Saturday, 12 January 2013 09:44

አንግሱኝ!

Written by  አዲስአለም ሀጎስ
Rate this item
(3 votes)

ግዜው ድሮ ነው፡፡ በቄስ ገብረስለሴ አማላጅነት የአቶ ዘሚካኤል ህልም እንዲሰማ በግራአዝማች ሹምየ የተመራ ያገር ሽማግሌዎች ተሰይመዋል፡፡ ግራዝማች ሹምየ ከቅዳሴ በኋላ ከቤተክርስትያን አጥር ውጪ በአለት የተከበበች ዋርካ ስር ለክብራቸው በተዘጋጀው ተንቀሳቃሽ ዙፋን ተቀምጠዋል፡፡ “ዘሚካኤል፤ ስራችንን የሚያስፈታ ምን ህልም ነው ያየኸው? እስቲ ባክህ ንገረን እንስማው” አሉ ግራዝማች ሹምየ፡፡ አቶ ዘሚካኤል ጥቁሩን የግራአዝማች ፊት በደንብ ሳያዩ ነጠላቸውን እያስተካከሉ ከወገባቸው ዝቅ ብለው አክብሮታቸውን ገለጡ፡፡ 

“አመሰግናለሁ፡፡ እጅግ በጣም አመሰግናለሁ ጌታዬ… አብሮ አደጐቼ አመሰግናለሁ፡፡ እንደምን አደራችሁ” አሉ፡፡ አቶ ዘሚካኤል ራሳቸውና ልጆቻቸዉ የሚላስ የሚቀመስ እህል አጥተው፣ መሳፍንቱ ግን በልተው ጠግበውና አጊጠው መኖራቸውን አሰቡና ንዴት ተሰማቸው፡፡ ወዲያው ግን ባገኟት አጋጣሚ ህይወታቸውን መለወጥ እንደሚችሉ እርግጠኝነት ተሰማቸው፡፡ “ቃሌንና ህልሜን ለመስማት በዚህ በርካታ ፍትህና ዕርቅ በተካሄደበት ዋርካ ስር የተገኛችሁ --- እንደምን አደራችሁ?” ለሰላምታቸው ግን መልስ የሰጠ የለም፡፡ 
“የድል ዜና እና አዋጅ በተነገረበት ዋርካ ስር ያላችሁ… ክብርና ሞገስ የሆናችሁ ያገር ሽማግሌዎች እንደምን ሰነበታችሁ?” አሁንም ለሰላምታው ምላሽ አላገኙም- ዘሚካአል፡፡
“ጀግኖች እና የጀግኖች ወላጆች … ”
ወሬያቸውን ሳይጨርሱ ግራአዝማች ጣልቃ ገብተው “አንተ ዘሚካኤል፣ እግዚአብሔር ይመስገን! ወደ ቁም ነገሩ በቀጥታ ግባ እንጂ፡፡ ህልምህ ምንድን ነው?” አሉ፡፡
“ቁም ነገሩ ከሳምንት በፊት ነው.. በቤተመንግስት ተገኝተን የግብር ስርዓት ፈፅመን፣ አመስግነን ወደየ ቤታችን ከተበታተን በኋላ እንቅልፍ እምቢ አለኝ…” ግራአዝማች በተቀመጡበት ተቁነጠነጡ፡፡
“አንተ ዘሚካኤል፤ ከተኛህ በኋላ ያየኸውን ህልም ተናገር!”
“እሺ የኔ ጌታ! እሺ የተከበራችሁ! ከቅዳሴ በኋላ አንዳችም ምግብ አለመብላታችሁን አውቃለሁ፡፡ ረሃባችሁ ይሰማኛል፡፡ ረሃብ የከፋው ስቃይ ነው፡፡ ድህነት ሃጥያት ነው፡፡ ፍትህ ማጣት የከፋው ቅጣት ነው…”
ሽማግሌዎች ትዕግስታቸው ተሟጧል፡፡ ግራአዝማች ፊታቸው በንዴት ሲለዋወጥ ለራሳቸው ተሰምቷቸዋል፡፡ በቁጣ “ማነህ ቄስ …” አሉ ከጎናቸው ላሉት ቄስ ገብረስላሴ “ለዚህ ነው ስራ ያስፈታኸን? ቁም ነገር ካለው በአጭሩ ይናገር፡፡ ካልሆነ ልንነሳ ነው”
