Saturday, 05 January 2013 11:41

የቤተ እስራኤላውያኑ ምሬት በተስፋይቱ አገር

Written by  አልአዛር ኬ
Rate this item
(1 Vote)

እኔ ታዋቂ በሆነው የእስራኤል የህክምና ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ተምሬ በዶክትሬት ዲግሪ የተመረቅሁ ሃኪም ሆኜ ሳለ፣ እዚሁ ቤርሽባ ከተማ በሚገኘው የሶርኮ ሆስፒታል ውስጥ እንድሠራ የተመደብኩት ግን በሀኪምነት ሳይሆን ህሙማንን ከበር ተቀብዬ እንዳስተናግድ ብቻ ነበር--”
ቤተእስራኤላዊ ዶክተር
ካለፈው የቀጠለ
የእስራኤል የአዲስ መጤዎችና የውህደት ሚኒስትር የሆኑት ሶፋ ላንድቨር፤ ቤተእስራኤላውያን እየደረሠባቸው ያለውን የዘርና የቀለም መድልዎ በመቃወም ድምፃቸውን ማሠማት መጀመራቸዉንና የተለያዩ የመብት ጥያቄዎቻቸውንም ለእስራኤል መንግስት ማቅረባቸውን የቆጠሩት፣የእስራኤል መንግስት ከከበረ ድንጋይ ያሠራውን ድንቅና ውድ የአንገት ጌጥ ምንነቱንና ዋጋውን ጨርሳ ለማታውቀው ሰጐን እንዳሠረላት አድርገው ነው፡፡

ሌሎች የእስራኤል ከፍተኛ ባለስልጣኖችም ቤተእስራኤላውያን እግራቸው የእስራኤልን ምድር ከረገጠበት ቀን አንስቶ “ኢትዮጵያ ውስጥ ከነበሩበት እጅግ አስከፊ የድህነት፣ የረሀብ፣ የበሽታና የጦርነት አስከፊ ህይወት ውስጥ በማውጣት ለእስራኤል ዘመናዊና የተደላደለ ኑሮ በማብቃት” የዋለላቸውን አቻየለሽ ውለታ ባለመረዳት ተገቢውን ዋጋ አልሠጡትም በሚል የሰነዘሩት ቅሬታ ቤተእስራኤሉ ዘንድ መድረሱ አልቀረም፡፡
እነዚህ ከፍተኛ የእስራኤል ባለስልጣናት የመንግስታቸው እጅ አመድ አፋሽ መሆኑ ተሰምቷቸው፣ በንዴትና በቅሬታ የተንጨረጨሩት እንዲሁ በባዶ ሜዳ እንዳልሆነ ለማስረዳት የሚያቀርቡት ማስረጃ የቤተእስራኤል “Poster Boys” (የተሳካላቸው ቤተእስራኤላውያንን) ነው፡፡ “ሁልሽም በጣም በሚያስገርምና በሚያሳፍር ሁኔታ የረሳሽው ነገር ቢኖር የተከበረው የእስራኤል መንግስት ከዚያ እጅግ አስከፊ የኢትዮጵያ የረሀብ፣ የበሽታ፣ የድህነትና የጦርነት ኑሮ መከራውን አይቶ ባያወጣሽና ለዚህ የተደላደለ ዘመናዊ የእስራኤል ህይወት ባያበቃሽ ኖሮ ዛሬ አዳሜ ዘርሽ እንኳ አይገኝም ነበር! ከመጣችሁ በሁዋላስ ቢሆን ምን ጐደላችሁ? የእናንተው ሰው የሆነው ፖለቲከኛው ሸሎሞን ሞላ፣ የተከበረው የእስራኤል ክኔሴት (ፓርላማ) አባል-- ኧረ እንዲያውም አፈጉባኤ ሁሉ ሆኖላችኋል፡፡ አንድ የእናንተው ልጅም በዝነኛው የእስራኤል የመከላከያ ሠራዊት ውስጥ የእኛ ልጆች በቀላሉ ሊያገኙት የማይችሉትን የኮሎኔልነት ማዕረግ ማግኘት ችሏል፡፡ ሌሎች የእናንተው ዘመዶችም ዶክተሮች፣ ዲፕሎማቶች፣ ጠበቆች፣ ተመራማሪዎችና የፋሽን ሞዴሎች ለመሆን በቅተዋል፡፡ የውጭ ጉዳይ መስሪያቤታችን በእስራኤል መንግስት መልካም ፈቃድ የተነሳም፣የእናንተው እህት የሆነችውን በላይነሽ ዝቫድያን እትብቷ በተቀበረበትና ባደገችበት ሀገር በኢትዮጵያ የእስራኤል መንግስት ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር አድርጐ ሾሞላችኋል። ቆይ! ከዚህ የበለጠ የእስራኤል መንግስትና ህዝብ ምን ያድርጉላችሁ? ምንስ ይፍጠሩላችሁ?” በማለት (በተለይ የአዲስ መጤዎችና የማዋሀድ ሚኒስትሯ ሱፋ ላንድቨርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቪግዶር ሊይበርማን) ሽንጣቸውን ገትረው ይከራከራሉ፡፡
አንድ ሰው ተጫምቶት ሲጓዝበት የነበረውን ጫማ ተጫምተው ቢያንስ ጥቂት መቶ ሜትሮችን እንኳ ሳይጓዙ በስሜት ብቻ በመገምገም፣ ስለዛ ሰውዬ አካሄድም ሆነ ፍጥነት የሚሰጥ ውሳኔ መቼም ቢሆን እንደ ትክክለኛ ግምገማና ውሳኔ ሊቆጠር አይችልም፡፡ የእስራኤል ከፍተኛ ባለስልጣናት ስለቤተእስራኤላውያን ያቀረቡት ክርክር ግን በስሜታዊነት ብቻ የቀረበ ነው፡፡ ያቀረቡት ክርክር የታሪኩን ሙሉ ስዕልና ዝርዝር ጨርሶ የማያሳይ ብቻ ሳይሆን ለማሳየትም አንዳችም አይነት ሙከራ የማያሳይ ነበር፡፡
የእስራኤል ባለስልጣናት ስለ ቤተእስራኤላውያን ስኬትና “ሁሉም ነገር መልካም” (all is good and fine for them) እንደሆነላቸው ለማሳየት የሚጠቅሷቸው “Poster Boys” ዛሬ ከደረሱበት የተሻለ ደረጃ ላይ ለመድረስ ምን አይነት የዘር ልዩነትና የቀለም መድልኦ እንደደረሰባቸው ለአንዴም እንኳ አውስተውት አያውቁም፡፡ ባለስልጣኖቹ እነዚያ ቤተእስራኤላውያን የዛሬውን የተሻለ ደረጃ ለማግኘት ምን ያህል ፈርጀ ብዙ የሆነ ችግር ተጋርጦባቸው እንደነበር ተናግረው አያውቁም፡፡ የእስራኤል ባለስልጣናት ቤተእስራኤላውያን የተጋረጠባቸውን ከፍተኛ ችግር ተቋቁመው ለማለፍ ከተቀረው የእስራኤል ማህበረሰብ በተለየ ሁኔታ እጥፍ ድርብ መስዋዕትነት ከመክፈል በቀር የተለየ ምርጫ እንዳልነበራቸውና አሁንም እንደሌላቸው መቼም ቢሆን በይፋ መስክረው አያውቁም፡፡
