Saturday, 09 February 2013 11:55

እንጨዋወት

Written by 
Rate this item
(3 votes)

‘ሲስተም ፌይለር’…

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
የካቲት ተጋመሰሳ! (“ገንዘብ መቁጠር ሲያቅትህ ወር ቁጠር…” ያልከኝ ወዳጄ…አሁን፣ አሁን እየገባኝ ነው!)
ስሙኝማ…ግራ እየገባን ያለ ነገር አለ፡፡ ይሄ ቴክኖሎጂ ምናምን የሚሉት ነገር..አለ አይደል ጥቅሙ ሥራን ማቅለልና መልክ ማስያዝ፣ የእኛንም መጉላላት ለማስቀረት አይደል እንዴ! ዓለም ስንት ሥራ እየሠራ ባለበት ሰዓት እኛ ሚጢጢዋ ነገር ሁሉ አቃተችን ማለት ነው!
የምር እኮ…ግራ እያጋባን ነው፡፡ “አገልግሎታችን ሁሉ ኮምፒዩተራይዝድ ሆኗል፣ ከእንግዲህ መጉላላት የለም…” ምናምን ተብሎ ደስ ሲለን ለአገልግሎት ስንሄድ ምን ይባላል መሰላችሁ…“ኮምፒዩተሩ አልሠራ አለ!” (ስሙኝማ…ይቺ አባባል ምን ትመስላለች መሰላችሁ…በቃ ልክ እርስ በእርስ ጣት መጠቋቆም እንደምንወደው ሁሉ ኮምፒዩተሩ ላይም ‘ጣታችንን የምንጠቁም’ ነው የሚመስለው፡፡ አልሠራ ያለው ኮምፒዩተሩ ነው እንጂ ኮምፒዩተሩን የሚያንቀሳቅሰው ወይም ሰው አይደለም፡ አሪፍ አይደል!)
እናላችሁ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ይሄ ‘ሲስተም’ የሚሉት ነገር ልክ የሆነ ወርድና ስፋት ያለው እየመሰለን መጥቷል፡፡ አሁን፣ አሁን “ሲስተሙ አልሠራ አለ” የሚሉት ነገር ከአንዳንድ ለምድር ለሰማይ ከከበዱ መሥሪያ ቤቶች ስንሰማ…ግር የሚል ነገር አለ፡፡ መጀመሪያ ‘ሲስተሙ’ ሥራ ላይ ከመዋሉ በፊት በቂ ሙከራ አልተደረገበትም ማለት ነው! ልክ ነዋ…ነገሮች “ባገኝ ባጣ…” አይነት ነገር እየሆኑብን ነዋ! በ“ባገኝ ባጣ…” አለ አይደል… ከሆነ ይሆናል ካልሆነ አይሆንም…‘ፉል ስቶፕ’!
‘ሲስተም’ ምናምን የሚባሉ ነገሮች ግን የራሳቸው የቀረጻ፣ የሙከራ፣ የማረጋጋጫ ምናምን ነገሮች አሏቸው አይደል እንዴ! እና አንድ ነገር ገና ከመጀመሩ “ሲስተም አልሠራ አለ…” ምናመን ነገር ሲባል…ቴክኖሎጂ ላይ እምነት እንድናጣ ነው የሚያደርገን፡፡ የመዘመናችን ነገር ከ‘ፌስ ቡክ’ አላልፍ ብሎ ግራ የገባን ነው የሚመስለው፡፡ (ስሙኝማ…እንዴት ነው አሪፍ የሆነው ነገር ሁሉ ወደ እኛ ሲመጣ የሆነ ጭራና ቀንድ የሚያበቅለው! አሁን ለምሳሌ ‘ፌስቡክ’ የሚሉትን ነገር…ካወቅንበት የሚገኝበት ዕውቀትና መረጃ በምንም ሊለካ የማይችል ነው፡፡ ሆኖም በ‘የፌስቡክ’ ገጽ የሚለጠፉትን ምስሎች፣ የሚጻፉትን መልእክቶች ምናምን ስታዩ የምር አስቸጋሪ ነው፡፡ አለ አይደል…“‘ደመ መራራነታችን’ ይሄን ያህል ጠልቆ በፌስቡክም ገባ እንዴ!” ምናምን የሚያሰኝ ነው፡፡) እናላችሁ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…‘ሲስተም’ የሚባለውን ነገር “ሀይ!” የሚልልን ይጥፋ! ልክ ነዋ… “እሰይ ስለቴ ሰመረ፣ ኑሮዬ ዘመነ” ምናምን ብለን ለመዝፈን ሲቃጣን ምን ይሆናል መሰላችሁ…‘ሲስተም ፌለር’ ይገጥማል! ስሙኝማ…አንዳንድ ጊዜ “‘ሲስተሙ’ም እንደ እኛ ክፉ፣ እንደ እኛ ‘ምቁ’ ሆነ እንዴ ምናምን ያሰኛል፡፡ የምር…ካነሳነው አይቀር… እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ምን መሰላችሁ፣ ‘ደመ መራራነት’ በዛ፡፡ በዛው ልክ ክፋት በዛ፣ ምቁነት በዛ ጥላቻ በዛ!
