Monday, 07 November 2011 12:45

በጥቅምት “አንድ አጥንት” “አንድ አጥሚት?”

Written by  እምሻው ገ/ዮሐንስ
Rate this item
(0 votes)

በዚህ ርዕሰ - ጉዳይ ላይ ለመወጋወግ ሳሰላስል በሀሳቤ ወደ ስነ-ቃልነት እየተሸጋገረ ያለ አንድ ሕዝባዊ ግጥም ትዝ አለኝ!
“እስከዛሬ ድረስ የስጋ ጣዕም ሳላቅ
እንዴት ይጣፍጣል ታናሽና ታላቅ!”
(እዚህች ላይ! ማነሽ እህቴ! አላማችን በቀጥታ እንጅ በቅኔ ለመወጋወግ ስላልሆነ ይሄ የ”ታናሽና ታላቅ” ጉዳይ ተነሳ ብለሽ ያንን ሁሌ “መንትዮቹ” ምናምን እያልሽ እምታደርቁኝን ጉዳይ እዚህ ላይ ደግመሽ እንዳታነሺ አደራ!)
ውድ አንባቢያን ይሄ በዘመን መለወጫና የመስቀል ድርብ የበአላት ጥቃት የቆሰለ ኪሳችንን ለማከምና በምላሹም ቢያንስ ለእራሱ “የአንድ አጥንት” ፕሮፖዛሉን በመቅረጽ ከተፍ ያለውና እየሸኘነው ያለው የጥቅምት ወር ጭኖት በመጣው ንፋስ ምክንያት ከ “አበባነት” ይልቅ “አቧራነቱ” የተረፋችሁ ሁሉ ለዛሬው “የጥቅምት አበባ” የሚለውን የሁለመናው ሸጋ ድምፃዊ የንዋይ ደበበን ዜማ ተውሰን

“የጥቅምት አቧራ ነሽ አሉ 
በከልሽው አካሌን በሙሉ”
በሚል አጣጥመን ስለ “ጥቅምት፣ አጥንትና አጥሚት” ጥቂት እንወጋወጋለን፡፡
መቼስ በሀገራችን ባህል መሠረት በከተማ ሆነ በገጠር ከተሜው ከቅርጫም ከልኳንዳም፣ ገጠሬውም ሲቀና የጐረቤት በሬ ገደል ገብቶበት በትብብርም፤ አለዝያም ቢያንስ “የቆቁን” ሲልም “ሚዳቋና ብሆሩን” አድኖ ጥቅምትን አጥንት ሳይነክስ አያሳልፍም ነበር፡፡ (እዚህች ላይ ማነህ ወንድሜ “እኛ መስኩን ሁሉ በችግኝ ስናለብስ እነሱ ከስር፣ ከስር እያሰሉና ቀን እየቆጠሩ ከፍ ሲል ጠብቀው በመመገዝ ለመወልወያ መሣሪያ ያደርጉታል በዚህ ምክንያትም አውሬው ሁሉ ተሰደደና የአደን ባህላችን ጠፋ ብለህ ያማረርክልኝ እኔ እምጨምርልህ ነገር ቢኖር “ዛፍ ትከል ተንከባከብ” በሚለው መመሪያ መሠረት ተክለህ ብቻ ዞር አትበል ነው)፡፡
አሁን ለታ ነው በቀደም በጊዜ ወደ ቤቴ በማዝገም የተከራየሁዋትን ታዛ ከፍቼ አልጋዬ ላይ አረፍ ስል፣ የኔን ክፍል ተካፋይ ጓዳ በታሸገ የእንጨት በር ድንበርነት የተከራዩዋት ባልና ሚስቶች የሚባባሉት ሁሉ እንደወትሮው ሁሉ ጥርት ብሎ ይሰማኝ ነበር፡፡
“ሰማሽ የኔ ፍቅር፤ እሱን ነገር እባክሽ በደንብ እሳት ይምታው፤ ጥሬ ነገሮችን ማግበስበስ ድሮ ቀረ” የዘንድሮ ጤና እንደሁ ለመበከል ጥቂት ይበቃዋል” ይላል አቶ አባወራ ከፍ ብሎ
“ኧረ እባክህ በሀገራችን እኮ በየአጥቢያው “ፀበል” እንጅ “ነዳጅ” ፈለቀ አልተባለም ስለዚህ መፍትሔው ምግብን እንደነገሩ ማገንፈል ሲታመሙ ደግሞ እድሜ ለፀበሉ እሱን ግጥም ማድረግ አለዝያ ቢታመሙ ጋዝ አይጠጣ ቢጠጣስ የሌትሩ ዋጋ ከሰው ደም በልጦ” “ወይ አንቺ ድሮስ በክርክር ማን ሊችልሽ ኖሯል፤ በይ እሺ ደግሞ አደራሽን ጨውን እንዳትሞጅሪበት፤ ለራሴ ሰሞኑን ደግሞ ግፊቴ ከፍ ብሏል”
“ችግር የለውም ብቻ ቅቤውን አሁን ልጨምረው ወይስ ሊወጣ ሲል ይሻላል?”
