Saturday, 09 February 2013 12:06

የዓመቱ “ሰቃይ” የፖለቲካ እንቆቅልሽ!

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ለጠራራ ፀሐይ “ዝርፊያ” የጠራራ ፀሐይ “ዘለፋ!”
ዛሬ ወጋችንን በእንቆቅልሽ ብንጀምር ምን ይመስላችኋል? ታዲያ የፖለቲካ እንቆቅልሽ ነው፡፡ ለነገሩ ፖለቲካችን መቼ ከእንቆቅልሽ ወጥቶ ያውቃልና ነው!! (ኑሮአችንስ ቢሆን?) አሁን ለማንኛውም “እንቆቅልሽ?” ብያችኋለሁ “ምን አውቅልሽ” ካላችሁኝ ልቀጥል፡፡ “በአገራችን ብዛታቸው እንደቆጠራቸው ሰው አይነት ከፍና ዝቅ የሚሉት ምንድን ናቸው?” ምናልባት ጠጠር የሚልባችሁ ከሆነ (እንደ ጦቢያ ፖለቲካ ማለቴ ነው!) ፍንጭ ልስጣችሁ እንዴ? (ፍንጭት ግን አልወጣኝም!) ፍንጭ ከሰጠኋችሁማ ምኑን እንቆቅልሽ ሆነ! ስለዚህ በቁርጠኝነት ሙከራችሁን ቀጥሉ፡፡ ወጋችንን ወደ መቋጨቱ ገደማ ስንደርስ ታዲያ መልሱን ሹክ እላችኋለሁ (በምስጢር!)
እስቲ ፖለቲካ በፈገግታችንን ከምድረ አሜሪካ እንጀምረው፡፡ የቤቱ አዛውንት (አያት ነገር ይመስሉኛል) በድንገተኛ የልብ ህመም ራሳቸውን ይስቱና ቤተሰባቸው ተደግናጦ በብርሃን ፍጥነት ሆስፒታል ያደርሷቸዋል፡፡ እዚያም ሲደርሱ ጥብቅ የህክምና ክትትል (IC) የሚሰጥበት ክፍል እንዲገቡ ይደረጋሉ፡፡ (የፖለቲካ IC ቢኖር ጥሩ ነበር!) ከረዥም ሰዓት በኋላ የመረመራቸው ሐኪም ብቅ ይልና፤ “ሽማግሌው አዕምሮው ሞቷል፤ ልቡ ግን ይመታል” በማለት ለትልቁ ልጃቸው ይነግረዋል፡፡ (እንቆቅልሽ አይመስልም?) ልጅም፤ “እንዴ ዶ/ር፤ በቤተሰባችን ውስጥ እኮ አንድም የዲሞክራት ፓርቲ አባል ኖሮ አያውቅም!” አለው - ለዶክተሩ፡፡ (አያችሁልኝ የፈረንጅን ነገር ፍለጋ!) አዕምሮአቸው ሞቶባቸው ልባቸው የሚሰራ ዲሞክራቶች ናቸው ለማለት እኮ ነው፡፡
እስቲ ወደ ዋና አጀንዳችን ደግሞ እንግባ፡፡ እኔ የምላችሁ ግን… ኢቴቪ እዳውን ከፈለ እንዴ? (እዳችንን ማለቴ ነው!) ለምን መሰላችሁ የጠየቅኋችሁ? ኢቴቪ “አይለቀውም… አይለቀውም!” የሚል ነገር አባባሽ ቢያገኝ ኖሮ እኮ… የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዎችን የማስተላለፍ ባለመብት ነኝ ከሚለው ተቋም ጋር ቡጢ መግጠሙ አይቀርም ነበር ብዬ ነው፡፡ ደግነቱ አላገኘም፡፡ በነገራችሁ ላይ ኢቴቪ ክፍያ ሳይፈፅም ጨዋታውን ሲያስተላልፍ “እጅ ከፍንጅ” መያዙን እንደ ትልቅ “ሼም” መቁጠር አለብን እንዴ? (ኢቴቪ እኮ ለህዝብ ጥቅም ብሎ ነው - እንደ ኢህአዴግ!) አንድ የህትመት ሚዲያ ላይ ደግሞ “ኢቴቪ የአገር ገፅታን አበላሸ” የሚል ወቀሳ ተሰንዝሮበት አንብቤአለሁ (So what? ራሱ የገነባውን ገፅታ፤ ራሱ አፈረሰ!) እኔ ግን የቲቪ ስክሪናችን ላይ ከመጣው “ሂሳብ አልተከፈለም” የሚል “አሳጭ ፅሁፍ” ይበልጥ የገረመኝ ራሱ ኢቴቪ በራሱ ሚዲያ የሰጠው በቁጣ የታጀበ “ዘለፋ” ነው (ካፈርኩ አይመልሰኝ ይሏል ይሄ ነው!) እናላችሁ… አንድ ምሽት በ2 ሰዓት ዜና ላይ ኢቴቪ ድንገት ንዴቱን አወረደው፡፡

