Saturday, 19 January 2013 14:39

የማደንዘዣ መድሃኒቶችና የሙያተኞች ፈታኝ ገጠመኞች

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

ጥንታውያን ግሪኮች ከባድ የህመም ስቃይን ለመቀነስ ወይንም ከበድ ላሉ የቀዶ ህክምና ሥራዎች በድብደባ ራስን የማሳት ዘዴን ይጠቀሙ ነበር፡፡ ለጥርስ ህክምናም ሐኪም ዘንድ የቀረበ ታማሚ በደህና ቡጢኛ መንጋ ጭላውን በቦክስ ይመታና ራሱን እንዲስት ይደረጋል፡፡ ግሪካውያኑ ይህንን ዘዴ በሥራ ላይ ከማዋላቸው በፊት ከበድ ያለ ቀዶ ህክምናን ለማከናወን የታማሚውን እጅና እግር ጥፍር አድርጐ በማሰርና እንዳይንቀሳቀስ በማድረግ ህክምናውን ያከናውኑ ነበር፡፡ ይህ ዘዴ በሽተኛውን ለከፍተኛ ስቃይና ለተጨማሪ ህመም በመዳረጉ የህክምና ባለሙያዎቹ ታማሚውን ደብድቦ ራሱን እንዲስት በማድረግ የማከም ዘዴን ተግባራዊ ማድረግ ጀመሩ፡፡ ታማሚው ለቀዶ ህክምና ወደ ኦፕሬሽን ክፍል በሚገባበት ወቅት የህክምና ባለሙያው አሳቻ ቦታ ላይ ጠብቆ በዱላ አናቱን ይለውና ራሱን ስቶ እንዲወድቅ ያደርገዋል፡፡ ከዚያም ቀዶ ሐኪሙ ሰውየው ነቅቶ ራሱን ከማወቁ በፊት በአፋጣኝ የቀዶ ህክምናውን አከናውኖ ማጠናቀቅ ይኖርበታል፡፡

ይህ ዘዴ ለዓመታት ተግባራዊ ሲደረግ የኖረና የበርካቶችን ህይወት የታደገ ቀደምት የህክምና ዘዴ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ይህን ኋላቀር አሠራር በዚህ ሁኔታ መቀጠል እንዳይችል ያደረገው ግኝት እ.ኤ.አ በ1772 ዓ.ም ጆሴፍ ፕሪስትሪ በተባለ ተመራማሪ እውን ሆነ፡፡ በህክምናው ዓለም እጅግ ታላቅ ግኝት ከሚባሉት መካከል አንዱ እንደሆነ የሚነገርለት የማደንዘዣ መድሃኒት፤ የቀዶ ህክምና አገልግሎት ወደተሻለ ደረጃ እንዲሸጋገር ከፍተኛውን አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ የማደንዘዣ (የሰመመን) መድሃኒት ስሙን ያገኘው ከጥንት የግሪክ ስልጣኔ ሲሆን (anesthesia) ወይንም (without sensation or feeling) በማደንዘዝ የህመም ስሜትን ማስወገድ የሚል ስያሜ ተሰጥቶት እ.ኤ.አ በ1772 ዓ.ም ሥራ ላይ ዋለ፡፡ ለማደንዘዣ አገልግሎት ለመጀመሪያ ጊዜ ሥራ ላይ የዋለው መድሃኒት ናይትረስ ኦክሳይድ (Nitrous Oxide) በመባል ይታወቃል፡፡ ይህ የማደንዘዣ መድሃኒት ተጠቃሚውን ሰው በሳቅ የማፍነክነክ ባህርይ ስላለው "Laughing gas" (አስቂኙ ጋዝ) የሚል መጠሪያም ተሰጥቶት ነበር፡፡

