Saturday, 16 February 2013 12:19

ኢትዮጵያውያን በ‹‹ተስፋዊቷ ምድር›› ደቡብ አፍሪካ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(2 votes)

ጣፋጭ እና ጋዜጠኞች
የዋልያዎቹን የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ በቀጥታ በስፍራው ተገኝቶ ለመከታተል እድሉን ያገኘን ጋዜጠኞች ከብሄራዊ ቡድኑ ጋር ወደ ጆሃንስበርግ የበረርነው በአንድ ቦይንግ ነበር፡፡ ደቡብ አፍሪካ የገባነው የ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የመክፈቻ ስነስርዓት በጆሃንስበርግ ሶከር ሲቲ ስታደዬም ሊደረግ በዋዜማው ነበር፡፡ ዋልያዎቹ ኔልስፕሪት ሲቀመጡ ጋዜጠኞች በጆሃንስበርግ መክተማችን ግድ ነበር፡፡ ለነገሩ በጆሃንሰበርግ ኢትዮጵያውን በብዛት መኖራቸው ከብሄራዊ ቡድኑ እንጅ ከአፍሪካ ዋንጫው አጠቃላይ ድባብ እንድንርቅ አላደረገም፡፡ በጆሃንስበርግ የምትገኘው የኢትዮጵያውያን ስደተኞች መናሐርያ የሆነችው ልዩ አካባቢ ለብሄራዊ ቡድኑ ድጋፍ ስትዘጋጅ ቆይታለች፡፡ ከሶስት ዓመት በፊት ደቡብ አፍሪካ ዓለም ዋንጫን ባዘጋጀችበት ወቅት ይህን አካባቢ አውቀዋለሁ፡፡ ያን ጊዜ በዚሁ የከተማዋ ክፍል ይነግዱ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ያልሸቀሉት የዓለም ዋንጫ ነገር አልነበረም፡፡ የዓለም ዋንጫ ተሳታፊ ብሄራዊ ቡድኖች ማልያዎች ፤ የተሳታፊ አገራት ባንዲራዎች፤ የጨዋታ መግቢያ ትኬቶች እና ቩቩዜላዎች በጆበርግ መርካቶ እንደጉድ ተቸብችበዋል ፡፡ ዘንድሮ ገበያውን ሙሉ ለሙሉ ኢትዮጵያዊ ነገር አጥለቅልቆታል ማለት ይቻላል፡፡

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለ31 ዓመታት ርቆ ወደቆየበት አፍሪካ ዋንጫ ሲገባ ንግዱም፤ ስደቱም፤ ወገናዊነቱም የአገር ቤት ጉዳይ ሆነ፡፡ ዋልያዎቹን፤ እኛን የስፖርት ጋዜጠኞች እና ሌሎች ተጓዦችን የያዘው የኢትዮጵያ ቦይንግ ገና ጆሃንስበርግ ከተማ የሚገኘው ኦሊቨር ታምቦ አየር ማረፊያ ሲደርስ ኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች ያደረጉት አቀባበል እጅግ አስገራሚ ነበር፡፡ ኢትዮጵያውያኑ የአየር ማረፊያውን የእንግዳ መቀበያ ተርሚናልን አጣበውት እንኳን ደህና መጣችሁ ብለዋል፡፡ አዛውንት፣ ጐልማሳ፤ ህፃናት፣ ሴቶች በኢትዮጵያ የባንዲራ ቀለማት ተውበው፤ የዋልያዎቹን ባለሸንተረር ደማቅ ማልያ ለብሰው ‹‹ኢትዮጵያ አገራችን›› እያሉ፤ ከዚያም ደግሞ‹‹ እንበላዋለን›› በሚለው የድጋፍ ዜማ አቀባበላቸውን እጅግ አሳምረውታል፡፡ ጆሃንስበርግን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሜዳ አስመስለዋት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ የጆበርግ መርካቶ በኢትዮጵያ የሰንደቅ አለማ ቀለማት ዙሪያ ገባዋን አሸብርቃለች፡፡ እንኳንስ ኢትዮጵያውያኑ የመኪናዎቻቸው ኮፈን፤ ህንፃዎቻቸው ባንዲራ ለብሰዋል፡፡ በኢትዮጵያውያን ባለቤትነት የተያዙ ህንፃዎች ላይ የብሄራዊ ቡድኑን አባላት ፎቶዎችን የያዙ ግዙፍ ፖስተሮች ተሰቅለዋል፡፡

በየህንፃዎቹ ደጃፍ በሚገኙ ትናንሽ ‹ስታንድ› የሚሏቸው ሱቆች እና የአንዳንድ የኢትዮጵያውን መደብሮች መግቢያዎች አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ቀለም በየፋሽን አይነቱ ለሽያጭ ቀርቦ ይታይ ነበር፡፡ የጆበርግ መርካቶ መውጫ መግቢያው በጃሉድ ‹‹የርግብ አሞራ›› እና በቴዎድሮስ ባጫ “ምንግዜም ዋልያ” ዘፈኖች እንደታጀበ ድምቅምቅ ብሏል፡፡
