Print this page
Saturday, 26 January 2013 17:17

የእስራኤል “ኩሽሞች” (ባሪያዎች)

Written by 
Rate this item
(3 votes)

አሳ ሁልጊዜ በመረብ ብቻ አይጠመድም፡፡ የመኖሪያ ቤት ግዢ የብድር ፕሮግራሙ እንዲህ ያለ አሳዛኝ ውጤት በማስመዝገብ ሲከሸፍ፣ ብዙዎቹ ቤተእስራኤሎችና እነሱን ለመርዳት ተብለው የተቋቋሙ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የእስራኤል መንግስት ቤተእስራእሎችን ለማዋሀድ በሚል የቀረፃቸውን ሌሎች ፕሮግራሞች የአፈፃፀማቸውን ጉዳይ መለስ ብሎ ለመገምገም አረፍ የሚልበት ታዛና የጥሞና ጊዜ ያገኛል ብለው ተስፋ አድርገው ነበር፡፡

በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ የድሩዝ ማህበረሠብ አባላት ተለይተው ከሚታወቁበት ነገሮች አንዱ ለሚኖሩበት ሀገር መንግስት ያላቸው የማያወላውል ታማኝነት ነው፡፡ በድፍን የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ውስጥ በሀገሬ የሚኖሩ ድሩዞች የተቃውሞ ድምፃቸውን አሠሙብኝ ወይም ደግሞ በአመጽ ተነሱብኝ ብሎ ስሞታውን ያሠማም ሆነ የሚያሠማ መንግስት ለመድሀኒትም ቢሆን ተፈልጐ አይገኝም፡፡ በ1970ና 80ዎቹ የሊባኖስ የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት የራሳቸውን ሚሊሻ በማቋቋም ነፍጥ አንስተው ውጊያ የገጠሙት ህልውናቸዉን አደጋ ላይ ከጣሉት ታጣቂ የሚሊሻ ቡድኖች ጋር እንጂ ከሊባኖስ መንግስት ወታደሮች ጋር አልነበረም፡፡ ቤተእስራኤሎችም በእስራኤል የሚኖሩ “ድሩዞች” አይነት ነበሩ፡፡

እግራቸዉ የእስራኤልን መሬት ገና ከመርገጡ ጀምሮ የሂብሩ ጋዜጦች መብታቸውንና ነፃነታቸውን የሚጋፋ፣ ሠብአዊ ክብራቸዉንም የሚያንቋሽሽ አስከፊ የጥላቻ ዘመቻ ሲከፍቱባቸው፤ ያይጥ ምስክር ድንቢጥ እንዲሉ ጋዜጦችንም ተከትለው የተለያዩ የእስራኤል ተቋማት፣ የተለያዩ የእስራኤል የመንግስት ባለስልጣናት፣ የሀይማኖት መሪዎችና የማህበረሠብ አባላት ተዘርዝሮ የማያልቅ የዘረኝነት በደል ሲፈጽሙባቸው በእስራኤል መንግስት ላይ የነበራቸው ተስፋና እምነት እንደተጠበቀ ነበር፡፡ ቤተእስራኤሎቹ ለእስራኤል መንግስት የነበራቸውን ክብርና እምነት እንዲህ በቀላሉ እሰየው ብለው ለድርድር የሚያቀርቡት ጉዳይ ጨርሶ አልነበረም፡፡ የተስፋዋ ሀገራችን በሚሏት እስራኤል ይሆናል፤ ያጋጥመናልም ብለው ጨርሰው ባልገመቱት ሁኔታ ያ ሁሉ ግፍና በደል ወደው እስኪጠሉ ድረስ ሲፈራረቅባቸው የእስራኤል መንግስት በወቅቱ የሠጣቸዉ መልስ አልነበረም፡፡ በዘርና በቀለማቸው የተነሳም ኢትዮጵያ ውስጥ ይኖሩ በነበረበት ጊዜ እንኳ ማንም ብሏቸው ወይም ጠርቷቸው የማያውቀውን “ኩሽም” (ባሪያ) የሚል መዘባበቻ ሲሆኑ የእስራኤል መንግስት ግን ተፈልጐም እንኳ ሊገኝ አልቻለም ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ ግን ቤተእስራኤላውያን ከተጣዱበት የዘረኝነት መጥበሻ ላይ እንዳሉ በፀጥታ መገላበጥን እንጂ በሚያምኑትና በሚያከብሩት የእስራኤል መንግስት ላይ ልባቸውን ለማሻከርም ሆነ ፊታቸውን ለማጥቆር ጨርሶ አልሞከሩም፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ በዚያን ወቅት በእስራኤል መንግስት ላይ ይህን ለማድረግ የሚያስችል አንጀት አልነበራቸውም ነበር፡፡

