Saturday, 02 February 2013 11:50

ጠቅላይ ቤተ ክህነት በአራት የሚዲያ ተቋማት ላይ ክሥ መሠረተች

Written by 
Rate this item
(5 votes)

 የጎፋ ቅ/ገብርኤል ምእመናን በደብሩ አስተዳዳሪ ተማረዋል

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ‹‹መሠረተቢስ መረጃዎችን በማስተላለፍ ሕዝቡን ለማደናገር ይሠራሉ›› ባላቸው የሚዲያ ተቋማት ላይ ክስ መመሥረቱን አስታወቀ። በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ በወጣው ደብዳቤ እንደተገለጸው÷ ክሥ የተመሠረተባቸው አራቱ የሚዲያ ተቋማት÷ የኛ ፕሬስ ጋዜጣ፣ አርሒቡ፣ ሊያ እና ሎሚ የተባሉ መጽሔቶት ናቸው፡፡
የቅዱስ ፓትርያሪኩን ዜና ዕረፍት ተከትሎ ያለውን የሽግግር ወቅት በሰላማዊ መንገድ ለማከናወን ቅ/ሲኖዶስ በአንድነትና በመደማመጥ መንፈስ በተለያዩ ጊዜያት ጉባኤያትን በማድረግ፣በውጭም በውስጥም ያለውን ተጨባጭ ኹኔታ በመዳሰስና በሐቅ ላይ በመመርኮዝ የስድስተኛውን ፓትርያርክ ምርጫ ለማካሄድ ተግባራዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ መኾኑን መምሪያው ገልጾ÷ ‹‹አንዳንድ የነጻው ፕሬስ አባላት ሓላፊነት በጎደለው መንፈስ በመንፈስ ቅዱስ የሚመራውን የቅ/ሲኖዶስ ጉባኤ ውሎ በማብጠልጠልና በመተቸት የሚያወጧቸው ዘገባዎች በእጅጉ አሳዛኝና ቤተ ክርስቲያኒቱን ኾነ ብለው ለመበጥበጥ የተነሡ ያስመስላል›› ብሏል፡፡
በሕዝብ ግንኙነት መምሪያው ደብዳቤ እንደተመለከተው፣ በስም የተጠቀሱት ፕሬሶች በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትም ኾነ በሚመለከታቸው አካላት ማብራሪያና መግለጫ ያልተሰጠበትን ዜና ‹‹ከልዩ ልዩ የመረጃ መረቦች አግኝተናል›› በሚል ሽፋን ጽፈዋል፡፡ መምሪያው ‹‹በአባቶች መካከል ጠብና ችግር አለ ብሎ አንባቢው እንዲያምን ለማድረግ የሚጻፉ ናቸው›› ያላቸው እኒህ ጽሑፎች፣‹‹መሠረተቢስ አሉባልታዎች ብቻ ሳይሆኑ ቤተ ክርስቲያኒቱን የማፈራረስና ቅ/ሲኖዶሱን የመበታተን ዓላማ ያነገቡ ናቸው፡፡››
በመኾኑም በስም በተጠቀሱት አራት የፕሬስ ውጤቶች ላይ ቤተ ክርስቲያኒቱ ክሥ መመሥረቷንና ሕግና ሥርዐቱ በሚፈቅደው መሠረት ጉዳዩን በመከታተል የሕግ እርምት እንዲወሰድ በመንቀሳቀስ ላይ መኾኗ ተመልክቷል። ትክክለኛ መረጃን ለሕዝቡ ለማድረስ የሚመለከታቸውን አካላት በማነጋገር እውነተኛውን ዜና የሚያስተላልፉ የግል ሚዲያ ተቋማትን ቤተ ክርስቲያኒቱ እንደምታደንቅና እንደምታመሰግን በደብዳቤው የገለጸው መምሪያው፣ በሚመለከተው የቤተ ክርስቲያኒቱ አካል መግለጫ ያልተሰጠባቸው ዘገባዎች ሁሉ ‹‹የሽግግር ወቅቱ በሰላማዊ መንገድ እንዳይከናወን የሚጥሩ ሰዎች የሚያናፍሱት የሐሰት ወሬ›› መኾኑን ሕዝቡ እንዲያውቀው ጠይቋል፡፡