በደቡብ አፍሪካ ኤምባሲ ለ30 ቀናት ቆይታ የተሰጠንን ቪዛ ይዘናል፡፡ በአፍሪካ ፉትቦል ኮንፌደሬሽን የተሰጠን አክሪዲቴሽን መታወቂያ እዚያው በጆሃንስበርግ አገኘን፡፡ ከዚያ ለ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ወደ ታላቁ ሶከር ሲቲ ስታድዬም የገባነው ሰተት ብለን ነበር፡፡ የመክፈቻውን ዝግጅት እና የኬፕ ቨርዴ እና የደቡብ አፍሪካ ጨዋታን በሶከር ሲቲ ስታድዬም አንድ ላይ ሆነን ታድመናል፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ ሁለቱን የምድብ ጨዋታዎች ያደረገበት የሞምቤላ ስታድዬም ከጆሃንስበርግ 420 ኪሎሜትር ርቃ የምትገኝ ኔልስፑሪት የተባለች ግዛት የሚገኝ ነው፡፡ በጆሃንስበርግ ያረፍነው ጋዜጠኞች ሁለት የደርሶ መልስ ጉዞዎችን በአውቶብስወደ ኔልስፕሪት በማድረግ ዋልያዎቹ ከዛምቢያ እና ከቡርኪናፋሶ ጋር በሞምቤላ ስታድዬም ያደረጋቸውን ጨዋታዎች ተከታትለናል፡፡ ኢትዮጵያና ናይጄርያ ያደረጉትን የምድብ 3 ጨዋታ ደግሞ ከጆሃንስበርግ 120 ኪሎሜትሮች ርቃ ወደ የምትገኘው ሩስተንበርግ ተጉዘን አይተናል፡፡ ብዙዎቻችን የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች በጆሃንስበርግ የ12 ቀናት ቆይታ አድርገናል፡፡ ሁሉንም የኢትዮጵያ የምድብ ጨዋታዎች የተከታተልነው በየስታድዬሞቹ በሚገኘው የሚዲያ ልዩ ትሪቢውን በመቀመጥ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ እንደባለሙያ በአንድ ትልቅ አህጉራዊ ውድድር ልንቀስም የሚገባውን ልምድ በስፋት እንድናገኝ አስችሎናል፡፡
የዋልያዎቹን ሶስት ጨዋታዎች ለመመልከት ወደ ኔልስፕሪት እና ሩስተንበርግ ከተጓዝንባቸው ቀናቶች ውጭ በሌሎቹ ግዚያት ውሎ መግቢያችን ጆበርግ መርካቶ ነበር፡፡ የስፖርት ጋዜጠኞች በአስጨናቂዋ የጆሃንስበርግ ከተማ ለነበረን ቆይታ መመቸት ደግሞ አንዲት ኢትዮጵያዊትና መላው ቤተሰቧ ከፍተኛ ሚና ነበራቸው፡፡ የመኝታ፤ የምግብና የትራንስፖርት አገልግሎት በተመጣጣኝ ዋጋ በመስጠት ከፍተኛውን ትብብር ያደረገችልን ይህች ምስጉን ሴት ጣፋጭ ትባላለች፡፡ ጋዜጠኞች በጣፋጭ እና በመላው ቤተሰቧ በሚንቀሳቀሰው ቅዱስ ገብሬል ገስት ሃውስ ከሞላ ጎደል ምቹ ቆይታ ነበራቸው፡፡ መላው የጣፋጭ ቤተሰብ በኢትዮጵያዊ የእንግዳ ተቀባይነት ባህል ተንከባክቦናል፡፡ በጆሃንስበርግ የሚገኘው ቅዱስ ገብሬል ገስት ሃውስ ያገኘነው አገልግሎት፤ ወገናዊ ድጋፍ እና ትብብር የኢትዮጵያ ጨዋታዎችን ለመመልከት ወደ ኔልስፕሪት እና ሩስተንበርግ ያደረግናቸውን አድካሚ ጉዞዎች ያካካሰ ነበር፡፡
በነገራችን ላይ ጣፋጭ የጆበርግ መርካቶ አውራ ሴት ናት፡፡ ብዙ ስደተኞችን በማቋቋም ባለውለተኛ ይሏታል፡፡ ኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች ደቡብ አፍሪካ ገብተው እንዲሳካላቸው፤ ስራ እንዲጀምሩ እና ኑሮውን እንዲላመዱ በማድረጓ በአድናቆት እና በፍቅር ጆሃንስበርግ ውስጥ ስሟ የሚነሳላት ጠንካራ ሴት ናት፡፡ ጣፋጭ በጆበርግ መርካቶ ፎቆች አሏት፡፡ በጣም የሚታወቀው በጆበርግ መርካቶ የሚገኘው አቢሲኒያ ህንፃ ነው፡፡
አንድነታቸው የሚያምርባቸው 12ኛዎቹ ተጨዋቾች
በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩትና የሚሰሩት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ለዋልያዎቹ እንደ 12ኛ ተጨዋቾች ይቆጠራሉ ያለው አዳነ ግርማ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ እና ዛምቢያ በምድብ 3 የመክፈቻ ጨዋታ አንድ እኩል ከተለያዩ በኋላ በወቅቱ የቡድኑ አምበል ሆኖ መግለጫ በሰጠበት ወቅት ነው፡፡
ዋልያዎቹ የምድብ 3 ግጥሚያዎችን በኔልስፕሩዊት እና በሩስተንበርግ ከተሞች በሚገኙት ስታድዬሞች ያደረጉባቸው ቀናትን ስደተኞቹ ኢትዮጵያውያን እንደ ብሄራዊ በዓላቸው አድርገውታል፡፡ የኢትዮዽያን ሰንደቅ አላማ ለብሰው፤ የባንዲራው ቀለማትን በተለያዩ የቲሸርት፤ የኮፍያ፤ የካባ ፋሽኖች አሰርተው፤ የሰውነት ክፍሎቻቸውን በአረንጓዴ ቢጫ ቀይ ቀለሞች አዥጎርጉረው የቡድኑን ጨዋታዎች በማራኪ ድጋፋቸው አድምቀውታል፡፡ በ50 ሺዎች የሚቆጠሩ እነዚህ ደጋፊዎች ለ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ከፍተኛ ድምቀት ማላበሳቸው በተለያዩ የአህጉሪቱ እና አለም አቀፍ ሚዲያዎች ተወስቶላቸዋል፡፡