የዚህ ማደንዘዣ የማደንዘዝ አቅም ጥሩ ቢሆንም ታማሚውን በቀዶ ህክምናው ወቅት እንደደነዘዘ የማቆየቱ ጉዳይ እምብዛም አጥጋቢ አልነበረም፡፡ በዚህ ምክንያትም ተመራማሪዎቹ ከዚህ የተሻለ የማደንዘዝ አቅም ያላቸውና ረዘም ላሉ ሰዓታት ታማሚው እንደደነዘዘ ለማቆየት የሚያስችሉ የማደንዘዣ መድሃኒቶችን ለመሥራት ጥረታቸውን ቀጠሉ፡፡ የአመታት ድካምና ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ እ.ኤ.አ በ1846 ዓ.ም ይበልጥ ጠንካራና አስተማማኝ የሆነ Either (ኢተር) የተባለ ማደንዘዣ ተሰርቶ በሥራ ላይ ዋለ፡፡ ቀስ እያለም ክሎሮፎርም፣ ሃሎቲንና ኬታሚን የተባሉ የማደንዘዝ ብቃታቸው ከፍ ያለ የማደንዘዣ መድሃኒቶች እየተሰሩ በጥቅም ላይ መዋል ጀመሩ፡፡ የማደንዘዣ መድሃኒት የምጥ ህመምን ለማስወገድ ለመጀመሪያ ጊዜ በጥቅም ላይ የዋለው ለንግስት ቪክቶሪያ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያወጉናል፡፡ የማደንዘዣ (የሰመመን መድሃኒቶች) ዛሬ ዛሬ እጅግ ወደተሻለ ደረጃ ላይ በመድረሳቸው ታማሚው አንዳችም አይነት የህመም ስሜት ሳይሰማው ህክምናውን ለማከናወን እንዲችል እያደረጉት ይገኛሉ፡፡ በቀዶ ህክምናም ሆነ በሌሎች ከበድ ያሉ ህክምናዎች ወቅት በአብዛኛው ተግባራዊ የሚደረጉት ሁለት አይነት የማደንዘዣ አሰጣጥ ሥርዓቶች ናቸው፡፡ ከእነዚህ መካከል አንደኛው (General Anesthesia) የሚባለው ሲሆን ይህም በአብዛኛው ከወገብ በላይ ላሉ ማለትም ለሆድ ውስጥ ህክምና፣ ለኩላሊት፣ ለሳንባ፣ ለልብና ለጭንቅላት ህክምናዎች ተግባራዊ የሚደረግ የማደንዘዝ ህክምና ነው፡፡ በዚህ የሰመመን ህክምና ጊዜ የማደንዘዣ ባለሙያው (አንስቴቲስቱ) የሰውየውን ትንፋሽ ተቀብሎ ለበሽተኛው ትንፋሽ በመስጠት ቀዶ ህክምናው እስከሚጠናቀቅ ድረስ የሚቆይበት አሠራር ነው፡፡ ይህ የማደንዘዣ ህክምና በርካታ አደጋዎች ያሉትና የማደንዘዣ ሰጪ ባለሙያውን ከፍተኛ ትኩረት የሚጠይቅ ሥራ ነው፡፡ ሁለተኛው የማደንዘዣ የምንለው ሲሆን ይህ የማደንዘዣ አይነት በነርቮች ውስጥ ባሉ መዋቅር ውስጥ መድሃኒቶችን በማስገባት ሰውየው ራሱን ሳይስት ህክምናው በሚደረግበት አካባቢ ብቻ እንዲደነዝዝ የማድረግ ሥራ ነው፡፡ ለምሣሌ ሄሞሮይድና ፌስቱላን ለመሳሰሉ ህክምናዎች ይህ ዘዴ እጅግ ተመራጭ ነው፡፡ አሁን አሁን ይህ የማደንዘዣ ህክምና በኦፕሬሽን ለሚወልዱ ሴቶችም በጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል፡፡ ይህ የማደንዘዝ ህክምና አንዲት እናት