Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 05 January 2013 11:14

ጨረቃ እንደ ፀሐይ

Written by 
Rate this item
(6 votes)

ጥልቅ የሆነ የንባብ ፍቅር ያደረበት ልጅ እያለ ነው። ቤተሰቦቹም ቀለም ቀመስ ስለሆኑና ኑሯቸውም የተደላደላ ስለነበር የንባብ ጥማቱን ለማርካት ችግር አልገጠመውም፡፡ በሀገሪቱ ውስጥ ለሚታተሙ ሳምንታዊ እና እለታዊ ጋዜጦች እንዲሁም መጽሔቶች አመታዊ ክፍያቸው ተከፍሎ ቤቱ ድረስ ይመጡለታል። መጽሐፍቶችማ ትልቁን የቤታቸውን መደርደሪያ ተርፈው በየቦታው ነው ተዝረክርከው የተቀመጡት፡፡
አነበበ፣ አነበበ፣ አነበበና … ጭንቅላቱ በእውቀት ተወጠረበት፡፡ እውነትም ጭንቅላቱ ይከብደው ነበር፡፡

ወላጆቹ በፕሮግራም የሚኖሩ አይነት ነበሩ፡፡ ለልጅ አወላለዳቸውም እቅድ ነበራቸው፡፡ እናት በመጀመሪያ መንታ ወንድ ልጆች ዱብ አደረጉ! እነዚህ ህጻናት ገና ከመሬት ከፍ ሳይሉ ከእናትና አባት ማናቸው እንደሆኑ እንጃ እንጂ ተሳሳቱና እናት ጸነሱ፡፡ እና ያለ እቅድ፣ ሳይፈለግ የመጣውን ጽንስ ተመካክረው እንዲጨናገፍ ወሰኑ፡፡ መንደርተኛው ወልደው ማሳደግ አቅቷቸው ጽንስ አጨነገፉ ብሎ እንዳያማቸው ማጨናገፉን በድብቅ፣ በባህላዊ ዘዴ እንዲሆን ተስማሙ፡፡ ያሰቡት ሁሉ ግን አልሆነም፡፡ ምንም ቢሞከር ጽንሱ አልጨነገፍም ብሎ ሶስት፣ አራት … ዘጠኝ ወር ሆነውና ሲያነብ ጭንቅላቱ የሚከብደው ልጅ ተወለደ፡፡ 
ሲያነብ ሲያነብ … ሀሳብ መጣላት፡፡ “ለምንድነው እኔ ጽሑፎቼን ለየጋዜጦቹ እና መጽሔቶች ዝግጅት ክፍል የማልከው?” ብሎ ራሱን ጠየቀ፡፡ ይህን እስከዛሬ ባለማሰቡ ራሱን እንደሞኝ ቆጠረ፡፡ “ጅል” ብሎ ተሳደበ ራሱን፡፡
አዲስ አሳቡን ለእናቱና አባቱ አካፈላቸው፡፡ እነርሱም በጽንስነቱ ወቅት በወሰኑበት የሞት ቅጣት ዱላ ጨንግፎ ሳይጨነግፍ አካሉ ቀጭጮ፣ ጭንቅላቱ ተልቆ፣ የአእምሮው እድገት ዘገምተኛ ሆኖ ለተፈጠረው ልጃቸው ተጠያቂዎች (ጠያቂ ባይኖርም) እነርሱ ስለሆኑ ልጃቸውን ባዩ ቁጥር በሀዘን ይጎዳሉ፡፡ ያሳዝናቸዋል። ስለሚያዝኑለት ይንከባከቡታል፡፡ ስለዚህ ሃሳቡን ሲያማክራቸው ሁለቱም በደስታ ተቀበሉት፡፡
ጻፈ -ብዙ ደብዳቤዎች ለተለያዩ ጋዜጦች እና መጽሔቶች፣ ለተለያዩ አምዶቻቸው ጻፈ፡፡ አሁን ማንበቡን አቆየና ለጋዜጦች እና መጽሔቶች መጻፍ ላይ ብቻ አተኮረ፡፡ በመቶ የሚቆጠሩ ጽሁፎች ልኮ ፖስታዎች ፈጀ፡፡ ከነዚህ መሀል ግን አንዱም ጽሑፍ የትኛውም ጋዜጣ እና መጽሔት አምድ ላይ ታትሞለት አያውቅም፡፡ ቢሆንም መጻፉን ቀጠለ፡፡