ባልና ሚስቱ ይህንን ሲባባሉ እኔም የግዴን እያዳመጥኩ፣ በሀሳቤ ደግሞ እኒህ ጥንዶች ቢያንስ “የጥቅምትና አጥንት” ባህሉን እና ብሒሉን ሳይዘነጉ ወደ “ልኳንዳ ቤት” ጐራ ማለታቸው አስደስቶኝ የትዳርን መልካምነት ሳሰላስል ከአፍታ በቀር መቆየት አልቻልኩም፡፡ ምክንያቱም የተጣደው በሠላም በሰለ መሰለኝ ንግግራቸው እንዲህ አናጠበኝ!
“በል እንካ ትኩሱን ያዝ! ሲቀዘቅዝ ጣዕሙን ያጣል፤ ለማንኛውም ከላዩ ላይ ልድገምህና ለእኔ ብረት ድስቱን ልያዝ፤ ምክንያቱም አጥሚት ደስ የሚለኝ ከወደቂጡ ነው፡፡”
መቼስ እድሜና ጨርቅ ካለጊዜው አያልቅምና በዚህ አብዛኞቻችን ስለ “ኑሮ” ስናቅድና ስንመኝ እያጠፋነው ባለው ኑሯችን ውስጥ፣ የደረስንበትን ዘመን ዘርፈ ብዙ ፈታኝነት የምታሳይ ሁኔታ አብረን ለመገንዘብ ያህል ባለፈው ሳምንት ከክ/ሀገር የመጣው ዘመዴ እንዲህ አወጋኝ!
“ቦታው ወንዝ ተሻግረውና ድንበር አሳብረው ከጐረቤት ሀገር “ሱዳን” በ”ሕግ” ይሁን በ”ሔይግ” ተፈቅዶላቸው የሚገቡ ባዕዳን፣ ከምግብ ዘር ከሽንኩርት እስከ ባቄላ፤ ከዕንቁላል እስከ በሬ እንስሳቱን ከነነፍሳቸው በ”ግዥ” አይሉት በ”ግፍ” እንደ ሽፍታ ንብረት ነድተውና ጨነው የሚወስዱባት፣ ሀገሬውም “የጫኝ” ተመልካች የሆነበት እና ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የ”ቅርጫ” ባህሉን ላለመተው የቅርጫት “ድንች” ገዝቶ በመደብ እየመደበ በሚከፋፈልበት ሀገርና ሁኔታ ላይ ይሄው ዘመዴ ለአዛውንት ወላጆቹ የ”ጥቅምት አንድ አጥንት”ን ወግ በ”እርጥብ” ቢጤ ሊያደርስ ላይ ታች ሲል ከአንደኛው ጐዳና ላይ የእንስሳቱ ስዕል የተሳለበትና በትልቁ የተፃፈ ማስታወቂያ አይኑን ይጠልፈዋል፡፡ ጠጋ ሲልም
“የበግ
የፍየል
የበሬ…እንደፍላጐትዎ በኪሎ ሃያ ብር ብቻ!”
ይሄ ዘመዴ መጀመሪያ ማስታወቂያውን ያየበት አይኑን ተጠራጠረ፤ ቀጠለና ከሃያ አመት በፊት ተለጥፎ የተተወ ማስታወቂያ መሰለው፤ ጨክኖ ሲጠጋ ግን ነገሩ እውነት ነበርና አንዱ ቁጡ ጐልማሳ ሻጭ ተቀብሎ “የምንድነው የምትፈልገው?” አለው፡፡
አይን አዋጅ የሆነበት ዘመዴም “ያው እንግዲህ ከጥሩው ነዋ! ከደህነኛው!”
