Saturday, 12 January 2013 09:35

ኢቴቪ በገና በዓል ሰርፕራይዝ አደረገን! ለፋሲካስ?

Written by  ኤሊያስ
Rate this item
(11 votes)

“አሁን ያለወትዋች የቴሌቪዥን ግብር እንከፍላለን” የኢቴቪ ተመልካቾች
በቀጥታ ወደ ፖለቲካ ወጋችን ከመዝለቄ በፊት ሰሞኑን ከአንድ ወዳጄ የሰማሁትን ቀልድ ላካፍላችሁ አንድ የአገር ውስጥ ጋዜጠኛ ለቀድሞው ጠ/ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ (ነፍሳቸውን ይማረውና) ጥያቄ ያቀርብላቸዋል፡፡
ጋዜጠኛው - “እስቲ በጣም ያዘኑባቸውን ጊዜያት ይንገሩኝ--” አቶ መለስ - “በህይወቴ በጣም ያዘንኩት ሁለት ጊዜ ነው - ህወኀት ሲከፋፈልና አርቲስቶችን ያነጋገርኩ ጊዜ!”

መቼም አርቲስቶች ቀልዱ መልካም ስምና ዝናችንን የሚያጎድፍ ነው ብለው እንደማይቀየሙ እተማመናለሁ (ቀልድ እኮ የጥበብ ዘርፍ ነው!) ማርክ ትዌይን የተባለው ታዋቂ አሜሪካዊ ደራሲና ነገር አዋቂ (ተረበኛ) ጋዜጦች “ማርክ ትዌይን ሞቷል” የሚል ዘገባ ማውጣታቸው ሲነገረው ምን እንዳለ ታውቃላችሁ? ብቻ ይናደዳል ብላችሁ እንዳትጠብቁ፡፡ እሱ እቴ! ንዴት ሲያልፍም አይነካው፤ያበግናል እንጂ! እናም እንዲህ ሲል መለሰ “መሞቴን በተመለከተ የወጣው ዘገባ እጅግ ተጋኗል!” በቃ እንዲህ ተሳልቆ አለፈው (እናንተም እንዲሁ ብላችሁ እለፉት!) 
እኔ የምለው --- የዘንድሮን የኢቴቪ የገና በዓል ልዩ የመዝናኛ ዝግጅት እንዴት አገኛችሁት? እኔማ ኢቴቪ የዓመት በዓል የአየር ሰዓቱን ሸጠው እንዴ? ብዬ ነበር፡፡
ምን ላድርግ! ያለመደበትን ሲያዝናናን እኮ ዋለ! ሃቁን ልንገራችሁ አይደል-- እኔ መቼም ከኢቴቪ ጋር ከተዋወቅሁ ጀምሮ እንደዘንድሮ የገና በዓል ተመችቶኝ አያውቅም፡፡ እናንተ-- ውሸት ምን ያደርጋል ---- ድንቅ ዝግጅት እኮ ነበር (አምልጦናል እንዳትሉኝና እንዳልበሽቅ!) አንዱ ጓደኛዬ በዝግጅቱ በጣም ከመደመሙ የተነሳ ምን እንዳለ ታውቃላችሁ? “ሁሌም ገና በሆነ የሚያስብል ዝግጅት ነው” (እኔም እስማማለሁ!)እኔ የምለው---- ለምንድነው ግን ዝግጅቱ እንዲህ አሪፍ የሆነው? ይሄማ ግልፅ ነው፡፡
በአርቲስቶች የተሞላ ዝግጅት እንዴት አሪፍ ላይሆን ይችላል? ለነገሩ በዝግጅቱ ላይ አርቲስቶች እንዲሳተፉ ያደረጉት (የፈቀዱት ልበል እንጂ) የኢቴቪ ሃላፊዎችም ለአዝናኝነቱ ትልቅ አስተዋፅኦ አድርገዋል፡፡ እነሱ ባይፈቅዱ እኮ እንደወትሮው ተደባብረን ነበር በዓሉን የምንውለው፡፡ (ምን ተገኝቶ ይሆን የፈቀዱት?)
