Print this page
Sunday, 20 January 2013 12:47

ቅ/ሲኖዶስ የፓትርያሪክ ምርጫ ሂደቱ እንዲቀጥል ወሰነ

Written by 
Rate this item
(0 votes)
  • •ውሳኔውን የተቃወሙት የቅ/ሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ የመልቀቂያ ደብዳቤ አስገብተዋል
  •  የሰላሙና የዕርቅ ሂደቱ ‹‹ኹኔታዎች ሲመቻቹ›› በሌላ አደራዳሪ አካል ይቀጥላል
  •  ‹‹6ውን ፓትርያሪክ በአንድነት ለ መምረጥ የተደረገው ጥረት አል ተሳካም›› የቅ/ሲኖዶሱ መግለጫ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ፣ የስድስተኛው ፓትርያሪክ ምርጫ ሂደት ሕገ ቤተ ክርስቲያንንና ቀኖናውን ጠብቆ እንዲቀጥል ወሰነ፡፡ ቅ/ሲኖዶሱ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ከጥር 6 - 8 ቀን 2005 ዓ.ም በወቅታዊ የቤተ ክርስቲያኒቱ ጉዳይ ላይ ሲያካሂድ የቆየውን የምልአተ ጉባኤ አስቸኳይ ስብሰባ ሲያጠናቀቅ ባወጣው ባለሦስት ነጥብ የውሳኔ መግለጫው ነው፡፡

ከአምስተኛው ፓትርያሪክ ኅልፈተ ሕይወት በኋላ በሰሜን አሜሪካ ከሚገኙ አባቶች ጋር ተጀምሮ ለቆየው የሰላምና አንድነት ጉባኤ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ልኡካኑን በመላክ፣ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ፣ ሊያቀራርቡ የሚችሉ በርካታ የሰላም አማራጮችን ማቅረቡን በመግለጫው ያስታወሰው ቅ/ሲኖዶሱ፤ ‹‹በዚያ በኩል ባሉ አባቶች ምንም ዐይነት የሰላም ፍንጭ አለመታየቱንና የሰላም ስምምነት ለመፈጸም አለመቻሉን›› ገልጿል፡፡ በአሁኑ ወቅት በመንበረ ፕትርክናው ከሚታየው ክፍተት አኳያ ቤተ ክርስቲያን ያለመሪ ለብዙ ጊዜ እንድትቆይ ማድረግ÷ ‹‹መንፈሳዊና ማኅበራዊ ሥራዋ እንዲስተጓጎል፣ መልካም አስተዳደሯ እንዲዳከም፣ ዕድገቷም እንዲቀጨጭ የሚያደርግ በመኾኑ›› ለስድስተኛው ፓትርያሪክ ምርጫ የተጀመረው ዝግጅት እንዲቀጥል መወሰኑን ቅ/ሲኖዶሱ አስታውቋል፡፡

ቅ/ሲኖዶሱ አሜሪካ ድረስ አራት ጊዜ ልኡካኑን መላኩን፣ በሰላም ፈላጊነቱም ‹‹ኑ እና አብረን እንሥራ፣ አብረን እንምረጥ›› ከማለት ውጪ ሌላ የሚጠበቅበት ሓላፊነት ሊኖር እንደማይችል በመግለጫው አመልክቷል፡ ፡ የስድስተኛው ፓትርያሪክ ምርጫ ከመከናወኑ በፊት የሰላምና አንድነት ጉባኤው ተካሂዶ ከቀድሞው አራተኛ ፓትርያሪክ ጋር በሰሜን አሜሪካ ያሉት አባቶች ወደ አገራቸውና ቤተ ክርስቲያናቸው እንዲገቡ፣ የመምረጥና የመመረጥ መብታቸው እንደሚጠበቅላቸው፣ በዚህም ስምምነቱ እንዲፈጸምና ነገሩ እንዲቋጭ በሚገባ ቢያስረዳም የተጠበቀው ስምምነት ሳይፈጸም መቅረቱን በመግለጫው አትቷል፡፡ ይህንንም ቅ/ሲኖዶሱ እጅግ አሳዛኝ ኾኖ እንዳገኘው ገልጿል፡፡