በጠራራ ፀሃይ ተፈፀመ ላለው “ዝርፊያ” ተመጣጣኝ ምላሽ ሰጠ፡፡ አንዳንዶችም ለጠራራ ፀሃይ “ዝርፊያ” የጠራራ ፀሃይ “ዘለፋ” ሲሉ የኢቴቪን ጀግንነትና ወኔ አደነቁ፡፡ እንደኔ እንደኔ ግን ያልተገባ አድናቆት ነው፡፡ ለነገሩ ያኛውም ወገን (ባለመብቱን ማለቴ ነው) ትንሽ ሳያበዛው የቀረ አይመስለኝም! ስንት ሺ ዩሮ ነበር የጠየቀው? (ግድብ እየገነባን መሆኑን አያውቅም እንዴ?) ካላወቀም ጥፋተኛው ራሱ ኢቴቪ ነው የሚሆነው!!
ቆይ አንድ ነገር ልንገራችሁ፡፡ ኢቴቪ ያንን የውጭ ተቋም “ክፍያ አስወደድክብኝ” በሚል ዘራፍ ያለበት ወዶ አይደለም፤ ለምዶበት ነው (ማነው ልማድ ሲሰለጥን ተፈጥሮ ይሆናል ያለው?) አሃ… የጦቢያን ነጋዴ “ለሆዱ ያደረ”፣ “ስግብግብ” ምናምን እያለ መዝለፍ ለምዶበት እኮ ነው! ይሄውላችሁ ዋጋ (ክፍያ) ተወደደብኝ ያለ ወይም ደግሞ “ስንጥቅ ሊያተርፍብኝ ነው” ብሎ የጠረጠረ ደንበኛ፤ ምን ያደርጋል መሰላችሁ? ብስጭቱን ጓዳው ትቶ ለድርድር ይተጋል (ያለ አመሉ?) እናላችሁ… ኢቴቪ “ነቄ” ቢሆን ኖሮ “ውዱን ክፍያ” አስቀንሶ ያለአንዳች ብስጭትና ዘለፋ ሥራውን ይቀጥል ነበር (Business as usual ብሎ!) ድርድሩም ባይሳካም ደግሞ ችግር የለውም (የዓለም መጨረሻ እኮ አይደለም!) መቼም ዘለፋው የተሰነዘረበት ተቋም፤ ነገሩን ሰምቶት ከሆነ እንዴት ግራ እንደሚጋባ አስቡት፡ (እንቆቅልሽ ነው የሚሆንበት!)
አያችሁ… የአፍሪካን ዋንጫ ጨዋታዎች ለኢቴቪ ለማስተላለፍ ከ1ሺ ፐርሰንት በላይ የዋጋ ጭማሪ አድርጓል የተባለው ተቋም፤ Local (ኢትዮጵያዊ ማለቴ ነው) ቢሆን ኖሮ እኮ ችግር የለውም ነበር፡፡ (ገበና ለገበና እንተዋወቃለና!) ይኸኛው ግን ዓለም አቀፍ ተቋም ነው - Strictly በነፃ ገበያ መርህ የሚመራ!! (ነፃ ገበያና ዕዝ ኢኮኖሚን ማጣቀስ አያውቅም - እንደ ኢህአዴግ!) እናም በዋጋው የተስማማ ከፍሎ አገልግሎት ያገኛል፤ ያልተስማማ ይቀርበታል፡፡ (እጅ ጥምጠዛ እኮ የለም!) አያችሁ… ኢቴቪ እዚህ አገር ነጋዴ “ዋጋ አስወደደ” በሚል ወዶ እስከሚጠላ እንደሚብጠለጠል አሳምሮ ያውቃል! (ምን ማወቅ ብቻ?) እናም በአገር ውስጥ ልማድና ደንብ ዓለም አቀፍ ቢዝነስ ለማካሄድ ዳዳው፡፡ እኔማ “እንኳንም በዚህ አለፈልን!” አልኩኝ፡፡ እንዴ… ኢቴቪ ቢነሳበት ኖሮ እኮ ወዶ እስኪጠላ በማይሰማው ቋንቋ “ያስታጥቀው” ነበር - ያውም በተረትና በምሳሌያዊ አባባል የበለፀገ! “የኒዮሊበራል ቅጥረኛ!”፣ “ፀረ-አፍሪካ!”፣ “የኢምፔሪያሊዝም ግልገል” ወዘተ…ወዘተ ሊለው ይችል ነበር እኮ፡፡ (አንድዬ አተረፈና!) ትንሽ የቆጨኝ ግን ኢቴቪ ተቋሙን “ኪራይ ሰብሳቢ!” ሳይለው መቅረቱ ነው!! ትክክለኛ የኪራይ ሰብሳቢ ምሳሌ እኮ ይሄ ተቋም ነው (መብቱ ቢሆንም!)