እናንተ---- አንጋፋዎቹ ድምፃውያን ኩኩ ሰብስቤና ነፃነት መለሰ እርስ በእርስ ያደረጉት ኢንተርቪው ጉደኛ እኮ ነበር፡፡ እውነቱን ለመናገር --- የአርቲስቶቻችንን ዘርፈ ብዙ ተሰጥኦ ያየንበት ልዩ የገና አውዳመት ዝግጅት እንደነበር መካድ አይቻልም፡፡ አያችሁልኝ አይደል-- የኩኩ ሰብስቤን የኮሜዲያንነት ተሰጥኦ! ምንም እንኳን በቅርበት የሚያውቋት ሰዎች “የሌሎችን ድምፅ የማስመሰል ችሎታ” እንዳላት ሲናገሩ ብሰማም እኔ ግን ከዚያም የላቀ ችሎታ ነው ያየሁባት፡፡ እኔ የምለው ግን --- እስከዛሬ ይሄን ችሎታዋን እንዴት ደብቃን ተቀመጠች (ግፍ እኮ ነው!) የአለማየሁ እሸቴንና የራሷን የነፃነትን ዘፈኖች አስመስላ በመዝፈን ቀላል አዝናናችን እንዴ! ፕሮግራሙ እንዳለቀ አብሮኝ የነበረ ጓደኛዬ ዓይኑን ከተከለበት ሞባይል ላይ ነቅሎ ምን እንዳለኝ ታውቃላችሁ? “ፌስ ቡክ ላይ ሁሌ ኢህአዴግን እየተቸ የሚፅፍ እገሌ የሚባል ልጅ ነበረ” አለና ቀጠለ “አሁን ምን ብሎ እንደፃፈ ታውቃለህ ? I enjoy Etv after such a long period of time” (ከረዥም ጊዜ በኋላ በኢቲቪ ተዝናናሁ ማለቱ ነው) እንዴት አይዝናና! (ኢቴቪ ሰርፕራይዝ እኮ ነው ያደረገን!) ልክ ብሄራዊ ቡድናችን ከ31 ዓመት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ እንዳለፈው ዓይነት ማለት እኮ ነው፡፡
ሌላው ወዳጄ ደግሞ “ኢቴቪ እንዲህ ዓይነት ፕሮግራም ማቅረብ ከጀመረ በየዓመቱ የቴሌቪዥን ግብር ክፈሉ የሚል ውትወታ አያስፈልገውም” አለኝ፡፡ “እንዴት?” አልኩት፡፡ “ሁሉም ራሱ አውቆ ይከፍላላ!” (መልዕክቷ ለኢቴቪ ሃላፊዎች መሰለኝ!) በነገራችሁ ላይ ይሄን የገና በዓል ዝግጅት ሃሳብ ያመነጨው ሰው (ሰዎች) ሽልማት ይገባቸዋል፡፡ ከስንት ዘመን በኋላ እኮ ነው የተዝናናነው፡፡
መቼም ከዚህ በኋላ ኢቴቪ ለአውዳመቶች በሚያቀርባቸው ልዩ ዝግጅቶች ከባድ ፈተና እንደሚገጥመው ጥርጥር የለውም፡፡ ለምን መሰላችሁ ---- ከገናው ያነሰ ከሆነ ማንም ዞር ብሎ አያይለትማ! እናም የፋሲካ ልዩ ዝግጅት ከገናው የላቀ እንጂ ያነሰ እንዳይሆን የኢቴቪ ሃላፊዎች ከአሁኑ ጀምሮ ማሰብ መጀመር አለባቸው፡፡ የገና ዝግጅት ስኬት ምስጢሩ ሌላ ሳይሆን ሃሳብ እኮ ነው ---ዝም ብሎ ተራ ሃሳብ ግን አይደለም፡፡
እስከዛሬ በኢቴቪ ያልተሞከረ አዲስ የፈጠራ ሃሳብ የታከለበት ዝግጅት ነበር፡፡ የስኬት ሊቆች ምን ይላሉ መሰላችሁ ? “አንድን ነገር በየጊዜው በተመሳሳይ መንገድ እየሰሩ የተለየ ውጤት የሚጠብቁ ሰዎች የዋሆች ናቸው” ይሄን አባባል ተከትለን ኢቴቪ ለዓመታት የዋህ ነበር ብንል ያስኬደናል፡፡ በዘንድሮ የገና በዓል ግን አሰራሩን በመለወጡ የተለየ ውጤት አምጥቷል፡፡ የተጨበጨበለት ድንቅ ዝግጅት አስኮምኩሞናል፡፡