በመሪ አለመኖር ምክንያት የቤተ ክርስቲያን ሥራ በእጅጉ እየተጎዳ እያየ ተጨማሪ ጊዜ መስጠት ቤተ ክርስቲያንን ለከፍተኛ ውድቀት የሚዳርግ፣ በእግዚአብሔርና በታሪክ ፊት ወቀሳን የሚያስከትል መኾኑን በመገንዘብ ቀደም ሲል አስመራጭ ኮሚቴ መሠየሙን ያስታወሰው የቅ/ሲኖዶሱ መግለጫ፣ የምርጫውም ሂደት ‹‹በእግዚአብሔር ቸርነትና በምእመናን ድጋፍ ሕገ ቤተ ክርስቲያንና ቀኖናው ተጠብቆ እንደሚከናወን ፍጹም ጥርጥር የለንም›› ብሏል፡ ፡ የፓትርያሪክ ምርጫ ጊዜው በቁርጥ ባይታወቅም እስከ ጥር መጨረሻ ድረስ ዕጩ እንዲያቀርብ የተሠየመው የአስመራጭ ኮሚቴው ሂደት እንደሚወስነው ከመግለጫው በኋላ ለጋዜጠኞች ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ከፍተኛ ሓላፊዎች ተገልጿል፡፡

ውጥረት ሰፍኖበት እንደነበር በተገለጸው የምልአተ ጉባኤው ስብሰባ÷ ‹‹የዕርቀ ሰላሙን ፍጻሜ በጊዜ ገደብ ጠብቀን በውጭ ከሚገኙት አባቶች ጋር ምርጫውን በአንድነት እናካሂድ›› የሚሉ ሊቃነ ጳጳሳት በውሳኔ መልክ የወጣውን የቅ/ሲኖዶሱን መግለጫ በከፍተኛ ደረጃ መሞገታቸው ተዘግቧል፡፡ ከእኒህም አንዱ የኾኑት የቅ/ሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል፣ የማክሰኞውን ስብሰባ ትተው መውጣቸው የተገለጸ ሲኾን፤ ዘግይቶ በደረሰን ዜና መሠረት ደግሞ ከዋና ጸሐፊነት ሓላፊነታቸው የመልቀቂያ ደብዳቤ ለዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪኩ ማቅረባቸው ተሰምቷል፡፡

ዋና ጸሐፊው በወቅታዊ አጀንዳ በተላለፈው ውሳኔ በአቋም ከመለየታቸው ባሻገር፤ ‹‹በጽ/ቤቱ ስም ሳላውቃቸው የሚወጡ ደብዳቤዎች አሉ›› የሚለው አቤቱታቸው በሓላፊነታቸው ላለመቀጠል እንደምክንያት እንደሚጠቅሱ የመንበረ ፓትርያሪኩ ምንጮች ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ ብፁዕ ዋና ጸሐፊው ሳላውቃቸው በጽ/ቤቱ ስም ይወጣሉ ካሏቸው ደብዳቤዎች መካከል ዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪኩ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴርን እገዛ ጠይቀውበታል የተባለው ደብዳቤ እንደሚገኘበት ተመልክቷል፡፡

በዚህ ደብዳቤ ዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪክ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል የጠቅላይ ቤተክህነቱ ከፍተኛ ሓላፊዎች ሥራቸውን እንዳይሠሩና ምርጫውን በአስቸኳይ እንዳያካሂዱ ዕንቅፋት እየፈጠሩባቸው በመኾኑ፣ መንግሥት እገዛ እንዲያደርግላቸው መጠየቃቸው ነው የተዘገበው፡፡ ዐቃቤ መንበሩ የመንግሥትን እገዛ በደብዳቤ መጠየቃቸውን ተከትሎ ቅድሚያ የዕርቀ ሰላሙ ጉዳይ እንዲቋጭና ወደ ምርጫው እንዲገባ በሚበዙት ተሳታፊዎች ተይዞ የነበረው አቋም እንዲዳከም አስተዋፅኦ ማድረጉን ነው ታዛቢዎች የሚናገሩት፡፡ ለጋዜጠኞች ጥያቄዎች ምላሽ ከሰጡት የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ከፍተኛ ሓላፊዎች አንዱ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ፣ ዐቃቤ መንበሩ ለመንግሥት የጻፉት ደብዳቤው እንዳለ አምነው ይዘቱ ግን ‹‹በአጠቃላይ ስለ አንዳንድ ሥራዎች ሂደት እንጂ ከዐቢይ ጉባኤው ጋር የሚገናኝ ጉዳይ የለውም›› ብለዋል፡፡

ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ በሦስት ዙር ሲካሄድ ስለቆየው የሰላምና አንድነት ጉባኤ ቀጣይነት የተጠየቁት ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ፣ ‹‹ከግማሽ መንገድ በላይ ተኪዷል፤ እንደ አቋም የኢትዮጵያው ሲኖዶስ መኾን መደረግ ያለበትን የሰላም አቋም አሟጦ ጨርሷል፤ ከዚህ በላይ የሚደረግ ነገር የለም›› ቢሉም ቀደም ሲል ከነበረው አደራዳሪ አካል ይልቅ÷ ግራ ቀኙን አይቶ የተለያዩ አማራጭ ሐሳቦችን ደፍሮ ለማቅረብ፣ ተጽዕኖ ለማሳደር የሚችል ብቃትና አቅም ያለው አካል ሲገኝ ቅ/ሲኖዶሱ እያጠና የመጨረሻዋ ሰላም እስክትረጋገጥ ድረስ ይቀጥልበታል የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በቅ/ ሲኖዶሱ መግለጫ ላይም እንደተመለከተው÷ በውጭ ያሉት አባቶች የተሰጠውን የሰላም ዕድል ተጠቅመው ወደ ሰላሙና አንድነቱ ለመምጣት ፈቃደኞች ኾነው እስከተገኙ ድረስ ኹኔታዎች ሲመቻቹ ቀደም ሲል የተጀመረውን የሰላምና ዕርቅ ሂደት እስከ መጨረሻው ለመቀጠል አሁንም ዝግጁ መኾኑን አረጋግጧል፡፡

ቅ/ሲኖዶሱ በወቅታዊ የቤተ ክርስቲያኒቱ ጉዳይ ላይ ያደረገው ውይይትና ያሳለፈው ውሳኔ÷ ከኅዳር 26 - 30 ቀን 2005 ዓ.ም በዳላስ ቴክሳስ ለሦስተኛ ጊዜ በተካሄደው ጉባኤ አበው ላይ የተሳተፉት ልኡካን ባቀረቡት አጠቃላይ ሪፖርት ላይ የተመሠረተ መኾኑ በቅ/ሲኖዶሱ መግለጫው ላይ ተመልክቷል፡፡ በዳላሱ ድርድር ላይ ለዕርቁና ሰላም ስምምነቱ አለመፈጸም እንደዋነኛ ምክንያት የተጠቀሰው÷ ‹‹የቀድሞው ዐራተኛ ፓትርያሪክ መንበራቸው ክፍት ስለሆነ ወደ መንበራቸው መመለስ አለባቸው፤ በሙሉ የፓትርያሪክነት ሥልጣንም ቤተ ክርስቲያንን መምራት አለባቸው፤ ይህ የማይደረግ ከኾነ ግን አንስማማም›› የሚለው በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ አባቶች አቋም ነው፡፡