ለወሊድ ስትሄድ ከወገብ በታች በማደንዘዝ ምንም አይነት ህመም ሳይሰማት ልጁን ማውጣት የሚያስችል ነው፡፡ ህክምናው በዋጋው አነስተኛ ከመሆኑም በተጨማሪ ሐኪሙ (የወላዷን) ሁኔታ በሚገባ እየተከታተለና ከወላዷ ጋር ስላለችበት ሁኔታ እየተነጋገረና መረጃ እየተቀበለ የሚሰራው ህክምና ስለሆነ ባለሙያዎቹ ይህንን የማደንዘዝ ህክምና ተመራጭ ያደርጉታል፡፡

የሰመመን መድሃኒት ከሚሰጣቸው ህሙማን መካከል በመድሃኒቱ ደንዝዘው በቀዶ ህክምናው ወቅት የሚከናወኑትን ተግባራት ፈጽመው የማያውቁና የማያስታውሱ በርካታ ህሙማኖች ቢኖሩም በተሰጣቸው የማደንዘዣ መድሃኒት አማካኝነት ደንዝዘው መንቀሳቀስ ባይችሉም ህመሙ የሚሰማቸውና በቀዶ ህክምናው ወቅት የሚደረጉ ነገሮችን የሚያዳምጡ ህሙማንም አሉ፡፡ ይህንንም (Anesthesia Awarenes) ይሉታል ባለሙያዎቹ፡፡ እነዚህ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ከተለያዩ ሱሶች ጋር በተያያዘ (ሲጋራና ሐሺሽ ማጨስ፣ የአልኮል መጠጦችን) በብዛትና ረዘም ላሉ ጊዜያት ከመጠቀም ጋር ሊገናኝ እንደሚችልም ባለሙያዎቹ ይናገራሉ፡፡ አንድ ሰው ሊቀበለው ከሚችለው የማደንዘዣ መድሃኒት በላይ መስጠት ሰውየውን ለአደጋ በማጋለጥ ወደ ሞት ሊወስደው እንደሚችልም እነዚሁ ባለሙያዎች ይገልፃሉ፡፡ ይህንን ክስተትም ባለሙያዎቹ "Death on the table" (የጠረጴዛ ላይ ሞት) ሲሉ ይጠሩታል፡፡ ይህ ክስተት ህመምተኛው ከተሰጠው ማደንዘዣ (የሰመመን መድሃኒት) መንቃት ሲያቅተውና በዚያው ህይወቱ ሲያልፍ ወይንም ለፈውስ ተጋድሞበት የነበረው የቀዶ ህክምና ጠረጴዛ መገነዣው ሲሆን ባለሙያዎቹ የሚጠቀሙበት መግለጫ ነው፡፡ ለጠረጴዛ ላይ ሞት በርካታ መንስኤዎች ቢኖሩም ዋናዋናዎቹ ከዚህ የሚከተሉት ናቸው፡፡ የበሽታው ሥር መሰደድና የኦፕሬሽኑ አስቸጋሪነት፣ በኦፕራሲዮኑ ወቅት በሚደረግ የጥንቃቄ ጉድለት፣ የማደንዘዣ አለርጂነት፣ ለማደንዘዣ መድሃኒቶች ያልተጠበቀ ምላሽ መስጠትና ከአቅም በላይ መጠን ያለው የማደንዘዣ መድሃኒት መጠቀም ዋነኞቹ ናቸው፡፡

በኦፕሬሽን ክፍል ውስጥ ከቀዶ ሐኪሙ እኩል ለህክምናው ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርገውና ለበሽተኛው በህይወት መመለስ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው የሰመመን ሰጪ ባለሙያው ነው፡፡ ለዚህም ነው የአኒስቴዥያ ሙያን "ህይወትን በአደራ ተቀብሎ በአደራ የመመለሻ ሙያ ነው" የሚሉት፡፡ የማደንዘዣ ሰጪ ባለሙያ ወይንም የሰመመን ሰጪ ባለሙያ በሚሉት ስያሜዎቻቸውም ባለሙያዎቹ አይስማሙም፡፡ ይህ ስያሜ ሙያውን በትክክል የሚገልጽ አይደለም ሲሉ ይቃወሙታል፡፡ ሙያው የአንስቴዥያ ሙያ እየተባለ ሊጠራ ይገባዋልም ይላሉ፡፡ የአንስቴዥያ ሙያ የሰው ልጅ በህይወትና በሞት መካከል በሚገኝበት የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ በመገኘት የሰውየውን ህይወት በአደራ አቆይቶ የመመለስ ጉዳይ እንደመሆኑ ሙያው ከፍተኛ ጥንቃቄና አትኩሮትን የሚሻና ለቅንጣት ስህተት ቦታ የማይሰጥ ነው፡፡ በዚህ ሙያ ውስጥ ያለ ሙያተኛ በሥራው ላይ የሚፈጽመው ቅንጣት ስህተት ህመምተኛው በዛው በተጋደመበት የኦፕሬሽን ጠረጴዛ ላይ እስከዘለዓለሙ እንዲያሸልብ ሊያደርገው ይችላል፡፡ በአኒስቴዥያ ሙያ ውስጥ ያለ አንድ አኒስቴቲስት በአንድ ጊዜ ለምን ያህል ጊዜያት ለህሙማን ማደንዘዣ መስጠት እንደሚችል በግልጽ የተቀመጠና የተገደበ ነገር ባይኖርም፣ በውጪው ዓለም የማደንዘዣ ባለሙያው በአንድ ቀን ከሶስት ጊዜያት በላይ የማደንዘዣ መድሃኒቶችን እንዲሰጥ አይፈቀድለትም፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ የሰመመን ሰጪ ባለሙያው የሰመመን መድሃኒቱን በሰጠ ቁጥር በተለያዩ መንገዶች ወደ ራሱ የሚያስገባቸው መድሃኒቶች በመኖራቸውና እነዚህ መድሃኒቶች ደግሞ ቀስ በቀስ የሰመመን ሰጪ ባለሙያው ራሱን በማደንዘዝ ሥራውን ትኩረት ሰጥቶና አስቦ ለማከናወን እንዳይችል ያደርገዋል የሚል ነው፡፡

በአንድ የቀዶ ህክምና ክፍል ውስጥ ከቀዶ ሐኪሞቹና ከነርሶቹ ጋር ተመሳሳይ የሥራ ቱታ ለብሰውና ፊታቸውን በጭንብል ሽፍነው - እያንዳንዷን የህመምተኛውን እንቅስቃሴ በከፍተኛ ትኩረት እየተከታተሉ የሰመመን መድሃኒቶችን በመስጠት ህመምተኛውን ለኦፕሬሽን ዝግጁ የሚያደርጉት እነዚህ ባለሙያዎች፣ ከቀዶ ህክምናው በኋላ በህመምተኛው ላይ የሚያስተውሏቸው ለየት ያሉ ገጠመኞችና በሥራቸው ላይ ያጋጠሟቸው በርካታ አሳዛኝና አስደሳች ገጠመኞችም አሏቸው፡፡ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ለ17 ዓመታት በአንስቴዥያ ሙያ ውስጥ ሲሰራ የቆየው አንስቴቲስት ክብረት አበበ፤ በእነዚህ ረዘም ያሉ የሥራ ጊዜያት በርካታ አስደሳች፣ አሳዛኝና አስገራሚ ገጠመኞችን አስተናግዷል፡፡ ሙያውን እጅግ አጥብቆ እንደሚወድ የሚናገረው አቶ ክብረት፤ አንድ ህመምተኛ በአንስቴቲስቱ በኩል ካላለፈና ዝግጁ ካልሆነ በስተቀር ወደቀዶ ህክምናው ሊያልፍ አይችልም፡፡ የማደንዘዝ ሥራ ያለፍላጐትና