Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 12 January 2013 09:31

ክቡር ሚኒስቴር በመልስዎ ውስጥ ያልነገሩን መልሶች Featured

Written by 
Rate this item
(4 votes)

ሙሼ ሰሙ (የኢዴፓ ፕሬዚዳንት)
ላለፉት ስምንት ዓመታት ለመሰረተ ልማት ግንባታ ከፍተኛ ትኩረት የሰጠው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ልማትንም ሆነ እድገት በማያወላዳ መልኩ ማረጋገጥ አልቻለም፡፡ አወዛጋቢ ቢሆኑም ኢኮኖሚያችን ላለፉት ስምንት ዓመታት ከአምስት ፐርስንት አጠቃላይ ዓመታዊ ምርት እድገት ተነስቶ አሁን ወደ አስር ፐርሰንትና ከዛም በላይ እንዳደገ በርካታ ዋቢዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡
ይህም ሆኖ እድገቱ ያስከተለው ኢኮኖሚያዊ ለውጥ እንደሚወራለት የመሰረተ ልማት፣ የገበያ ትስስርና የምርታማነትን ችግር ፈቶ የኢኮኖሚዊ መዋቅር ሽግግርን በአስተማማኝ ሁኔታ በማረጋገጥ እድገቱ (Growth) በሂደት ወደ ልማት (Development) ተስፋፍቶ የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ማሻሻል የሚችል አስተማማኝ ኢኮኖሚ መሆኑን ማረጋገጥ አለመቻሉ የብዙዎቻችን ጥያቄና የሃገሪቱ ፈተና እንደሆነ መቀጠሉ ግልጽ ነው፡፡

በርካታ የኢኮኖሚ ምሁራን እንደሚስማሙት ከሆነ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ እድገት ተመላሽን (Economic Return) ከግምት ውስጥ ያላስገባ፣ በኢንተርፕረነርሺፕ ላይ ያልተመሰረተና ቀጣይነቱ ያልተረጋገጠ፤ ሃገራዊ ሃብት በከፍተኛ ደረጃ በመንግስት ተጽእኖ ስር እንዲወድቅ በማድረግ የግል ኢኮኖሚ ዘርፉን ያቀጨጨና ያሰናከለ ከመሆኑም በላይ መንግስት የልማትም ሆነ የእድገቱ ብቸኛ አሳላጭ እንዲሆን አድርጓል፡፡ 
ከበርካታ ሃገራት ተሞክሮ ለመረዳት እንደሚቻለው ከሆነ በተለይ መንግስትን ማዕከል አድርጎ ሃገራዊ ሃብትን በማግበስበስ (Forced Accumulation) ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ ፍልስፍና ለምርታማነትና ለዜጎች ሁለንተናዊ ልማት ትኩረት የማይሰጥ፣ ለግል ኢኮኖሚ ዘርፉን ግብአት የሆኑ እንደ ካፒታል፣ ጥሬ እቃና መሰል ሌሎች አቅርቦቶችን በማሟጠጥ የሚያዳክም፤ እንደ ሙስና፣ ብክነትና ዝርክርክነት ላሉ የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ጠንቆች የተጋለጠ፣ ለፖለቲካ ፍጆታ ሲባል ከዜጎች መካከል ጥቂቶችን በመምረጥ ልዩ ትኩረት የሚሰጥ፤ አብዛኛውን ዜጋ ለፖለቲካ መሳርያነትና መጠቀሚያነት የሚያመቻች በመሆኑ ኢኮኖሚው ፍልስፍናው እድገትና ልማትን በሚፈለገው መጠን ማስመዝገብ የማይችል ለመሆኑ በምክንያትነት ከሚጠቀሱ ማሳያዎች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