እንደ እስራኤል ድሩዞች ተደርገው መቆጠር ጀምረው የነበሩት ቤተእስራኤሎች ማንም ሊያደርጉት ይችላሉ ብሎ ባልገመተው ሁኔታ በእስራኤል መንግስት ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በተቃውሞ አደባባይ በመውጣት የእየሩሳሌምንና የሌሎችም የእስራኤል ታላላቅ ከተሞች ለአንድ ወር በዘለቀ ጠንካራ የተቃውም ስብሠባና ሠልፍ ቀውጢ ያደረጉት ሀይማኖታቸውን በተመለከተ በከፍተኛ ሀፍረት ላይ የጣላቸውና በእጅጉ ያሸማቀቃቸው በደል ከደረሠባቸው በኋላ ነበር፡፡ ቤተእስራኤሎች ከዚህ በፊት በከፍተኛ ትዕግስትና ሆደ ሠፊነት ይዘዋቸው የነበሩት የተለያዩ ፈርጀ ብዙ ችግሮች ሁነኛ መፍትሄ እንዲያገኙ የእስራኤል መንግስትን ሳያሠልሱ መወትወት የጀመሩትና አልፎ አልፎም የተቃውሞ ድምፃቸውን ማሠማት የጀመሩትም ከዚህ ጊዜ በኋላ ነው፡፡ የእስራኤል መንግስት ግን የቤተእስራኤሎችን ችግር የተረዳው ገልብጦ በተቃራኒው ነበር፡፡ ለእስራኤል መንግስት የቤተእስራኤሎች ችግር እውነተኛ ችግር ሳይሆን እነሱን ለማዋሀድ በሚል የሚያደረግላቸው መጠነ ሠፊ እርዳታ ስለበዛባቸው ከመቅበጣቸው የተነሳ የመጣ ችግር አድርጐ ነበር፡፡ እናም በየጊዜው የሚያቀርቡትን የመፍትሄ አቤቱታ ለማዳመጥ የሚያስችል ጊዜውም ሆነ ልቦናና የመስሚያ ጆሮ አልነበረውም፡፡

ይልቁንስ ነገሩ ሁሉ የምግብ ፍላጐት ከመብላት ጋር ይመጣና ይጨምራል እንደሚባለው ሆኖበት ነበር፡፡ እናም አንዱ ጥፋት በጊዜ የመታረም እድል ማግኘት ሳይችል በሌላኛው ላይ እየተደራረበ ሄዶ፣ ቤተእስራኤሎቹን ከተቀረው የእስራኤል ማህበረሠብ ጋር በሚገባ ለማዋሀድ በሚል በእስራኤል መንግስት ተደግሶ የነበረውን “የቅልቅሉን” ድግስ የተጠሩት እንግዶች ሊቀምሱት እንዳይችሉ አድርጐ በአሳዛኝ ሁኔታ እንጀራውን አሻገተው፣ ወጡን እጅ እጅ እንዲል አደረገው፡፡ የእስራኤል መንግስት ቤተእስራኤሎች የራሳቸውን ቤት መግዛት እንዲችሉ ለማበረታታት በሚል በሠጣቸው ብድር አማካኝነት እስከዛሬ አስር አመት ድረስ አስር ሺ አምስት መቶ የሚሆኑ ቤተእስራኤላውያን አብዛኞቹ ባለ አንድ መኝታ ቤት የሆኑ አፓርታማዎችን ወይም የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለመግዛት ችለዋል፡፡ ከተቀሩት ውስጥ አብዛኞቹ በመንግስት የኪራይ ቤቶች ውስጥ ሲኖሩ፣ ከዛሬ አስር አመት ወዲህ ወደ እስራኤል የመጡት ደግሞ ዛሬም ድረስ በመጠለያ ጣቢያዎችና በተንቀሳቃሽ ቤቶች ውስጥ ይኖራሉ፡፡ ለቤተእስራኤሎች ተዘርግቶ የነበረው የመኖሪያ ቤት ግዢ የብድር ፕሮግራም እንደተገለፀው የተወሰኑትን የቤት ባለቤት ሊያደርጋቸው ቢችልም የሚፈለገውንና ቀድሞውኑ የታሠበለትን ውጤት ሳያመጣ እንደከሸፈ በእስራኤል ክኔሴት (ፓርላማ) ተመስክሮበታል፡፡ ለዚህ ደግሞ ከእስራኤል መንግስት ሌላ በተጠያቂነት ቀርቦ ቃሉን ሊሠጥ የሚችል ተጠያቂ አካል ሊኖር አይችልም፡፡ እንዴት ቢባል… የእስራኤል መንግስት ይህን የብድር ፕሮግራም የጀመርኩት ቤተእስራኤሎችን ለመርዳት በሚል “ቅን” መንፈስ ነው በማለት ሞቅ ያለ ፕሮፓጋንዳውን ቢለቅም ለፕሮግራሙ አፈፃፀም ሙሉ ቀልቡንና ልቡን ጨርሶ አልሠጠም ነበር፡፡ ፕሮግራሙን ለማስፈፀም የተጠቀመባቸው ስትራተጂዎች በሙሉ የተንጋደዱና አቅም ባላቸው ባለሙያዎች የተያዙና የተመሩ ጨርሶ አልነበሩም፡፡ የፕሮግራሙ ጠቅላላ አሠራርም የግብር ይውጣ ነበር፡፡