እናላችሁ ---ኢቴቪ ለገና አርቲስቶችን ጋብዞና አሳትፎ እንዳዝናናን ሁሉ ለፋሲካ ደግሞ ታዋቂ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችን (ከገዢውም ከተቃዋሚዎችም) ጋብዞና አሳትፎ ቢያዝናናን ዝናው ሰማይ ይነካል የሚል እምነት አለኝ (ከምሬ እኮ ነው!) ይታያችሁ---- የኢህአዴግ ጉምቱ አመራር ከመድረክ ፓርቲ አቻቸው ጋር መድረክ ላይ ወጥተው እርስ በእርስ ኢንተርቪው ቢደራረጉ! (ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንጂ ደመኞች እኮ አይደሉም!) እናም ----ስለፖለቲካው ምህዳር መጥበብና መስፋት፣ ኢህአዴግ ለ30 እና 40 ዓመት በስልጣን ላይ ለመቆየት ስላለው ህልምና ምኞት፣ መድረክ የምርጫ ስነምግባር ደንቡን አልፈርምም ብሎ አሻፈረኝ ስለማለቱ፣ ስለ97 እና 2002 ዓ.ም ምርጫ ወዘተ--- ትዝታቸውን አንስተው ልክ እንደአርቲስቶቹ እየተተራረቡና እየተቀላለዱ ቢጨዋወቱ ---- በጣም ነው የሚያዝናኑን፡፡ ኢቴቪ ይሄን ፕሮግራም ሲያሰናዳ ግን ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርበታል (ፖለቲከኞቹ ጉድ ይሰሩታል ብዬ እኮ ነው!) እውነቴን እኮ ነው----ቆይ ፖለቲከኞቹ የአውዳዓመት መዝናኛ መሆኑን ዘንግተውት እንደምሩ ፖለቲካችን ንትርካቸውን ቢያጧጡፉትስ? (ኢቴቪ የማን ያለህ ሊል ነው!)
በነገራችሁ ላይ የፋሲካውን ልዩ የኢቴቪ መዝናኛ ፕሮግራም የበለጠ አስደሳች ለማድረግ የሚያስችል ሌላም ሃሳብ አለኝ (ለማን እንደምቆጥበው ግራ ገባኝ እኮ!) ምን መሰላችሁ? ፖለቲከኞቹ ልክ እንደነኩኩ አንዳቸው የሌላኛቸውን ድምፅ እያስመሰሉ እንዲኮምኩ ማበረታታት ይቻላል፡፡ በደንብ ሳስበው ግን ይሄኛው እንኳ ብዙም የሚሳካ አልመሰለኝም፡፡
አያችሁ ---- የእነኩኩ የተሳካው የአርቲስትነት ነፍስ ስላላቸው እኮ ነው፡፡ እነዚህኞቹ ግን ነፍሳቸው ሁሉ የተሰራው ከፖለቲካ ብቻ ስለሆነ እንዲህ ያለው ኩምክና የሚሆንላቸው አይመስለኝም፡፡ ቢችሉም እንኳ የፖለቲካ ኩምክናና የጥበብ ኩምክና ለየቅል ነው፡፡ ስለዚህ በምትኩ ሌላ ነገር አስቤአለሁ፡፡ ምን መሰላችሁ? የፖለቲከኞቹን ድምፅና ነገረ ስራቸውን አስመስለው የሚኮምኩ ኮሜዲያኖች ማፈላለግ ይቻላል (ሞልተዋል እኮ!) ይታያችሁ ----ኮሜዲያኑ እዚያው ዝግጅቱ ላይ የሚሳተፉ ትላልቅ ፖለቲከኞችን ድምፅና የአነጋገር ቃና አስመስለው እየተናገሩ (ያውም ከእነአክታቸው) በሳቅ ሲያፈርሱን! በዚያውም የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች የሚያስፈሩ ጭራቆች ሳይሆኑ እንደኛው የሚቀለድባቸው ወይም የሚኮመክባቸው ተራ ሰዎች መሆናቸውን ለ“ልማታዊው ህዝባችን” ለማስገንዘብ መልካም አጋጣሚ ይፈጥርልናል (የፖለቲከኞች ገፅ ግንባታ ማለት እኮ ነው!)
