Saturday, 26 January 2013 14:59

የፖለቲካ “ሰውነት ቢሻው” ቢገኝማ ሽረት ነበር!!

Written by 
Rate this item
(4 votes)

አንዳንዴ ምን እንደማስብ ታውቃላችሁ? የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ፍፁም ነፃ መሆኑን የሚያረጋግጥ አዲስ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ግኝት የሚፈጥርልን ብናገኝ (ቻይናን ምን ይሳናታል?) በገንዘብ ባንችል እንኳን በ”ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ” ስም እንማጠናቸው ነበር… (ቻይና ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ስታውቅ አይደል?)

ወዳጆቼ፤ የጥምቀት በዓል እንዴት አለፈ እባካችሁ? በሸጋ ያለፈ ይመስለኛል (እኔ ከናንተ ባላውቅም) ከሁሉም ያስደመመኝ ግን ምን መሰላችሁ? በጥምቀት ይወረወር የነበረው ሎሚ ተረት ሆኖ (እንደ ድህነት? ማለት ነው) ዘንድሮ በፕሪም ተተክቷል የሚባል ነገር ሰምቻለሁ፡፡ “ወጭ ለምኔ” ያሉ የዘመኑ ወጣቶች ደግሞ (በሬ ለምኔ እንደሚባለው) የሞባይል ነምበራቸውን ቆነጃጅቱ ደረት ላይ ሲወረውሩ እንደዋሉም የአውዳመት የወሬ ምንጮቼ ሹክ ብለውኛል፡፡ በደቡብ አፍሪካው የባለፈው ሰኞ የብሄራዊ ቡድናችን ግጥምያ እለት የተባለውን ሰምታችሁልኛል? “ውበት ሲለካ የኢትዮጵያ ሴቶች ናቸው ለካ!” የሚለውን ማለቴ ነው፡፡ (ለነገሩ ሲያንሳቸው እኮ ነው!!) ነገርዬውን ዝም ብዬ ሳስበው ግን የኢትዮጵያን እንስቶች ውበት ድንገት ያጐሉት ያለፈው የአፍሪካ ዋንጫ ሻምፒዮን ከሆነችው ዛምቢያ ጋር ገጥመው (ያውም በጐደሎ ተጫዋቾች) ድንቅ የኳስ ጥበብ ያሳዩት የብሄራዊ ቡድናችን አባላት ይመስሉኛል - (ያዳኑን እነ አዳነን ማለቴ ነው!) የሴቶቻችን ውበትማ አዲስ ክስተት አይደለማ!! እኔ የምለው ግን… በኢቴቪ ቀርቦ አስተያየቱን የሰጠ አንድ

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ያበደ አድናቂ፤ ቡድናችንን ከእነሜሲ ጋር ሁሉ ሲያነፃፅር እንደ ነበር ሰምታችኋል? (ቢጋነንም ከጋለ ስሜት የመነጨ ነው ብለን እንለፈው) በነገራችሁ ላይ… ይሄ ህዳሴያችን ብዙ ታሪኮቻችንን እያደሰልን አይመስላችሁም! (በእድል እኮ አይደለም በትጋት እንጂ!) ከህዳሴው ጋር ያልታደሰልን ዋናው የህይወታችን ክፍል ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? ያልታደለው ፖለቲካችን ብቻ!! እንኳንስ ሊታደስ ቀርቶ ጭርሱኑ ወደ ኋላ… ወደ ጥንቱ የጨለማ ዘመን (dark age) እየጐተተን፣ የዓለም መሳቂያ መሳለቂያ ሊያደርገን ዳር ዳር እያለ እኮ ነው! ፖለቲከኞችን በማሰር፣ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ጋዜጠኞች ለስደት በመዳረግና ወህኒ ቤት በመከርቸም፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ነፃ እንቅስቃሴ በማፈን፣ በሙስናና በመልካም አስተዳደር እጦት፣ በሰብአዊ መብት ጥሰት፣ ወዘተ… ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ስሟ እየተነሳ መሆኑ ፀሃይ የሞቀው አደባባይ ያወቀው እውነት ነው፡፡ በእርግጥ እንዲህ ያለውን ውንጀላ ባልወለደ አንጀታቸው የሚሰነዝሩት የኢትዮጵያ በጐ ነገር የማይዋጥላቸው እንደ ሂዩማንስ ራይት ዎች ያሉ ጨለምተኛ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እንደሆኑ ሁሌም ገዢው ፓርቲያችን ይነግረናል (እንዳንሳሳት ብሎ እኮ ነው!) ችግሩ ግን ምን መሰላችሁ? እዚሁ ከምርጫ ቦርድ ህጋዊ ሰርተፊኬት ተሰጥቷቸው የሚንቀሳቀሱትም ህጋዊ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የተሟጋቹን ውንጀላ አንድም ሳያስቀሩ ይቀበሉታል፡፡