በሌላ በኩል በአሁኑ ወቅት በቤተ ክህነቱ የተለያዩ ደረጃዎች የሚታዩ አስተዳደራዊ ችግሮች እየተባባሱ መኾናቸው፣ በየጊዜው ለአዲስ አድማስ ዝግጅት ክፍል እየደረሱ ያሉ የካህናትና ምእመናን አቤቱታዎች ያስረዳሉ፡፡ በተደጋጋሚ የዘገብነው በሰሜን ወሎ ሀ/ስብከት የቅ/ላሊበላ ደብረ ሮሃ ገዳም አስተዳደራዊ ችግር ዋነኛ ማሳያ ሲሆን በአስተዳደሩ ላይ ሲነሣ የቆየውና የከተማውን አስተዳደር ጨምሮ በመንግሥትና በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ከፍተኛ አካላት ዘንድ ሳይቀር በሚገባ የሚታወቀው የካህናቱና ምእመናኑ ጥያቄ በተለያዩ አጋጣሚዎች መመሪያ እንደተሰጠበት ቢነገርም እስከ አሁን በተጨባጭ ምላሽ እንዳላገኘ ነው የተዘገበው፡፡
ለመልካም አስተዳደር እንዲያመች በሚል በጥቅምቱ የቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባ ውሳኔ÷ ለአራት በተከፈለው በአዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሥር በሚገኙ አንዳንድ አድባራትም ከሙስናና ብልሹ አሠራር ጋራ ተያይዘው በካህናቱና ምእመናኑ የሚነሡ በርካታ ጥያቄዎች እንዳሉ ለዝግጅት ክፍሉ የሚደርሱ መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡ በደቡብ አዲስ አበባ ሀ/ስብከት የጎፋ መካነ ሕያዋን ቅ/ገብርኤል ካቴድራል÷ በካቴድራሉ አስተዳዳሪ ከእርሳቸውም ጋር በጸሐፊነት፣ በሒሳብ ሹምነት እና በገንዘብ ያዥነት በሚሠሩ የአስተዳደሩ ሠራተኞች ላይ ካለፈው ዓመት መጨረሻ ጀምሮ የሚነሡትና ከሀ/ስብከቱ ጽ/ቤት ባሻገር የመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቱ ጭምር እንደሚያውቀው የተነገረው አንድ የችግሩ አብነት ነው፡፡
በካቴድራሉ ሰንበት ት/ቤት እንደሚያገለግሉ የገለጹት ምእመናኑ ለዝግጅት ክፍላችን በሲዲና በሰነድ ያደረሷቸው መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፣ በክብረ በዓላትና በተለያዩ ጊዜያት ደብሩ በመባዕና በስእለት ለሚያገኘው ገንዘብና ንብረት ቆጠራ የሚካሄደው ግልጽነትንና ተጠያቂነትን የሚያሰፍነውን መመሪያ በመከተል ሳይሆን በአስተዳዳሪው ቀራቢዎች ነው፤የካቴድራሉ ገንዘብና ንብረት በትክክለኛ ሞዴላ ሞዴሎች ገቢ አይደረጉም፡፡ ከካቴድራሉ የንዋያተ ቅድሳት መሸጫና ሱቁ በተጓዳኝ ከሚሠራቸው የጨረታና የጉዞ አገልግሎቶች የሚሰበሰበው ገቢ በአግባቡ አይታወቅም፡፡
ሁለተኛውን ፓትርያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስን ለመዘከር በተሠራው የአንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ከሚማሩ ተማሪዎች ክፍያ በሁለት ደረሰኞች የሚሰበሰብ ሲኾን አንዱ ደረሰኝ በካቴድራሉ ሰበካ ጉባኤም ሆነ በሀ/ስብከቱ አይታወቅም፡፡ ከፍለው ለመማር አቅም የሌላቸውን ተማሪዎች በበጎ አድራጊዎች ስፖንሰርሽፕ ለመደገፍ አስተዳደሩ የሚከተለው አሠራር ለምዝበራ የተጋለጠ በመኾኑ በችግረኛ ተማሪዎች ስም እየተነገደ ነው፡፡
