Saturday, 12 January 2013 09:51

የቤተእስራኤላውያኑ ምሬት በተስፋይቱ አገር “ጥሩ ኢትዮጵያዊ ማለት የሞተ ኢትዮጵያዊ ብቻ ነው--”

Written by  አልአዛር ኬ
Rate this item
(0 votes)

በተለያዩ ህብረ ቀለማት ያሸበረቁ ላባዎች ለአይን ማራኪ የሆኑ ወፎችን ይፈጥራሉ፡ ቤተእስራኤላውያን በኢትዮጵያ ያሳለፉት ከእጅ ወደ አፍ የሆነ የድህነት ህይወት እንደነበር መናገር ቀባሪውን እንደማርዳት ይቆጠራል፡፡
እናም ማራኪ ወፍ ለመሆን የሚያስችል ጌጠኛ ላባ አልነበራቸውም፡፡
በዘመቻ ሙሴም ሆነ በዘመቻ ሰሎሞን ወቅት የመዘጋጃ ጊዜአቸውን ያሳለፉት ዘመቻውን ያስተባብሩ የነበሩ የተለያዩ መንግስታዊ ያልሆኑ የአይሁድ ድርጅቶች ይሠጧቸው በነበረው የምግብ፣ የመጠለያ፣ የአልባሳትና፣ የጤና እርዳታ ነበር፡፡ በልባቸው ለዘመናት አትመው ይዘዋት የነበረው የተስፋዋ ሀገራቸው እስራኤል የተቀደሰችም ነበረችና ወደ እስራእል ለመግባት ያደረጉትን የመጨረሻ ዝግጅት ያጠናቀቁት በቻሉት መጠን ራሳቸውን በማዘጋጀት ነበር፡፡