ለምሳሌ ቤተእስራኤላዊው አቭርሃም ይስሃቅ፤ በ1999 ዓ.ም ቤርሽባ ከሚገኘው ታዋቂወ የቤን ጉርየን ዩኒቨርሲቲ በህክምና ሳይንስ በዶክትሬት ዲግሪ በመመረቅ ሃኪም ለመሆን የበቃ የመጀመሪያው ቤተእስራኤላዊ መሆኑን የእስራኤል ባለስልጣናትና የህክምና ባለሙያዎች አንስተው አይጠግቡም ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ዩኒቨርሲቲው፤አቭርሃም ወደ እስራኤል ከመሄዱ በፊት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጥቁር አንበሳ ህክምና ፋካልቲ የሁለተኛ አመት ትምህርት መከታተሉን ለመቀበል እንኳ ፈቃደኛ እንዳልነበረ፣ ሁለት ጊዜ የመግቢያ ፈተና መውሰዱንና ሁለቱንም በከፍተኛ ውጤት ማለፉን እንዲሁም ወደ ዩኒቨርሲቲው ገብቶ መማር ከጀመረበት አንስቶ እስከተመረቀበት ጊዜ ድረስ ስለደረሰበት የዘርና የቀለም ልዩነት መድልዎ፤ ከተመረቀ በኋላም በእንዴት ያለ የስራ መደብ እንዲያገለግል እንደተደረገ አንዲትም ቃል እንኳ ተንፍሰው አያውቁም፡፡
እነዚህ የእስራኤል ባለስልጣናትና የህክምና ባለሙያዎች እንዲያው ሌላው እንኳ ቢቀር የእስራኤል የሂብሩ ቋንቋ ጋዜጦች ስለእሱ ያወጡትን ዘረኛና ክብረ ነክ ዘገባዎች ሃይ ለማለት ጨርሰው ፈቃደኞች አልነበሩም፡፡
ዶክተር አቭርሃም ይስሃቅ ያንን እጅግ ፈታኝ ጊዜ ሲያስታውስ፤“በእያንዳንዱ ቀን የከፋ የዘረኝነት ጥቃትና መድልዎ ይደርስብኝ ነበር፡፡ ከዩኒቨርሲቲው ቤተመጽሐፍት መጽሐፍ ለማግኘት እንኳ በጣም እቸገር ነበር፡፡ የዘረኝነት ጥቃቱ አስከፊ ስለነበር ስነልቦናዬን ጨርሶ አቃውሶት ነበር፡፡ ነገር ግን የደረሰብኝን ችግር ሁሉ ተቋቁሜ ከማለፍ በቀር ሌላ ምርጫ አልነበረኝም። ጥርሴን ነክሼ በመታገል ከተመረቅሁ በኋላም ቢሆን ችግሩ አልለቀቀኝም፡፡ ልብ አድርግ! እኔ ታዋቂ በሆነው የእስራኤል የህክምና ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ተምሬ በዶክትሬት ዲግሪ የተመረቅሁ ሃኪም ሆኜ ሳለ፣ እዚሁ ቤርሽባ ከተማ በሚገኘው የሶርኮ ሆስፒታል ውስጥ እንድሠራ የተመደብኩት ግን በሀኪምነት ሳይሆን ህሙማንንን ከበር ተቀብዬ እንዳስተናግድ ብቻ ነው፡፡ ለእነሱ ሰዎች ቢሆን ኖሮ (ከቤተእስራኤላውያን ውጪ ላሉት ዜጐች) ይህንን አይነት ስራ እንኳን ለተመረቀ ሀኪም ይቅርና ገና በትምህርት ላይ ላለ “ድሬሰር” እንኳ አይሰጡትም፡፡ ግን ምን ታደርገዋለህ? ይህንንም ተቋቁሞ ከማለፍ በቀር ሌላ ምርጫ የለኝም” ብሏል። (ዶክተር አቭርሃም አሁን እዚያው እስራኤል የጦር ሃይሎች ሃኪም ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል)