ባለፈው ታሕሳስ ወር ለንባብ የበቃውን “ኒው አፍሪካን” የተሰኘ መፅሄት ሳገላብጥ ምን አገኘሁ መሰላችሁ? በፖለቲከኞች ስለመኮመክ የተፃፈ ነገር አግኝቼ እጅጉን ተደነቅሁ፡፡ ያውም እኮ በአገር መሪ ነው የሚኮመከው፡፡ ደግሞ ሩቅ አገር እንዳይመስላችሁ - እዚህቹ አፍሪካችን ውስጥ! የኡጋንዳውን መሪ ፕሬዚዳንት ዮዌሪ ሙሴቪኒን ድምፅና ቅላፄ አስመስሎ በመናገር ስለሚታወቅ ኡጋንዳዊ ኮሜዲያን የሰፈረ መጣጥፍ ነው ያነበብኩት፡፡ ሴጉጃ የተባለው ኮሜዲያን እዚያው ኡጋንዳ ውስጥ የሁለተኛ ደረጃ መምህር ነው - የታሪክ፡፡
ኮሜዲያንነት የትርፍ ጊዜ ስራው ቢሆንም ከፍተኛ ገቢ እንደሚያገኝበት ይናገራል፡፡ የሰዎችን ድምፅ ማስመሰል ተሰጥኦዬ ነው የሚለው ሴጉጃ፣ የአገሩን ፕሬዚዳንት ብቻ ሳይሆን የአሜሪካውን ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማን፣ የዚምቧቡዌውን ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤን፣ የሊቢያ ፕሬዚዳንት የነበሩትን ሙአመር ጋዳፊንና የሌሎችንም አገራት መሪዎች ድምፅ በማስመሰል ከፍተኛ ዝናን አትርፏል፡፡ ማስመሰል ስላችሁ ደግሞ ሰዎች መለየት እስኪያቅታቸው ድረስ ማለቴ ነው፡፡ ለምሳሌ ከሁለት ዓመት በፊት የሙሴቪኒ “ናሽናል ረዚስታንስ ሙቭመንት” ፓርቲ በናምቡሌ ስታዲየም ለደጋፊዎቹ ቅስቀሳ ለማድረግ ጥሪ አቅርቦ ነበር፡፡ ገና ፕሮግራሙ ከመጀመሩ በፊት ግን ይሄ ኮሜዲያን መድረክ ላይ ወጥቶ ልክ እንደሙሴቪኒ ንግግሩን ጀመረ፡፡ አብዛኛው ታዳሚም ፕሬዚዳንቱ የሚናገሩ መስሎት አፉን ከፍቶ ሲያዳምጥ ነበር፡፡ ንግግሩን ሲጨርስም ሴቶች ሰብሰብ ብለው ወደተቀመጡበት ስፍራ በመሄድ ሰላምታ ሲሰጣቸው፣ ተንበርክከውና እጅ በመንሳት ነበር አፀፋውን የመለሱት፡፡ ፕሬዚዳንት ሙሴቪኒ መስለዋቸው! (እኛም እንደሴጉጃ ያለ ኮሜዲያን ያስፈልገናል) አንድ ጊዜ ደግሞ በኤፍኤም ሬዲዮ ቀርቦ ልክ እንደሙሴቪኒ ባደረገው ንግግር ብዙ ኡጋንዳውያንን ሸውዷል አሉ (ፕሬዚዳንቱም ራሳቸው ሳይሸወዱ አይቀሩም!) ሴጉጃ በኤፍኤም ካቀረበው የፕሬዚዳንቱ ንግግር በጥቂቱ እንመልከት - “ ፕሬዚዳንት መሆን ገነት መግባት የሚመስላቸው ሰዎች ሁለቴ ቢያስቡ ይሻላቸዋል፡፡ እንደኡጋንዳ ያለ አገር መምራት ቀላል አይደለም--- ሃቁን ለመናገር ኡጋንዳን መምራት ነዳጅ የሌለው ፎር ዊል ድራይቭ በተቆፋፈረ መንገድ ላይ መንዳት ማለት ነው----እንዲህ ያለውን መኪና ለመንዳት ደግሞ ልምድና ራዕይ ያላቸው ሰዎችን ይፈልጋል--”
እኔን ከሁሉም ያስገረመኝ ግን ምን መሰላችሁ? ኮሜዲያኑ ስራውን በሚያቀርብበት መድረኮች ከሚታደሙት መካከል ራሳቸው ፕሬዚዳንት ሙሴቪኒ አንዱ መሆናቸው ነው፡፡ መታደማቸው ብቻ አይደለም የገረመኝ፣ ኮሜዲያኑ እንደእሳቸው አስመስሎ ሲናገር እንባ በእንባ እስኪሆኑ ድረስ በሳቅ መፍረሳቸው ነው (ሲቀለድበት በሳቅ የሚፈርስ መሪ ማግኘት መታደል አይደል!) “ወደመድረኩ መቅረቤን እንደተመለከቱ ሙሴቪኒ በሳቅ ፍርስ ብለው እንባቸውን ጠረጉ፡፡