ኢትዮጵያውያኑ በደቡብ አፍሪካ በኢኮኖሚ ስደት፤ በትምህርት እና በስራ በተለያዩ ግዛቶች የከተሙ ናቸው፡፡ እነዚህ ኢትዮጵያውያን በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ሰሞን በፍፁም የአገር ፍቅር መንፈስ እና አንድነት በነቂስ ወጥተው ለቡድናቸው ከፍተኛ ድጋፍ አድርገዋል፡፡

በሶስቱ የደቡብ አፍሪካ ከተሞች ጆሃንስበርግ ፤ ኔልስፕሪት እና ሩስተንበርግ በየስቴድዮሞቹ ደጃፍ እና ውስጥ አግኝቼ ሳነጋግራቸው ብሄራዊ ቡድኑ ኢትዮጵያዊነታቸውን አድሶታል ብለዋል፡፡ አንዳንዶቹ እንደውም የአፍሪካ ዋንጫው ላይ ኢትዮጵያ በመሳተፏ በብዙ ደቡብ አፍሪካውያን እንደ ፓኪስታናዊያን ወይም እንደ የሌላ አገር ዜጋ የምንታይበትን ገፅታ ያስተካከለ ብለውታል፡፡ በደቡብ አፍሪካ በሚኖሩ ስደተኛ ኢትዮጵያውያውያን ከጅምሩ ቀዝቀዝ ብሎ ይታይ የነበረው 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ እንዲደምቅ ማነሳሳታቸው ከፍተኛ የሚዲያ ትኩረት ያገኘ ነበር፡፡ “ሉክሎካል” የተባለ የኔልስፕሪት ከተማ ጋዜጣ ለኢትዮጵያ ጨዋታ በከተማው የተገኙ ደጋፊዎችን በማድነቅ የሰራው አንድ ዘገባ ለዚህ ምሳሌ ይሆናል፡፡ ርእሱን ‹ኢትዮጵያውያን ከተማዋን በቀይ አደመቋት› ብሎ ሰፊ ዘገባ ያቀረበው ጋዜጣው ኢትዮጵያውያኑ ቡድናቸውን ለመደገፍ ወደ ኔልስፕሪት ከተማ ከተለያዩ የደቡብ አፍሪካ ግዛቶች የመጡበት ብዛት ያስደንቃል ብሎ ከናይጄርያ ከዛምቢያ ደጋፊዎች በከፍተኛ ደረጃ የላቀ ድጋፍ እና ድባብ መፍጠራቸውን አትቷል፡፡ የኢትዮጵያ ቡድን ከባለሜዳው የደቡብ አፍሪካ ቡድን በእጅጉ የተሻለ ጨዋታ ማሳየቱን፤ የኢትዮጵያ ደጋፊዎች የሞምቤላ ስታድዬምን በአረንጓዴ ቢጫ እና ቀይ ቀለማት ከማድመቃቸውም በላይ በማራኪ ድጋፋቸው ማሳመራቸውን ሁሉ አውስቷል፡፡ ኢትዮጵያ ከዛምቢያ እና ከቡርኪናፋሶ ጋር ስትጫወት በኔልስፕሪት የተገኙ በርካታ ኢትዮጵያውያን ከተማዋን አጥለቅልቀዋታል፡፡ ወደ ሞምቤላ ስታድዬም በብዛት ገብተዋል፡፡ ይህ ሁኔታም አፍሪካ ዋንጫውን ካዘጋጁ የደቡብ አፍሪካ ከተሞች ኔልስፕሪት በብዙ የትኬት ሽያጭ እንድትመራ አድርጓታል፡፡
የዋልያዎቹ ደጋፊዎች ቡድናቸውን ሙሉ 90 ደቂቃ በመደገፋቸው ይለያሉ፡፡ የተቀናቃኝ ቡድን ደጋፊዎችን በሚያስገርም ስፖርታዊ ጨዋነት ሲያበሽቁም ያስደስታሉ፡፡
በኔልስፕሪቱ ሞምቤላ ስታድዬም ከኢትዮጵያ እና ቡርኪናፋሶ ጨዋታ በፊት በድምፅ ማጉያ የጃሉድ ‹‹የርግብ አሞራ›› የተለቀቀላቸው የሚያምሩ ደጋፊዎች ነበሩ፡፡ ከስታድዬም ውጭ ደግሞ በለበሱት አረንጓዴ ቢጫ ቀይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ማልያ ፤ በባንዲራቸው ቀለማት ባጌጡ መኪኖቻቸው በክላክስ እና በቩቩዜላ ጥሩንባቸው የሚያምር ድባብ ለ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ፈጥረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በምድብ 3 የመጨረሻዋን ጨዋታ ከውድድሩ ሻምፒዮን ናይጄርያ ጋር ባደረገችበት ሩስተንበርግ ተመሳሳይ ሁኔታ ነበር የተስተዋለው፡፡ በሩስተንበርግ በሚገኘው የሮያል ባፎኬንግ ስታድዬም የተደረገውን ጨዋታ ለመታደም ከጆሃንስበርግ በመነሳት በተደረገው ጉዞ ላይም አስደናቂ ድጋፍ አሰጣጥ አሳይተዋል፡፡

ከጆበርግ ወደ ሩስተንበርግ በሚወስዱ አውራ ጎዳናዎች የኢትዮጵያ ስም እና ቀለም በማይረሳ ሁኔታ ደምቆ ነበር፡፡ እንደኢትዮጵያውያን ሁሉ በርካታ የናይጄርያ ዜጎች በስደት በደቡብ አፍሪካ ነዋሪ ናቸው፡፡ ታድያ ከጆሃንስበርግ እስከ ሩስተንበርግ በተደረገ ጉዞ በየአውራ ጎዳናው የኢትዮጵያ እና የናይጄርያ ደጋፊዎች ባንዲራ በለበሱ መኪናቸው እየተበሻሸቁ እና ቡድኖቻቸውን በጭፈራ እያወደሱ ሲተሙ ማየት ለበርካታ ደቡብ አፍሪካውያን የሚያስደንቅ ትእይንት ነበር፡፡

