ ፍላጎት ያውቁ የነበሩት ጃንሆይ፤ ለመከላከያ ሚኒስቴር ትዕዛዝ አስተላልፈውላቸው ወደ አየር ኃይል በመዛወር የአየር ትራፊክ ቁጥጥር ኃላፊ ሆነው ያገለገሉት ግርማ፤  በእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታቸው ኤርትራ ከሚገኘው የብሪትሽ ካውንስል ጽ/ቤት በአስተርጓሚነት ለጥቂት ጊዜ ከሰሩ በኋላ በኤርትራና በኢትዮጵያ የሲቪል አቪየሽን አሰራር በአለማቀፍ ደረጃ ታዋቂ እና ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸውን የህይወት ታሪካቸው ይጠቁማል፡፡የቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ የክብር ኮከብ ኒሻን የተሸለሙት ፕሬዚደንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ፤ በግል ለፓርላማ ተወዳድረው በማሸነፍ ጥቅምት 23 ቀን 1954 ዓ.ም በንጉሠ ነገሥቱ በተከፈተው ስብሰባ የፓርላማ አባል የሆኑ ሲሆን በ1954 ዓ.ም የመጀመሪያው ሴሽን የሁለተኛው ፓርላማ የመጀመሪያው ስብሰባ ፕሬዚደንት ሆነው ተመርጠዋል፡፡ ለሦስተኛ ጊዜ ያደረጉት የፓርላማ ውድድር ባለመሳካቱና ወደ መንግስት ስራ ዳግመኛ ላለመግባት በመወሰናቸው ወደ ግል 
ስራቸው በማምራት ንግድና እርሻን ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ በደርግ ስርዓት ደግሞ ዳግም ወደ መንግስት ስራ ተመልሰው የኤርትራ ጉዳይ ልዩ ኮሚሽን ኮሚሽነር፣ የእርሻ ልማት ሚኒስቴርና በኤርትራ የቀይ መስቀል ፕሬዚዳንት በመሆን አገልግለዋል፡፡ ካለፉት 11 ዓመታት አንስቶ እስካሁን ድረስ በኢፌዲሪ ፕሬዚዳንትነት በማገልገል ላይ የሚገኙት አቶ ግርማ ወ/ጊዮርጊስ፤ የፊታችን ማክሰኞ የ89 ዓመት ልደታቸውንና የ60 ዓመት የአገልግሎት ዘመን በዓላቸውን በሸራተን አዲስ እንደሚያከብሩ ታውቋል፡፡ የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበርና ሸራተን አዲስ በጋራ በሚያሰናዱት በዓል ላይ ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ የተለያዩ የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት፤ የውጭ አገር 
አምባሳደሮች፤ አትሌቶችና አርቲስቶች እንዲሁም ከአፍሪካ፤ ከአውሮፓና ከአሜሪካ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ይገኛሉ ተብሏል፡፡
በሌላ በኩል የአቶ ግርማን ከውልደት እስከ ጉልምስና የህይወት ዘመን በሚሸፍነውና በ1996 ዓ.ም. በበለጠ አበበ ተዘጋጅቶ በታተመው ‹‹ድሮና ዘንድሮ›› የተሰኘ መጽሐፍ ላይ የተመሰረተ ፊልም ሊሰራ እንደሆነ ታውቋል፡፡

 

Read 6776 times Last modified on Saturday, 05 January 2013 10:49

Latest from