(ታዲያ ምን ተሻለ?) ምን መቀበል ብቻ… “መች ተነካና… ይታያል ገና!” ባይ ናቸው፡፡ (የገዢውን ፓርቲ ጉድ ማለታቸው እኮ ነው!) እኔ የምለው ግን… የአገር ሽማግሌዎች ቡድን መሪ የሆኑት ባለውለታችን ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሃቅ ፓርቲዎችን የማስታረቅ በጐ ሚናቸውን እንዴት ዘነጉት? ለነገሩ በእሳቸውም አይፈረድም እኮ! (የአውሮፕላን ወጪ ገደላቸዋ!) እንዴ… በ97 የፖለቲካ ቀውስ ጊዜ ታስረው የነበሩትን የቅንጅት አመራሮች ከመንግስት ጋር ለማስማማት ከአሜሪካ ኢትዮጵያ የነበረውን ጉዞ የውሃ መንገድ አድርገውት ነበር እኮ! ያውም በገዛ ገንዘባቸው እየተመላለሱ፡፡ ግን ምናለ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚመላለሱበትን የአየር ትኬት ስፖንሰር ቢያደርጋቸው? (የአገር ጉዳይ አይደለም እንዴ?!) ለማንኛውም ግን ፕሮፌሰሩ አንዴ እንደምንም ወደ አገራቸው ጐራ ብለው ኢህአዴግንና ተቃዋሚዎቹን “አንተም ተው! አንተም ተው!” ቢሏቸው ሳይሻል አይቀርም ባይ ነኝ፡፡

(እረስቼው! ምርጫ ቦርድም ለካ ሌላው የፓርቲዎች የኩርፊያ ሰበብ ነው) እሱ እንኳን እርቅ ሳይሆን “ማጥራት” ነው የሚሻለው፡፡ አንዳንዴ ምን እንደማስብ ታውቃላችሁ? የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ፍፁም ነፃ መሆኑን የሚያረጋግጥ አዲስ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ግኝት የሚፈጥርልን ብናገኝ (ቻይናን ምን ይሳናታል?) በገንዘብ ባንችል እንኳን በ”ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ” ስም እንማጠናቸው ነበር… (ቻይና ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ስታውቅ አይደል?) እንዴ… ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ ከ15 አመት በኋላ በጐ እንቅስቃሴ የጀመረው እግር ኳሳችን እንኳ የእነቬንገርን ቀልብ ስቧል እየተባለ እኮ ነው፡፡ ፖለቲካችን ግን ይኸው 21 አመት ወደኋላ መምዘግዘግ ይዞላችኋል - ያውም ህዳሴያችንን ይዞ (ወይ ነዶ አሉ!) አያችሁ… ይሄ ክፉ ፖለቲካችን የጀመርኩትን የጥምቀት ወግ ሳልጨርስ እንዴት ጐትቶ ውስጡ እንደዶለኝ! (ፖለቲካችን እርግማንና ወቀሳ ምሱ ነው አሉ!) እኔ የምለው… በዘንድሮ የጥምቀት በዓል መዲናዋ እንዴት እንደፀዳችና እንደተዋበች በደንብ አስተውላችኋል? እንዴ… ከተማዋ 125ኛ ዓመት ልደቷን አንድ አመት ሙሉ ስታከብርም እኮ እንዲህ አላማረባትም! (አክብሮ መና ይሏል ይሄ ነው!) እውነቴን ነው የምላችሁ… የመዲናዋ ወጣት በዓሉን ያከበረው “ለጥምቀት ያልሆነ ከተማ…” በሚል አዲስ ምሳሌያዊ አባባል ይመስላል፡፡

(ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ እንዲሉ!) ቆይ ግን ያልፀዳና ያልተዋበ የመዲናዋ ስፍራ አለ እንዴ? (ማዘጋጃ ቤት ሲያሾፍ እንደኖረ የገባን አሁን ነው!) ለወትሮው የሽንትና የቆሻሻ ክምር የነበሩ ስፍራዎች ሁሉ ፀድተውና በተለያዩ ቀለማት ተኳኩለው “ሸገር” ተውሰን ያመጣናት ከተማ ልትመስለን ምን ቀራት? መርካቶ ሰባተኛ አካባቢ እንዴት በባንዲራና በፊኛ አሸበርቆ እንደነበር መስተዳድሩ አይቶት ይሆን? (ማን ነበር “ይደገም ቅዳሜ” ያለው…) ከምሬ ነው… መቼም አይቶት ከሆነ የመዲናዋ ልደት “በህዝብ ጥያቄ በድጋሚ ይከበራል” ማለቱ አይቀርም! እኔ ግን የልደቱን በድጋሚ መከበር ምንም ቢሆን እንደማልደግፍ ከወዲሁ አቋሜን ልገልፅ እወዳለሁ፡፡ እንደ 34ቱ ፓርቲዎችም ፒቲሽን ማሰባሰብ ከጀመርኩ አንድ ሁለት ቀናት አልፎኛል፡፡ አያችሁ… ባለፈው ተመክሮ እንደተገነዘብነው መስተዳድሩ የፓርቲና የፌሽታ ነገር አይሆንለትም፡፡ (ፍንዳታ ቢጤ ነው!) የመዲናዋን 125ኛ አመት ከአንድ አመት በላይ እኮ ነው ያከበረው፡፡ (ለመሆኑ ጊነስ ላይ ተመዘገበለት ይሆን?) እናላችሁ… ራሴ ያነሳሁትን የይደገም ጥያቄ ራሴ መቃወሜን እወቁልኝ፡፡ አንድ ጥያቄ ግን አለኝ፡፡ መስተዳድሩ የመዲናዋን ልደት ከአንድ አመት በላይ ሲያከብር (ራሱ ነው ያለን!) ምን ማስታወሻ የሚሆን ነገር ለከተማዋ ሰራላት? (ከፕሮፓጋንዳው ውጭ ማለቴ ነው!) ይኸውላችሁ… እኔ ከጥምቀቱ የወጣቶች ቡድን ምን ቁምነገር ቀሰምኩ መሰላችሁ? የመዲናዋ ወጣት ሲፈልግና ልቡ ያመነበት ጉዳይ ሲሆን እንደንብ መንጋ ነው - የያዘውን ስራ ዶግ አመድ ያደርገዋል፡፡ አድምቶ ይሰራዋል! (በኢህአዴግ ቋንቋ!) ይታያችሁ… የፅዳት ሠራዊት የለ! የህዝብ ንቅናቄ የለ! 1ለ5 አደረጃጀትማ ጭርሱኑ ትዝ ያለውም የለ!! አያችሁልኝ… ወጣት ባመነበት ጉዳይ ላይ እንዲህ አጀብ ያሰኛል - ያውም ያለ አንዳች የካድሬ ፕሮፓጋንዳና አጀብ!!

እኔማ ምን አሰብኩ መሰላችሁ? ጥምቀት ለምን ሁለቴ አይከበርም አልኩኝ (ግን ለራሴ ነው) (ከተማዋ እኮ አበባ መሰለች!) ጥምቀት እንዲህ ከሆነ ግን ለምንስ የፖለቲካ ጥምቀት፤ የዲሞክራሲ ጥምቀት፣ የልማት ጥምቀት፣ የመልካም አስተዳደር ጥምቀት፣ የጥበብ ጥምቀት፣ የፕሬስ ነፃነት ጥምቀት፣ የመድብለ ፓርቲ ስርአት ጥምቀት፣ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ጥምቀት ወዘተ… ወዘተ… አያሌ የህዳሴ ጥምቀቶችን አይኖሩንም ስልም ተመኘሁ - ሁሉም በአንድ መንፈስ ከልቡ የሚያከብረው፡፡ ባይገርማችሁ… በፕሮፓጋንዳ ያልተካበደ ህዳሴ እንዴት እንዳማረኝ አልነግራችሁም (አምሮት መብቴ መሰለኝ!) ውድ አንባቢያን፡- ፕሮፓጋንዳ ያልበዛበት ፖለቲካ የት እንደሚገኝ የምታውቁ ከሆነ ብትጠቁሙኝ ወሮታውን እከፍላለሁ፡፡ እኔ የምለው ግን… እኔ ብቻ ነኝ ወይስ እናንተም ናችሁ የፖለቲካ ህዳሴ የናፈቃችሁ? ለነገሩ ባይናፍቃችሁም አይፈረድባችሁም! (ተስፋ ቆርጣችሁ እኮ ነው!) እንዴ ፖለቲካችን “ከርሞ ጥጃ”፣ “ታጥቦ ጭቃ” ሲሆንባችሁስ? እውነቱን ልንገራችሁ አይደል… በጥንቱ አካሄድማ የፖለቲካ ህዳሴን መመኘት ባዶ ህልም ከመሆን ፈፅሞ አያልፍም፡፡ ለውጥ የምንሻ ከሆነ በብሄራዊ የእግር ኳስ ቡድናችን ላይ የምናየውና የምንሰማው አይነት አዲስ አቅጣጫና አካሄድ ልንከተል ግድ ይለናል፡፡በእርግጥ በአንድ ጀንበር ስር ነቀል ለውጥ መጠበቅ ሲበዛ የዋህነት ነው፡፡ እንኳንስ በጦቢያ ፖለቲካ ቀርቶ በየትም አገር ቢሆን ሁሉም ነገር ቀስ በቀስ እያደገ ነው የሚመጣው፡፡