በተስፋ የተሞላው የዋልያዎቹ ስንብት
ዋልያዎቹ የምድብ 3 ግጥሚያዎችን ጨርሰው በመጀመርያው ዙር ከውድድሩ ከተሰናበቱ በኋላም በመጨረሻም ጆሃንስበርግ ከተማ በሚገኘው ዘመናዊው የሳንድተን ማእከል በሚገኝ ሆቴል በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ እና ኮሚኒቲ በተዘጋጀ የሽኝት ግብዣ ተደርጓል፡፡ በስነስርዓቱ ለዋልያዎቹ በቀረበ አድናቆት የእናንተ ተሳትፎ የአፍሪካ ዋንጫ ያለ ኢትዮጵያ እንዳማይደምቅ ተረጋግጧል ተብሏል፡፡ በዚሁ የሽኝት ግብዣ ላይ ለጨረታ የቀረበው የአዳነ ግርማ 19 ቁጥር ማልያ በ97 ሺ ራንድ 200ሺ ብር አካባቢ ነው የተሸጠው፡፡ የአምበሉ ደጉ ደበበ ማልያ ደግሞ በ42ሺ ራንድ 65ሺ ብር አካባቢ አውጥቷል፡፡ የ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ኳስ በ42ሺ ራንድ 90ሺ ብር አካባቢ ተጫርቶ ተወስዷል፡ በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያውን በዋልያዎቹ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ መርካታቸው በዚሁ የሽኝት ግብዣ ላይ ለተጨዋቾቹ ሲሰጡት በነበረው አድናቆት የተገለፀ ነበር፡፡

በምድብ 3 መክፈቻ ጨዋታ ላይ ኢትዮጵያ እና ዛምቢያ ባደረጉት ጨዋታ ደጋፊዎች ቩቩዜላ እና ሌሎች ቁሳቁሶችን ወደ ሜዳ በመወርወራቸው ካፍ የጣለውን የ10ሺ ዶላር ቅጣትም አቶ አድማሱ አርፊጮ የተባሉ በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊ እጅ በእጅ በመክፈል ድጋፋቸውን ገልፀዋል፡፡ በነገራችን ላይ ኢትዮጵያውያኑ ደጋፊዎች በዛምቢያ ጨዋታ ስታድዬም በመረበሽ ለሰሩት ጥፋት በሮያል ባፎኬንግ ስታድዬም ይቅርታ የጠየቁበትን ባነር ይዘው በመግባት በስፖርታዊ ጨዋነት ስህተታቸውን አርመውታል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በቀጣይ በሚኖሩት የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ውጤታማ ሆኖ ብራዚል ወደ የምታስተናግደው 20ኛው የዓለም ዋንጫ በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ ለተሳትፎ እንዲበቃ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡ በዚህ ተስፋቸው ግንባር ቀደም የሆኑት ደግሞ በአፍሪካ ዋንጫው ለብሄራዊ ቡድኑ እንደአስራሁለተኛ ተጨዋች በመሆን የማይረሳ ድባብ እና ድጋፍ የፈጠሩት በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ የኢትዮጵያ ስደተኞች ናቸው፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ ከ31 ዓመት በኋላ በአፍሪካ ዋንጫ ሲሳተፍ ከምድቡ በጊዜ በሲሰናበትም የነበረው አጠቃላይ ተሞክሮ ስኬታማ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በአጠቃላይ የዋልያዎቹ የ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ቡድኑ ያልነበረውን ልምድ የቀሰመበት፣ ያለበትን የእግር ኳስ ደረጃ የለካበት፣ ስለ ኢትዮጵያ እግር ኳስ ለዓለም ያሳወቀበት ነበር፡፡ ይህም በተለያዩ አህጉራዊ እና አለምአቀፋዊ ሚዲያዎች እንደተገለፀው ለመጭው ጊዜ ከፍተኛ ተስፋ የሚያሳድር ሆኗል፡፡

የጆበርግ መርካቶ እና ገፅታው