እጃቸው እርጥብ የነበሩት ለራሳቸውና ለልጆቻቸው አዳዲስ ልብሶችን በመግዛት፣እጅ ያጠራቸው ደግሞ የነበሯቸውንና የአይሁድ ድርጅቶቹ የሠጧቸውን ልብሶች አጥበው ለብሠው ነበር፡፡ የረጅም ዘመናት የድህነት ህይወት የራሱን ወፍራም አሻራ ያተመበትን ወዙ የተመጠጠ ጐስቋላና የገረጣ ፊታቸውንም ባገኙት አንባሬ ጭቃ ቅባት በማውዛት፣ በእነሱ አቅምና ችሎታ መጠን ወደ ቅድስቲቱ ሀገር አምረውና ደምቀው ለመግባት በእጅጉ ተጣጥረው ነበር፡፡
ይህ ሁሉ መሽሞንሞናቸው ግን የእስራኤላውያኑን ቀልብ ሊስቡና በአይናቸውም ዘንድ ሞገስን ሊያስገኝላቸው ሳይችል ቀረ፡፡ ገና ወደ እስራኤል እንደገቡ እስራኤላውያኑ እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት አቅፈው ቢስሟቸውም ከኢትዮጵያ ስለሚመዘዘው ዘርና ቀለማቸው፣ ስለ አዳፋ ልብሳቸው፣ ስለተጐሳቆለውና ስለገረጣው ሰውነታቸው ካይናቸው ይልቅ ልባቸው አብዝቶ ተጠይፏቸው ነበር፡፡
በድፍን የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት እጅግ የሠለጠነና በስነምግባር የታነፀ ነው እየተባለ ዝናው ይናኝለት የነበረው የእስራኤል የሂብሩ ቋንቋ ፕሬስም፣ የአዲስ መጤዎቹን ባይተዋር ቤተእስራኤላውያን ነፃነትና ሰብአዊ መብት የሚጋፋ ሰብአዊ ክብራቸውንም ክፉኛ የሚያንቋሽሽና የሚያዋርድ ከፍተኛ ዘመቻ በመክፈት፣የእስራኤላውያኑን ዘረኝነትና ገና በማለዳው በቤተእስራኤሎች ላይ የያዙትን የልባቸውን መጠየፍ አለአንዳች ይሉኝታ ይፋ አደረገው፡፡ በየትኛውም ሀገርና የመንግስት ስርአት ውስጥ ቢሆን ፕሬስ እሳት ነው፡፡ እሳት መልካም አገልጋይ መጥፎ አለቃም ነው፡፡
በአግባቡ የተያዘ እሳት የሚሠጠውን ግልጋሎትና ከቁጥጥር ውጭ የሆነው ደግሞ የሚያደርሰውን ጥፋት ማንም ቢሆን በቀላሉ መረዳት ይችላል፡፡ የእስራኤል ፕሬስም በቤተእስራኤላውያኑ ላይ ከፍቶ የለቀቀባቸዉ ከቁጥጥር ውጪ የሆነ እሳትን ነበር፡፡
ቤተእስራኤላውያኑ ገና ወደ እስራኤል ከመግባታቸው እስራኤላውያኑ በዘር ጥላቻ ተመርዘው ያቀረቡላቸዉ ምግብ ጠንቀኛ መድሀኒት ቢሆንባቸውና አለመጠን ግራ ቢያጋባቸውም መርሳት ክፋትን ለመበቀል ምርጡ ዘዴ መሆኑን መገንዘብ በመቻላቸው፣ሁሉን ነገር ለመርሳት ሞክረው ነበር፡፡
በላይ በላዩ እንደ ጋራ ላይ ናዳ የወረደባቸው የዘረኝነት ጥቃት ግን ለመርሳትም እንኳ እድል ሳይሠጣቸው ቀረ፡፡
የእስራኤል የደም ባንክና የአምቡላንስ አገልግሎት ድርጅት የሆነው “ማገን ዴቪድ አዶም” ያለ አንዳች ተጨባጭ ማስረጃ እንዲሁ በግምት ብቻ ቤተእስራኤላውያኑ የለገሱትን ደም በኤችአይቪ/ኤድስ ቫይረስ የተበከለ ነው በሚል እየደፋ ሲያቃጥል መኖሩን ይፋ አደረገ፡፡ እንደ ማሻ ሐሮሽና እና ሪሾን ላዚወን የመሳሠሉ የከተማ ማዘጋጃ ቤቶች ቤተእስራኤላውያን ወደ ከተሞቻቸው መጥተው እንዲሰፍሩና እንዲኖሩ ጨርሶ እንደማይፈልጉ በግልጽ አሳወቁ፡፡
ከእስራኤል የኦርቶዶክስ አይሁዶች ጠንካራ ሀይማኖታዊ ቡድኖች ውስጥ አንዱ የሆነው “ሐባድ” የቤተእስራኤላውያንን አይሁድነት እንደማይቀበል በመግለጽ፣የቤተእስራኤላውያን ልጆች ቡድኑ አቋቁሞ በሚያስተዳድራቸው የመዋዕለ ህፃናት ትምህርት ቤቶች ውስጥ ገብተው መማር ጨርሶ እንደማይችሉ በጥብቅ አስገነዘበ፡፡ ፔታህ ቲክቫህ በተሰኘ ከተማ ውስጥ የሚገኘው የኒር ኤዚዎን ትምህርት ቤትም፣ ቤተእስራኤላውያን ተማሪዎች በትምህርት አቀባበላቸው ሰነፎች ስለሆኑና ሌሎች እስራኤላዊ ተማሪዎችን ስለሚጐትቱ አንድ ላይ መማር አይገባቸውም በሚል ቤተእስራኤላዊ ተማሪዎችን ለይቶ በመልቀም በአንድ ክፍል ውስጥ ማጐሩን ትንሽም እንኳ ቅር ሳይለው በይፋ ማሳወቅ ቻለ፡፡
የእስራኤል ባንኮች፣ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች፣ የአየር ማረፊያዎች ባለስልጣን፣ የመብራት ሀይል ኮርፖሬሽን ወዘተ ደግም በተራቸው ቤተእስራኤላውያንን ሠራተኞቻቸው አድርገው ለመቅጠር ምንም አይነት ፍላጐት እንደሌላቸው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ አቋማቸውን ግልጽ አደረጉ፡፡ በርካታ ቤተእስራኤላውያን ከሚኖሩባቸው የእስራኤል ከተሞች ውስጥ በግንባር ቀደምትነት የምትጠቀሰው ከተማ ኪርያት ማላኪህ ናት፡፡ ይህችን ከተማ እስራኤላውያን ቤተእስራኤሎችን በሚገባ ያዋሀድንባት ሞዴል ከተማችን እያሉ ነጋ ጠባ ያሞካሹዋታል፡፡ ነገር ግን ከየትኞቹም ከተሞች በላቀ ሁኔታ በቤተእስራኤላውያን ላይ አይን ያወጣ የዘረኝነት ጥቃት የሚካሄደው በዚች ከተማ ውስጥ ነው፡፡
