Sunday, 20 January 2013 12:43

በወጉ ያላሳደገውን ልጅ፣ የእከሌን ልጅ ይመስላል፤ ይላል

Written by 
Rate this item
(6 votes)

አንድ የአገራችን ገጣሚ ስለ አይጥ፣ ስለድመት፣ ስለውሻና ስለሰው የፃፈው ግጥም ጭብጡ በስድ ንባብ ቢታሰብ የሚከተለውን ተረት ይመስላል፡፡

አንዲት አይጥ ከዕለታት አንድ ቀን “ድመት” የሚል ግጥም ትጽፋለች አሉ፡፡ የግጥሙ ይዘት “ድመት ባይርባት ኖሮ እኔን አሳዳ አትበላኝም ነበር” የሚል ነው፡፡ አይጥ የፃፈችውን ግጥም ድመት ታገኛለች፡፡ ድመትም “አይጥ” የሚል ግጥም ትጽፋለች - እንደምላሽ መሆኑ ነው፡፡

አይጥና ድመት የፃፉትን ግጥሞች ሰው ያገኛል፡፡

ሰውየው፤ የቤቱ ባለቤት መሆኑ ነው፤ እጅግ አድርጐ ይናደዳል፡፡ ወረቀት ጽፈው በማየቱ እንጂ ስለምን እንደፃፉ አላነበበውም፡፡ ብቻ በንዴት

“አሃ! አይጥና ድመት በእኔ ላይ ግጥም መፃፍ ከጀመሩ፤ ተስማምተው ተነሱብኝ ማለት ነው። አድማ ነው! በጭለማ ወረቀት መበተን የመጥፎ ጊዜ ምልክት ነው፡፡ ትውልዱ ከፋ ማለት ነው። ስለዚህ እርምጃ መውሰድ ይገባኛል!” ሲል አሰበ፡፡ በመጨረሻም እንዲህ የሚል ውሳኔ አሳለፈ፡፡

“በቃ ሁለቱም ይቀጡ

ለዚያችም ወጥመድ ዘርጉ

ለዚችም ገመድ አምጡ!”

በትዕዛዙ መሠረት ወጥመድ ተዘረጋና አይጢት ተያዘች፡፡ ድመትም በገመድ ተጠፍራ ታሠረች። አይጥ ልትሞት ወደማጣጣሩ ደረሰች፡፡ ድመት በታሰረችበት እህል ውሃ አጥታ በረሃብ ልትሞት ተቃረበች፡፡

አይጥ ድመትን፤ “ለባለቤቱ ከምታሳብቂ፣ ልብ ካለሽ መልስ አትጽፊልኝም ነበር?” አለቻት፤ ወጥመድ ውስጥ ሆና!

ድመትም፤ ብስጭትጭት ብላ፤

“ቀጣፊ ነሽ! የፃፍኩልሺን መልስ ለጠላት አሳልፈሽ ከመስጠት አታነቢውም ነበር? በግልጽ አቋሜን ትረጂ ነበር! ከእንግዲህማ ስፈታ ቁም - ስቅልሽን ባላሳይሽ ዕውነት ድመት አደለሁም!” በማለት ትዝታለች!

አይጥ ድመት አሳብቃ በወጥመድ አስያዘችኝ ስትል፣ ድመት ደግሞ ለሷ የፃፍኩላትን ምላሽ ለጠላቴ (ለቤቱ ባለቤት) ሰጠችብኝ ትላለች፡፡ የቤቱ ባለቤት ደግሞ ስለምን እንደተፃፉም ሳያነብ ፍርድ ይሰጣል፡፡

ይህን የሆነውን ሁሉ ውሻ ቁጭ ብሎ ይታዘባል፡፡

“ወይ ግሩም! እነዚህ ፍጡሮች ሲሞቱም አይማማሩም!

ጠላት እንደሆኑ ኖረው ጠላት እንደሆኑ ሊሞቱ ነው፡፡ ጌታችንም፤

ጨካኝ ፍርደ -ገምድል ነው

በቀሉን ብቻ የሚያምን

በቋፍ በሥጋት የሚኖር

አንዱን ጥፋት ለማጥፋት፣ ሌላ ጥፋት የሚሠራ

ቁጥቋጦዎችን ለመንቀል፣ የሚጣላ ከተራራ…

ማንም ከማንም ላይሻል፣ ማንም ከማንም ላይበልጥ

አገር እንደበሬ ጠልፎ፣ ጥሎ ለመብላት መሯሯጥ

መንተፍተፍ…መተላለፍ፣ መጠላለፍ ሁሉን ማርገፍ!