በጆሃንስበርግ እምብርት ወይም በዚያው አጠራር ‹ኢነር ሲቲ› ወይም ‹ሴንተራል ቢዝነስ ዲስትሪክት› ተብሎ የሚታወቀው አካባቢ አሁን ስሙ እየተቀየረ ነው፡፡ ይህን የከተማው ክፍል አንዳንዶች ትንሿ አዲስ አበባ ወይም ትንሿ ኢትዮጵያ ይሉታል፡፡ በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች መናሐርያ የሆነው ይህ ሰፈር በዋናነት ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ የሚደረግበት በመሆኑ፤ የንግድ ሁኔታው፤ የመነገጃው ሱቆች እና መደብሮች አሰራር እና በዙርያው ያለው ግርግር ደግሞ የጆበርግ መርካቶ ብሎ አካባቢውን ለመጥራት ያስገድዳል፡፡
በጄፒ ጎዳና የሚገኘው ይህ አካባቢ ታውን ብለው የሚጠሩትም አሉ፡፡ በአፓርታይድ ዘመን በዚህ የጆሃንስበርግ ከተማ ክፍል የነበሩ ነዋሪዎች ነጭ የአገሪቱ ዜጐች ብቻ ነበሩ፡፡ ጥቁሮች በዚህ አካባቢ ለመስራት እና የህክምና አገልግሎት ለማግኘት ብቻ ይመጡበታል፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያውያን ባለቤት የተያዙት የአካባቢው ህንፃዎች ድሮ ‹ሜዲካል አርት ቢውልዲንግስ› ተብለው ይጠሩ ነበር፡፡ በዶክተሮች፤ በጤና ባለሙያዎች እና በፋርማሲስቶች የተያዙ ነበሩ፡፡ ከአፓርታይድ መገርሰስ በኋላ ግን አካባቢው እያረጀ ሄደ፡፡

በተለይ የዓለማችን ቁጥር 1 የወንጀል ሰፈር የሚባለው ሂልብሮው የተባለ ሰፈር አሁን ኢትዮጵያውያን ከከተሙበት የጄፔ ጎዳና ጋር ተጎራብቶ በእግር ለመንቀሳቀስ የማይታሰብበት አካባቢ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ባለፉት 10 ዓመታት ግን ኢትዮጵያውያን በአካባቢው የነበሩ ህንፃዎችን በማደስ፤ ለገበያ ምቹ እንዲሆኑ በማድረግ መስራት ጀመሩ፡፡ ይበልጥ ደግሞ ከዓለም ዋንጫ በፊት ባሉት ሁለትና ሶስት ዓመታት ከዚያ ወዲህ አካባቢው ቅልጥ ያለ የከተማ ውስጥ የገበያ ሰፈር እየሆነ መጥቷል፡፡ በደቡብ አፍሪካ የአገሪቱ ሰራተኛ ዜጎች ገቢ በየጊዜው እየመጠቀ መሄዱ ለኢትዮጵያውያንና ለሌሎች አገራት ስደተኞች የንግድ ስራዎች ሰፊ እድሎችን በመፍጠር ቀጥሏል፡፡
ከጆበርግ መርካቶ ተነስተው ኢትዮጵያውያኑ እና የሌሎች አገራት ስደተኞች የተለያዩ ምርቶችን በደቡብ አፍሪካ የተለያዩ ግዛቶች ወደየሚገኙ የመኖርያ ሰፈሮች፤ የገጠር መንደሮች የህዝብ መናሐርያ ስፍራዎች በማዞር ንግዳቸውን ያጧጡፋሉ፡፡ ብዙዎቹ የገበያው እቃዎች በቻይና እና ህንድ የጅምላ ነጋዴዎች በመርከብ በኮንተኔሮች ተጭነው ደቡብ አፍሪካ ይገባሉ፡፡
ኢትዮጵያውያኑ እና የሌላ አገር ስደተኞች ከኤስያውያኑ እነዚህን የገበያ ምርቶች በጅምላ እና በችርቻሮ በመግዛት በየመጋዘኖቻቸው ያከማቻሉ፡፡ በየሱቆቻቸው እና ወደ ደንበኛ ነጋዴዎቻቸው በማከፋፈልም ገበያውን ያጥለቀልቃሉ፡፡
በመላው አገሪቱ ያሰራጫሉ፡፡ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ውልዋርስ እና ኤድጋርስ የተባሉ የደቡብ አፍሪካ እውቅ የገበያ ማእከሎችን በመጎብኘት በዚያ ያዩዋቸውን የወቅቱ ፋሽን ምርቶች ናሙና በመውሰድ ወደ ቻይና በመጓዝ እና ግንኙነት በመፍጠር አስመጥተው ወቅታቸው ቢያልፍ እንኳን ሶስት እና አራት እጥፍ ዋጋቸውን አርክሰው ለገበያ በማቅረብ ስኬታማና ተወዳጅ ነጋዴዎች ሆነዋል፡፡ በጆበርግ መርካቶ የሚሰሩ ነጋዴዎች ዋና የሽያጭ አቅርቦታቸው በአልባሳት፤ በጫማ እና በጨርቃጨርቅ ምርቶች ላይ ቢያተኩርም የተለያዩ የኮስሞቲክስ እቃዎች፤ ቦርሳ ሻንጣ ቀበቶ ፤ የቤት ውስጥ እቃዎች እና መገልገያዎችንም የሚነግዱ አሉ፡፡ በጆበርግ መርካቶ ህንፃዎች ውስጥ የሚሰሩትን በርካታ ምግብ ቤቶች በማስተዳደርም የተሳካላቸው አሉ፡፡ ከምግብ ቤቶቹ አንደኛው በርሱ ፍቃድ ምግብ ቤት ይባላል፡፡ በርካታ ሰዎችን በሚያስተናግደው በዚህ ምግብ ቤት ከቁርጥ ጥሬ ስጋ፤ ፍም ጥብስ፤ ክትፎ፤ በያይነቱ እና ሌሎች ኢትዮጵያዊ ምግቦችን ማግኘት ይቻላል፡፡ አንድ ስኒ ቡና 6 ራንድ ‹እስከ 12 ብር› በተሟላ የቡና አፈላል ስርዓት አፍልተው የሚሸጡ በየምግቤቶቹ ደጃፍ እና በአንዳንዶቹ ሱቆች አቅራቢያ ይገኛሉ፡፡