ቅ/ሲኖዶሱ ይህን አስመልክቶ በመግለጫው በሰጠው ማብራሪያ÷ ከዛሬ ኻያ ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ ዐራተኛ ፓትርያሪክ የነበሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ በወቅቱ ባደረባቸው ሕመም ነሐሴ 18 ቀን 1983 ዓ.ም በጠሩት አስቸኳይ የቅ/ሲኖዶስ ጉባኤ ሥልጣናቸውን ለማስረከብ መጠየቃቸውን አስታውሷል፡፡ ይኹንና ቅ/ ሲኖዶስ የቀድሞው ፓትርያሪክ በሕክምናም በጠበልም እየተረዱ ሊድኑ እንደሚችሉና ሐላፊነታቸውን ይዘው እንዲቀጥሉ ፈቃዳቸው እንዲኾን ቢለምናቸውም ሐሳባቸውን ከማጽናት በቀር ተለዋጭ መልስ እንዳልሰጡት ገልጧል፡፡

በመኾኑም ጉዳዩ በጥልቀት ሲጠና ሰንብቶ ነሐሴ 28 ቀን 1983 ዓ.ም የቀድሞውን ዐራተኛ ፓትርያሪክ ጥያቄ ተቀብሎ ሥልጣኑን መረከቡን፣ ኾኖም ግን ፓትርያሪኩ ሓላፊነታቸውን ለመወጣት የሚችሉበት ዕድል እንዳለ የሚጠቁም ፍንጭ ለማግኘት ለዐሥር ወራት ያህል ቢጠብቅም ባለመስጠታቸው ለኑሯቸው የሚያስፈልገውን ሁሉ፣ ደመወዝም መኪናም ፈቅዶላቸው በገዳም በጠበል እየታገዙ፣ በሕክምናም እየተረዱ በጸሎት ተወስነው እንዲኖሩ መወሰኑን አውስቷል፡፡ ከዚህ በኋላ ቤተ ክርስቲያን ያለመሪ ለብዙ ጊዜ እንድትቆይ ማድረግ የሚያስከትለውን ጉዳት በመገንዘብ የአምስተኛው ፓትርያሪክ ምርጫ እንዲካሄድ ግንቦት አራት ቀን 1984 ዓ.ም መወሰኑን ጠቅሷል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ አራት ሊቃነ ጳጳሳት ከሀገር ውስጥና ከውጭ አህጉረ ስብከት ከቤተ ክርስቲያናቸው ተነጥለው ሲወጡ፣ ዐራተኛ ፓትርያሪክ የነበሩትም በሞያሌ በኩል ኬንያ ገብተው ለሰባት ዓመት ከቆዩ በኋላ፣ ሁሉም በሰሜን አሜሪካ ተሰብስበው በታሪክ ታይቶም ተሰምቶም የማይታወቅ ድርጊት በመፈጸም በስደት አገር ሲኖዶስ አቋቁመናል ማለታቸው ተገልጿል፡፡ ፓትርያሪክም ኾነ ሊቀ ጳጳስ ከአገር ውጭ ሲኖዶስ ማቋቋም ይቅርና ያለቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ አንድ የፋሲካ በዓል ከሀገሩና ከሀ/ስብከቱ ውጭ ማክበር በቀኖና ቤተ ክርስቲያን የተከለከለ በመኾኑ ስሕተቱን በመነጋገር ለማረም በታኅሣሥ ወር 1999 ዓ.ም ልኡክ ቢላክም አናነጋግርም ከማለት አልፎ፣ በዚያው ዓመት ወርኃ ጥር የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት በማከናወናቸው የቤተ ክርስቲያንን ቀኖና ለማስጠበቅ ሲባል ቅ/ሲኖዶስ ቃለ ውግዘት ማስተላለፉን፣ ስማቸውንና ሐዋርያዊ ሥልጣናቸውን ማንሣቱን ጠቅሷል፡፡

