Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Monday, 07 November 2011 12:35

መኮንኑ - “ኧረ ዙሪያውን ተከበናል ጄኔራል?” ጄኔራሉ - “አሪፍ ነዋ! በፈለግነው አቅጣጫ እንተኩሳለን”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን አንዲት ድመት አንድ አውራ ዶሮ ታይና አድፍጣ ልትበላው ትፈልጋለች፡በእርግጥ ልትበላው አይገባትም በህጉ፡፡ አውራ ዶሮው በመሠረቱ ድመት አውራ ዶሮ የመብላት ባህል የላትም በሚል በቸልተኝነት ግቢው ውስጥ እየተጐማለለ ይዝናናል፡፡ አመሻሽ ላይ ነው፡፡ 
በመጨረሻ ድመቷ ዘልላ ከመያዙዋ በፊት፤ ምክንያት እንደሚያስፈልጋት አሰበችና እንዲህ አለችው
“እንደምን ውለሃል አያ አውራ ዶሮ?”
አውራዶሮም፤ “ደህና ነኝ፡፡ እንደምን ውለሻል እመት ድመት”
እመት ድመትም፣
“ሌሊት ሌሊት እየጮህክ ሰዎችን ከእንቅልፋቸው እየቀሰቀስክ እስከዛሬ ስትረብሽ ከርመሃል፡፡ ከእንግዲህ ግን ይሄ አጉል የምትጮኸው ነገር ያበቃል፡፡ አሁን እርምጃ ልወስድብህ ነው” አለችው፡፡

አውራ ዶሮው፤ እመት ድመት እንደተሳሳተች በመገመት፤ 
“እመት ድመት ሆይ በጣም ተሳስተሻል፡፡ እኔ የምጮኸው ሰዎች ማለዳ እንዲነሱና እንዲነቁ የዕለት ሥራቸውን በጠዋት እንዲጀምሩ፤ በዚህም ኑሯቸውን ለማስተካከል እንዲችሉ እንጂ ለመረበሽ አይደለም፡፡ እንዲያውም እኔ ባልኖር በትክክል ጊዜን ለማወቅ አይችሉም ነበር” አለና ተከላከለ፡፡
እመት ድመት ግን በግትርነት፤
“ሰዎች ጊዜውን ለማወቅ ቻሉም አልቻሉም እኔ እራቴን ሳልበላ ማደር የለብኝም” ብላ ዘላ ቀጨም አደረገችው፡፡