ዓለም ባንክ መንግስት በተለምዶ ከሚሰጠው መረጃ ጋር ያለመጣጣም አባዜ ያለበት ቢሆንም የዘንድሮ የዓለም ባንክ ሪፖርት ግን ራሱ ዓለም ባንክም ሆነ መንግስት ከሚሰጠው መረጃ በተለይ ከፍ ብሎ የ10.4 በመቶ አጠቃላይ ሃገራዊ ምርት እድገት ማስመዝገቡን ገልጿል፡፡ የሪፖርቱ ምንጩ በተደጋጋሚ እንደሚወሳው በአብዛኛው ከአንድ ምንጭ የሚቀዳ ከመሆኑም በላይ በጣት በሚቆጠሩ የዓለም ባንክ ሰራተኞች ያውም በአብዛኛው ከአዲስ አበባ ሳይወጡ መንግስት በሚያቀርባላቸው መረጃ ላይ ተመስርተው የተለያዩ ስልቶች በመጠቀም የሚቀምሩት በመሆኑ ምክንያት ልዩነቱም ሆነ አንድነቱም የሚገርም አይደለም፡፡ በስሌት ደረጃ በዓለም ባንክ ሪፖርት መሰረት ተመዘገበ የተባለው የ10.4 በመቶ አጠቃላይ ሃገራዊ ምርት እድገት ካለፈው ዓመት እድገት ጋር ሲነጻጸር የተወሰነ ጭማሪ አሳይቷል፤ ነገር ግን ይህ የዓለም ባንክ አጠቃላይ የሃገራዊ ምርት እድገት ሪፖርት ከተጠቀሰው የቁጥርና የፐርሰንት ስሌት ውጭ ልማትን በማረጋገጥ የዜጎችን ሕይወት ምን ያህል መለወጥ ቻለ ወይም ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ከመፋታት አኳያ ምን ያህል ፋይዳ ነበረው ለሚለው ጥያቄ መልስ መስጠት የቻለ አይደለም፡፡
ማንም ዜጋ ሊመሰክረው በሚችለው ደረጃ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ተመላሽንና የግል ክፍለ ኢኮኖሚውን ነጻነትን ማዕከል አድርጎ እድገትን ወደ ኢኮኖሚያዊ ልማት ማሸጋገር ያልቻለበት ምክንያት ኢኮኖሚያችን በተዛባና በተዛነፍ መልክ የአንድ ወገን ኢኮኖሚያዊ ስሌትን ማለትም ፍጆታና ፍላጎትን ብቻ በማሳበጡ መሆኑ ያታወቃል፡፡ ይህ የአንድ ወገን እብጠት ደግሞ ለከፍተኛ ግሽበትና የኑሮ ውድነት አቀባባሎ ሰጥቶናል፡፡ ለዚህ ደግሞ መንግስት ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ሃብትን በጥቅሉ በራሱ ቁጥጥር ስር በማግበስበስ ለግዙፍ መሰረተ ልማቶች ብቻ ማዋሉ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ይህ አካሄድ የፈጠረው ግሽበትና ግሽበቱን ተከትሎ የተንሰራፋው የኑሮ ውድነት ዜጎች ሕይወታቸውን ማሻሻል እንዳይችሉ እጅ ከወርች አስሮ በድህነት አዙሪት ውስጥ እንዲዳክሩ ዓይነተኛ ምክንያት መሆኑን ቀጥሏል፡፡