“ለሕጻናት” ከሚሉት አምዶች አንስቶ አያሌ ማህበራዊ፣ ባህላዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ለሚዳሰስባቸው፤ ብዙ የፍልስፍና ሃሳቦች ለሚሰፍርባቸው አምዶች ጻፈ፡፡ እናትና አባቱ እሱን ላለማሳዘን “አይዞህ፣ ጽሑፎችህ ይታተሙልሃል” ይሉታል፡፡ መቼም ቢሆን እንደማይታተሙለት ግን ያውቃሉ፡፡ “ተራ እየጠበቁ ነው” ብለው ይነግሩታል፣ እና ይጽፋል … ይጽፋል! ጭንቅላቱም ይከብደዋል፡፡
አንድ ቀን አባቱ ልብስ ሊቀይሩ ቁም ሳጥናቸውን ሲከፍቱ በውስጥ በኩል ባለው መስታወት ምስሉ ታየው፡፡ “ኧረ አባዬ! እየኝማ ጭንቅላቴ ካንተ ጭንቅላት ይበልጣል … ታድዬ!” አላቸው፡፡ አባት “አአዎ” አሉና የመጣባቸውን እንባ ዋጡት፡፡ በየጊዜው የራስ ቅሉ መጠን እያደገ በመሄድ ላይ ነው፡፡ ጽሑፎቹን የሚልክላቸው፤ ተገዝቶለትም የሚያነባቸው ሶስት ጋዜጦች ታትመው የሚወጡት በአንድ ድርጅት ስር ነው፡፡ ጋዜጦቹ አመታዊ የምስረታ በአላቸውን ሲያከብሩ ከደረሷቸው አስቂኝ የደብዳቤ መልዕክቶች መሃል በየአምዶቻቸው ስር ጥቂቶቹን ይዘው ወጡ፡፡ ከነዚህም ውስጥ አብዛኞቹ ደብዳቤዎች በኤልሻዳይ የተጻፉ ነበሩ፡፡
አንባቢዎች ደብዳቤዎቹን ወደዷቸው፡፡ ሆዳቸውን ታቅፈው፣ አይናቸውን እየጠረጉ በሳቅ ተንፈረፈሩ፡፡ ከህፃን ልጅ አንደበት እንደሚሳሙ ቃላት ጣፋጭ፣ የዋህ፣ ባዶና አስቂኝ ነበሩ፡፡ ሲያነብ፣ ብዙ ሲያስብ ጭንቅላቱን ከሚከብደው ኤልሻዳይ የተጻፉት ደብዳቤዎች ርዕሰ አንቀጽ ይሁን ብሎ የተፃፈው ጽሑፍማ … ውይ ሲያስቅ!
ከዚያን ጊዜ ወዲህ በአንባቢያን ጥያቄ መሰረት በየሳምንቱ በቅምሻ መልክ የኤልሻዳይ ጽሑፎች ከነበሩበት ተፈልገው ታተሙ፡፡ ብዙዎች ወደዱዋቸው፤ ሳቁባቸው፡፡ ኮሜዲያን ከጽሑፎቹ በመነሳት አጫጭር ጭውውቶችን ጻፉ … ጨረቃ ፀሐይ ሆነች፡፡ ምንም ጽሑፎቹ ብዙ ቢሆኑም ያለማቋረጥ በየጊዜው በመታተማቸው አለቁ፡፡ የጋዜጦቹ አዘጋጆች ኤልሻዳይ ደብዳቤ ላይ ባገኙት አድራሻ ስልክ ደወሉ፡፡
“እባክዎትን ኤልሻዳይን ፈልጌ ነበር?” ስልኩን ያነሳችው የኤልሻዳይ እናት ናት፡፡
“ማን ልበል? ከየት ነው?”
“ከ Posterity ጋዜጣ”
“ኤልሻዳይ የለም” ሀዘን የተጫነው ድምጽ፡፡
“የት ሄዶ ነው?”
“አይ ይይ…!”
“ችግር አለ?”
“አዎ --- ኤልሻዳይ አርፏል”
“መቼ?!”
“አመታዊ በአላችሁን ከማክበራችሁ ጥቂት ቀደም ብሎ”
“በጣም ያሳዝናል፡፡ እግዚአብሔር ያጥናችሁ። የፈለግነው ተጨማሪ ጽሑፎችን እንዲያዘጋጅልን ነበር። እናዝናለን …”
በነጋታው የኤልሻዳይ ዜና-እረፍት ሞኛ-ሞኝ ጽሑፎቹ ይቀርቡበት በነበረው ቦታ ታወጀ፡፡

Read 6785 times