የአፍሪካ ተቃዋሚዎች ስልጣንም ሆነ ዲሞክራሲ ዛሬውኑ ካልተንበሸበሽን ብለው የሙጥኝ ሲሉባቸው ፈረንጆቹ ምን እንደሚሉ ታውቃላችሁ? “ዲሞክራሲ ሂደት ነው!” ይሉና ይገላገሏቸዋል፡፡ እንዴ ምን ያድርጉ ታዲያ? ለነገሩ የእኛዎቹንም እኮ እናውቃቸዋለን… ምርጫን የሞት ሽረት ጉዳይ ያደርጉት የለም እንዴ! ለዚህ እኮ ነው የሥነልቦና ትምህርት የሚያስፈልጋቸው፡፡ ከምሬ ነው… ፖለቲከኞቻችን የAttitude ለውጥ ካላመጡ ፖለቲካው መቼም አይለወጥም! እኔማ የስነልቦና ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ አሰልጣኝም (coach ወይም mentor ነገር) ይፈልጋሉ ባይ ነኝ! (ኢህአዴግንም ይጨምራል!) ፖለቲካ እኮ ብስለትም ብልህነትም ይፈልጋል፡፡ አጉል ብልጣብልጥነት ብቻውን የትም አላደረሰማ!! (ካላመናችሁኝ ኢህአዴግን ተመልከቱት!) ከችኩሉ ጥላቻ ተኮር ፖለቲካችን የምንላቀቀውም በጥሩ አሰልጣኝ ድጋፍ ይመስለኛል (የፖለቲካ ሰውነት ቢሻው ቢገኝማ ሽረት ነበር!) የሚገርማችሁ ግን በፖለቲካው ውስጥ ፀጉራቸው እስኪሸብት ኖረውበትም ዘንድሮም ቅንጣት ታህል ያልተለወጡ አያሌ ፖለቲከኞች በጦቢያ ምድር ሞልተው መትረፋቸው ነው፡፡ ልብ አድርጉ! እኔ ፈፅሞ የአገሬን ፖለቲከኞች የማንኳሰስ ድብቅ አጀንዳ የለኝም፡፡ የማንም ተላላኪም አይደለሁም! (ለምሳሌ የሻዕቢያ!) ራሳቸው ፖለቲከኞቻችን እኮ ራሳቸውን ለማንኳሰስ ማንንም አያክላቸውም!! (እዳ እኮ ነው የገባነው!) ባለፈው ሰሞን የኢንጂነር ሃይሉ ሻውል ፓርቲ የቀድሞ አመራሮች የቆየ ውዝግባቸወን እንደ አዲስ ሊጀምሩ መሆኑን ሰምቼ እንዴት እንደተቃጠልኩ አልነግራችሁም፡፡