ያኔ ዶክተር አቭርሃምን በተመለከተ ሰፊ ዘገባ ያቀረቡ የእስራኤል የሂብሩ ቋንቋ ጋዜጦች የመጀመሪያም ሆነ የመጨረሻ ትኩረታቸው ከነበሩት ሁለት ጉዳዮች አንደኛው “በረሃብ፣ በበሽታና፣ በጦርነት ከምትታወቀው ሀገር ከኢትዮጵያ የመጣው ወጣቱ አቭርሃም ይስሃቅ፤ ሲጀመር ወደ ዝነኛው የቤን ጉርየን ዩኒቨርሲቲ እንዴት መግባት ቻለ? (ማን አባቱ ነው ያስገባው በሚል ቅሬታ አይነት) የሚለው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የሚሰጠውን ከፍተኛ ትምህርት ለዚያውም “እጅግ የተራቀቀውን የእስራኤል “የህክምና ሳይንስ” ትምህርት እንዴት መረዳት ቻለና ጭራሽ እንደሌሎቹ እስራኤላውያን እሱም በዶክትሬት ዲግሪ ለመመረቅ በቃ የሚለው ነበር፡፡
አቭርሃም ይስሀቅ በታዋቂ የእስራኤል ዩኒቨርሲቲ የተመረቀ ዶክተር ቢሆንም ለእስራኤል ባለስልጣናት በተለይ ደግሞ ህሙማንን ከሆስፒታሉ ግቢ በር ላይ እየተቀበለ እንዲያስተናግድ ብቻ ለመደቡት የሶሮኮ ሆስፒታል ሃላፊዎችና የህክምና ባለሙያዎች ግን ገና “አምሀ - አረትዝ” ወይም ቤተእስራኤል በመሆኑ እውቀትም ሆነ ችሎታ የሌለው ሰው (እነሱ እንዳሉት ደደብ ላለማለት) ነው፡፡ እንደ ዶክተር አቭርሃም ይስሃቅ ሁሉ ሌሎች ቤተእስራኤላውያንም በእስራኤል ምድር መኖር ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ እለት በዕለት የሚደርስባቸውን ከፍተኛ የዘርና የቀለም ልዩነትና መድልዎ በመቋቋም በህክምና፣ በህግ፣ በዲፕሎማሲ፣ በፖለቲካ፣ በምርምርና በፋሽን ኢንዱስትሪው መስክ ተሰማርተው የተሻለ ስኬት ማስመዝገብ ችለዋል፡፡
ይሁን እንጂ እነዚህ በእጅ ጣቶች ልክ እንኳ የማይቆጠሩ “የተሳካላቸው” የተባሉት ቤተእስራኤላውያን ከሚወክሉት የህዝብ ቁጥር አንፃር ሲለካ፣ በተለይ ደግሞ ከቀረው የእስራኤል ህብረተሰብ ጋር ሲነፃፀር እዚህ ግባ የማይባሉና ሁሉም አይን ውስጥ ቢገቡ እንኳ ጨርሶ የማይቆረቁሩ ናቸው፡፡
የኔዘርላንድ ሰዎች “ደረቅ ሳል የሞትን መቃረብ የሚያበስር ጡሩምባ ነው” ይላሉ፡፡ ቤተእስራኤላውያን እየደረሰባቸው ያለውን የዘርና የቀለም ልዩነት ችግር አስመልክቶ ማሰማት የጀመሩት የተቃውሞ ድምጽም እንደዚሁ ነው፡፡ ከፊት ለፊታቸው የተጋረጠባቸውን ፈርጀ ብዙና መጠነ ሰፊ ችግር ለመቋቋም ባለመቻላቸው የተነሳ፣ በቀላሉ ወደሞት እየገፋቸው ወዳለ አስከፊ ህይወት ውስጥ እየሰመጡ መሆናቸውን የሚያመለክት የጩኸት ድምጽ ነው፡፡
ባዶ ጆንያ መቼም ቢሆን ራሱን ችሎ አይቆምም፡፡ የቤተእስራኤላውያኑ ጩኸትም ባዶ ጆንያ መሆናቸውንና ራሳቸውን ችለው ለመቆም አለመቻላቸውን የሚጠቁም ነበር፡፡ ጭልፊት አሞራ ዝንብ ይዞ አይበላም የሚባለው ራስን ለማዋደድና ሌላውን አቃሎ ለማየት ነው፡፡ የእስራኤል መንግስትም ሆነ ተራው ህዝብ የቤተእስራኤላውያኑን ድምጽ ለመረዳት የሞከሩት በጣም በሚያስገርም ሁኔታ ገልብጠው ነው፡፡ ይህን ያደረጉትም ጉዳዩ ስላልገባቸው ወይም ስላልተረዱት ሳይሆን ራሳቸውን ለማዋደድና የቤተእስራኤሎችን ጩኸት ለማቃለል በማሰባቸው ብቻ ነው፡፡