ይህን የብድር ፕሮግራም አሠራር በትኩረት በመከታተል አፈፃፀሙን በደንብ መገምገም የቻሉ የማህበራዊ ኑሮ ጥናት ባለሙያዎች፤ የእስራኤል መንግስት ቀድሞውን ቢሆን የእስራኤል “ኩሽም” የሆኑትን ቤተእስራኤሎች ከተቀረው “ናሽም” (ነጭ) የእስራኤል ማህበረሠብ ተለይተው በአንድ አካባቢ ብቻ ተከማችተው እንዲኖሩ ለማድረግ እጅግ በረቀቀ መንገድ ነድፎ ያዘጋጀው ፕሮግራም ነው እያሉ በሰላ ትችት ሲያብጠለጥሉት ኖረዋል፡፡ ይህን የባለሙያዎች ትችት ትክክል ነውም አይደለምም ብሎ መከራከሩ አጨቃጫቂ ሊሆን ይችላል፡፡ የሆኖ ሆኖ ግን የእስራኤል መንግስት በፈለገው አይነት አላማ ቢያዘጋጅም የመጨረሻው ውጤቱ ግን ከቀረበው ትችት ጋር አንድ አይነት ነበር፡፡ የመኖሪያ ቤት ለመግዛት ብድር የወሰዱ ቤተእስራኤሎች አብዛኞቹ ስራ አጥ ነበሩ፡፡ ስራ አላቸው የሚባሉትም ቢሆን እጅግ ዝቅተኛ ክፍያ በሚያስገኙ የስራ መስኮች ላይ የተሰማሩ ነበሩ፡፡ እናም ከወሰዱት ብድር ላይ ትንሽ ጨምረው በተሻሉና መካከለኛ ገቢ አላቸው ወደሚባሉትና ሁሉም አይነት የመሠረተ ልማት አገልግሎቶች በተሟሉባቸው አካባቢዎች ውስጥ ቤት ለመግዛት የሚችሉ አልነበሩም፡፡ ሁሉም በብድር ያገኙትን ገንዘብ ይዘው ያመሩት ርካሽ የመኖሪያ ቤቶች ወደሚሸጡባቸው፣ ምንም አይነት የመሠረተ ልማት አገልግሎቶች ባልተዘረጉባቸው ኋላቀርና ጭራሹኑ ወደተዘነጉት አካባቢዎች ነበር፡፡ ይህም ሁኔታ በድህነት የተቆራመዱ፣ በጨለማ የተዋጡና፣