ያለፍቅር ከተሰራ የሰውን ህይወት በቀላሉ ሊያሰነጥቅ የሚችል ሥራ ነው ይላል፡፡ በ17 ዓመት የአኒስቴቲስትነት የሙያ ዘመኑ እጅግ በርከት ያሉ ገጠመኞችን ቢያስተናግድም ከእውቁ የማህፀን ሐኪም ከፕሮፌሰር ሉክማን ጋር ያደረገውን ግን ፈጽሞ አይረሳውም፡፡ አንዲት የሃምሣ አመት ሴት በማህፀን እጢ ችግር ወደ ሆስፒታሉ ይመጣሉ፡፡ በወቅቱ የሴትየዋ ክብደት 67 ኪሎ የሚመዝን ሲሆን በማህፀናቸው ውስጥ ያደገው እጢ መጠን ደግሞ ከሰላሣ ኪሎ በላይ ክብደት ያለው ነበር፡፡ ይህ ከሴትየዋ ጠቅላላ ክብደት ጋር ተመጣጣኝነት ያለውን እጢ ለማውጣት ሲታሰብ ዋንኛውና አሳሳቢው ጉዳይ ለሴትየዋ የሚሰጠው የማደንዘዣ ህክምና በምን መልኩ ይሰጥ የሚለው ነበር፡፡ የማደንዘዣ መድሃኒቶች በአብዛኛው የሚሰጡት ታማሚውን በጀርባው በማስተኛት ቢሆንም ይህንን አሠራር በእኚህ ሴት ላይ ተግባራዊ ለማድረግ ፈጽሞ የማይታሰብ ሆነ፡፡ ምክንያቱም በጀርባቸው በሚተኙበት ወቅት የእጢው ክብደት ሙሉ በሙሉ በሰውነታቸው ላይ በማረፍ ስለሚሸፍናቸው ነበር፡፡ ሁኔታው አስቸጋሪ ቢሆንም ለእኚህ ሴት በመቀመጥ የሚሰጠው የማደንዘዣ መድሃኒት እንዲሠራላቸው ይወሰንና ህመምተኛዋ በዚህ መልኩ የማደንዘዣ መድሃኒት ተሰጥቶአቸውና የተሣካ ኦፕሬሽን ተደርጐ የማህፀን እጢው ወጥቶላቸዋል፡፡ ይህም በሆስፒታሉ የህክምና ታሪክ ውስጥ እጅግ ስኬታማ የህክምና ተግባር የተከናወነበት እና እስከቅርብ ጊዜ ድረስም በሪከርድነት ተጠቃሽ የነበረ ስራ መሆኑን አቶ ክብረት ይናገራል፡፡ ህሙማን የማደንዘዣ መድኒቶችን በሚወስዱበት ጊዜ የተለያዩ ባህሪያትን ያሳያሉ፡፡

በመድሃኒቱ ኃይል መደንዘዝ ሳይችሉ ቀርተው ህመሙ እየተሰማቸው ህክምናው ከሚደረግላቸው ጀምሮ ከሰመመን መድሃኒቱ በቶሎ መንቃት አቅቷቸው ለሰዓታት ራሳቸውን ስተው እስከሚቆዩት ድረስ በርካታ ህሙማንን አግኝቷል፡፡ አቶ ክብረት በዚህ የአስራ የአንስቴቲስትነት ሙያው ገና ከተወለደ ህፃን ልጅ ጀምሮ 100 ዓመት እስከሆናቸው አዛውንት ድረስ አስተናግዷል፡፡ በተለይ በህፃናት የማደንዘዣ መድሃኒት አሰጣጥ ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄና ትኩረት መደረግ እንዳለበት የሚናገረው አቶ ክብረት፤ በአንድ ወቅት ሣንቲም በመዋጡ ምክንያት የመተንፈሻ አካሉ ተዘግቶ ወደ ሆስፒታሉ መጥቶ የነበረውን ህፃን ታሪክ ያስታውሳል፡፡ ህፃኑ የዋጠው ሳንቲም በአየር ማስተላለፊያ ቱቦው ላይ በማረፍና ቱቦውን በመዝጋቱ ምክንያት የአየር እጥረት አጋጥሞት ነበር፡፡ ለህፃኑ ተገቢውን የሰመመን መድሃኒት