ሁሉም መርገፍ!!” አለ፡፡

* * *

ከመጠላለፍ ይሰውረን፡፡ አደቡን ይስጠን፡፡ በተጠራጠርነው ሁሉ ፍርድ ከመስጠት ያድነን፡፡

እየደጋገምን የምናጠፋው ጥፋት እኛን ራሳችንን ይዞ እንዳይጠፋ መጠንቀቅ ያባት ነው! የምንገባው ቃል መፈፀሙን የሚያረጋግጥልን አንድም ታሪካችን፣ ሁለትም ለራስ መታመናችን ነው! በተግባር የምንሠራው በቃል የምናወራውን ካልመሰለ ዕቅዳችን፣ ስትራቴጂያችን ሁሉ፤ ውሃ የበላው ቤት እንደሚሆን አንርሳ! በታሪክ ያየነው ስህተት እንዳይደገም መጣጣር አዲስ ታሪክ መሥራት ነው!

“ታሪክ ራሱን ይደግማል” ፣ ይላል ታሪከኛው ሁሉ

እኔን ያሳሰበኝ ግና፡- ታሪክ በደገመ ቁጥር፤ ዋጋው እጅግ መቀጠሉ፤”ይለናል ሜይ ግሪንፊልድ፡፡ የሚያስከፍለን ዋጋ ብዙ ነው እንደ ማለት ነው፡፡

በርናርድ ሾው የተባለው ፀሐፊ “የአንዱ ሥጋ ለአንዱ መርዝ ነው፡፡ የአንዱ ዕድሜ ናፍቆት፤ የሌላው ዕድሜ መከፊያና ማዘኛ ነው! (one man’s meat is one man’s poison, one age’s longing another age’s loathing) የሚለው ይሄን ብጤውን ነው፡፡ የሚያስከፋን እየቀነሰ የሚናፍቀን የሚጨምርበትን ሁኔታ ለመፍጠር መደማመጥ፤ መግባባትና መተሳሰብ ያሻናል፡፡

ከፊል በእጅ፣ ከፊል በዲጂታል የሚከፈት ሠረገላ ቁልፍ (both manual and digital at the same time) ይዘን ለውጥ ማምጣት ከባድ ነው - ዘይትና ውሃ እንዲሉ፡፡ “ባለራዕይ-ለማኝ ዐባይ ሲገደብ የምሰጥህ ሁለት ብር አበድረኝ ይላል” እያሉ የአራዳ ልጆች እንደሚሳለቁት እንዳይሆን፤ በማንኛውም ረገድ ራስን መቻል እንደሚኖርብን ልብ እንበል፡፡ በምግብ ራሳችንን ችለን ረሀብተኛ ዲሞክራሲ ይዘን እንጓዝ ብንል የማያዋጣንን ያህል፤ በባዶ ሆድም ዲሞክራሲን አንግቦ መጓዝ ወንዝ አያሻግረንም፡፡ ጥቂት የናጠጡ ሀብታሞችና አያሌ የኔ-ብጤዎች ያሏት ሀገርም ሆነ ሰላሟን አጥታ ብዙ ሀብታሞችን ያፈራች ሀገር እንድትኖረን አይደለም ደፋ-ቀና የምንለው፡፡ እንደጥንቱ መፈክር “ጉዟችን ረጅም ትግላችን መራራ” ነው ማለትም አያዛልቀንም፡፡ ሁሌም ረጅም፣ ሁሌም መራራ መሆን የለበትምና! “ጊዜ ነው ይላል ሻጥረኛ፤ በጊዜ አሳቦ ሊተኛ!” ይለናል ፀጋዬ ገ/መድህን፡፡ “ሁሉ ነገር ሂደት ነው” በሚል መጠቅለያ ያለ ለውጥ፣ ያለ ዋስትና መራመድ አይቻልም፡፡ The change should be incremental እንደሚሉት ነው ፈረንጆቹ። የለውጥ አንቀሳቃሹ በአብዛኛው ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ነው፡፡ በዕውቀት የተገነባ፣ ለውጥ የገባው፣ ዛሬ ላይ የተደረሰው ብዙ ለውጥና መስዋዕትነት ታይቶ መሆኑን የተረዳ ወጣት እንጂ “Fast” በሚል ታርጋ የታሸገ የቢዝነስ ተሯሯጭ ለብ-ለብ ትውልድ ብቻ እንዳይሆን አገርና ነገር የገባው ወጣት መገንባት ያስፈልጋል፡፡ ያልፈጠርነውን፣ ያላስተማርነውን፣ በአግባቡ ያላነፅነውን ልጅ የሌለ ቅፅል ሰጥተን ብናሞካሸው ረብነት የለውም፡፡ በአናቱ ቅቤ ጣል ያለበት ሹሮ ዓይነት ካፒታሊዝም ኑሮአችን ቅቤ በቅቤ ነው እንደማያሰኝ ሁሉ፤ በእንዲህ ያለ ሥርዓት ውስጥ የሚያድግም ልጅ በአርቲፊሻል የተኳኳለ ከመሆን በቀር ኦርጅናሌ እንደማይሆን እናስተውል፡፡ “በወጉ ያላሳደገውን ልጅ የእከሌን ልጅ ይመስላል፤ ይላል” ማለት ይሄው ነው፡፡

Read 5450 times