ሌሎች እንግዶችም እየሳቁ ነበር፡፡ እኔ ያየሁትን ማመን አልቻልኩም፡፡ በሁኔታው ተደስቼ ስለነበር እኔም ስቄአለሁ፡፡ መድረክ ላይ በነበርኩበት ጊዜ ሁሉ ሙሴቪኒ በጣም ሲስቁና እንባቸውን ሲጠርጉ ነበር፡፡ እኔ ግን ላለመሳቅ ራሴን መቆጣጠር ነበረብኝ” በማለት ኮሜዲያኑ ተናግሯል፡፡ መቼም እውነት አይመስልም አይደል? ግን እውነት ነው - ኒው አፍሪካን መፅሄት እንደዘገበው፡፡ በተረትና ምሳሌ የተሞሉት አስቂኝ የሙሴቪኒ ንግግሮች እንደሚስቡት የሚናገረው ሴጉጃ፣ ነገረ ስራቸው ሁሉ አስቂኝ እንደሆነና ከፕሬዚዳንት ይልቅ ኮሜዲያን እንደሚያስመስላቸው ለመፅሄቱ ተናግሯል፡፡
እንዲያም ሆኖ ግን ፕሬዚዳንቱን እንደሚወዳቸውና አድናቂያቸው እንደሆነ ነው ኮሜዲያኑ የተናገረው፡፡
በኮሜዲ ስራዎቹም በክፉ እንደማያነሳቸው ገልጿል (ከዚህ በላይ ምን ሊል ፈልጎ ይሆን?) አያችሁ ---እኛም እንዲህ ዓይነት ፖለቲከኞች ላይ ኮምኮ የማያስቀይም ኮሜዲያን ነው የምንፈልገው፡፡ በሳቅ ፍርስ አድርጎ እንባ በእንባ የሚያደርግ ኮሜዲያን በባትሪ ይፈለጋል፡፡
ምናልባት ተፈልጎ ከጠፋ ግን ተስፋ መቁረጥ የለም፡፡ ራሱን ሴጉጃን ከኡጋንዳ ማምጣት ይቻላል (ኡጋንዳ እኮ ቅርብ ናት!) እናላችሁ--- እንዲህ ዓይነት በፖለቲከኞች ላይ የሚኮምክ (ከጀርባቸው ሳይሆን እንደሙሴቪኒ ባሉበት) ኮሜዲያን ከተገኘ የፋሲካው የኢቴቪ የመዝናኛ ፕሮግራም “የሰቀለ” ይሆናል፡፡
አሁን ደግሞ ትንሽ ስለወቅታዊ ፖለቲካ እናውራ፡፡
እኔ የምላችሁ---- የዘንድሮ አንዳንድ መራጮች ነቃ ነቃ አላሉባችሁም? (በኢቴቪ የሚቀርቡትን ማለቴ እኮ ነው) ለምን የምርጫ ካርድ እንደወሰዱ ሲያስረዱ እኮ እኔ ነኝ ያለ ካድሬ ያስንቃሉ፡፡ (አስቀንተውኝ እኮ ነው) እኔማ ቢቸግረኝ ምን እንዳሰብኩ ታውቃላችሁ ---- ምናልባት “የመራጮች ሰራዊት” ተፈጥሮ ቢሆንስ ብዬ ጠረጠርኩ፡፡ ጥርጣሬዬ ግን የክፋት እንዳይመስላችሁ ----ለምን መረጃው ለህዝብ ይፋ አይሆንም ከሚል ብቻ ነው፡፡
ሁሉም ዜጋ በመራጮች ሰራዊት የመታቀፍ እድል እንዲያገኝ ከሚል ቀና ሃሳብ እኮ ነው (መቼም የኢህአዴግ አባል ካልሆናችሁ አይባልም አይደል?) አንዱ ወዳጄ ደግሞ ስለመራጮች ሰራዊት ሳጫውተው ምን ቢለኝ ጥሩ ነው? “ኢህአዴግ ስንት ሰራዊት ሲፈጥር የእግር ኳስ ሰራዊት እስከዛሬ እንዴት ትዝ ሳይለው ቀረ?” አይለኝ መሰላችሁ! ግን እኮ እውነቱን ነው --- የእግር ኳስ ሰራዊት እስከዛሬ ሳይፈጠር መዘግየቱ ትዝብት ውስጥ የሚጥል ነገር ነው፡፡ ግን አሁንም መፍጠን ይቻላል! ከ31 