ከሌላው የእስራኤል ህብረተሠብ በእጅጉ የተጉላሉ “የኩሽም ቤተእስራኤሎች” የመኖሪያ ጌቶዎች እንዲመሠረቱ ዋነኛ ምክንያት ለመሆን በቃ፡፡ የማታ ማታ አፍላ፣ ኪርያት ጋት፣ ኦር ይሁዳ፣ ኪርያት ማላኪህና የመሳሠሉት በተለያዩ የእስራኤል ከተሞች ውስጥ የሚገኙ ሠፈሮች “ናሽም” እስራኤላውያን ዝር የማይሉባቸዉ ወይም ዝር ሊሉባቸው በጣም የሚፈሯቸው የቤተእስራኤሎች መኖሪያ ጌቶ ሠፈሮች በመሆን አለም አቀፍ እውቅናን ለመጐናፀፍ ቻሉ፡፡ አሳ ሁልጊዜ በመረብ ብቻ አይጠመድም፡፡ የመኖሪያ ቤት ግዢ የብድር ፕሮግራሙ እንዲህ ያለ አሳዛኝ ውጤት በማስመዝገብ ሲከሸፍ፣ ብዙዎቹ ቤተእስራኤሎችና እነሱን ለመርዳት ተብለው የተቋቋሙ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የእስራኤል መንግስት ቤተእስራእሎችን ለማዋሀድ በሚል የቀረፃቸውን ሌሎች ፕሮግራሞች የአፈፃፀማቸውን ጉዳይ መለስ ብሎ ለመገምገም አረፍ የሚልበት ታዛና የጥሞና ጊዜ ያገኛል ብለው ተስፋ አድርገው ነበር፡፡ ይህንን ተስፋ ያደረጉትም “አንዴ የተሸነፈ ሁለት ጊዜ ያፍራል” የሚለው እድሜ ጠገብ የማስተዋልና የብልሀት አነጋገር መቼም ቢሆን ለእስራኤል መንግስት አይጠፋውም ከሚል ግምታቸው በመነሳት ነበር፡፡ ቶማስ ሐንዴ የተባለ ደራሲ “Mr. Nicholas” በሚል ርዕስ በ1952 ዓ.ም ባሳተመው መጽሀፍ፤ አደጋን ለመጋፈጥ የማይፈልጉ ቦቅቧቃ ሰዎች፤ ምንም ቢያደርጉ ምን በአስደናቂ ነገሮች የተሞላ ህይወት ለመኖርና አስደናቂ ውጤቶችን ለመቀዳጀት ከቶውንም አይችሉም ይላል፡፡ ይህ የቶማስ ሒንዴ አባባል በቀላልና አጭር አገላለጽ ሲቀመጥ “ጀብዱ ለጀብደኞች፣ (Adventure is for fare adventurous) ማለት ነው፡፡ ከ1973 ዓ.ም የዬም ኪፑር ጦርነት ድል ማግስት ጀምሮ እስከአሁን ድረስ በወይዘሮ ጐልዳ ሜየርም ሆነ በቤንጃሚን ናታንያሁ ጠቅላይ ሚኒስትርነት የተመራው የእስራኤል መንግስት ወታደራዊ የሆነውን ነገር ለጊዜው ትተን ማህበራዊ ጉዳዮችን ብቻ በተመለከተ የወሠዳቸውን የተለያዩ የፖሊሲም ሆነ ሌሎች እርምጃዎችን በስሱ በመገምገም ብቻ የእስራኤል መንግስት ጀብዱ (Adventure) አድናቂና ጀብደኛ (Adventurous) መንግስት እንደሆነ ለመገንዘብ ምንም አይነት የአዕምሮ ብሩህነትን አይጠይቅም፡፡

አሳዛኙ ነገር ግን እነዚያ ቤተእስራኤሎችና የቤተእስራኤል ድርጅቶች ይህንን በወጉ መገንዘብ አለመቻላቸው አሊያም ጨርሰው መዘንጋታቸው ነበር፡፡ በዚህ የተነሳም የእስራኤል መንግስት፤ የመጀመሪያው ውሸት ወደ ሁለተኛው ውሸት ይመራል እንደሚባለው አይነት ከመጀመሪያው ስህተት ወደ ሁለተኛው ተሸጋገረ፡፡ የእስራኤል መንግስት ቤተእስራኤሎችን ለማዋሃድ በነደፈው ማስተር ፕላን፣ የስራ እድልን በተመለከተ ያስቀመጠው ዋነኛው ግቡ ለቤተእስራኤሎች የሙያና የክህሎት ስልጠና መስጠት የሚል ነው፡፡ በዚህ መሠረት የእስራኤል የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ለቤተእስራኤሎቹ በቂያቸው ነው ብሎ የመረጠላቸው የሙያና የክህሎት የስልጠና መስኮች የብረታብረት፣ የእንጨት ስራ፣ የነርሲንግ፣ የሆቴል መስተንግዶና፣ የልብስ ስፌት ናቸው፡፡ የእውነት ለመናገር ባለእጅነትን አምላክ ሁልጊዜ ለቤተእስራኤሎች ብሎ የጣፈው ሙያ ይመስላል፡፡ ይህ ላይ ላዩን ሲያዩት አሪፍ ነገር ይመስላል፡፡ ነገር ግን ቤተእስራኤሎች አስቀድሞ በተመረጠላቸውና በተወሰነባቸው በእነዚህ የስልጠና መስኮች የሙያ ስልጠና እንዲወስዱ ዝግጅት እየተደረገ ባለበት ወቅትም ሆነ ከዚያ ቀደም ብሎ እነዚህ የስራ መስኮች በፍልስጤማውያንና በሌሎች ዜጐች ከአፍ እስከደገፋቸው ተይዘው ነበር፡፡ እናም ቤተእስራኤሎቹ እንደታሰበው ሰልጥነው ቢወጡም፣ በእስራኤል የስራ እድል መድረክ ላይ ተወዳድረው ስራ ማግኘት በእጅጉ አዳጋች ሆነባቸው፡፡ በመጨረሻም ያተረፉት ነገር የእስራኤልን አውራጐዳናዎች ማጽዳት፣ መናኛ ስራዎችን እጅግ መናኛ በሆነ ክፍያ መስራትና የእስራኤል የአዲስ መጤዎችና የውህደት ሚኒስቴር የሁልጊዜም የእርዳታ ጥገኛ ሆኖ መቅረትን ነበር፡፡ በትምህርትና በሌሎች የማህበራዊ ዘርፎች የተገኘው ውጤትም ከዚህ ጨርሶ የተለየ አልነበረም፡፡ ቤተእስራኤላውያን በተሻለ ተዋህደውበታል ተብሎ ሊጠቀስ የሚችለው ተቋም ቢኖር የእስራኤል የጦር ሀይል ብቻ ነው፡፡