የሆኖ ሆኖ የእስራኤል ባለስልጣናትም ሆነ ሌሎቹ የቤተእስራኤላውያኑን ጉዳይ በተመለከተ ቀደም ብሎ በተገለፀው አይነትና ሁኔታ ለመከራከር መሞከራቸው በግልጽ ማረጋገጥ የቻለው አንድ እውነት ቢኖር፣ እስራኤላውያን ቆሻሻ ልብሳቸውን አደባባይ ላይ አውጥተው በሰዎች ፊት ለማጠብ አለመፈለጋቸውን ብቻ ነው፡፡ ምንም እንኳ ጠቅላላ ሁኔታው እንዲህ አይነት መልክ ቢኖረውም የእስራኤል መንግስትና ባለስልጣኖቹ የሚተርኩት ሌላም ታሪክ አላቸው። እስራኤል ውስጥ ከሙት ባህር አጠገብ ከሚገኙት አለታማ ተራሮች መካከል አንዱ “ማሳዳ” ይባላል፡፡ በዚህ በሳዳ ተራራ ላይ በ70 አመተ አለም ታላቁ ሄሮድስ ሁለት ታላላቅና ምርጥ ቤተመንግስቶችንና ጠንካራ የመከላከያ ምሽግ በመገንባት ለቅንጦት ህይወት ያለውን ፍቅርና ጠላቶቹ እንዳያጠቁት የነበረውን ከፍተኛ ፍርሃት ለመላው አለም አሳይቶበታል፡፡
የማሳዳ ተራራ ግን ከዚህ ይልቅ በመላው አለም ዘንድ ተለይቶ በይበልጥ የሚታወቀው 916 የሚሆኑ አይሁድ ተዋጊዎች ከሄሮድስ የሮማ ወታደሮች ጋር የመጨረሻውን ውጊያ ያካሄዱበትና በሮማውያን እጅ ሰብአዊ ክብራቸው ተገፎ፣ በባርነት ከመኖር ይልቅ ሞትን በመምረጥ ራሳቸውን በራሳቸው ያጠፉበት ታሪካዊ ቦታ መሆኑን ነው፡፡
ቀደም ባለው ጊዜ እስራኤላውያን አይሁዶች ማሳዳን ለሰብአዊ ክብርና ለነፃነት የሚደረግ ትግልና የሚከፈል መስዋዕትነት ዋና ምልክት አድርገው በመቁጠር፣ ተሰደው ይኖሩ በነበረበት ቦታ ሁሉ የሚደርስባቸውን ይህ ቀረሽ የማይባል የዘር መድልዎና የሰብአዊ ክብራቸውን መዋረድ በመቃወምና በመታገል ከፍተኛ መስዋዕትነትን ሲከፍሉ ኖረዋል፡፡
የዛሬው የእስራኤል ትውልድና መንግስትም ስለ አሁኗ እስራኤል ሲያስረዱ፣ የማሳዳን ገድል መቼም ቢሆን የማይዘነጉት እስራኤላውያን አይሁዶች፣ ዛሬ የሚኖሩላት ሀገር እስራኤል እንደ ማሳዳ ተዋጊ ዜጐች ለነፃነታቸውና ለሰብአዊ ክብራቸው መከበር የህይወት መስዋዕትነት ለመክፈል የማይገደዱባት፣በነፃነትና በክብር የሚኖሩባት ሀገር መሆኗን ይበልጥ ለማስረገጥ ነው፡፡