ከዚህ በኋላ ጉዳዩ በዕርቅና በሰላም ተቋጭቶ በውጭ ያሉት አባቶች ወደሀገራቸውና ወደ ቤተ ክርስቲያናቸው እንዲገቡ ለማግባባት ጥያቄ ያቀረቡ ወገኖችን ሐሳብ ተቀብሎ በሐምሌ 2002 ዓ.ም በሰሜን አሜሪካ ቨርጂኒያ በሦስተኛ ወገኖች የሐሳብ ልውውጥ ቢያደርግም ‹‹ከመሠረተ ጉዳዩ ጋር ተያያዥነት የሌለውና ያልተጠበቀ ቅድመ ኹኔታ›› በመቀመጡ ሰላምና አንድነቱ ሳይሳካ ቀርቷል ብሏል፡፡

ከዚህ በኋላ ቅ/ሲኖዶሱ ለሰላሙ መፋጠን ያጸደቀውን ‹‹ወሳኝ የኾነ የመጨረሻ የሰላም አቋም›› ሲዘረዘር÷ ዐራተኛው ፓትርያሪክ ወደ አገራቸው ተመልሰው፣ ደረጃቸውና ክብራቸው ተጠብቆ፣ የሚያስፈልጋቸው ሁሉ ተሟልቶላቸው፣ በመረጡት ቦታ በጸሎት ተወስነው እንዲኖሩ፣ ነባሮቹንም ኾነ በእነርሱ አንብሮተ እድ የተሾሙ አዲሶቹ አባቶች አስመልክቶም ቀኖናውን በቀኖና አሻሽሎ፣ ሐዋርያዊ ሥልጣናቸውን ሰጥቶ፣ ስማቸውን መልሶ፣ በሀገረ ስብከት መድቦ ለማሠራት ፈቃደኛ መኾኑን በየካቲት ወር 2004 ዓ.ም በአሪዞና ፊኒክስ በተካሄደው ጉባኤ ይፋ ማድረጉን አስረድቷል፡ ፡ ይኹንና አሁንም ከቤተ ክርስቲያን ጋር ተያያዥነት የሌላቸው ጉዳዮች በማንሣታቸውና የቀረበውንም ጥሪ ባለመቀበላቸው የተጠበቀው ሰላምና አንድነት ሊገኝ እንዳልቻለ አብራርቷል፡፡

የዐራተኛውን ፓትርያሪክ ስደት ከተለመደው የአባቶች ስደት ልዩ የሚያደርገው የቀድሞው ዐራተኛው ፓትርያሪክ መንበራቸውን ራሳቸው በመልቀቃቸውና በማስረከባቸው፣ ያለምንም ምክንያት ሀገራቸውንና ቤተ ክርስቲያናቸውን ጥለው ከአገር በመውጣታቸው፣ በስደት አገር ሲኖዶስ በማቋቋማቸው መኾኑን ቅ/ሲኖዶሱ በመግለጫው አትቷል፡፡

ቅ/ሲኖዶሱ የቀድሞውን ዐራተኛ ፓትርያሪክ በፓትርያሪክነት የሥልጣን ደረጃ የማይቀበልባቸውን ምክንያቶች ሲዘረዝርም፡- ‹‹ይህን የመሰለ ታላቅ መንፈሳዊ ሥልጣን ሲፈልጉ ተረከቡኝ፣ ሲፈልጉ መልሱኝ እየተባለ የሚከራከሩበት ባለመኾኑና ይህን ጥያቄ ማስተናገድ በቤተ ክርስቲያን ሥርዐተ አልበኝነት እንዲሰፍን መፍቀድ በመኾኑ፣ ቅ/ሲኖዶሱ ለምኗቸው አይኾንም ብለው ጥለው የሄዱ በመኾኑ፣ ከዚህም የታሪክ መዛግብት እንደሚመሰክሩትና የቅ/ሲኖዶስ አባላትም እንደሚመሰክሩት የቀድሞውን ዐራተኛ ፓትርያሪክ ከመንበረ ፓትርያሪኩ አስወጪም ወጪም ኾነው ድርጊቱን ያፋጠኑ በወቅቱ ሰብሳቢ የነበሩና ኋላም ከእነርሱ ጋር የነበሩት አባት እንጂ ሌላ ባለመኾኑ፣ አምስተኛው ፓትርያሪክ በሕገ ቤተ ክርስቲያን ተሹመው የተሠራው የኻያ ዓመታት ሥራ ደምስሶና ሠርዞ ወደኋላ በመመለስ ዐራተኛ ፓትርያሪክ ብሎ መቀበል ፍጹም የማይቻል በመኾኑ ነው›› ብሏል፡፡ ስለዚህም በመግለጫው በቀዳሚ ተራ ቁጥር በተገለጸው አቋሙ÷ ቅ/ሲኖዶሱ የቀድሞውን ዐራተኛ ፓትርያሪክ በፓትርያሪክነት የሥልጣን ደረጃ እንደማይቀበል በማያሻማ ኹኔታ በድጋሚ መወሰኑን አስታውቋል፡፡