በጆበርግ መርካቶ ብዙ ግርግር አለ፡፡ ብዙ ነጮች እና የሌላ አገር ዜጎች በጎዳናው ብዙ አይታዩም፡፡ ኢትዮጵያውያን፤ ናይጄርያውያን፤ ደቡብ አፍሪካውያን፤ ዚምባቡዌያውያንና የሌሎች አገር ዜጎች ውለው የሚገቡበት አካባቢ ሆኗል፡፡ የመኪናው ግርግር አያድርስ ነው፡፡ በተለይ የታክሲዎች ሩጫ እና እሽቅድምድም ያስመርረራል፡፡ የጆበርግ ታክሲዎች ወያላዎች ስለማያሰሩ ተሳፋሪዎችን የሚጣሩት ለጆሮ በሚሰቀጥጠጡ ክላክሶች መሆኑ ግርግሩን አስጨናቂ ያደርገዋል፡፡ የጆበርግ መርካቶ በደቡብ አፍሪካ ላሉ የኢትዮጵያውያን ስደተኞች ማእከላዊ መናሐርያ ነው፡፡
በመላው የደቡብ አፍሪካ ግዛቶች የሚገኙ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን መገናኛቸው እዚያው ነው፡፡ ቡና ይጠጣሉ፤ ዘመድ አዝማድ ይጠያየቃሉ፤ የአበሻ ምግቦችን ይመገባሉ፤ ባህል ወጉን ይጋራሉ፡፡ የተለያዩ የንግድ መረጃዎችን ይለዋወጣሉ፡፡ የጅምላ እና የችርቻሮ ንግዳቸውን ከሽርኮቻቸው ጋር ያቀላጥፋሉ፡፡ በተለያዩ ቦታዎች በሚገኙ የኢንተርኔት ካፌዎች ከቤተሰቦቻቸው ጋር በሶሻል ሚዲያ ድረገፆች ግንኙነት ያደርጋሉ፡፡ በገበያው በሚገኙ አንዳንድ ሱቆች እንደቡና፤ በርበሬ፤ ቅመማቅመሞችን ስለሚሸጡ አስቤዛዎቻቸውን ይሸምታሉ፡፡

ፀጉር ቤቶቹ የወንድም የሴትም ሞልተዋል፡፡
በጆበርግ መርካቶ በኢትዮጵያውያን አማካኝነት ለደቡብ አፍሪካውያን ብቻ ሳይሆንነ ለሌሎች አገራት ስደተኞችም ኑሮን የሚያሻሽሉበት እድል ተፈጥሯል፡፡ ኢትዮጵያውያኑ በሽያጭ፤ በፅዳት፤ በጥበቃ፤ በቤት ሰራተኝነት እና በሞግዚትነት ስራዎች ለደቡብ አፍሪካ፤ ለዛምቢያ እና ዚምባቡዌ፤ ለማላዊ እና ለናይጄርያ ለተለያዩ አገራት ዜጎች ሰፊ የስራ እድል ፈጥረዋል፡፡ በገበያው ውስጥ ከኢትዮጵያውያን ሌላ በሌሎች አገር ዜጎች የተያዙ ስራዎች ጥቂት ናቸው፡፡ አንዳንድ ናይጄርያውያን በጎዳናው የሚሰሩት የችርቻሮ ንግድ አለ፡፡ ደቡብ አፍሪካውያኑም በጄፔ ስትሪት የጎዳና ላይ ፀጉር ቤት አቁመዋል፡፡ አንዳንድ የኢንተርኔት ካፌዎችን በማስተዳደር ደግሞ የደቡብ አፍሪካ እና የዚምባቡዌ ዜጎችም ይንቀሳቀሳሉ፡፡ በተለይ ሊጠቀስ የሚችለው በየህንፃዎቹ በደረጃዎች አካባቢ ያሉ የህዝብ ሽንት ቤቶችን ለአንድ ሰው በ2 ራንድ ወይም በአራት ብር እያከራዩ አገልግሎት የሚሰጡት ደቡብ አፍሪካውያን ናቸው፡፡
ገና ማለዳ በግርግር ተከፍቶ እስከቀትር የሚቆየው የጆበርግ መርካቶ በሚያስገርም ሁኔታ ከ10 ሰዓት በኋላ በፍጥነት ጋብ ማለት ይጀምራል፡፡ በየጎዳናው ‹ስታንድ› በሚባሉ እንደአርከበ ሱቅ አይነት ትናንንሽ መነገጃዎች እና በህንፃዎቹ ውስጥ ያሉት መደብሮች እስከአመሻሹ አይነግዱም፡፡ ከ10 ሰዓት በኋላ ለችርቻሮ የተሰቀሉ ነገሮች በፍጥነት እየወረዱ በየሻንጣው ይታጨቃሉ ፡፡ በየህንፃው ያሉ የጅምላ እና የችርቻሮ መደብሮችም በጥድፊያ ይጠረቃቀማሉ፡፡ ወደ ህንፃዎቹ የሚያስገቡ ዋና መግቢያዎች ላይ የጥበቃ ሰራተኞች መታየት ይጀምራሉ፡፡ ብዙዎቹ ሱቆች በፍርግርግ ብረት በትላልቅ ጓጉንቸር ቁልፎች ይከረቻቸማሉ፡፡ ይሄው በ10 ሰዓት ገበያውን የመበተን እና የመዝጋት ልምድ ከዘራፊዎች ለመትረፍ በነበረ ስጋት ተጀምሮ አሁን መደበኛ አሰራር ሆኗል፡፡ኢትዮጵያውያኑ በሺዎች በከተሙበት የጆበርግ መርካቶ በኢትዮጵያውያኑ ነጋዴዎች ባለቤትነት በተያዙ ህንፃዎች መከበብ ጀምሯል፡፡ ህንፃዎቹ እንደአመችነታቸው ለተለያዩ ባለሱቆች ተከራይተዋል፡፡