ነገር ግን እንዲህ ያለው የእስራኤላውያን ገለፃ ከሁሉም ይልቅ በደንብ ሊያብራራልን የሚችለው “ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ” የሚለውን የኢትዮጵያውያኑን አነጋገር ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ተጨማሪ ነገር መናገር ከተቻለ ሊጠቀስ የሚችለው ዋና ጉዳይ፣እስራኤላውያን የራሳቸው ታሪክ እስረኞች መሆናቸውን ነው፡፡ እንደ እውነቱም ከሆነ እስራኤላውያንና መንግስታቸው የትናንትና ታሪካቸውን እንጂ አሁን ምን እየፈፀሙ እንደሆነ ቀልብና ልቦናቸውን ሰብስበው ራሳቸውን የሚመረምሩበት የጥሞና ጊዜ ጨርሶ ያገኙ አይመስሉም፡፡ እነሱ የዛሬዋ እስራኤል፣ ህዝቦቿ ሰብአዊ ክብራቸውና ነፃነታቸው ተከብሮና ተጠብቆ በእኩልነት የሚኖሩባት ሀገር ናት ቢሉም በገሃድ የሚታየው እውነታ ያሉትን ማረጋገጥ ይቅርና በመጠኑ እንኳ የሚደግፍ አይደለም፡፡ ለምን ቢባል ከጠቅላላው የእስራኤል ህዝብ አንድ ነጥብ አምስት በመቶ የሚሆነውን የሚወክሉት ቤተእስራኤላውያን ከኢትዮጵያ ነቅለው በመውጣት፣ የተስፋዋና የቃል ኪዳኗ ሀገራችን በሚሏት በእስራኤል መኖር ከጀመሩበት ካለፉት ሃያ ሰባት አመታት ጀምሮ የእለት ተዕለት ህይወታቸውን የሚገፉት በዘርና በቀለማቸው የተነሳ፣ ነፃነታቸው ክፉኛ ተረግጦና ሰብአዊ ክብራቸው ክፉኛ ተዋርዶ ነው፡፡
የእስራኤል ራቢኔት ወይም የሀይማኖት መሪዎች ጉባኤ በ1975 ዓ.ም የቤተእስራኤላውያኑን አይሁድነት በመቀበል የእስራኤል “የመመለስ ወይም የአሊያህ ህግ” (The Law of Return) መሠረት፣ ወደ እስራኤል እንዲገቡ ካዘዘ ከአስር አመት በኋላ፣የእስራኤል መንግስት መጀመሪያ በ1985 ዓ.ም በዘመቻ ሙሴ ከዚያም በ1991 ዓ.ም በዘመቻ ሰሎሞን አማካኝነት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ቤተእስራኤላውያንን “የስጋዬ ቁራጭ፣ የአጥንቴም ፍላጭ” ብሎ በአስገራሚና አስደናቂ ሁኔታ ወደ ቅድስቲቱና የተስፋዋ ሀገር እስራኤል እንዲገቡ ማድረግ ችሏል። ቤተእስራኤላውያኑን ያሳፈረው የመጀመሪያው አውሮፕላን ቴልአቪቭ በሚገኘው የቤን ጉርየን አውሮፕላን ማረፊያ እንደደረሰም የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩትን ይስሃቅ ሻሚርንና በአንድ ወቅት እስራኤልን በጠቅላይ ሚኒስትርነት የመሩትን ጀነራል ኤሁድ ባራክን ጨምሮ በርካታ የእስራኤል መንግስት ባለስልጣናትና እስራኤላውያን እንግዶች ቤተእስራኤላውያኑ ከተሳፈሩበት አውሮፕላን ወርደው ገና እግራቸው መሬቱን እንደነካ ስለተጐሳቆለው ሰውነታቸውና ስለ አዳፋው ልብሳቸው ትንሽም እንኳ የመጠየፍ ስሜት ሳያሳዩ፣እቅፍ አድርገው በመሳም “ወደ ተስፋዋ ሀገራችሁ እንኳን በደህና መጣችሁ!!” በማለት መልካም ምኞታቸውን ገልፀውላቸው ነበር፡፡