በዚህም ምክንያት ኢኮኖሚው መጠነ ሰፊ የሆነ የአቅርቦትና የጥራት ችግር ቀስፎ የያዘው ስለሆነ በምንሸምተው ምርት ጥራት ሆነ ደረጃ አሊያም ዋጋ ላይ መተማመን የሚታሰብ ጉዳይ አይደለም፡፡ ክፍተቱን ተጠቅሞ ለመክበር ያቆበቆበው አቅራቢም የፍጆታና ቁሳቁስ አቅርቦት በተዛባበት ሁኔታ ማንኛውም ነገር ዋጋ ያወጣል ወይም ይሸጣል ከሚል ስንኩል ሰነልቦና ከሚመነጭ ስግብግበነት በገበያው ውስጥ የሚያሰራጨው ቁሳቁስና ሸቀጣ ሸቀጥ በየስርቻው ለጤና ጠንቅ በሆነ መንገድ ተመርቶ ልዩ ድጋፍ እየተደረገለት ከወዳጅ አገሮች ስለሚግበሰብስ፣ ሕጻን፣ አዛውንት ሳይል ጤንነትም ሆነ ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥልና አካባቢን የሚበክል፤ ከጠቀሜታም አኳያ የአገልግሎት ዘመኑ እዚህ ግባ የማይበል አንዳንዴም በደቂቃዎች የሚቆጠር ነው፡፡ ይህ ደግሞ በሕይወትና በጤንነት ላይ ካለው ጉዳት በተጨማሪ የውጭ ምንዛሪያችን፣ የንግድ ስርዓታችንና ሃገራዊ ምርታችን ላይ የሚሳድረው አሉታዊ ተጽእኖ የትየለሌ ነው፡፡
ጥራት ጎደለውና ደረጃውን ያልጠበቀ የሸቀጣ ሸቀጥና የፍጆታ አቅርቦት ለጤና ጠንቅ ነው፡፡ ጤናው የተዛባና የተሰናከለ ዜጋ ደግሞ ምርታም ሊሆን አይችልም፡፡ ምናልባትም ጊዜውና ገንዘቡ የሚያባክነው በሕክምናና እራሱን በማስታመም ከመሆኑም በላይ ደረጃውን ያልጠበቀ ቁሳቁስ ደግሞ ያለወቅቱ እየተበላሸ ለተደጋጋሚ ወጭና ለብክነት አልፎ ተርፎም ለአደጋ ሲያጋልጥ ማየት የተለመደ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የውሃ ፋሳሽና የኤሌክትሪክ መስመር ቁሳቁሶች በምግበ በኩልም ከሕፃናት ወተት ጀምሮ እስከ ዘይትና የመድሐኒት አቅርቦት ድረስ ባሉ ፍጆታዎች ዙርያ በሚታዩ የጥራት ጉድለቶች ምክንያት የተከሰቱ የጤንነት እክሎች የሕክምና አዋቂዎችን እያወዛገቡ መገኘታቸው በቂ ምሳሌ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
ማንኛውም ኢኮኖሚ በአንድ በኩል ሚዛኑን በጠበቀ አቅርቦትና ፍላጎት ካልተመራ በሌላ በኩል ደግሞ ነጻ የገበያ ውድድር ስርዓትን ካልተከተለና የተረጋጋ መሆን ካልቻለ መሰረታዊ ችግር ከሆነው ግሽበትና የኑሮ ውድነት በተጨማሪ የአቅርቦት ዋጋ እለት በእለት ማሻቀቡን ተከትሎ ዜጎችና በጥቅሉ ሃገር ደረጃውንና ጥራቱን ላልጠበቀ አልባሌ ሸቀጣ ሸቀጥና ቁሳቁስ ማራገፊያነት መጋለጣችን አሌ ሊባል አይችልም፡፡ መንግስት ችግሩን በዘወርዋራ መንገድ ለመፍታት ሲባል የአጭር ጊዜ መፍትሄ እየደረደረ ከመዳከር ይልቅ ለግሽበቱና ለዋጋ ንረቱ መንስኤ የሆኑ መሰረታዊ ሕጸጾችን በግልጽ የሚታወቁ በመሆናቸው ስር ነቀል የፖሊሲ ለውጥ ማካሄድ ይጠበቅበታል፡፡ ከችግሩ ጥልቀት አኳያ የእርምት እርምጃው ቢያንስ ቢያንስ ግሽበቱን በማስቆም የዋጋ ንረቱን ማውረድ ባያስችለውም የግሽበቱን ፍጥነት ባለበት በመግታት ለዜጎች የእፎይታ ጊዜ መፍጠር ይችላል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን በአጠቃላይ በገንዘባችን ጥንካሬ ተማመነን ለዓመታት ለመቆጠብ አይደለም ዛሬ ኪሳችን ውስጥ በሚገኝው ገንዘብ የመግዛት አቅም ታግዘን ወደ ገበያ መውጣት የማይሞከርና ምናልባትም ለውርድት የሚዳርግ ጉዳይ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡
ይህ የገሃዱ ዓለም እውነታ እንደተጠበቀ ሆኖ ሰሞኑን የተከበሩ አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ከተወካዮች ምክር ቤት አባላት ከቀረበላቸውና ጥያቄዎችና ከላይ ካነሳኳቸው ጉዳይች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ካላቸው ጉዳዮች መካከል፤ በተለይ ትኩረቴን የሳበው የግሽበት ወረርሽኙን መለዘብ አስመልክቶ የሰጡት መልስ ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት የተከበሩ አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ግሽበቱን ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ተመሳሳይ ወር ጋር በማነጻጸር የሰጡት የግሽበት ቀንሷልና ዋጋ ወርዷል ትንታኔ በውስጥ ሌላ ትንታኔ ያለው መሆኑን መተንተን አስፈላጊ መስሎ ታይቶኛል፡፡
አቶ ሃይለማርያምን ግሽበት በከፍተኛ ሁኔታ እንደቀነሰ የእቃ ዋጋ መረጋጋት እያሳየ እንደሆነ ሲገልጹ ለዚህ መንስኤ ያደረጉት ዓይነተኛው ምክንያት መንግስት የተከተለው ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ (Monetary Policy) እንደሆነ በመግለጽ ነው፡፡ የፖሊሲ ጉዳዮቹን በኃላ ስለምመለስባቸው አሁን ስለ ግሽበቱ መቀነሱ ለመግባባት ይረዳን ያክል በጥቂቱ በጥቂቱ ሃሳቦቼን ላብራራ፡፡ከላይ ለማንሳት እንደሞከርኩት ግሽበት ቀንሷል ዋጋ ተረጋገረቷል ሲባል ምን ማለታችን እንደሆነ በቅጡ ካልተረዳነው የትንታኔያቸው ስውር ፕሮፓጋንዳ ሰለባ መሆናችን አይቀርም፡፡ ከዚህ በመነሳት የአቶ ሃይለማርያም ደሳለኝን መልስ በቅጡ ስንመረምረው ግሽበት ቀንሷል የሚለው ትንታኔያቸው በከፍተኛ ደረጃ በጊዜ የተገበደና አስፈላጊ ግብአትና መረጃዎችን በማሳጠር የተቀመረ ስሌት መሆኑን እንረዳለን፡፡ ከዚህ አኳያ ትንታኔው እውነታነት ቢኖረው እንኳን እውነታው ሊሆን ትርጉም የሚኖረው በአንጻራዊነት ብቻ ነው፡፡
የእውነታው አንጻራዊነት የሚመነጨውም በጥያቄና መልሳቸው ላይ አንዳብራሩት ንጽጽሩ የተደረገው የዛሬ ዓመት በተመሳሳይ ወር ላይ የነበረውን አጠቃላይ የእርሻና ኢንዱስትሪ ምርት (Composite Goods) ዋጋ ከዘንድሮ ተመሳሳይ ወር አጠቃላይ የምርት አቅርቦት ተመሳሳይ ወር ዋጋ ጋር በማወዳደራቸው ነው፡፡ የአምና ተመሳሳይ ወር የአቅርቦቶች ዋጋ ከዘንድሮው ተመሳሳይ ወር ዋጋ ጋር ሲወዳደር በጥቅል ከተያዙት የእርሻና ኢንዱስትሪ ምርቶች ውስጥ በአንዳንዶቹ አቅርቦቶች ላይ የዋጋ ቅናሽ ታይቶ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ የተናጠል የግሽበት ቅንስናሽ በአጠቃላይ በማዕቀፉ ውስጥ በታጨቁት የእርሻና ኢንዱስትሪ ምርቶች (Composite Goods) ላይ የሚኖረው ዋጋን የማቅጠንና የማዝቀጥ ዝንባሌ የመረጃውን አግባብነትን (Relevance) ከሚገመተው በላይ የሚያሳንሰው ሲሆን አጠቃላይ የግሽበቱ ቅንስናሽ ደግሞ በዜጎች የመግዛት አቅም ላይ የሚኖረው አዎንታዊ ተጽእኖ የተለካው ለኑሮ በዕለት ከእለት ፍጆታነት አስፈላጊ ባልሆኑ አቅርቦቶች ላይ በተከሰተ ቅንስናሽ ሳሆይሆን በሌሎች አቅርቦቶች ላይ ተመስርቶ ከመሆኑ የተነሳ ምክንያታዊነት የሚጎደለውና ንጽጽሩ መሰረታዊ ግብአቶች ያላሟላ ያደርገዋል፡፡ ይህ ደግሞ ተመዘገበ የተባለውን የግሽበት ቅንስናሽ በዜጎች ሕይወት ላይ የሚያስከትልውን ውጤቱ ከዜሮ በታች አድርጎታል፡፡
እስኪ እያንዳንዱን ጉዳዮች በዝርዝር እንመልከታቸው ፡፡ አንደኛ ላለፉት በርካታ ዓመታት ያለማቋረጥ በከፍተኛ ሁኔታ ሲያሻቅብ የነበረው መንግስት አቀርቦት ኢኮኖሚው ሊሸከመው ከሚችለው በላይ የናረ የገንዘብ ስርጭተና ዝውውር እንዲፈጠር በማድረጉ የተከሰተ መሆኑ የተወቀ ነው፡፡
ከዚህ አኳያ ግሽበቱ ተሻሽሏል ማለት የሚቻለው በአንጻራዊነት በአንዳንድ አቅርቦቶች ላይ የዋጋ ቅናሽ በመፈጠሩ ሳይሆን በአብዛኛውና በተለይ ደግሞ ለእለት ተዕለት ኑሮአችን አስፈላጊ የመሆኑ አቅርቦቶች ላይ እውነተኛ የዋጋ ቅናሽ ሲከሰት ብቻ ነው፡፡ ይህ ግን በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ በተግባር አልታየም፡፡
የተለያዩ ቁሳቁሶችና የግንባታ አቅርቦቶችን ጨምሮ የትራንስፖርት ዋጋን ትርጉም ባለው ደረጃ መለወጥ ባይችልም የነዳጅ ዋጋ ላይ መጠነኛ ቅናሽ ታይቷል፡፡ ይህ ግን አንደኛ ደረጃ የኑሮ ግብአት የሆኑትን የጤፍን፣ የስጋን፣ የቅቤና የዘይትን ወይም የጥራጥሬና የስንዴን ምርት ላይ ተጽእኖ መፍጠር አልቻለም፡፡ እንደውም በተጻራሪው ከዓምናው አንጻራዊ ወር ጋር ሲወዳደር ዘንድሮ እንደጤፍ ያሉትና ሌሎች መሰል የጥራጥሬ ግብዕቶች ላይ አንጻራዊ የዋጋ ጭማሪ ታይቷል፡፡ በዚህም ምክንያት የተጠቀሰው አንጻራዊ የሆነና በውስን አቅርቦቶች ላይ ታየ የተባለው የግሽበት ቅናሽ በዜጎች ኑሮ ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ሊያስመዘግብ አይችልም፡፡
ሁለተኛው በጥያቄና መልሱ የቀረበው የግሽበት ቅናሽ ትንታኔ ያላካተተው ወይም በንጽጽር ያላቀረበው ግብአት የዜጎች ገቢ ጉዳይ ነው፡፡