ለምግብ ቤት፤ለቢሮ፤ ለፀጉር ቤት፤ለኢንተርኔት ካፌ ለከረንቦላ እና ለጫት መሸጫና መቃሚያም ተሸንሽነዋል፡፡ አንዳንዶቹ በምድር ቤቶቻቸው መጋዘኖች፤ ሌሎች ደግሞ የመኪና ማቆሚያ ፓርኪንግ ያላቸው ናቸው፡፡ በጄፔ ጎዳና ድሮ የህክምና ማእከል የነበረ አንድ ባለ11 ፎቅ ህንፃ ካለፉት 5 ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያዊያን ንብረታቸው አድርገውት ማጀስቲ ህንፃ ተብሏል፡፡ ሌሎች ህንፃዎችም አሉ፡፡ አቢሲኒያ የታዋቂዋ ኢትዮጵያዊት የቆየች ስደተኛ ጣፋጭ ባለቤትነት የተያዘ ህንፃ ነው፡፡ ጆበርግሞል የተባለም አለ፡፡ ከ10 ዓመት ቀደም ብሎ ወደ ደቡብ አፍሪካ በገቡ ሁለት ኢትዮጵያውያን በሽርክና የያዙት ናዲባስ ህንፃም በዚያው በጆበርግ መርካቶ ይገኛል፡፡ የህንፃው ሙሉ ስም ናዲባስ ሆልሴል ማርኬት የሚል ነው፡፡ ታዴ እና ጌታቸው ይባላሉ፡፡ በአንዱ ቢሯቸው ገብቼ አጭር ቆይታ አድርጊያለው፡፡ ቢሮው ውስጥ አንድ ጊዜ ማንዴላ ሌላ ጊዜ ዙማ የሚፈራረቁበት በፍሬም የተቀመጠ ፎቶን እየተመለከትኩ ነበር፡፡ ስደት እውቀት መሆኑንና ብዙ ኢትዮጵያውያን ወደ ደቡብ አፍሪካ መጥተው ኑሯቸውን ለማሸነፍ በሚያደርጉት ጥረት በስራ ፈጣሪነታቸው እንደተሳካላቸው የነገረኝ ጌታቸው ስለህንፃቸው ስያሜም አጫውቶኛል፡፡
ሁለቱ ኢትዮጵያውያኖችን በሽርክና ለያዙት ህንፃቸው በመጀመርያ የሰጡት ስያሜ ማዲባ የሚል ነበር፡፡ የደቡብ አፍሪካውን የነፃነት ተጋይ ኔልሰን ማንዴላ በዙሉ የሚጠሩበትን ስማቸውን መታሰቢያ ማድረጋቸው ነው፡፡ የከተማው አስተዳደር ግን ይህን አሰያየማቸውን ልትነግዱበት ነው ብሎ ከለከላቸውና ‹ኤም›ን በ‹ኤን› ቀይረው ህንፃው ናዲባስ ብሎ ለመጥራት ተገድደዋል፡፡ ታዴ እና ጌታቸው በደቡብ አፍሪካ ቤተሰብ መስርተውና ልጆች ወልደው በተረጋጋ መንፈስ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ ሁለቱም ኢትዮጵያውያንና ደቡብ አፍሪካውያን ወንድማማች ህዝቦች ናቸው ብለው ያምናሉ፡፡ ይህን አስተሳሰባቸው በማንፀባረቅም በመልካም ሁኔታዎች እየሰሩ ናቸው፡፡ ለአገራቸው ኢትዮጵያ ብዙ መልካም ነገሮች ያስባሉ፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው በሰፊ የኢንቨስትመንት ስራ ለመንቀሳቀስ እቅድም አላቸው፡፡

ቤተሰብ አኗኗር እና አዲሱ ትውልድ
በደቡብ አፍሪካ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ከ75 በመቶ በላይ የሚሆኑት ወንዶች ናቸው፡፡ ብዙ ኢትዮጵያዊ ሴቶችን ማግኘት ያስቸግራል፡፡ ዋናው ምክንያት ደቡብ አፍሪካ ለመግባት የሚደረጉ ጉዞዎች ብዙዎቹ ሁኔታዎች ለሴቶች አስቸጋሪ በመሆናቸው ነው፡፡ ይህ ሁኔታ በደቡብ አፍሪካ ላሉ ወንድ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ብዙም አልተመችም፡፡ ትዳር ለመመስረት እና የፍቅር ጓደኛ ለማግኘት የሚከብድ ሆኗል፡፡
አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ደግሞ በኢትዮጵያ ሴቶች መጥፋት ብዙም የተቸገሩ አይመስሉም፡፡ ከደቡብ አፍሪካ ከለር ወይም ክልሶች ጋር ግንኙነት እየፈጠሩ ናቸው፡፡ ትዳር የመሰረቱ እና የተዋለዱ ብዙ ናቸው፡፡ እዚያው ጆሃንስበርግ ውስጥ በሰማሁት ወሬ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደርባን በሚባለው የደቡብ አፍሪካ ግዛት በርካታ ኢትዮጵያውያን ከህንዳዊያን ጋር ተዋልደው መኖር ጀምረዋል፡፡ በሩስተንበርግ ከተማ ያገኘኋቸው ኢትዮጵያውያን ስደተኞችም ነበሩ፡፡ አንዱ ጎልማሳ ኢትዮጵያ ከናይጄርያ ጋር የምታደርገውን ጨዋታ ለማየት ወደ ሮያል ባፎኬንግ ስታድዬም በእግር እየተጓዝን ስለህይወቱ በጥቂቱ አውግቶኛል፡፡
ጨዋታውን ለመመልከት ወደ ስታድዬሙ ሲሄድ ከአንዲት ደቡብ አፍሪካዊ የወላደቸውን ሁለት ታዳጊዎች ይዞ ነበረ፡፡ጎልማሳው እነዚህ ልጆቼ ሲያድጉ አንድም በደቡብ አፍሪካ የፖለቲካ ሰዎች ይሆናሉ ካልሆነ ደግሞ ወደ አባታቸው አገር ኢትዮጰያ ተመልሰው ኢንቨስተር መሆናቸው አይቀርም ብሏል ፡፡ለዓለም ዋንጫ ወደ ደቡብ አፍሪካ በተጓዝኩበት ወቅት ያላስተዋልኩት አዲስ ገጠመኝ ግን ነበር፡፡ ከ3 ዓመት በፊት ብዙዎቹ በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ስደተኞች ትዳር መስርተው ልጅ የማፍራቱን ነገር አይደፍሩትም ነበር፡፡