ያ የእስራኤል ከፍተኛ ባለስልጣናትና የተራው ህዝብ የእንኳን ደህና መጣችሁ መሳም ግን የ”ይሁዳ መሳም” ነበር፡፡ ሆኖም ቤተእስራኤላውያኑ የእስራኤል መንግስት ለዘመናት በተስፋና በጉጉት ሲጠባበቋት ወደነበረችው ሀገር እስራኤል በማምጣት የዋለላቸው ውለታ በእጅጉ ከብዷቸው ስለነበር፣ ከምስጋና ውጭ ለስሞታና ለማማረር የሚሆን ትንሽም እንኳ ጊዜ አልነበራቸውም፡፡ እናም አስከፊ ለሆነ የዘርና የቀለም ልዩነትና መድልዎ እንዲሁም ለከፋ የሰብአዊ ክብራቸው መዋረድ አሳልፎ የሰጣቸው ያ የባለስልጣናት የ”ይሁዳ መሳም” እንደሆነ ለመረዳት ጥቂት ወራት ፈጅቶባቸው ነበር፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ በቅርጫቱ ውስጥ ያስቀመጥነውን አሳና በቤታችን እያስተናገድነው ያለውን ጥቁር እንግዳ ጠረን መቀየሩን ወይም ላፍንጫ ያዝ ማድረጉን ለማወቅ ከሶስት ቀን በላይ መጠበቅ አያስፈልግም፡፡ ቀድሞ የጐመራው የእስራኤል ባለስልጣናትና ህዝብ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልካም ምኞት፣ ከሁሉም ቀድሞ ለመጠውለግ ሶስቱን ቀናት እንኳ ለመጠበቅ አላስቻለውም፡፡ የእስራኤል መንግስትና ህዝብ ቤተእስራኤላውያኑን በዘራቸውና በቀለማቸው የተነሳ እንደ እውነተኛ ወገናቸውና የእስራኤል ዜጋ አድርገው ከልባቸው ለመበል በከፍተኛ ሁኔታ መቸገራቸውን ወይም ጨርሶ አለመፈለጋቸውን በይፋ ማሳወቅ የጀመሩት በ1985 ዓ.ም የተካሄደው ዘመቻ ሙሴ በወጉ መጠናቀቁ ገና በይፋ እንኳ ሳይነገር ነበር፡፡
ቤተእስራኤላውያኑም ለሺ አመታት ሲያልሙትና ሲመኙት የነበረው ወደ ቅድስቲቱና የተስፋዋ ሀገር እስራኤል ለመግባትና ከምታፈልቀው የማርና ወተት ሲሳይ ለመንበሻበሽ የነበራቸው ታላቅ ተስፋ እንደጉም በኖ መጥፋቱን የተረዱት እግራቸው የቃል ኪዳኗን ሀገር ሀ ብሎ ከረገጠበት ከሶስት ወራት በኋላ ነበር፡፡ በዘራቸውና በቀለማቸው የተነሳ ከእስራኤል ጠቅላላ ማህበረሰብ የኑሮ ደረጃ ውስጥ ለእነሱ የተፈቀደው የኑሮ ደረጃ የትኛው እንደሆነ አቅጣጫው የተነገራቸው ያኔ የዛሬ ሃያ ሰባት አመት ነበር፡፡
የሃያ ስድስት አመቱ ቤተእስራኤላዊ ተማሪ ሞላት አራሮ፣ እየደረሰበት ያለውን ከፍተኛ የዘር መድልዎና ልዩነት አደባባይ በመውጣት፣ በአንድ ሰላማዊ ሠልፍ ላይ የገለፀው “እባካችሁ እንደ አውሬ አትዩኝ፣ እኔም እንደናንተው ሰው ነኝና እባካችሁ ስሙኝ” የሚል መፈክር በማንገብ ነበር፡፡ “በ1980ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ወላጆቻችን ወደ እስራኤል በገፍ ሲመጡ ልክ ገነት እንደገቡ ያህል ተሰምቷቸው ነበር፡፡ በእስራኤል የገጠማቸው ግን ጥላቻ ብቻ ነው፡፡ እኔን እንደሰው ሳይሆን ልክ እንደ በረሮ በመቁጠር፣ ማንም እየመጣ ሳያመናጭቀኝና ሳያንገላታኝ ያሳለፍኩት አንድም ቀን እንኳ የለም” ይህን የተናገረው ደግሞ በአንድ የገበያ ማዕከል ተቀጥሮ የሚሠራው የ40 ዓመቱ ቤተእስራኤላዊ ጐልማሳ አዲሱ ሞሀል ነው፡፡
