Saturday, 09 February 2013 10:46

‹‹የመራጭነት ምዝገባው›› አስጨናቂ ነበር ተባለ

Written by  ዓለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

በምርጫ 97 ዓ.ም በመራጭነት ለመመዝገብ ጥብቅ ቁጥጥር ይደረግባቸው የነበሩት መስፈርቶች በዘንድሮው የአካባቢና የማሟያ ምርጫ በቸልተኝነት መታለፋቸውን የጠቆሙ መራጮችና የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፤ የነዋሪነት ማረጋገጫ የቀበሌ መታወቂያ፣ በቀበሌው የነበረው የነዋሪነት ዘመን ቆይታና ከ18 ዓመት በላይ የሚለው የዕድሜ ገደብ በሚገባ መሟላቱ ሳይረጋገጥ የመራጭነት መታወቂያ ካርድ መሠጠቱን ገለጹ፡፡ ምርጫ 97ን ከመጪው ምርጫ ጋር በማነጻጸር አስተያየታቸውን የሰጡን ተመዝጋቢዎች፤ያን ጊዜ የምርጫ ካርድ ለመውሰድ በተጠቀሱት መስፈርቶች መሠረት፣ ጥብቅ ቁጥጥር ተደርጎ የሚሰጥ ሲሆን መስፈርቱን ያላሟላ መራጭ ካርዱን እንዳይወስድ ይከለከል እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ለዘንድሮው የአካባቢና የማሟያ ምርጫ ግን ዜጐች ቤታቸው በራፍ እየተንኳኳ አስጨናቂ በሆኑ የማግባባት ሂደቶች፤ ሕጉ እና መመሪያው የሚጠይቀው አንዱም መስፈርት መሟላቱ ሳይረጋገጥ ‹‹ሰው›› መሆኑ ብቻ እየታየ የምርጫ ካርድ እንዲወስዱ ሲገደዱ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ በመጪው ሚያዚያ 2005 ዓ.ም የሚካሄደውን ምርጫ ዝግጅት ከ97 ምርጫ ጋር ያነፃፀሩት የአንድነት የቀድሞ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዶ/ር ሃይሉ አርአያ፤‹‹አንድ ዜጋ ምርጫ የመምረጥ ወይም ያለመምረጥ የምርጫ ካርድ የመውሰድ ወይም ያለመውሰድ መብቱ የተጠበቀ መሆን ሲገባው የግዴታ ግፊት በማድረግ አሁን በሥልጣን ላይ ያለውን ፓርቲ እንዲመረጥ መቀስቀስ የዴሞክራሲ ሂደት መክሸፉን ያመላክታል›› ብለዋል፡፡

ፕ/ር መረራ ጉዲና በበኩላቸው፤‹‹ዜጐች ተወካዮቻቸውን እንዲመርጡ መቀስቀስ ተገቢነት ያለው ቢሆንም የዚህኛው ምርጫ አካሄድ ግን ይለያል፤ያን ጊዜ ምርጫ ካርድ ለመውሰድ አንድም መስፈርት ማጓደል ክልክል ነበር፤ አሁን ግን የተመዝጋቢውን ቁጥር በማግዘፍ ምርጫ ያለ ለማስመሰል የምርጫ ካርድ ዕደላ ተያይዘዋል፡፡›› ብለዋል፡፡ ‹‹ኅብረተሰቡ የሚደረገውን ሁሉ ጠንቅቆ ያውቃል›› ያሉት ፕ/ር መረራ፤ “ከዚህ በኋላ ወዴት እንደሚሄድ አይታወቅም እንጂ የዴሞክራሲ ግንባታ የሚባለው አቁሟል” ብለዋል፡፡ ‹‹የዚህ የመራጭነት ምዝገባ ቅስቀሳ ስልት ውጤትም አምባገነናዊ የፖለቲካ ሥርዐትን መገንባት ነው›› የሚሉት ፕሮፌሰሩ፤ ‹‹በ1997 ዓ.ም ምርጫ ቢያንስ ምርጫ የሚመስል ነገር ነበረው፤ የአሁኑ ግን ምርጫም ቅርጫም መሆን አይችልም፡፡›› በማለት አስተያየታቸውን ለአዲስ አድማስ ሰጥተዋል፡፡

የቀድሞው የኦሮሞ ፌዴራሊስት ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኦፌዴን) ሊቀመንበር የነበሩት አቶ ቡልቻ ደመቅሣ፤ “ገዥው ፓርቲ እርሱን የሚመርጠውንና የማይመርጠውን ለይቶ ስለሚያውቅ፣ የሚመርጠውን ብቻ ለይቶ የምርጫ ካርድ እንዲወስድ ይገፋፋል የማይመርጠው መስሎ ከታየው ብዙ መመዘኛዎችን እያስቀመጠ ከተሣታፊነት እንዲገለል ያደርጋል፡፡ አሁንም እያደረገ ያለው ይህንኑ ነው” ብለዋል፡፡ አያይዘውም ‹‹እኛን ይመርጣል ብለው የሚያስቡትን ያለ ብዙ ውጣ ውረድ እያስተናገዱ ነው›› ብለዋል፡፡ በዚህኛው የመራጮች የምዝገባ ሂደት ሁለት ጉዳዮችን መታዘባቸውን የጠቀሱት የአንድነት ሊቀመንበር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ አንደኛው ‹‹ኮሙኒቲ ፖሊስ›› የሚባሉ የመንደር ውስጥ ፀጥታ አስከባሪ ፖሊሶች ሥራቸው ጥበቃ ሆኖ ሳለ በየቤቱ ሄደው ተመዝገቡ እያሉ መሆናቸው፤ ሌላኛው ሦስት እና አራት ጊዜ በየቤቱ በመመላለስ ሂዱና ተመዝገቡ በሚል የሚቀሰቅሱ አካሎች መኖራቸውን ገልፀዋል፡፡ ይህ ደግሞ በተዘዋዋሪ ኢህአዴግን ምረጡ ማለት እንደሆነና በዜጐች የግል ውሣኔ ውስጥ ጣልቃ እንደመግባት ሊቆጠር እንደሚችል ዶ/ር ነጋሶ አስታውቀዋል፡፡

በተነሱት አስተያየቶች ዙሪያ ምላሻቸውን እንዲሰጡን ያነጋገርናቸው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሕዝብ ግንኙነት ምክትል ኃላፊ አቶ ይስማው ጅሩ በበኩላቸው፤ አንድ ዜጋ ከላይ የተጠቀሱትን መስፈርቶች አሟልቶ ሲገኝ ብቻ የመራጭነት ካርድ እንደሚሰጠው ገልጸው ‹‹በዚህኛው የመራጮች ምዝገባ ሂደትም ይኸው ተግባራዊ ተደርጓል፡፡›› ካሉ በኋላ ‹‹እነዚህ ሁሉ መመዘኛዎች ሳይሟሉ መራጮች እየተመዘገቡ ነው የሚል አቤቱታ እስከዛሬ ከየትኛውም ወገን እንዳልደረሳቸው›› ተናግረዋል፡፡

Read 3043 times Last modified on Saturday, 09 February 2013 14:12