“ጥሩ! ደህነኛ ምናምን ብሎ ነገር የለም ዋናው ያንተ ትዕዛዝ ነው”
ግን ከየትኛው ይሻለኛል?”
“መልስህ ልቤን ታደርቃለህ፤ ደረቅ ለራሴ ውሃ ጥም አድርቆኛል… ለመሆኑስ ስንት ኪሎ ይሁንልህ?”
“ምናባቱ በቃ የመጣው ይምጣ ሁለት ኪሎ ይሁንልኝ በአርባ ብር!”
ቁጡው ሰውዬ ይበልጥ ተቆጣ “ትቀልዳለህ? ለምን ልትሆንህ ነው ሁለት ኪሎ? ምን አይነት ሰው ነው እባካችሁ”
“እንዴ መቼስ ሰው እንደቤቱ አይደል እንዴ መሆን የሚችለው ደግሞም የሚወስነው ኪሴ እና ሐቅሜ ይመስለኛል”
“ቆይ ከየትኛው ነው የምትፈልገው? ለምን ጉዳይ ኑሯል?”
“እንዴት ከየትኛው?”
“እኔኑ ትጠይቃለህ እንዴ!
“እሺ አንዴ እርስዎ ያማርጡኝ!”
“እሺ ከእርጥቡ ከበጠጡና ከዕበቱ ነው ወይስ ለማገዶ ከፈለጉ ደግሞ ከኩበቱ?”
“እንዴ እኔ እኮ ስጋ ቤት መስሎኝ ነው ስጋ ለመሸመት”
“ኧረ እባክህ ኪሎ ስጋ በሃያ ብር ልትዘርፍ? ቀባባ ውጣ በሃያ ብር ስጋ ለመብላት ካርቱም መሄድ ስለሚጠበቅብህ ከመገደቡ በፊት በጊዜ አባይ ግባ! ጥፋ ከዚህ በጠጣም! እበታም! በሚል “በብርንዶ ስጋ” ፋንታ “ብርድ፣ ብርድ” የሚሉ ስድቦችን ጠግቦ መባረሩን ያወጋኝ በተሰበረ ቅስሙ ነበር፡፡
ድሮ፣ ድሮ የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ሆነን ሦስተኛና አራተኛ ክፍል አካባቢ ስማር የሳይንስና አማርኛ ትምህርት ክፍለ ጊዜያት ተከታታይ እንደነበሩ ትዝ ይለኛል፡፡ እናም የሳይንስ መምህር “አተርና ባቄላ ከስጋ ይበልጣሉ” ብለው አስጽፈውና አስረድተውን ሲወጡ፣ ወዲያውኑ በእግራቸው ይገቡ የነበሩት የአማርኛ መምህራችን “ደሀ በሕልሙ ቅቤ ባይጠጣ እከክ በወረሰው” የሚያስጠኑን “ስድብና ምሳሌ” ለሳይንስ ትምህርታችን ምላሽ መሆኑ የገባኝ አሁን ነፍስ ካወቅሁ በኋላ ነው፡፡ (እዚህች ላይ ማነህ ወንድሜ ጥራጥሬ በይበልጥ ለሰውነት ግንባታ ይረዳል የምትለኝ አባባል አልተዋጠልኝም፤ ምክንያቱም አባቶቻችን በዕውቀት የዋዛ አይደሉምና አንተ እንደምትለው ቢሆን ኖሮ በአባባላቸው ውስጥ የምናገኘው ምሳሌያዊ ሀረግ “ስጋ አለቀ ቢለው ፈስ ቀለለ አለ የሀገሬ ሰው” የሚል በሆነ ነበር፡፡
በየጥጋጥጉ ምግብ ቤት፣ ዛሬ ዛሬ ያቺ ጥቁሯ አይደርቄ ጐመን እንኳን በሀቅም ሁለት ቅጠሏን ሆና እና ተግጦ የተቀመጠ ከመሰለ ቁራጭ ጐድን ጋር በአነስተኛውና በጥቃቅኑ ተደራጅታ፣ በክፍያዋ የዶሮን ዋጋ ስታስወጣ ይሄ “ቬጅቴሪያንነት”ም በራሱ ከኢኮኖሚ አንፃር ትርጉም አልባ ነው፡፡