በካቴድራሉ ደጃፍ መንግሥት በሰጠው ፈቃድ በካቴድራሉ ወጪ የሚሠራው የዝክረ ቴዎፍሎስ ዐደባባይ ሦስተኛ ዓመቱን ቢያስቆጥርም በየጊዜው ኾነ ተብሎ ዲዛይኑንና ጥራቱ ጠብቆ እንዳይሠራ እየተደረገ ግንባታው እየተጓተተ ነው፡፡ በግንባታው ሰበብ የሚገዙ የግንባታ ማቴሪያሎችና በቃል ኪዳን ሰነድ የተሰበሰበው ገንዘብ የግለሰቦች መኖሪያ ቤት መሥሪያና የግል ኑሮን ማበልጸጊያ እንደኾነ በምሬት የሚናገሩት ምእመናኑ÷ በቀድሞው አስተዳደር በአግባቡ ተጠብቆ የቆየው የካቴድራሉ ሕንጻ ቤተ መቅደስና የቅጽረ ቤተ ክርስቲያኑ ገጽታ በወቅቱ አስተዳደር ትኩረት የተነፈገው በመኾኑ በከፍተኛ ደረጃ መጎሳቆሉን፣ በአንጻሩ በካቴድራሉ ይዞታዎች በቤተ ክርስቲያን ቅጽር መገኘት የማይገባቸው ግለሰቦች ከአስተዳደሩ ጋራ በፈጠሩት የጥቅም ትስስር ለቤተ ክርስቲያን ቅድስናና ክብር ተቃራኒ የኾኑ ንግዳዊ ሥራዎችን (የከሰል፣ የአጠና ሽያጭና የአሳማ ርባታ) እንደሚያካሂዱ የሚናገሩት በከፍተኛ የሐዘን ስሜት ተውጠው ነው፡፡
ምእመናኑ በሰነድና በቃል ማብራሪያ አስደግፈው በካቴድራሉ አስተዳደር ላይ የሚያሰሟቸው አቤቱታዎች÷ የሰበካ ጉባኤ ቃለ ዐዋዲን፣ የቀኖና ቤተ ክርስቲያንንና የክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ጥሰትን የተመለከቱ ተጨማሪ አቤቱታዎችን ያካተተ ሲሆን ካለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ጀምሮ ለመፍትሔው እንቅስቃሴ ሲደረግባቸው መቆየቱ ተገልጧል፡፡ አቤቱታዎቹ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በሠየመው አጥኚ ኮሚቴ በሚጣሩበት ወቅት የካቴድራሉ አስተዳደር ያመነባቸው ከመኾኑም በላይ ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ ለአምስት ዓመታት በአስተዳዳሪነት የቆዩት ቆሞስ አባ ኀይለ መለኰት ይኄይስ ከሓላፊነት ተነሥተው ለካቴድራሉ መንፈሳዊ አገልግሎትና የልማት አቅም በሚመጥን አለቃ እንዲተኩ ተወስኖ እንደነበር ምእመናኑ ያስታውሳሉ፡፡
ውሳኔውን በአግባቡ ተፈጻሚ በማድረግ መፍትሔ እንዲሰጣቸው በጥቅምት መጨረሻና በጥር መጀመሪያ ላይ ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጽ/ቤትና ለቅ/ሲኖዶስ ጽ/ቤት ጥያቄዎቻቸውን በተደራጀ አኳኋንና በሰላማዊ መንገድ እያቀረቡ እንደሚገኙ ምእመናኑ ገልጸው÷ የካቴድራሉ አስተዳደር ግን ይባስ ብሎ ‹‹አቤቱታ አቅራቢዎችን ተባብረዋል›› በሚል ዐሥር የካቴድራሉን ካህናት ከደመወዝና ከሥራ ማገዱን፣በካቴድራሉ ይዞታ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቶቻቸውም እንዲለቁ ማዘዙን፣ ካቴድራሉ የሚገባውን ብቁ አስተዳደር እንዲያገኝ በሥርዐት የሚንቀሳቀሰውን የሰንበት ት/ቤት አመራርም በዐመፀኝነትና በፖለቲከኝነት በመወንጀል ከፍተኛ ጫና እየፈጠሩበት መኾኑን አስረድተዋል፡፡ በሓላፊነት ላይ የሚገኙት የካቴድራሉ አስተዳዳሪ ከሥልጣናቸው መነሣት ብቻ ሳይሆን የሕዝብን ሀብት ለብክነትና ለምዝበራ በመዳረጋቸው በሕግ መጠየቅ እንዳለባቸው የሚከራከሩት አቤቱታ አቅራቢዎቹ፣ በሕግ አገባብ ለሚመለከተው የፍትሕ አካል አስፈላጊውን ማስረጃ ለማቅረብ ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውን አስታውቀዋል፡፡


Read 5878 times Last modified on Saturday, 02 February 2013 11:54