Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Print this page
Saturday, 05 January 2013 10:42

የገና ዋዜማ እንግዶች 100 የዲላ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች አዲስ አድማስን ጐበኙ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

አንድ መቶ የሚሆኑ የዲላ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ክፍል ተማሪዎች ከትላንት በስቲያ ካዛንቺስ የሚገኘውን የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ጎበኙ፡፡ የጉብኝቱ ዓላማ ተማሪዎቹ በዩኒቨርስቲው ውስጥ ስለጋዜጠኝነት በንድፈ ሃሳብ ደረጃ የተማሩትን በተግባር ለማየትና እያንዳንዱን የስራ ሂደት ቦታው ድረስ ተገኝቶ ለመመልከት እንደሆነ የጉብኝት ቡድኑ ሃላፊዎች ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ አዲስ አድማስን  ከመጎብኘታቸው በፊት የኦሮሚያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት፣ ፋና ብሮድካስቲንግ፣ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅትንና የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ድርጅትን (ኢዜአ) እንደጎበኙ የጠቆሙት ከቡድን ሃላፊዎቹ አንዱ የሆኑት መምህር ኃይለመስቀል ዘውዴ፤ በትላንትናው ዕለት ዋልታን እንደጎበኙና ዛሬ ወደ ዲላ ዩኒቨርስቲው እንደሚመለሱ አስታውቀዋል፡፡

የዲላ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በየዓመቱ ተመሳሳይ የመስክ ጉብኝት እንደሚያደርጉ የቡድኑ ሌላው ሃላፊ መምህር ሰለሞን ታቦር ተናግረዋል፡፡ ተማሪዎቹ በአዲስ አድማስ ዝግጅት ክፍል በቡድን በቡድን ሆነው ባደረጉት ጉብኝት፣ የጋዜጣው ስራ የሚከናወንባቸውን የተለያዩ ክፍሎች ተዟዙረው የተመለከቱ ሲሆን በጋዜጣው ዝግጅት ክፍል ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚገኘውን “የአሰፋ ጎሳዬ መታሰቢያ ቤተመፃህፍት”ንም ጎብኝተዋል፡፡ ከጉብኝቱ ጎን ለጎንም ስለዜና ምንጮችና አሰባሰብ፣ ስለአምዶች ዝግጅት፣ስለሪፖርተሮችና ኤዲተሮች የስራ ሃላፊነት፣ ስለጋዜጣው ዲዛይን አሰራር፣ ስለማስታወቂያና ፅሁፎች ምጣኔ እንዲሁም በሌሎች ተያያዥ የስራ ሂደቶች ዙሪያ ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ተማሪዎቹ በመጨረሻም ስለጋዜጠኝነት ሙያዊ ስነምግባር፣ ወደፊት ስለሚጠብቃቸው ፈተናና ውጣ ውረድ ከጋዜጣው ዋና አዘጋጅ ከገጣሚ ነቢይ መኮንን ሰፊ ማብራርያ አግኝተዋል፡፡ ዋና አዘጋጁ በንግግሩ መግቢያ ላይ “አዲስ አበባን እንዴት አገኛችኋት?” በሚል ለተማሪዎቹ ላቀረበው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ላይ ተመስርቶ በሰጠው ማብራርያ፤ “ስለ አዲስአበባ ስጠይቃችሁ ስለኑሮ ውድነቱ፣ ስለህንፃው፣ ስለመንገዱ፣ ስለሽንት ቤቱ  አውርታችሁልኛል፡፡ ህዝቡን ግን አልጠቀሳችሁልኝም፤ የጋዜጠኝነት መሠረቱ ደግሞ ሰው ነው፡፡ Human side story እንዲሉ” በማለት ሁሌም በጋዜጠኝነት ሙያቸው ዋና ትኩረታቸውን ሰው ላይ እንዲያደርጉ ምሳሌዎችን በማጣቀስ አስረድቷል፡፡ ጋዜጣው ስለተቋቋመበት ዓላማ ሲያስረዳም “አዲስ አድማስ የፖለቲካ ጽንፍን ሳይሆን በጽንፎቹ መካከል ያለ ማንም አንባቢ እንዲያነብ፣ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ንባብ እንዲስፋፋ ነው የተቋቋመው” ያለው ገጣሚ ነቢይ መኮንን፤ የጋዜጠኛን ዋነኛ ኃላፊነት ለተማሪዎቹ ሲያብራራ “ጋዜጠኛ Watchdog ነው፡፡ ጋዜጠኛ መንግሥትን በዓይነ ቁራኛ በመከታተልና የመንግሥትን አካሄድ በማሳየት ሲሳሳት ወይም ወዳልሆነ አቅጣጫ ሲሄድ፣ ለህዝብ የሚያሳውቅ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ መረጃ ያለው ህብረተሰብ ለመፍጠር ይጠቅማል” ብሏል፡፡ ከዓመት በኋላ ተመርቀው ወደ ጋዜጠኝነት ስራ እንደሚገቡ ለሚጠበቁት ተማሪዎቹ ሙያዊ ምክር ሲለግስም ፤ “ጋዜጠኞች ኢንተርቪው ለማድረግ ሲሄዱ ለአለባበሳቸው ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው ያለው ዋና አዘጋጁ፤ “ቦታውን የሚመጥን መልካም አለባበስ ለሥራው መቃናት ይጠቅማል፡፡ አለባበሳችንን አይቶ ቅድመ ፍርድ የሚሰጥና ለመረጃ ክፍት ላለመሆን በሩን የሚዘጋ ሰው ሊኖር እንደሚችል አንርሳ፤ ጋዜጠኛ እንደ አርቲስት simple ነው የሚለው ነገር የሚያዋጣ አይመስለኝም” በማለት ለተማሪዎቹ አብራርቷል፡፡ ከአዲስ አድማስ መስራቾች አንዱ የሆነው ነቢይ መኮንን ጋዜጠኛ እንዴት ጊዜውን መጠቀም እንዳለበት ሲያስረዳም “ጋዜጠኛ የጊዜ አጠቃቀም ማወቅ አለበት፤ ከሳምንት እስከ ሳምንት ራሱን ማዘጋጀት ይጠበቅበታል” ብሏል፡፡ከሶስት ዓመት በፊት የተመሰረተበትን 10ኛ ዓመት በዓሉን ያከበረው አዲስ አድማስ፤ በታህሳስ 1992 ዓም “እኔ ማወቄ የሚገባኝ ህዝብ ሲያውቅ ነው” በሚል አነጋገሩ በሚታወቀው አቶ አሰፋ ጎሳዬ ጠንሳሽነት የተቋቋመ 
ፖለቲካዊ፤ ማህበራዊ ፤ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ጥበባዊና ባህላዊ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ በመስራት የሚታወቅ የግል
ጋዜጣ ነው፡፡

Read 5621 times

Latest from