ግሽበትን አስመልክቶ የሚደረግ ንጽጽር በተለይ ደግሞ የአምናውን ግሽበት ከዘንድሮ ዓመት ተመሳሳይ ወር ግሽበት ጋር በሚወዳደርበት ሁኔታ የዜጎች ገቢ ላይ የተከሰቱ ለውጦች ካሉ ከግምት ውስጥ መግባታቸው የግድ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ ስናጤን ግን ላለፉት አምስትና ከዛም ለዘለቁ በርካታ ዓመታት የተከሰተውን መጠነ ሰፊ ግሽበት ተከትሎ የገቢ ጭማሪ አልተደረገም፡፡ እንደውም ከሁለት ዓመት ቀድም ብሎ ባሉት ዓመታት መንግስት የበጀት ጉድለቱን ለማሟላት በሚል የተከተለው መጠነ ሰፊ የገንዘብ ስርጭትና ዝውውር የመግዛት አቅምን በእጅጉ በመጉዳቱ ገቢያችን በአንጻራዊነት ቀንሷል፡፡ በተከታታይ ለስምንት ዓመታት የተከሰተው ግሽበትም እንዲሁ ተመጣጣኝ በሆነ የገቢ ማስተካከያ ያልታረመ በመሆኑ ምክንያት በአንጻራዊነት በአንዳንድ ውም በሁለት ያውም መሰረታዊ ያልሆኑ አቅርቦቶችና ምርቶች ከአምናው ተመሳሳይ ወር ዋጋ ጋር ተወዳድረው የታየው የዋጋ ቅናሽ በዜጎች ሕይወት ላይ ተጨባጭ ለውጥ እንዳስከተለ ትርጉም ያለው የግሽበት ቅንስናሽ ተደርጎ ሊወስድ አይችልም፡፡
በሶስተኛው ደረጃ ሊነሳ የሚገባው ጉዳይ የመሰረተ ልማት ግንባታው በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ በመጣበትና ጋብ ማለት ባልቻለበት ሁኔታ ግሽበት ቀንሷል የሚለው መረጃ አጠራጣሪ ጥያቂዎችን የሚያስነሳ መሆኑ ነው ፡፡ መንግስት እጅግ ሰፋፊ ፕሮጀክቶችን በመቀየስ የአባይ ግድብ፣ የስኳር፣ የስራ እድል ፈጠራን አካቶ የተለያዩ የውሃ፣ የመብራትና የመኖርያ ቤት አቅርቦትን የመንገድና ሌሎችንም ያካተተ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን እያካሄድ ይገኛል፡፡ በመከላከያ ኢንዱስትሪ በኩልም እጅግ ከፍተኛ ወጭን የሚጠይቁ መጠነ ሰፋፊ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡ በዚህ ላይ ከክቡር ሚኒስትሩ እንደሰማነው ከሶስት ያላነሱ ግዙፍ ስታድዮሞች ግንባትም ታክለውበታል፡፡
እነዚህ ግንባታዎች እጅግ ከፍተኛ ወጭ የሚጠይቁ በመሆናቸው ምክንያት ከገቢ ግብር በሚሰበሰበው መዋዕለ ንዋይ ብቻ ግንባታቸውን እውን ማድረግ አይችልም፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ላለፉት ተከታታ ዓመታት እንደሚታወቀው መደበኛም ሆነ መደበኛ ላልሆኑ መንግስታዊ ስራዎች የሚያስፈልገው የመዋዕለንዋይ መጠንና ፍላጎት እያደገ በመምጣቱ የተፈቀደው የመንግስት በጀት በቁጥር ደረጃ የሚያሻቅብ ጉድለትን ያስመዘገበ ነው፡፡
እነዚህ ሁሉ ጉድለቶችና የመሰረተ ልማት ግንባታ ፍላጎቶች በገቢ ግብር ብቻ መሟላት ካልቻሉ ሌሎች ምንጮች ምንድን እንድሆኑ በማያሻማ መልክ በተከበሩ ጠቅላይ ሚኒስቴር መብራራት ነበረባቸው፡፡ይህ ባለመሆኑና እነዚህ መሰረታዊ ነጥቦች በክቡር ሚኒስቴሩ የመዳሰስ እድል ስላልተሰጣቸው ከተጨባጭ ሁኔታዎች ተነስተን በኢኮኖሚው ላይ ያላቸውን አሉታዊና አዎንታዊ ተጽእኖ በምክንያት በጥቂቱ መተንተን ያስፈልጋል፡፡