ቤተእስራኤሎች እውነተኛ እስራኤላዊ መሆናቸውንና ለእስራኤል ያላቸውን ፍቅርና ታማኝነት የህይወት መስዋዕትነትም ቢሆን በመክፈል ለማሳየት ቁርጠኛ አላማ የያዘና ለዚህም የምራቸውን የተዘጋጁ ነበሩ፡፡ የእስራኤል የመከላከያ ሠራዊትን በገፍ የተቀላቀሉትም በዚህ የተነሳ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ ተቋምም ቢሆን ያጋጠማቸው የዘረኝነት መድልዎ እንዲህ በቀላሉ ተነግሮ የሚያልቅ አይደለም፡፡ የእስራኤል መንግስት ችግሮቹን በጊዜ ለመፍታት ባለመቻሉ ሳይሆን ፈጽሞ ባለመፈለጉ የተነሳ በሁሉም ነገር የመጨረሻውን ዝቃጭ ደረጃ የያዘ አንድ የእስራኤል ማህበረሠብ ለመፍጠር ቻለ፡፡ ቤተእስራኤሎችም የማታ ማታ ከመላው የእስራኤል ማህበረሠብ ተለይተው የዘረኝነት ጥቃትና መድልዎ ሰለባ ሆነውና የመጨረሻውን ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ይዘው ራሳቸውን አገኙት፡፡ ይህም ሁኔታ የአብዛኞቹን ቤተእስራኤሎች ቤተሠብ ክፉኛ አመሠቃቀለው፡፡ በእድሜ የገፉት ለከፍተኛ ግራ መጋባት ሲዳረጉ፣ ወጣቶቹ ደግሞ በከፍተኛ የማንነት ቀውስ ውስጥ በመውደቃቸው “ራስታ” ለመሆን ባዘኑ፡፡ እነዚሁ ቤተእስራኤሎች በከፍተኛ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ውስጥ ስለወደቁ፣ በወንጀል ድርጊት መሳተፍ፣ የወንጀል ቡድን አባል መሆን፣ አደንዛዥ እጽ መጠቀምና ማዘዋወር ድርጊት ውስጥ መሳተፍ ጀመሩ፡፡

በዚህም የተነሳ የቤተእስራኤል ወጣቶች የእስራኤልን እስር ቤቶች ማጨናነቅ ተያያዙት፡፡ ለህይወት ጉጉት ማጣታቸውና ከህይወት ትግል ማፈግፈጋቸውም መገዳደልንና ራስን ማጥፋትን እንደ ዋነኛ የችግር መገላገያ መፍትሄ አድርገው ይቆጥሩት ጀመር፡፡ የተቀረው የእስራኤል ህዝብ በአባታቸው ኖህ እንደተባረኩት ልጆች እንደ ሴምና ያፌት ናቸው፡፡ ማርና ወተቱን እለት ተዕለት እየተቆጣጠረ የቆዳ ስልቻቸውን የሚሞላላቸው የራሳቸው አሳላፊ አላቸው፡፡ የቤተእስራኤሎች ኩባያ ግን ባዶ ነው፡፡ ምክንያቱም ከሀገሪቱ የማርና የወተት ሠልፍ የእነሱ ተራ ከሁሉም የመጨረሻው ስለሆነ ነው፡፡ አሁን እነሱ ለአምላካቸው እያቀረቡት ያለው ፀሎት አንድ ብቻ ነው፡፡ አምላካቸው የራሳቸውን ነህምያ (ነቢይ) እንዲሠጣቸው!! አሜን ያድርግላቸው!

Read 9048 times
Administrator

Latest from Administrator