ዓመት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ያለፈው ብሄራዊ ቡድናችን ከደቡብ አፍሪካ እስኪመለስ ድረስ የእግር ኳስ ሰራዊት ፈጥሮ ሰርፕራይዝ ማድረግ ይቻላል - ብሔራዊ ቡድኑን፡፡ በዚህ አጋጣሚ ኢህአዴግ ሊፈጥራቸው እያሰበ በስራ ብዛት ሳይፈጥራቸው የቀሩ ሰራዊቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ስለገመትኩ አንዳንዶቹን ላስታውሰው እሻለሁ፡፡ ለምሳሌ -የዲያስፖራ ሰራዊት፣ የምሁራን ሰራዊት፣ የኢንቬስተሮች ሰራዊት፣ የአርቲስቶች ሰራዊት፣ የተማሪዎች ሰራዊት፣ የአስተማሪዎች ሰራዊት፣ የስራ ፈጣሪዎች ሰራዊት ወዘተ---እርግጠኛ ነኝ እኒህ በቅርቡ ተመስርተው ማየታችን አይቀርም (ወሳኝ እንደሆኑ ስለማውቅ እኮ ነው!) ከመሰነባበታችን በፊት ግን የገና በዓል ባለፈው ሰኞ ቢያልፍም እቺን የገና ቀልድ (የፈረንጅ ብትሆንም) ለአገሬ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደስጦታ ላበረክትላቸው እወዳለሁ (ግን ይቅርታ ጊዜው በማለፉ) - አንድ ቤተሰብ ውስጥ በመልክ ብቻ የሚመሳሰሉ መንታ ልጆች ነበሩ፡፡
ከመልካቸው ውጭ በተቀረው ሁሉ ተቃራኒ ናቸው፡፡ አንደኛው ብሩህ ተስፈኛ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ የለየለት ጨለምተኛ ነው፡፡ አባታቸው የገና እለት ጠዋት እስቲ የሚሆኑትን አያለሁ ይልና የጨለምተኛውን ልጅ መኝታ ክፍል በምርጥ አሻንጉሊቶችና መጫወቻዎች ይሞላለታል፡፡ የብሩህ ተስፈኛውን ልጅ ክፍል ደግሞ በፈረስ ፋንድያ ይሞላዋል፡፡ ምሽት ላይ አባት በጨለምተኛው ልጅ ክፍል ሲያልፍ ልጁ በስጦታዎቹ መሃል ተቀምጦ በምሬት ሲያለቅስ ያገኘዋል፡፡ “ለምንድነው የምታለቅሰው?” ሲል ጠየቀው አባቱ፡፡
“ጓደኞቼ የተገዛልኝን ስጦታ ሲያዩ ይቀናሉ፣ በእቃዎቹ ከመጫወቴ በፊት እላያቸው ላይ የተፃፉትን መመሪያዎች ማንበብ አለብኝ፣ በየጊዜው ደግሞ ባትሪዎች ያስፈልጉኛል፣ አሻንጉሊቶቹም አንድ ቀን መሰበራቸውም አይቀርም” ሲል መለሰ ጨለምተኛው መንታ፡፡
አባትየው በብሩህ ተስፈኛው ልጅ መኝታ ክፍል ሲያልፍ ግን የፋንድያው ክምር ላይ በደስታ ሲጨፍር አገኘው፡፡
“ምንድነው እንዲህ ያስደሰተህ?” ሲል ጠየቀው ልጁን፡፡
ልጁም “እዚህ ክፍል ውስጥ አንድ ቦታ ትንሽዬ ፈረስ አለች ብዬ ነው” በማለት መለሰ፡፡
አይገርማችሁም? ያኛው ጨለምተኛ መንታ በስጦታ ተንበሽብሾም ገና ወደፊት እንዲህ ይሆናል ብሎ ያለቅሳል፡፡
ይሄኛው ብሩህ ተስፈኛ ደግሞ ክፍሌ በፈረስ ፋንድያ የተሞላው እዚህ ክፍል ውስጥ ትንሽዬ ፈረስ ስላለች ነው ብሎ በደስታ ይቦርቃል፡፡ (የፖለቲካ ፓርቲዎች- ስጦታዬን ትልቅ ውለታ እንደዋልኩላችሁ እንዳትቆጥሩት አደራ እላችኋለሁ!)

Read 7282 times