አንደኛው የመዋእለንዋይ አቅርቦቱ ምንጭ ሊሆን የሚችለው ከብሔራዊ ባንክ የሚገኝ ብድር ሲሆን ከብሄራዊ ባንክ የሚገኝ ብድር ሲጠራ የብሄራዊ ባንክ ብድር ቢባልም ሁነኛ መጠሪያው ግን ገንዘብ ማተም ማለት ነው፡፡ መንግሰት የገንዘብ ሕትመትን ከገንዘብ ማግኛ ምንጭነት ከአሰራር ሂደቱ ያስወጣው መሆኑን በተደጋጋሚ እየተገለጸ የሚገኝ ቢሆንም የመሰረተ ልማት ግንባታ ፍላጎቱ ጋብ እስካላለ ድረስ የማተሙን ቀጣይነቱን በአዋጅ ማቋረጥ የማይቻል ጉዳይ እንደሆነ ግንዛቤ መውስድ ያስፈልግል፡፡
በሌላ በኩል የመዋዕለ ንዋይ ግብአቱ ምንጭ ብድር ነው፡፡ ብድሩ የሚገንው ከወዳጅ ሃገር ከሆነ ከፍተኛ ወለድ ያለበትና በአጭር ጊዜ የሚከፍል ሲሆን ሌላው ከዓለም አቀፍ አበዳሪ ድርጅቶች ለአዋጭነት የመሰረተ ልማት ግንባታው ሲታመንበት የሚሰጠው ብድር ነው፡፡ አስካሁን በተወካዮች ምክር ቤት የተፈቀዱ ብድሮችን በቅጡ ቢጤኑ በአብዛኛው ምንጫቸው የወዳጅ ሃገራት ብድሮች መሆናቸው ግልጽ ነው፡፡
ኢኮኖሚው ሊሸከመው ከሚችለው በላይ ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ ህትመት፣ ስርጭትና ዝውውር ከፍተኛ በሆነ ምርታማነትና ልማት ካልታገዘ የገንዘብ አቅርቦቶች ፍላጎትን በማጎልበትና በማሳደግ የዋጋ ግሽበትን እንደሚያባብሱ ግልጽ ነው፡፡ በዚህም ረገድ በኩል በተጨባጭ ሁኔታ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከግሽበት እንዴት ሊያገግም አንደሚችል በቂ ማብራርያ አልተሰጠም፡፡
ከፍተኛ ወለድ የሚያስከፍልና ለአጭር ጊዜ የሚሰጥ ብድር ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ልማትን ማረጋገጥ በማይችል ሃገር ውስጥ ገንቢ ሚና የሚጫወቱና አዳጊ ዘርፎችን ብድር ከፋይ በማድረግ እንደሚያዳክማቸውና እራሳቸውን በማበልጸግ አቅርቦትን ለማሳዳግና ምርታማነታቸውን ማረጋገጥ እንዳይችሉ እንቅፋት እንደሚሆነባቸው ግልጽ ነው፡፡
የምርታማነት ችግር ደግሞ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መሰረታዊ ችግር መገለጫ ነው፡፡
በአጠቃላይ ከላይ ለመመልከት እንደሞከርኩት በርካታ መሰረታዊ መፍትሄና ምላሽ የሚያሻቸው ጥያቄዎች በእንጥልጥል ባለበት ሁኔታ ግሽበት በዚህ ፐርሰንት ወርዷልና ደስ ብሎናል ደስ ይበላችሁ የሚለው ዜና ለኢትዮጵያውያኖች አሳማኝ ዜና ለመሆን ገና ብዙ ርቀት መጓዝ ይቀረዋል፡፡
ከዚህም በላይ ጠለቅ ብሎ ሊተነተን የሚቻለው የኢትየጵያ ውስብስብ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ሳይታከልበት የዕለት ተዕለት ኑሮአችን ለችግሩና ለፈተናው ለውጣውረዱ በቂ ምስክር ስለሆነ ክቡር ሚኒስቴር የግሽበት ቅንስናሽ ዜናዎን አሻሽለው ያቅርቡት እላለሁ፡፡

Read 11556 times