የአገር ቤቱን ቅ/ሲኖዶስ መጠናቀቅ ተከትሎ በሰሜን አሜሪካ በሚገኙት የቀድሞው ዐራተኛ ፓትርያሪክና ሌሎች ሊቃነ ጳጳሳት በስደት የተቋቋመው ሲኖዶስ ተሰብስቦ በመምከር ላይ መኾኑ ታውቋል፡፡ በተለይም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን ‹‹በፓትርያሪክነት ማዕረግ ላለመቀበል በማያሻማ ኹኔታ በድጋሚ ወስኛለኹ›› ባለው በኢትዮጵያው ቅ/ሲኖዶስ ውሳኔዎች በእጅጉ ማዘኑንም ገልጧል፡፡ የስብሰባው ተሳታፊ በኾኑት አንድ ሊቀ ጳጳስም ‹‹በሰሜን አሜሪካ ነጻና ገለልተኛ የኾነ ሲኖዶስ ይቋቋማል›› መባሉም ተዘግቧል፡፡

የሀገር ቤቱን ቅ/ሲኖዶስ ውሳኔዎች የሚተቹ ወገኖች፣ የቀድሞው ዐራተኛ ፓትርያሪክ በሕመም ምክንያት ሥልጣናቸውን እንደሚለቁ ቢያሳውቁም በብዙ አባቶች ምክር ወደ መንበራቸው ለመመለስ ወስነው እንደነበር፣ ኾኖም በወቅቱ ሰብሳቢ የነበሩት አባት ፈጥነው በሚዲያ እንዲሰጥ ባደረጉት መግለጫ ነገሩ መሰናከሉን በመጥቀስ÷ ‹‹ቅ/ሲኖዶስ በወቅቱ ለምኗቸው አይኾንም ብለው ጥለውት ሄደዋል›› የሚለውን የመግለጫውን ክፍል ይቃወማሉ፡፡

መግለጫው ሁሉም የቅ/ሲኖዶስ አባላት የሰጡበት ትችት ተካቶና ይኹንታቸውን አግኝቶ ለመውጣቱ ጥርጣሬ ያላቸው አስተያየት ሰጭዎች÷ ከፓትርያሪክ ምርጫው በፊት የዕርቀ ሰላሙን ሂደት ለማሳካት ተስፋው ጨርሶ ያልጨለመ በመኾኑ ሁሉም ወገኖች በየፊናቸው በተለያዩ መድረኮች የሚያደርጉትን ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡ በእነርሱ አስተያየት በሁለቱም ‹ሲኖዶሶች› ውሳኔና መግለጫ የተነሣ የሰላሙ ሂደት ላይ ተስፋ ከተቆረጠ ‹‹የቤተ ክርስቲያን አንድነት ዳግም በማይመለስበት ኹናቴ በከፋ የመከፋፈል አደጋ ውስጥ ይወድቃል፡፡››

Read 5650 times Last modified on Sunday, 20 January 2013 13:21
Administrator

Latest from Administrator