ቄስ ገብረስላሴ ከተቀመጡበት ድንጋይ ላይ ወገባቸውን ይዘው ተነስተው፣ በመስቀላቸው ካማተቡ በኋላ “ውዱን የጌታችንን ጊዜ እያቃጠልከው ነው፡፡ የምትናገረውን ቁም ነገር በሶስት አራት ቃል ተናገር” ብለው በተነሱበት አኳኋን ወገባቸውን ይዘው ተቀመጡ፡፡
አቶ ዘሚካኤል ቀስ በቀስ የተሰበሰቡትን ሰዎች ተመለከቱ፡፡ ተፅእኖ ፈጣሪ ናቸው ብለው ያመንዋቸው ቀኛዝማች ዘመንፈስን በዓይናቸው ፈለጉዋቸው፡፡ ብዙም ሳይቆዩ አገኙዋቸው፡፡
“ቀኛዝማች ዘመንፈስ፣ ቄስ ዳዊት፣ መምህር ለአኮ … አላችሁ?” ብለው ጠየቁ፡፡ ተሰብሳቢዎቹ ስማቸውን ወደ ተጠሩ ሰዎች ፊታቸውን እያዞሩ መኖራቸውን አረጋገጡ፡፡
“የተከበራችሁ አዋቂዎች፤ እኔን ከባችሁ እየተወያየን፣ የለማችና ሰላምዋን የጠበቀች ዓለም ፈጥረን ታየኝ፡፡ ህልሜን በአዋቂዎች ባስፈታ “ንገስ” አሉኝ፡፡ እኔ አቶ ዘሚካኤል ካልነገስኩኝ ያልተረጋጋችና ጫጫታና ድርቅ የሚበጠብጣት ዓለም ትሆናለች፡፡ ለዚህ ሃገር የሚያስብ የሚቆረቆር እኔን ይመረጠኝ አንድ ዓመት አንግሱኝ” አሉ ዘሚካኤል፡፡
እቺን ከተነፈሱ በኋላ አቶ ዘሚካአል እፎይታ ተሰማቸው፡፡ በዋርካው ስር ግን ጫጫታ ሆነ፡፡ ሁሉም ነገር አፍ ሆነ፡፡ “አይሆንም! አይሆንም! ንግስና የልጆች ጨዋታ አይደለም! የማይታለመውን …”
በየአቅጣጫው “አይሆንም” የሚለው ቃል በተደጋጋሚ ተስተጋባ፡፡ ግራአዝማች በጣም ተናደዋል፡፡ የተደፈርኩኝ ተዋረድኩኝ ስሜት ተሰማቸው፡፡ ይህን ችግር በጥበብ መፍታት እንዳለባቸው ወሰኑ፡፡ ቄስ ገብረስላሴ አንገታቸውን ደፍተው መጨረሻው እንዲያምር መፀለይ ጀመሩ፡፡ ግራአዝማች ከተንቀሳቃሽ ዙፋናቸው ተነስተው በእጃቸው ፀጥታ እንዲከበር አዘዙ፡፡ በጥበቃ ላይ የነበሩ አሽከሮች ከመሃል እየገቡ ፀጥታ እንዲሰፍን አደረጉ፡፡
ከሽማግሌዎቹ በቅርብ ርቀት ልዩነት ቆም ብለው እየታዘቡ የነበሩ እረኞችና ወጣቶች አፋቸውን ይዘው መጨረሻውን እየተከታተሉ ናቸው፡፡ ግራአዝማች ተረጋግተው “በአንድ ዓመት የንግስና ግዜህ ምን ለማድረግ ወስነሃል?” ብለው ጠየቁ
“ግብር እቀንሳለሁ፣ የሰዎችን መብት እንዲከበር፣ ሰላምና ልማት እንዲረጋገጥ…”
“ያልካቸው ሁሉ አሁን በተጨባጭ የሉም?”
“እያሉ ነው የኔ ጌታ! እኔ በህልሜ ያየሁትን እንዳስፈታሁኝ በዚች ቀን፣ በዚች ታሪካዊ ቦታ በአዋቂዎች፣ በአለቆቼና በእረኞች ፊት እንድናገር ስለተነገረኝ ነው፡፡ ይህም እውነት አለው፡፡”