እስቲ ይታያችሁ… ከኢህአዴግ ጋር የማይቀርላቸው “ልፍያ” ሳያንሳቸው እርስ በእርስ ፍልምያ መግጠማቸው ምን የሚሉት እዳ ነው (ወይስ የወዳጅነት ግጥምያ መሆኑ ነው!) እንዲህ ያሉት እኮ ፖለቲካም፣ ፓርቲም ወደሚለው ጉዳይ ከመግባታቸው በፊት ለራሳቸው ክብር መስጠትን የግድ መማር አለባቸው (እድሜማ አላስተማራቸውም!) ፈረንጆቹ postive attitude, self esteem ምናምን የሚለውን በደንብ በውስጣቸው ካሰረፁ በኋላ በማንኛውም ፈተናና ወከባ ተከበውም ቢሆን ፅናትና ብርታት ካላቸው ስኬት እንደሚቀዳጁም መማር፣ መሰልጠን፣ መለማመድ ያስፈልጋቸዋል፡፡ የምርጫ ሰሞን ወከባን ለማስቀረት ብልሃቱ ዝግጅት ብቻ ነው! ኢህአዴግ ከችግሩ (ኃጢያቱ) ነፃ ነው እያልኩ ግን እንዳይመስላችሁ፡፡ የችግሩ እናት ማን ሆነና! በነገራችሁ ላይ ለኢህአዴግ የሚሰጠው ስልጠና ማተኮር ያለበት… ጦቢያን ለማሳደግ፣ ለማበልፀግ፣ ከድህነት ለማውጣት፣ ዲሞክራሲን ለማስፈን ወዘተ ከላይ የተቀባሁት እኔና እኔ ብቻ ነኝ የሚለው ክፉኛ የተጣባው አመለካከቱ ላይ ነው፡፡ “ፀሃዩን ንጉስ” በመቃወም ወደ ትግል የገባ ፓርቲ እንዴት ያንኑ የተቃወመውን አመለካከት ያቀነቅናል? (ታሪክ ራሱን ይደግማል አሉ!) ይሄ ሁሉ ስጋት ከምን የመጣ እንደሆነ እንድታውቁልኝ እሻለሁ! አያችሁ… እስከዛሬ ኦክስፎርድ ዲክሽነሪ Famine የሚለውን ቃል Food Shortage, scarcity, starvation ወዘተ በማለት ከፈታ በኋላ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ምሳሌ የሚጠቅሰው ጦቢያን እንደነበር እናውቃለን አይደል! አሁን ደግሞ ሳናስበው “ኋላ ቀር ፖለቲካ” ለሚለውም ቃል ዳግም አገራችን በዲክሽነሪው ላይ እንዳትጠቀስና ዳግም ሼም በሼም እንዳንሆን ክፉኛ ሰግቻለሁ፡፡

እናላችሁ… አገሬን እወዳለሁ የሚል ዜጋ ሁሉ ጦቢያን ከኋላቀር ፖለቲካ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማውጣት ከፍተኛ እርብርቦሽ ያደርግ ዘንድ ጥሪ ቀርቦለታል፡፡ እኔ የምለው ግን… ሰሞኑን በድራማ መልክ በኢቴቪ የሚተላለፈውን ማስታወቂያ አይታችሁልኛል - በሁለት ጫማ የሚገዙ እንስቶች የተሰራውን ማለቴ ነው፡፡ በስተመጨረሻ ላይ አንደኛዋ አዲስ የገዛችው ጫማ ተረከዟን እንደላጣትና እግሯን እንዳቃጠላት ለጓደኛዋ በምሬት ስትነግራት “በደንብ ሳትመርጪ ለምን ገዛሽ?” ትላታለች (ዋጋሽን አገኘሽ በሚል ስሜት!) ለካስ ነገርዬው ለሚያዝያው የአዲስ አበባና አካባቢ ምርጫ የተሰራ ማስታወቂያ ነው፡፡ እኔ እኮ የቻይና ጫማ ገዝታ የተቃጠለች ነበር የመሰለኝ፡፡ (ቀላል ተሸወድኩ!) ለነገሩ የማይሆን ፓርቲ መምረጥ ከቻይና ጫማም የበለጠ ሊያቃጥል ይችላል፡፡ (ፈጣሪ ይጠብቀን እንጂ!) በመጨረሻ በምርጫው ለሚሳተፉ ፓርቲዎች (ከ29ኙ ውጭ) ሁሉ የሚመች ነጠላ ዜማ እንዳገኘሁላቸው ሳበስራቸው ኩራት ይሰማኛል (ቃል በቃል መቅዳት ያኮራል ተብሎ የለ!) እንዲህ የሚል ነው የዜማው ግጥም፡- በቃ በቃ አልፈልግም ሌላ ላይመች ላይደላ… (ከጫማው ማስታወቂያም ጋር ይሄዳል አይደል? በምርጫው የምትሳተፉ ፓርቲዎች ይመቻችሁ!!) ,

Read 5007 times