ኮሚክ ነገር እኮ ነው…የእኛ የግለሰቦቹ ክፋት ‘ፍሬኑ ተበጥሶ’ ሲንደረደር...አንዳንዴ ክፋት የግለሰቦች ጉዳይ ብቻ መሆኑ ቀርቶ…አለ አይደል…የሆነ ‘ኦርጋናይዜሽናል ቻርት’ የተሠራለት ነው የሚመስለው፡፡ ክፋት፣ ምቀኝነት፣ ጥላቻ ምናምን የተባሉ ነገሮች…የሆነ በስርአት የተዋቀረ አይነት መልክ ያላቸው ሲመስል አስቸጋሪ ነው፡፡
ሀሳብ አለን…‘ኒኦ ክፋቲዝም ምናምን የሚባል የ‘ቦተሊካ’ ስርአት ተፈልስፎ በመጽሐፍ መልክ ይውጣልንማ! አሀ… የራሳችን ‘ዳስ ካፒታል’ የሚኖረን ደረጃ ላይ ደርሰናላ! (በነገራችን ላይ ‘ኒኦ—ክፋቲዝም’ የእኛንና የወዳጅ አገር ‘አፎች’ን በማገናኘት የተፈጠረ ነው፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…ያው በምግብ ‘ሚስቶ’ የምንለው አይነት መሆኑ ነው፡፡ ‘ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች’ አይነት ሚስቶ እንትኖች ኦፊሴላዊ እውቅና አላቸው አይደል፡፡) እናማ… ክፋት ይህን ያህል እየተዋሀደን መምጣቱ ካልቀረ አርማ ወጥቶለት፣ ‘ሲንግል’ ተለቆለት፣ የኮሚዩኒኬሽን ባለሙያ ተመድቦለት (ቂ…ቂ…ቂ…) ‘መልክ’ ይውጣለትማ!
ደግሞ ሌላ እየበዛ የመጣ ነገር አለላችሁ…ስስት! የምር… በአጥር ተንጠልጥሎ “እከሊት፣ ከእራት የተረፈች ትንሽ ሹሮ ቢጤ አለችኝ፣ ነይ አባይኝማ…” ምናምን ማለት በአርኪዮሎጂስቶች ዋሻ ውስጥ በ‘አራሚክ’ ቋንቋ ተጽፎ ይገኝ እንደሁ እንጂ…እንኳን ልንሰማው “እንዲህ ይባል የነበረበትም ዘመን ነበር እንዴ!” የምንልበት ዘመን ደርሰናል፡፡ ልጄ…ዘንድሮ እንኳን “ሹሮ አባይኝ” ሊባል ቀርቶ…አለ አይደል…የሌላ ሰው ሹሮ ላይ ሁላችንም የይገባኛል ጥያቄ ያለን ነው የሚመስለው፡፡ ‘መስጠት’ የሚለው ቃል ሙሉ ለሙሉ ‘መውሰድ’ በሚለው ስለተተካ…ከ“እራት የተረፈች ሹሮ…” መጋበዝ “ሲያምርሽ ይቅር” የሚባል ነገር ሆኗል፡፡
እናላችሁ…ነገርዬው ሁሉ…አለ አይደል…“እንካ” ማለት እየቀረ “አምጣ” ማለት ብቻ እየገነነ የመጣ ይመስላል፡፡ የእኛ የግለሰቦቹን እንኳን ተዉትና…አንዳንዴ ከተለያዩ ክፍሎች የሚወጡ መመሪያዎች፣ ደንቦች ምናምን ላይ እንኳን ከጀርባቸው የሆነ “አምጣ” የሚል ጩኸት የገደል ማሚቶ ትሰማላችሁ፡፡ እናማ…“ይቺ ያው እንደተለመደው ለገንዘብ የወጣች ነች…” እያልን ማማታችን ከቁጥር ይግባልንማ!