እኔ የምላችሁ… ፅሁፌ መግቢያ ላይ ያቀረብኩትን የእንቆቅልሽ ጥያቄ ፈታችሁት? ይሄውላችሁ… በአገራችን ብዛታቸው እንደ ቆጣሪው ከፍና ዝቅ የሚሉት ምን መሰሏችሁ? የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ናቸው!! እንቆቅልሹ ግን የእኔ ፈጠራ እንዳይመስላችሁ! (ኮፒራይቱ የአንድ ቱባ ፖለቲከኛ ነው!) ኢህአዴግ ወደ ሥልጣን ከመጣ ጀምሮ የተለያዩ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በመመስረት በሊ/መንበርነትና በፕሬዚዳንትነት ወደ ሁለት አስርት ዓመታት ገደማ የመሩት (ያውም ምክትላቸው ከነመኖራቸውም ሳይታወቁ) ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ ናቸው ባለቤቱ! በቅርቡ በአገሪቱ ውስጥ ስንት ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዳሉ ሲጠየቁ ምን አሉ መሰላችሁ? “እሱ እንደቆጣሪው ይለያያል!” (የአመቱ ምርጥ የፖለቲካ እንቆቅልሽ!)
“እውነት ግን የተቃዋሚዎች ብዛት ምን ያህል ነው?” ማነው የሚጠየቀው - ኢህአዴግ ነው ምርጫ ቦርድ? ሌላው ቢቀር እኮ መረጃው ለኢቴቪ ጥያቄና መልስ ይሆነናል፡፡ (ድንገት ከተጋበዝን ብዬ እኮ ነው!) ግን ለምንድነው በኢቴቪ የተቃዋሚዎች ጥያቄና መልስ የማይጀመረው? (ኢቴቪ የጋራ ንብረታችን ነው ብዬ እኮ ነው!)
የኢህአዴግ ፅ/ቤት ኃላፊ የተከበሩ አቶ ሬድዋን ሁሴን በቅርቡ የሰጡት መግለጫ ተቃዋሚዎችን ጭስስ እንዳደረጋቸው ታዝባችሁልኛል? 28ቱ ፓርቲዎች ባለፈው ሳምንት በሰጡት ምላሽ ኢህአዴግ ነፍሴን “አግላይ!” ብለውታል (ብርቁ ነው እንዴ ማግለል!) እሱማ ይሄኔ እግሩን ዘርግቶ Mission Accomplished ይላል፡፡ እኔን ደግሞ “ጭስስ” የሚያደርገኝ ምን መሰላችሁ? የኢትዮጵያ ፖለቲካ ማጠንጠኛው “ብሽሽቅ” መሆኑ ነው!
በነገራችሁ ላይ ፕሮፌሰር በየነ ስለተቃዋሚዎች ብዛት የሰጡትን እንቆቅልሻዊ መልስ የሚያጠናክር አባባል 28ቱ ፓርቲዎች በሰጡት መግለጫ ውስጥ አግኝቻለሁ፣ እንዲህ ይላል፡-
“ኢህአዴግ ለራሱ ፖለቲካዊ ጥቅም የሚበጀው ሲሆን 75 የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳሉ ይናገራል” የሚለው መግለጫው፤ ሲያሻው ደግሞ ተቃዋሚዎች ውስጣቸው መፈተሽ አለበት በማለት የምርጫ ቦርድን ሥልጣን ይወስዳል ሲል ኢህአዴግን ይኮንናል፡፡ (አቤት የእንቆቅልሻችን አበዛዝ!)

Read 4660 times