እንዲሁም የድንችና ቲማቲም የኪሎ ሒሳብም ቢሆን “ቬጅቴሪያን” በመሆን ከስጋ የሚጽናኑበት ማምላጫ መሆኑ ተረት እየሆነ የመጣ ጉዳይ ነው፤ ምክንያቱም በብዙ ቦታዎች አንዲት ሠሐን አትክልት ተመግቦ የኪሎ “ምላስ ሠንበር” ዋጋ በትንሹ መክፈል ለተመጋቢው እየተለመደ የሄደ ጉዳይ ነው! (እዚህች ላይ ማነህ አንተ ወዳጄ! ጭሱ የካዛንችሱ “ምላስ ሰንበር” ስል ምን ትዝ አለኝ መሰለህ? ባለፈው የምላስ ሰንበር” የብዕር ስም ስለሆነው “ጅንስ” ጉዳይ ስናወራ “እንዴት ነው? ምግብህ ጅንስ ልብስህ ጅንስ ብዬ ብጠይቅህ “አዎ ይሄ እንኳን በባዮሎጂ ህግ መሠረት የዘራችን የጂንስ ጉዳይ ነው ያልከኝን ነገር ቆይቼ ሳስበው “ጅን” ለማለት መሆኑን ተረዳሁና ቢያንስ ቢያንስ እለት እለት፤ ከሎካል እስከ ጐርደን በምትለምጠው “ጅን” እንኳ አለማስታወስህ ገረመኝ”
በዚች ላይ ስለ “ቬጂቴሪያንነት” የሰማሁትን ለማከል ያህል፣ ስጋን ካለመመገብ ጀምሮ የእንስሳት ተዋጽኦን ለምሳሌ ከወተትና ቅቤ መራቅን ሕጉ ሲያካትት፤ የእንስሳቱን ቆዳ በሌዘር መልክ ለጃኬት ቀበቶ ሆነ ጫማ አለመጠቀምን አብሮ ስለሚደነግግ ቢያንስ በ”ቻይና ሲንቴቲክ” ጫማዎች የምንቃጠል እኔን መሳይ ወንድሞቼ ሳናውቀው “ሰሚ ቬጂቴሪያን” ተብለን የመጠራት መብታችንን ሳበስራችሁ በታላቅ ደስታ ነው፡፡
(እዚህች ላይ ማናችሁ እናንተ ሁለቱ ወንድሞቼ:- በአደባባይ “ቬጂቴሪያን” ነን ብላችሁ አውጃችሁ፣ በአደባባይ ደግሞ ቅዳሜና እሁድ በ”አውቶሞቢል”ም በ”አውቶቡስ”ም በተናጠል “ሽው እልም” የምትሉባቸው “ኮተቤ - ካራ” እና “ዱከም” ቆስጣ በብልት ተሰቅሎ፣ ፓውዛ እየበራበት በመደብና በኪሎ ይቸበቸባል ሲባል አልሠማሁምና እባካችሁ ቢያንስ በስመ ፒያሣ የ”ቢስ መብራት”ን እና የ”ዶሮ ማነቂያ”ን አቅጣጫ አታምቃቱ፡፡)
መቼም ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው ይሄ የ”ጥቅምትና አጥንት” ጉዳይ ባህላችን ለአብዛኞቻችን እንጅ ለሁላችንም ዳገት አለመሆኑን ለመገንዘብ በተለይ በአዲስ አበባና በሁሉም የክልል ከተሞች ወደ ሬስቶራንት፣ ልኳንዳና ግሮሰሪዎች ጐራ ብትሉ ሁኔታውን ለመታዘብ በቂ ነው፡፡ በዚያም ለብዙው ሰው የፀሐይ ሀይል የሆነው የ”አስራ ሦስት ወር ፀጋ” ለእነሱ አመቱን ሙሉ “ጥቅምት” አድርጐላቸው እንደብርቱ የ “ሀርሞኒካ ተጨዋች” በሁለት እጆቻቸው ሙሉ የጨበጡትን ቅልጥምና ጐድን ወደ አፋቸው የሚለግቱ ዜጐች ቁጥራቸው ቀላል አይደለምና ሁሌም በዚያ “ከታፊ” “ጠባሽ” ዝግጁ ሆኖ ይጠብቃቸዋል፤ ነገር ግን እስካሁን እርግጠኛ መሆን ያልቻልኩት ጉዳይ አጉራሽና አኛኪ ይኑራቸው አይኑራቸው ብቻ ነው፡፡ ይሄ እንደዚህ ከሆነ ደግሞ ሰዎቹ ጭንቀታቸው ለ”መዋጥ” ብቻ ይሆናል ማለት ነው፡፡ እናም እነዚያ ዜጐች በአናቱ ከእነሱ አንዱ ጠርሙስ ጨብጦ የማወራረጃ ሻምፓኙን በነቀነቀ ቁጥር፣ በዚሁ ቅጽበት በሀገሪቱ ውስጥ በመቶ የሚቆጠሩ ዜጐች የበሶ መበጥበጫ ብልቃጣቸውን ጥቂት በሶና ጨው ጨምረው በውሃ ለመበጥበጥ እንደሚነቀንቁ ከቶ ሊያውቅ አይችልም፤ አይፈልግምም፡፡ ግን የጨነቀው ነው፡፡ አንዳንዴ ተረትም ይኳሻል?