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ጅብ ሆዬ እሜቲት አህያ የሆነ ነገር ተሸክማ ስትሄድ አይቶ ምን አላት አሉ መሰላችሁ…“አንቺም ሲሳይ፣ የተጫንሽው ሲሳይ…” ብሎ አረፈላችሁ፡፡ እናማ…አንዳንድ ጊዜ ጫና ሲበዛብን የተጫንነው ነገር ይኑርም አይኑርም…“አንቺም ሲሳይ፣ የተጫንሽው ሲሳይ…” የምንባል ይመስለናል፡፡
እናላችሁ…አሁን፣ አሁን አንዳንድ መሥሪያ ቤቶች ያለው የተገልጋይ ሰልፍ የካምቦሎጆውን የጊዮርጊስና ቡና ግጥሚያ ‘አርማጌዶን’ ሊያስንቅ እየተጠጋ ነው፡፡ እናማ…የከምፒዩተርም ይሁን የግለሰብ…‘ሲስተም’ የሚባለው ነገር “ሀይ” ይባልልንማ! ብዙ ነገሮች እየናፈቁን ነው፡፡ የምር…ዘወር እያልን ከጀርባችን የማናይበት ጊዜ እየናፈቀን ነው፡፡ የመሸበት መንገደኛ እግሩ ታጥቦ እንዲያድር የሚደረግበት አይነት መተማማን…አለ አይደል… ‘የድንጋይ ላይ ጽሁፍ’ እየሆነ በመጣበት ጊዜ የምናምነውና የሚያምነን ሰው እየናፈቀን ነው፡፡ “እንዲህ ያለ ዘመን ዘመነ ግርምቢጥ…” ምናምን እንደሚባለው ሁሉ…አይደለም ጓደኛ ጎረቤት ምናምን፣ የሥጋ ዘመድ ተሁኖ እንኳን መተማማን እየጠፋ ነው፡፡ እምነታችንን ጥለን “ይቺን ገንዘብ በአደራ አስቀምጭልኝ…” “ገበያ ደርሼ እስክመጣ ልጆቹን ጠብቅልኝ…” ምናምን የምንልበት ዘመን እየናፈቀን ነው፡፡
በፊት ጊዜ ገድገድ ሲያደርጋችሁ፣ ሲያደናቅፋችሁ “እኔን ይድፋኝ!” ምናምን የሚል የማታውቁት ሰው መአት ነበር፡፡ አዎ “ብታምኑም፣ ባታምኑም” እንደሚባለው……እንዲህ የሚባልበት ጊዜ ነበር! (ከዚህ በፊት እንዳወራነው…አለ አይደለ… “ነበር” የሚለው ቃል እየበዛ ሲሄድ አሪፍ ምልክት አይደለም፡፡) አሁን፣ አሁን ግን አይደለም የማታውቁት ሰው፣ የምታውቁት ‘ሹሮ ተበዳዳሪ’ እና ‘ቡና አጣጪ’ እንኳን ሲያደናቅፋችሁ… “ምን ያወላክፈዋል፣ እያየ አይሄድም!” ምናምን ነው የሚላችሁ፡፡ እናማ… እንደው ገድገድ ሲያደርገን እጁን ሰደድ አድርጎ “እኔን!” የሚል ህብረተሰብ ናፈቀን፡፡
ጓደኛሞች ናቸው፡፡ አንደኛው የሆነ ዕቃ ጓድኝየው ጋር በአደራ ለማስቀመጥና ላለማስቀመጥ ሲያመነታ ጓደኝየው ምን ይለዋል…“እመነኝ ሀሳብ አይግባህ፣ ዕቃውን በሚገባ እጠብቅልለሁ” ሲለው ያኛው ደግሞ “አይደለም አንተን የገዛ ወንድሜንም አላምንም…” ይለዋል፡፡ ጓደኝየው ምን ቢል ጥሩ ነው …“ልክ ነህ፣ እኔም የአንተን ወንድም አላምነውም፡፡” ከማይታመንና አደራ ከማይጣልበት ዘመድና ወዳጅ ይሰውረንማ!
በየመሥሪያ ቤቱ በር ላይ ፈገግ የሚሉ የጥበቃ ሠራተኞች ማየት ናፈቀንማ፡፡ “አቤት ጌታዬ ምን ልርዳዎት…” ማለት ቀርቶ ዱላውን እየወዘወዘ “ወዴት ነው፣ መግባት አይቻልም” የሚል የጥበቃ ሠራተኛ በዝቷል፡፡
ስሙኝማ…እንደ እኛና ቢጤዎቻችን ግራ የገባው ምስኪን ምን አለ አሉ መሰላችሁ…
ግንብ ላይ ብሠራ እባቡ መከራ፣
በዛፍ ላይ ብሠራ አሞራው መከራ፣
በምድር ላይ ብሠራ እረኛው መከራ፣
የት ውዬ የት አድር ብዬ፡፡
እናላችሁ…ብዙ ነገር እየተበላሸ ‘ሲስተም ፌይለር’ የሚሉት ነገር እግር ተወርች እያሠረን ስለሆነ “ሀይ!” ይባልልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 5190 times