የስምንትና የአስራ አንድ አመት ሴት ልጆቿን ተቀብሎ የሚያስተምርላት የእስራኤል ትምህርት ቤት በማጣቷ ቤት ውስጥ ለመዋል የተገደደችው ቤተእስራኤላዊቷ ከፊሳ በበኩሏ፤“ለረጅም አመታት የቆሻሻ በርሜሎችን ከመድፋትና የመንግስትን ዳረጐት ከመጠባበቅ ያለፈ ህይወት እንዳይኖረን ተደርገን መኖራችን በጣም እጅግ በጣም አንገሽግሾናል” በማለት ምሬቷን ገልፃለች፡፡
ቤተእስራኤላውያኑ እንደዚህ ያሉትን መራራ የብሶት ድምጾች እንዲያሰሙ ያደረጋቸውን አስከፊ የዘር ልዩነትና መድልዎ እንዲሁም ከፍተኛ የሰብአዊ ክብር መዋረድ በደል የዛሬ ሃያ ሰባት አመት አሀዱ ብለው በመቀደስ የጀመሩት የስልጡኗና ሁሉም ዜጐች በእኩልነት ይኖራሉ የሚባልባት እስራኤል “የሰለጠኑ” ጋዜጦች ነበሩ፡፡
የአይሁድ ቅድስ መጽሐፍ በሆነው ታናካህ “ላሾን ሃራ” ወይም በሰዎች ላይ የሚሠነዘር ክፉ ንግግር አይሁዶች ሊፈጽሙት ይችላሉ ከሚባሉት ታላላቅ ሃጢያቶች ውስጥ አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ ዘመቻ ሙሴ መካሄድ ከጀመረበት ቀን አንስቶ የእስራኤል የሂብሩ ቋንቋ ጋዜጦች በቤተእስራኤላውያን ላይ ይዘውት ይወጡ የነበረውን በለየለት ዘረኝነት የተሞላና ሰብአዊ ክብራቸውን የሚያንቋሽሽ ዘገባ ያስተዋለ፣ይህ ሃይማኖታዊ ትዕዛዝ ፈጽሞ የተሻረ ወይም ለእነሱ የተፈቀደላቸው ቢመስለው ጨርሶ አይፈረድበትም፡፡
የእስራኤል የሂብሩ ቋንቋ ጋዜጦች ቤተእስራኤላውያኑን “በአፍሪካ ጫካ ወስጥ ሲኖሩ የነበሩና፣ ምንም አይነት ስልጣኔ ያልነካቸው “ታርዛን” ህዝቦች፣ ጫማቸውን ማቀዝቀዣ ውስጥ የሚያስቀምጡና ልብሳቸውንም በሽንት ቤት መቀመጫ ላይ የሚያጥቡ እጅግ ኋላቀር ህዝቦች፣ ከአስራ ሶስተኛው ክፍለ ዘመን በእስራኤል አውሮፕላን ተሳፍረው በቀጥታ ወደ ሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን የመጡ፣ ምንም አይነት ነገር ቢነግሯቸውም ሆነ ቢያስተምሯቸው ጨርሶ የማይገባቸው “አምሀ አርትዝ” ህዝቦች፣ ከሁለት አመት ህፃን ልጅ ባነሰ ሁኔታ እሳትና ፍትፍትን እንኳ ለይተው የማያውቁ የጨለማው አህጉር ጨለማ ህዝቦች ወዘተ” በማለት ሰብአዊ ክብራቸውን የሚያዋርድና መሠረታዊ መብታቸውን የሚጋፋ ከፍተኛ የዘረኝነት ዘመቻ ከፍተውባቸው ነበር፡፡
(ይቀጥላል)

Read 5132 times