Saturday, 02 February 2013 14:14

ንገስ ቢሉት ዛሬ ሰምበት ነው አለ (ተረገስ ቢውሪ ከረ ሰምበቱ ባረም) የቤተ-ጉራጌ ተረት

Written by 
Rate this item
(7 votes)

ሺጉሜን የተባለው የጃፓን ንጉሥ ቻ-ኖ-ዩ የተባለው የሻይ ስነስርዓት በጣም ደስ ይለው ነበር፡፡ በችሎቱ ላይ ዳኛ ሆኖ ሲቀመጥ እንኳ ሻዩን እያደቀቀ ይፈጭ ነበር ይባላል፡፡ ምክንያቱ የሚከተለው ነው፡- 

ከዕለታት አንድ ቀን የሻይ ነጋዴ የነበረ ወዳጁን
“ህዝቡ ስለ እኔ ምን ያስባል?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ነጋዴውም፤
“ማስረጃቸውን በግልፅ የማያቀርቡ ሰዎችን ትቆጣለህ፡፡ ሙልጭ አድርገህም ትሳደባለህ የሚል አስተያየት ነው ያለው፡፡ በዚህ ምክንያትም ህዝቡ እውነተኛውን ህጋዊ ማንነቱንና ጉዳዩን ወደ አንተ ለማቅረብ ስለሚፈራ እውነቱ በግልፅ አይታወቅም” ሲል ይነግረዋል፡፡
ንጉሡም፤
“አመሰግናለሁ! እንኳን ነገርከኝ፡፡ እኔ እስከዛሬ፤ ለሰዎች እቅጩን የመናገር ልማድ ነበረኝ፡፡ ስለዚህም ትሁቶቹና በድፍረት በአደባባይ የመናገር ድፈረት የሌላቸው ጨዋ ሰዎች እውነቱን ፍርጥ አድርገው አይገልፁም፡፡ ወደፊት ጠባዬን ማረም ይኖርብኛል” ይላል፡፡
ከዚህ በኋላ ንጉሡ ዙፋን ችሎት በሚቀመጥበት ጊዜ ሁሉ፤ አንድ የሚያስገርም ነገር ማድረግ ጀመረ ይባላል፡፡ በጨርቅ ተሸፍኖ የሻይ መውቀጫው/መፍጫው ከስሩ እንዲቀመጥለት ያዛል፡፡ በሀር ጨርቅ ተሸፍኖ ጥዋ መስሎ ይቀመጥለታል፡፡ ከዚያም አቤቱታ አቅራቢው ህዝብ አቤቱታውን ሲያሰማ እሱ ሻዩን እየወቀጠ ትኩረቱን ወደ ሙቀጫው በማድረግ ቁጣውን ይቆጣጠራል፡፡
ቀጥሎም የፈጨውን ሻይ በትክክል መድቀቅ አለመድቀቁን በእጁ እየነካ ያየዋል፡፡ ያረጋግጣል፡፡ ሻዩ በትክክል ከተፈጨ መንፈሱ የረጋና ሚዛናዊ መሆኑን ያስባል፡፡ በትክክልም አቤቱታ ማዳመጡን ያምናል፡፡ ሻዩ ያላግባብ የተወቀጠ ከሆነ ግን የተረበሸና ቁጠኛ ስሜት እንደነበረው ያውቃል፡፡
በረጋ መንፈስ የተፈጨው ሻይ፤ ፍርድ በትክክል መስጠቱንና አቤት ባዮቹም ረክተው መሄዳቸውን ይነግረዋል፡፡ ይሄኔ፤
“ተመስገን! ህዝቤ ሳያዝንብኝ፤ ረክቶና ደስ ብሎት ሄዷል ማለት ነው” ብሎ ፈገግ ይላል፡፡
* * *
ለህዝብ የሚቆረቆር ዕውነተኛ መሪ የህዝብን ብሶት ማዳመጥ፤ አቤቱታውን መስማት ያረካዋል። ህዝብ የልቡን ዕውነት የሚደብቅ ከሆነ ትክክለኛ አስተዳደር አለ ለማለት ያዳግታል፡፡ ዐይና - ውጣው በአደባባይ እንደልቡ ሲናገር፤ ጭምቱና ፈሪው ሃሳቡን ሳይገልጽ ይቀራልና ሥርዓቱ ሁሉንም ያስተናግዳል ለማለት አያስደፍርም፡፡ ሃሳቡን የሚገልጽ ህዝብ የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ምሰሶ ነው። በዚህ ረገድ በጥሞና የህዝብን የልብ ትርታ ለማዳመጥ የሚችል ጆሮ ያለው መሪ ያስፈልጋል፡፡ የመሥሪያ ቤት አለቃ፣ የማህበር መሪም ሆነ የፖለቲካ መሪ አስተዋይ አዕምሮ፣ ሆደ - ሰፊ አመራርና “ወደፊት ይህን ይህን ጠባዬን ማረም ይኖርብኛል” የማለት ድፍረት ሊኖረው ያሻል፡፡ ያን ካገኘን ታድለናል፡፡
የአንድ ሀገር ህዝብ እንደዜጋ የተፃፈን ጽሑፍ በነፃነት፣ በጥሞናና በጥንቃቄ አንብቦ የሚመረምር፤ ያሻውን ዓይነት የፖለቲካ ሥርዓት የሚከተል፣ በነፃነት አገዛዙን የሚቃወም፣ የሚተችና ሲያስፈልግ አይሻኝም የማለት መብቱን የሚያውቅ ሊሆን ይገባል፡፡ እንደአራሽ እንደላብ - አደርም የአቅሙን ያህል ማምረትና የኢኮኖሚ ህልውናውን ሊያጠናክር ይጠበቅበታል፡፡ እንደዜጋም ሆነ እንደሠራተኛ በአገሩ ይኖር ዘንድ የሚያሠራው፣ የሚያሳትፈው ሥርዓትና ህግ ሊያገኝም የግድ ነው፡፡
“ባገር እኖር ብዬ
ልጅ አሳድግ ብዬ
ከብት እነዳ ብዬ፤
ለባሻ ዳርኩለት ሚስቴን እቴ ብዬ”
እያለ የሚያለቅስ ባላገር በምንም ዓይነት ማየት የለብንም፡፡ ጊዜውም ቦታውም አይፈቅድምም። በፖለቲካ የተገፋ፣ በኢኮኖሚ የደቀቀ፣ ማህበራዊ ድርና ማጉ ውሉ የጠፋ ህብረተሰብ እንዳይኖር ነው የስትራቴጂያችን ዒላማ! ውሃ ጋ ከሆን አሣ፣ ግጦሽጋ ከሆን ሥጋ መብላትን ልናውቅበት ወቅቱ ያስገድደናል፡፡
አንድ የገዛ በሬው ሊወጋው የሚያሳድደው ባለበሬ ለአንድ የሰፈር አዛውንት፤ “እረ ይሄ በሬ እያሳደደ አስቸገረኝ“ ቢላቸው፤ “የት ነው የምትተኛው?” ብለው ጠየቁት አሉ፡፡ ባለበሬውም፤ “ቤቴ። ሣር ፍራሼ ላይ!” ይላቸዋል፡፡ ሽማግሌውም፤
“ታዲያ ቀለቡ ላይ እየተኛህ ዱሮስ ላያባርርህ ኖሯል እንዴ?” አሉት ይባላል፡፡ ሰውንም ቀለቡ ላይ ተኝተን ነፃነት አለህ ብንለው የለበጣ ነው የሚሆነው፡፡ ነፃነቱን ከኢኮኖሚ ጥቅሙ የሚያስተሳስር ሥርዓት መፍጠር ተገቢ ነው፡፡ ለተገቢ ሥርዓት ክሳቴ የሚታገሉ ሁሉ ጊዜን መሠረት ያደረገ ስትራቴጂ ይኖራቸው ዘንድ ወቅቱ ይጠይቃቸዋል፡፡
“ፊት የበቀለን ወፍ ይበላዋል” የሚለውን ተረት ሳንረሳ “የዘገየ ፍርድ ካልተፈረደ አንድ ነው”ን እያውጠነጠንን፤ ትክክለኛው ጊዜ ሲደርስ ግን “የሚሥማሩን አናት መምታት”ና አጋጣሚን በአግባቡ መጠቀም ወሳኝ መሆኑን ልናሰምርበት ይገባል፡፡ በወቅቱ ያልዘራም በወቅቱ ያልሰበሰበም ሁለቱም ከመራብና ከማስራብ አይድኑም - “ንገሥ ቢሉት ዛሬ ሰምበት ነው አለ” የሚለው የጉራጊኛ ተረት የሚነግረን ይሄንኑ ነው!!

Read 5236 times Last modified on Saturday, 02 February 2013 16:43