Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 12 January 2013 09:22

የቅ/ሲኖዶስ አስቸኳይ የምልአተ ጉባኤ ስብሰባ ሰኞ ይጀመራል

Written by 
Rate this item
(3 votes)

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ አስቸኳይ የምልአተ ጉባኤ ስብሰባውን የፊታችን ሰኞ፣ እንደሚያካሂድ ተገለጸ፡፡ በሲኖዶሱ አቸስኳይ ምልአተ ጉባኤ ስብሰባ፣ በሀገር ውስጥ እና በሰሜን አሜሪካ በስደት በሚገኙት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት መካከል በተጀመረው የዕርቅና ሰላም ውይይት ቀጣይነት ላይ በመነጋገር ዐቢይ ትርጉም ያለው ውሳኔ ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
አዲስ አድማስ ከጠቅላይ ቤተክህነቱ ምንጮች እንደተረዳው፤ ሲኖዶሱ በዕርቅና ሰላም ውይይቱ ቀጣይነት ላይ የሚወያየው፣ ከኅዳር 26-30 ቀን 2005 ዓ.ም በዳላስ ቴክሳስ በተካሄደው የዕርቀ ሰላም ጉባኤ የተሳተፈው ልኡክ በሚያቀርበው ሪፖርት ላይ በመመሥረት ነው፡

፡ የዳላሱ የሰላም ጉባኤ ኅዳር 30 ቀን 2005 ዓ.ም ያወጣው የጋራ መግለጫ እንደሚያመለክተው ውይይቱ ከቀደሙት ጊዜያት በተሻለ መከባበርና መደማመጥ የታየበት፣ በውግዘት የተለያዩት አባቶች በመንፈሳዊ አገልግሎት ሱታፌ ያደረጉበት፣ በተለይም በአራተኛው ፓትርያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ወደ አገር መመለስ ለዕርቀ ሰላሙ ስኬታማነት ዋንኛ መሠረት እንዳኾነ የጋራ ስምምነት የተደረሰበት በመኾኑ በዕርቀ ሰላሙ ይረጋገጣል ተብሎ ለሚጠበቀው የቤተ ክርስቲያን ሰላም እና አንድነት ተስፋ ሰጪ ኹኔታ አሳድሯል፡፡
ሁለቱ ወገኖች የአራተኛ ፓትርያሪክ ወደ አገር መመለስ የዕርቀ ሰላሙን ስኬት የሚወስን ዋነኛ ነጥብ መኾኑን ይስማሙ እንጂ በኢትዮጵያው ቅዱስ ሲኖዶስ ልኡካን በኩል “ቅዱስነታቸው ወደ ቅድስት አገራቸው ገብተው፣ ክብራቸው ተጠብቆና የሚያስፈልጋቸው ሁሉ ተሟልቶላቸው እርሳቸው በፈለጉት ቦታ ይኑሩ” የሚል አቋም በመያዙ በውጭ የተቋቋሙ “የስደት ሲኖዶስ” ተወካዮች ደግሞ አራተኛው ፓትሪያርክ “ወደ መንበረ ፕትርክናቸው ይመለሱ” የሚል አቋም በመያዛቸው ከሚፈለገው ስምምነት ላይ ለመድረስ አልታቻለም፡፡ ይኸው ልዩነት የውይይቱን ሂደት በማራዘሙ አራተኛውን የዕርቀ ሰላም ጉባኤ ከጥር 16-18 ቀን 2005 ዓ.ም በካሊፎርኒያ ሎሳንጀለስ ለማካሄድ ቀጠሮ ተይዟል፡፡ ቅ/ሲኖዶስ ከነገ በስቲያ ሰኞ የዕርቀ ሰላም ልኡካኑን ሪፖርት ሙሉ ይዘት በማዳመጥ የሚያደርገው ውይይት እና የሚያሳልፈው ውሳኔ በካሊፎርኒያ ለሚካሄደው አራተኛው የሰላም ጉባኤ ቀጣይነት ታላቅ ትርጉም እንዳለው ተመልክቷል፡፡ በዚሁ ስብሰባም የዕርቀ ሰላም ውይይቱን ሲያስተባብር የቆየው የሰላም እና አንድነት ጉባኤ በአዲስ መልክ ስለሚቋቋምበት አልያም ተደማጭነት ባላቸው ተጨማሪ አባላት ስለሚጠናከርባት ኹኔታ ውይይት እንደሚካሄድ ይጠበቃል፡፡
በሌላ በኩል በዕርቀ ሰላሙ ስለሚረጋገጠው የቤተ ክርስቲያን አንድነት ሲባል “ስድስተኛውን ፓትርያርክ ከመሾም እንታገሥ” በሚሉና “ዕርቀ ሰላሙ ይቀጥል፤ ስድስተኛውንም ፓትሪያርክ እንሹም” በሚሉት ሊቃነ ጳጳሳት መካከል ተፈጥሯል በሚባለው የአቋም ልዩነት ሳቢያ የሰኞው አስቸኳይ የምልአተ ጉባኤ ስብሰባ በውጥረትና በተለያዩ ተጽዕኖዎች የተሞላ ሊኾን እንደሚችል የዜናው ምንጮች ለዝግጅት ክፍሉ አስረድተዋል፡፡
“ዕርቀ ሰላሙ ይቅደም” የሚሉት አባቶች ሲኖዶሱ ለስድስተኛው ፓትርያርክ ምርጫ ዕጩ ሊቃነ ጳጳሳትን የሚያቀርብ አስመራጭ ኮሚቴ መሠየሙን በጥብቅ የሚቃወሙ ሲኾን “ዕርቀ ሰላሙ ቀጣዩን ፓትርያርክ ከመሾም ጋር ግንኙነት የለውም” የሚሉ አባቶች ደግሞ አስመራጭ ኮሚቴ መቋቋሙን በመደገፍ ኮሚቴው በአስቸኳይ ሥራውን እንዲጀመር ግፊት በማድረግ ላይ መኾናቸው ተገልጧል፡፡ ዕርቀ ሰላም ሳይፈጸም የሚከናወን የአዲስ ፓትርያሪክ ሢመት ቤተ ክርስቲያኒቱን ክፉኛ ሊከፋፍላት እንደሚችል በተለያዩ ሚዲያዎች የወጡ የካህናትና ምእመናንን የተማኅፅኖ መግለጫዎች በማሳሰብ ላይ እንደሚገኙ መዘገባችን ይታወሳል፡፡
ሰኞ በመንበረ ፓትርያሪኩ በሚካሄደው አስቸኳይ የምልአተ ጉባኤ ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ በሀገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ከ48 ያላነሱ ሊቃነ ጳጳሳት አዲስ አበባ በመግባት ላይ መኾናቸው ተዘግቧል፡፡ ሲኖዶሱ በታኅሣሥ ወር መጀመሪያ ላይ ያጸደቀው የፓትርያሪክ ምርጫ ሕገ ደንብ በስብሰባው ዳግመኛ እንዲመከርበት መጠየቁ የምልአተ ጉባኤው ተጨማሪ አከራካሪ አጀንዳ ሊኾን እንደሚችል ምንጮቹ አክለው ገልፀዋል፡፡

Read 5751 times