* * *


የማናቸውም ጥሩ ምክንያት መኖር አንዴ በልቡ ለመብላት ያሰበን ሰው ከማድረግ አያግደውም፡፡
“ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ ጅግራ ይሏታል” የተባለው ተረት የተገላቢጦሽ ሆነ ማለት ነው፡፡
ህዝብን ተሳታፊ የማያደርግ እንቅስቃሴ ዘላቂ አይሆንም፡፡ አመራር ሁሉ ሀቀኛ ተመሪ ያገኝ ዘንድ ግድ ነው፡፡ ተሳታፊነት በውዴታ እንጂ በግዴታ የሚሆን አይደለም፡፡ የህዝብ ቀዳሚ አብሪ ወጣቱ ነው፡፡ ወጣቱን ያልያዘ (መያዝም ቢሉ በውዴታና ከልብ) ለውጥ የሚያቆጠቁጥ አይሆንም፡፡ ቻይናዎች “ጀልባ ማንቀሳቀስ ከፈለግህ ወደ ወንዙ መቅረብ አለብህ” የሚሉት በአግባቡ ለመቅዘፍ እንዴት እንደሚቻል ልብ እንድንል ነው፡፡
መሪና ተመሪ ልባዊ ግንኙነት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ መሪና ተመሪ የአምሮ አቅም መመጣጠን (Congruence of wavelength) ሊኖራቸው ይገባል፡፡ መሪና ተመሪ የአቋም መጣጣም ሊኖራቸው ይገባል፡፡ መሪና ተመሪ ከጌታና ሎሌ ግንኙነት የተላቀቁ መሆን አለባቸው፡፡ መሪና ተመሪ የመተካካት ባህል ሊኖራቸው ይገባል እንጂ አይተኬ - ነኝ (indispensable) የሚል ሰው የሚኖርበት መሆን የለበትም፡፡
በተለይም ተመሪው ወይም ተከታዩ “መሪዬ ከሌለ ወዴት እደርሳለሁ?” የሚል ሥጋት ያለው ከሆነ፤ አንድም መሪው ብቸኛና አይተኬ ነኝ እንዲል ይገፋፋዋል፤ አንድም ደሞ ተመሪው ራሱን ለተተኪነት እንዲያዘጋጅ፤ በቆመበትና ባለበት ሁኔታ ያግተዋል፡፡ ቻይናዎች እንደሚሉት “ከዶሮዎች መካከል ያለች ፒኮክ በቀላሉ ትለያለች” ማለት ነው፡፡ መሪው አይተኬ ሆነ ማለት ይኼው ነው፡፡
ማንኛውም የፖለቲካ መሪ አይተኬ ነኝ ብሎ ሲያስብ ብዙ ዓይነት ባህሪያትን ያንፀባርቃል፡እኔ ያልኩት ምንጊዜም ልክ ነው ከሚል ተነስቶ፤ እኔ ያልኩት ካልተፈፀመ ሞቼ እገኛለሁ፤ ይላል፡፡ ያጠናውን፣ የፃፈውን የተናገረውን በሀገሩ ላይ ይፈትናል፡፡ ወይም ይፈትሻል፡፡ ኢኮኖሚው በእጁ ይወድቃል፡፡ በየጉዳዩ ላይ ቅድመ ፍርድ ይሰጣል፡፡ “ስታሊን እንደንስ” ሲል ማን ቁጭ ብሎ ያያል” ይላል ክሩስቼቭ፡፡ እሱ ሲስቅ አገር ይስቅ ዘንድ፣ እሱ ሲቆጣ አገር ይቆጣ ዘንድ ግድ ይሆናል ማለት ነው፡፡
አሁን አሁን የእኛን ሙሰኞች ከሙስና እንዲፀዱ ማድረግ “ውሻን አይጥ መያዝ ማስተማር” ዓይነት ከባድ ነገር እየሆነ መጥቷል፡፡ ሌባ ያዝ ተብሎ የተላከው፤ ራሱ ሲሰርቅ ይገኛል፡፡ ሲሰርቅ ተይዞ እሥር ቤት የገባው፤ ሌላ ዓይነት ሌብነት ተምሮ ይወጣል “ሞኝ ያስራል ብልጥ ይማራል” የተባለው ዓይነት፡፡
የሙስና ዲግሪ የሚሰጥ ቢሆን፤ በመሬት፣ በቤት፣ በቢሮክራሲ፣ በቴክኖክራሲ፣ በሌበር - አሪስቶክራሲ፣ በብሔር - አሪስቶክራሲ የሚሸለሙ ስንቶችን አፍርተን ነበር - ባይልልን ነው እንጂ፡፡
“የመጨረሻው ድህነት በህይወት ውስጥ ምንም ምርጫ ማጣት ነው፡፡”ይሉናል የፈረንጅ ፀሐፍት፡፡ ወይም ፀጋዬ ገ/መድህን እንደሚለን “ማጣት፤ በነብስህ ጫፍ ሩቅ አልመህ ሁሉን መሳት” ማለት ነው፡፡ በየጉዳዩ ላይ ምርጫ ያጣ ህዝብ እጅግ ደሀ ህዝብ ነው፡፡ ስለዲሞክራሲ፣ ስለፍትህ፣ ስለ ገዛ ኢኮኖሚው፣ ስለመናገር ነፃነቱ፣ ስለቤት ንብረቱ አማራጭ የሌለው፤ የዓለም ባንክ ባልደነገገው መንገድ የድህነት ምርኮኛ ነው፡፡ ከዚህ ይሰውረን፡፡ በየአቅጣጫው ዙሪያ ገባውን በችግር ማጥ የተወረረ ህዝብ ያልታደለ ነው፡፡ ያም ሆኖ እንደመኮንኑና እንደ ጄኔራሉ ውይይት፤ የታሪክ ምፀት ባለቤት መሆኑ ባይቆጭ ያንገበግባል፡፡
መኮንኑ - “ኧረ ዙሪያውን ተከበናል፤ ጄኔራል?” ሲል
ጄኔራሉ - “አሪፍ ነዋ በፈለግነው አቅጣጫ እንተኩሳለን” አለ አሉ፡፡ አዎንታዊነት? ጨለምተኝነት ትራጆ - ኮሜዲ? ወይስ ፋርስ ዞሮ ዞሮ ምፀት ነው፡፡

 

Read 4211 times Last modified on Monday, 07 November 2011 12:45