“ብለሃል፡፡ እኛም በትዕግስት ሰምተናል፡፡ ማነው ህልምህን የፈታልህ?” ጠየቁ - ግራአዝማች፡፡
“እባካችሁ አንግሱኝ” አሉ፡፡ አሁን ነገሩ ቀልድ መሰለ፡፡ የተሰበሰቡት ሰዎች ሳቁ፡፡ ዘሚካኤል እንደማይነግሱ ገባቸው፡፡ ግራአዝማች ዙፋናቸውን በዋዛ እንደማይለቁ እርግጠኛ ሆኑ፡፡
“አንድ ወርም ቢሆን አንግሱኝ” ጠየቁ ዘሚካኤል
“አይሆንም! አብደሃል… መታከም ያስፈልግሃል!”
“አብሮ አደጎቼ፣ ችግሬ ችግራችሁ አይደለም እንዴ? እባካችሁ አንግሱኝ…”
“ሰምተናል ጥያቄህን፣ አልተቀበልነውም፡፡ አንድ ወር ይቅርና አንድ ሰአትም አትነግስም፡፡ ይልቅ…”
አቶ ዘሚካኤል ከዋርካው ጥላ ውጪ ያገር ሽማግሌዎች ከበው ከሚመለከቱ እረኞች አንዱ የያዘውን ማንቲግ ተቀብለው፤ “በሰራዊት ጌታ ስም፡፡ በታቦት ስም፡፡ በዚህ ህዝብ ስም፡፡ በንግስናዎ ስም ይቺን ጦር ወርውሬ እስክትመለስ አንግሱኝ” ብለው የመጨረሻ ጥያቄ በልመና ጠየቁ፡፡ ይህ ካልሆነ ካሉበት ድህነት በተጨማሪ ሌላ ግፍና ስቃይ እንደሚደርስባቸው ስላወቁ ከመሬት ተደፍተው፣ ከግራአዝማች እግር ስር ሆነው ለመኑ፡፡ ከዋርካው ስር ፀጥታ ነገሰ፡፡ ሁሉም ጆሮ ሆኑ፡፡ ተያዩ፡፡ መጨረሻው ምን ይሆን ብለው መጠባበቅ ያዙ፡፡ ግራአዝማች ወደ ኋላቸው ተመቻችተው ቁጭ ብለው ካሰቡ በኋላ “እስቲ ይሁን እሺ” አሉ - ሁሉን ነገር ለማየትና ለመስማት ራሳቸውን እያዘጋጁ፡፡
ሽማግሌዎች አፋቸውን ያዙ፡፡ ነገሩን ለማየት እና ለመስማት ተቁነጠነጡ፡፡ አቶ ዘሚካኤል እጅግ በጣም ተደሰቱ፡፡ ዳግም የተወለዱ ያህል ተሰማቸው፡፡ ባለቤታቸው እና ልጆቻቸው ጠግበው የሚያድሩበት፤ ከሰው በላይ የሚሆኑበት ቀን ታያቸው፡፡ ከዋርካው ጥላ ውጪ ሆነው የያዙትን የእረኛ ማንቲግ በሃይል ወደ ላይ እንደ ሮኬት አወነጨፉት፡፡ እስኪመለስ በፍጥነት ይናገሩ ጀመር፤ “ልጅ መሐሙድ አስር በሬ፣ ፊታውራሪ ታጠቅ አንድ ሄክታር መሬት፣ አለቃ አዘናው ሃያ በግና ፍየል፣ ደጃች ሕሼ ሃያ ኩንታል ጤፍ፣ አንድ ኩንታል ማርና ቅቤ፣ ደጃች ሙስጠፋ አንድ ሺህ ብር ለሚስቴና ልጆቼ ይስጡልኝ፡፡ ግራአዝማች ሹምየ ያስፈፅሙልኝ፣ ቄስ ገብረስላሴ …”
የወረወርዋት ጦር ከላይ ተመልሳ ጭንቅላታቸውን ወጋቻቸው፡፡ ባሉበት ወደቁ፡፡ በሺዎች ተከበው ቁና ቁና ተነፈሱ፡፡ ሰውን ማየትና መለየት አልቻሉም፡፡ ሁሉነገር ጨለመባቸው፡፡ ትንሽ ቆይተው ቀና ለማለት ሞከሩና “ይፍቱኝ…” ብለው አረፉ፡፡

Read 5716 times