አሁን ሰሞን ደግሞ የሀገራችን አንኳሩ ችግር የመከረኛ ዜጐቿ የስራ ፈጠራ ክህሎት (ኢንተርፕሪነር ፖቴንሻል) ማነስ መሆኑ በስፋት ይሳቀል ይዟል፤ ግን እንዲያው በሞቴ ነገሮች ሁሉ በተጠና ሁኔታ ዋጋቸው እሳት እንዲሆንና ከየመደብሩ እንዲሠወር በተደረገበት ሁኔታ አሁን የእኔ ከጥራጥሬና ከእሕል ዘሮች “አርቴፊሻል ስጋ” የማምረት “ፕሮፖዛሌ” ምን ፋይዳ ሊኖረው ይችላል? ነው ወይንስ ስጋን ከአፈር ማምረት ይጠበቅብኝ ይሆን? ድንጋይ እንኳን ለ”ተደራጅ ፈላጮች”ም ባይሆን ለ“አደራጅ አስፈላጮች “ኮብል” የሚባል ስጋና ቅቤ መሆን እንደሚችል ማየት ጀምረናል፡፡ ድሮ ልጆች ሆነን እኮ እንስሳቱ እንደ ልብ ስለሚታዩ ቢያንስ “በግና ፍየል በምን ይለያያሉ?”
“በላት”
“በምን ልበላት?”
እየተባባልን ለመጫወት እንኳን ይበጁን ነበር!
የዘንድሮ ልጅ ግን ሲያምረው ይቀራል እንጅ እንደዚህ ለመጫወት በግና ፍየልን በአይኑ ለማየትስ በአብዛኛው መች ታደለ?
“ሰዶ ማሳደድ ቢያምርህ “ዶሮህን” በ”ቆቅ” ለውጥ የሚለው ተረታዊ ምሳሌ በአቅሙ ከዶሮ ጋር አብሮ ወደ “ቱርክ” በመሰደዱም ምክንያት አሁን አሁን በሁሉም ቦታዎችም ባይሆን ተረቱ “ሰዶ ማሳደድ ቢያምርህ ዝም ብለህ እሩጥ” በሚል እየተቀየረ ነው፡፡ አለዚያማ ለአንዲት የዶሮ ጫጩት መቶ ሃያ ብር፣ በብልት አስር ብር ሒሳብ መክፈል ለኔ ብጤው እንዴት አግባብነት ሊኖረው ይችላል፡፡ እንግዲህ በባዶ ሆድ ይህንን ያህል ከተወጋወግን ጥርሴን ነክሼ የጣልኳት የቅዳሜ እቁቤ ከመጣችልኝ ቅንጣቢ ቢጤም ቢሆን ለመሸመት ወደ ልኳንዳ ቤት ማዝገሜ አይቀርም፡፡ እናንተም ኪሳችሁን አይታችሁ ብትከተሉኝ ተቃውሞ የለኝም፡፡ ሠላም ሁኑልኝ፡፡

 

Read 3409 times Last modified on Monday, 07 November 2011 12:53