ይሰጠውና ሐኪሙ ወደ ህፃኑ ጉሮሮ ውስጥ መሣሪያ በማስገባት ሳንቲሙን በቀላሉ ከህፃኑ ጉሮሮ ላይ ያወጣዋል፡፡ እንደ ህክምና ሙያ ሥርዓትና ደንብ መሠረት፣ ከህፃኑ ጉሮሮ ላይ የወጣው ሳንቲም ለህፃኑ ቤተሰብ ተሰጠ፡፡ ሆኖም ህፃኑ ከኦፕሬሽን ክፍሉ መውጣት አልቻለም፡፡ ምክንያቱም በህፃኑ የአየር መተላለፊያ ቱቦ ላይ ተቀምጦ የነበረው ሣንቲም የአየር ማስተላለፊያ ቱቦው እንዲያብጥ በማድረጉና ህፃኑ መተንፈስ እንዳይችል ቱቦው ተዘግቶ በመቅረቱ ነበር፡፡ ሐኪሙ ከእሱ የሚጠበቀውን አከናውኖ ከክፍሉ ቢወጣም ህፃኑ ባለመውጣቱ ቤተሰቦቹ ግር አላቸው፡፡ ቆየት ብሎም ግርታው ቁጣ አስከተለ፡፡ ሐኪሙ ህክምናውን በአግባቡ አከናውኗል፡፡ ከዚህ በኋላ ያለው ጉዳይ የሰመመን ሰጪ ባለሙያው ነው፡፡ ህፃኑ ቢሞትም የገደለው እሱ ነው ብለው ቤተሰቦቹ የአቶ ክብረትን ከክፍሉ መውጣት በቁጣ መጠባበቅ ያዙ፡፡ ሁኔታው ከበድ ያለ ሲመስለው አቶ ክብረት ዶክተሩን ያስጠራዋል፡፡ የህፃኑን ህይወት ለመታደግ ሙያው የሚጠይቀውን መስዋዕትነት ሁሉ በመክፈል ላይ ያለ መሆኑን የተገነዘበው ሐኪሙም፤ ስለሁኔታው ለህፃኑ ቤተሰቦች ማስረዳት ጀመረ፡፡ ጉዳዩ ባይዋጥላቸውም የልጃቸውን የመጨረሻ እጣ ለመጠበቅ ዝምታን መረጡ፡፡ ከሰዓታት በኋላ የልጁ ትንፋሽ ሲመለስ ህፃኑን ጥብቅ ክትትል ወደሚሰጥበት ክፍል በማዛወር በከፍተኛ ክትትልና ጥበቃ ወደ ትክክለኛ የአተነፋፈስ ስርዓቱ እንዲመለስ በማድረግ የቀድሞውን ጤናማ ህፃን መልሶ ለቤተሰቦቹ ለማስረከብ ቻለ፡፡ ከህፃናት ጋር በተያያዘ አቶ ክብረት ሌላ ገጠመኝም አለው፡፡ ህፃኑ ከቤተሰቦቹ ጋር ምሽቱን ከአሜሪካ አዲስ አበባ ገባ፡፡ ጉዞ ያደከማት እናት ጡቷን ለህፃን ልጇ እንዳጐረሰች እንቅልፍ ሸለብ ያደርጋታል፡፡ ስትነቃ በአንገቷ ላይ ያደረገችው ሃብል ተበጥሶ መስቀሉ የልጇ ጉሮሮ ውስጥ መሰንቀሩ አወቀች፡፡ ልጇ ትንፋሽ አጥቶ ሲቃትት በከፍተኛ ድንጋጤ ተውጣ ልጇን ይዛ ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በረረች፡፡ የህፃኑ ትንፋሽ ከደቂቃ ደቂቃ እየደከመ፣ የሰውነቱ ቀለም እየጠቆረ ሄደ፡፡ ወደ ቀዶ ጥገና ክፍል ሲገባ ህፃኑ በህይወት ይመለሳል ብሎ ያሰበ አልነበረም፡፡ በቀላል የሰመመን መድሃኒት ህፃኑ ራሱን እንዲስት ተደርጐ ሐኪሙ መስቀሉን ከህፃኑ ጉሮሮ ውስጥ በቀላሉ ፈልቅቆ አወጣው፡፡ በአስገራሚ ፍጥነት የልጁ ሰውነት ወደ ቀድሞው ቀለሙ እየተቀየረ መጣ፡፡ የህፃኑም ቤተሰቦች ሆኑ በአካባቢው የነበሩ ሰዎች ሁኔታውን ለማመን አስቸግሯቸው ነበር፡፡


Read 5220 times