በዚች ከተማ ውስጥ ከሚካሄዱት የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ (ሪል ኢስቴት) ፕሮጀክቶች ውስጥ የአንዱ ፕሮጀክት ኮንትራክተር የሆነው ያዕቆብ ቫክኒን የሚገነባቸውን የመኖሪያ ቤቶች እንቅ ቢል እንኳ ለቤተእስራኤላውያን ሊሸጥላቸው እንደማይፈልግ ያለ አንዳች ማመንታት አሳወቀ፡፡
“Channel-2” የተሠኘው የእስራኤል ቴሌቪዥን ደግሞ በኪርያት ማላኪህ ከተማ ምክር ቤት ውስጥ የባር ይሁዳ ሠፈር ነዋሪዎች፣ለቤተእስራኤላውያን ቤት ለማከራየትና ላለመሸጥ እየተማማሉ ሲፈራረሙ በማሳየት ተመልካቹን ሁሉ አስገረመ፡፡
ይሄው ቴሌቪዥን ይህን ድርጊት ብቻ ማሠራጨቱ ስላልበቃው፣ ይግረማችሁ ብሎ የዚሁ የባር ይሁዳ ሠፈር ነዋሪዎች የሆኑ ሁለት እስራኤላውያን በየተራ ቀርበው “ጥሩ ኢትዮጵያዊ ማለት የሞተ ኢትዮጵያዊ ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ልክ እንደ አቶሚክ ቦንብ ይሸታሉ፡፡” በማለት ነውርንም ህግንም ሳይፈሩ የተናገሩትን የለየለት ዘረኛ ንግግር በተጨማሪ በማሠራጨት ማን አለብኝነቱን በሚገባ ለማስመስከር ቻለ፡፡
አሁን በቅርቡ የተጋለጠው ድርጊት ደግሞ የቤተእስራኤላውያን የወሊድ መጠን ባለፉት አስር አመታት ጊዜ ውስጥ በሀያ በመቶ የቀነሰበትን ሚስጥር የፈታና ቤተእስራኤላዊ እናቶች ላለፉት አስር አመታት ግቢያቸው የህፃናት የቡረቃ ድምጽ እርቆትና የሳራና የርብቃ አምላክ በሽልም ያውጣሽ ተብለው ሳይመረቁ፣ ማን ምን አድርጓቸው ወላድ ማህፀናቸው እንደነጠፈ የሚያስረዳው አሳዛኝ የዘረኝነት ገድል ነው፡፡
እንግዲህ ልብ አድርጉ፡፡ ከዚህ በላይ የተዘረዘሩት ታሪኮች በቤተእስራኤላውያኑ ላይ የተፈፀሙትን የዘረኝነት ጥቃቶች ላይ ላዩን ለማመልከት ለናሙና ያህል ብቻ የቀረቡ ታሪኮች ናቸው፡፡
ቤተእስራኤላውያን ተቆጥረውና ተዘርዝረው የማያልቁ እነዚህን መሰል የዘረኝነት ጥቃቶችን ላለፉት ሀያ ሠባት አመታት ወደው እስኪጠሉ ድረስ ሲቀበሉ ኖረዋል፡፡
በአይሁድ እምነት ዘንድ ለምዕመናኑ እንደ ዋና ዋና ፀጋዎች ተደርገው ከሚቆጠሩት መልካም ድርጊቶች ውስጥ አንዱ መልካም የእንግዳ አቀባበል ነው፡፡ የአይሁዶች የታናካህ ቅዱስ መጽሀፍ፣ ሰዎች ሳያውቁት የአምላክ ቅዱስ መላዕክት በእንግድነት ሊመጡባቸው ስለሚችሉ ለማናቸውም አይነት እንግዶች መልካም አቀባበልና መስተንግዶ በማድረግ፣የአምላክን ምርቃትና በረከት እንዲያገኙ የቀደመውን አባታቸውን አብርሀምን በምሳሌነት በመጥቀስ፣ የእርሱን አብነት እንዲከተሉ ያሳስባል፡፡
በዘፍጥረት 18 እንደተገለፀው፣ አብርሀም በድንኳኑ ደጃፍ ተቀምጦ ሳለ ሶስት ሰዎች በፊቱ ቆመው ባያቸው ጊዜ ሊቀበላቸው ከድንኳኑ ደጃፍ ተነስቶ ሮጠ፡፡ ወደ ምድርም ሠገደና ከዛፏ በታች እንዲያርፉ፣እግራቸውንም እንዲታጠቡና በቁራሽ እንጀራም ልባቸውን እንዲደግፉ ተማፀናቸው፡፡
ፈቃደኝነታቸውን እንዳገኘም በመልካም ሁኔታ አስተናገዳቸው፡፡ በአብርሀም መልካም መስተንግዶ ልባቸው ደስ የተሰኙ እንግዶችም በልጅ ፀጋ ያልታደለው የባለቤቱ የሳራ ማህፀን እንደሚለመልምና ልጅንም እንደምታገኝ አብስረውት ሄዱ፡፡
እነዚያ ሶስት እንግዶች የአምላክ መልዕክተኞች ነበሩና የነገሩት ብስራት አምላክ ለሠራው መልካም ስራ አምላክ የሰጠው ምርቃት ነበርና አብርሀም በኋላ የእስራኤላውያን አባት የሆነውን ይስሀቅን ማግኘት ቻለ፡፡
እስራኤላውያን በቤተእስራኤላውያን ላይ የዘረኝነት ጥቃት በመፈፀም ያጡትና የተላለፉት ይህንን የመልካምነትን ፀጋና ከመልካም ስራ የሚገኝን የአምላክን በረከት ነው፡፡ ነገሮች ሁሉ በዚህ ብቻ ቢያልፉ ኖሮ ግን ለሁሉም ወገን ጽድቅ በሆነ ነበር፡፡
(ይቀጥላል)

Read 3970 times