ዘንድሮ ግን ሁሉ ነገር ተለውጧል፡፡ ብዙዎቹ ወጣት ኢትዮጵያውያን ቤተሰብ መስርተዋል፡፡ ልጆች ወልደዋል፡፡ በእድሜያቸው ከ3 ወር እስከ 4 ዓመት የሚሆናቸው ህፃናት በዝተዋል፡፡ ወላጆቻቸው ልጆቻቸውን በጥሩ ትምህርት ቤት አስተምረው የማሳደግ እቅድ ይዘዋል፡፡ የእናት አገራቸውን ቋንቋ እንዲማሩም ያስባሉ፡፡ ወደ አገራቸው ተመልሰው እንዲሰሩ እና ወገኖቻቸውን እንዲጠቅሙም ይመኙላቸዋል፡፡
ኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች በደቡብ አፍሪካ ከጆሃንስበርግ ሌላ፤ በደርባን፤ በኬፕታውን፤ በሩስተንበርግ ይሰራሉ፤ ይኖራሉ፡፡ ደቡብ አፍሪካውያን ከሌሎች አገራት ስደተኞች ይልቅ ለኢትዮጵያውያኑ አድናቆትና ክብር ይሰጣሉ፡፡ ኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች ሃይማኖተኞች፤ እንግዳ ተቀባይ እና አክባሪዎች እንዲሁም ትጉህ ሰራተኞች መሆናቸውን በመግለፅ ያመሰግኗቸዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያውያን በንግድ ስራዎቻቸው ለደቡብ አፍሪካውያኑ የገቢ አቅም የተመቸ ገበያ በመፍጠር መለኛ መሆናቸውን በመጥቀስ ያወድሷቸዋል፡፡
በጆሃንስበርግ ተቀማጭ የሆኑ ኢትዮጵያውያን አብረው በገበያ እንደሚሰሩ የሚኖሩትም አብረው ነው፡፡ ዩቬል፤ ቤራ እና ቤድፎርድ በተባሉ የጆሃንስበርግ ሰፈሮች ኢትዮጵያውያኑ አፓርትመንቶችን ፤ ቪላ ቤቶችን በመከራየት ይኖራሉ፡፡ ከኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች ቋሚ የመኖርያ ፍቃድ እና የደቡብ አፍሪካ ዜግነት ያላቸው ጥቂት ናቸው፡፡ በኢኮኖሚ እና ፖለቲካ ጥገኝነት ከደቡብ አፍሪካ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሆም አፌርስ በየወሩ ወይም በየዓመቱ የሚታደስ ዶክመንቶችን በመያዝ ብቻ እየሰሩ የሚኖሩት ብዙ ናቸው፡፡ ይሄው አኗኗር ኢትዮጵያውያኑን እንደልብ ከመንቀሳቀስ ያገዳቸው ይመስላል፡፡ በደቡብ አፍሪካ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በቂ ኢንቨስትመንት እንዳይኖራቸው እንቅፋት ሆኖባቸዋል፡፡
የባንክ ሂሳብ መክፈት ስለማይችሉም ነግደው ያተረፉትን ገንዘብ እንደልብ ለማዘዋወር አዳጋች ሆኖባቸዋል፡፡ የንግድ ስራዎቻቸውን ለማስፋፋት፤ አክሲዮን መግዛት አልቻሉም፡፡
በሊዝ ንብረት መያዝ ተስኖአቸዋል፡፡ የባንክ አገልግሎት ባለማግኘታቸው የሚኖራቸውን ገንዘብ በህገወጥ መንገድ እንዲያዘዋውሩ፤ በ አስተማማኝ ደህንነት እንዳይስቀምጡ ምክንያት እየሆነባቸውም ነው፡፡
የተስፋዊቷ ምድር የምትባለው ደቡብ አፍሪካ አዲስ መጤ ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች አልጋ በአልጋ አይደለችም፡፡ እንደድሮው አዲስ መጤዎች ከነባሮቹ ምንም አይነት ድጋፍ ስለማያገኙ ነው፡፡
ስለዚህም በቆይታቸው እንዲሳካላቸው በመጀመርያ ጥሩ የመነገጃ ብር፤ ከዚያም የስራ ፈጠራ እንዲሁም ከፍተኛ የስራ ትጋት ያስፈልጋቸዋል፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው ደግሞ አንድ በአዲስ አበባ የማውቀው ወጣት የጀመረው ስራ ነው፡፡ ይህ ወጣት በኡጋንዳ ለበርካታ ዓመታት በስደት ቆይቶ ደቡብ አፍሪካ ከገባ ገና ሶስት አመት ቢሆነው ነው፡፡
በጆሃንስበርግ ለመስራት የፈጠረው ሃሳብ ያስገርማል የተለያዩ ፍራፍሬዎችን ልጦና ከትፎ በማዘጋጀት በፕላስቲክ እቃዎች አሽጎ በጆበርግ መርካቶ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን በየሱቅ ደጃፋቸው እየተገኘ በማከፋፈል የንግድ ስራውን ያቀላጥፋል፡፡ እመነኝ በቅርብ አመት ይህ ስራ ሚሊዬነር ያደርገኛል ብሎኛል፡፡ ሌላ በጆበርግ ካገኘኋቸው ኢትዮጵያውያን አንዱ ነጋዴ አይደለም፡፡ ወጣቱ የኮምፒውተር ሶፍትዌር ኢንጂነር ነው ፡፡ ቢኒያም ይባላል፡፡
ይህ ወጣት የኢንተርኔት የማህበረሰብ ድረገፆችን በአማርኛ ቋንቋ ማሰራት የሚያስችልን ሶፍትዌር ፈጥሮ የመጨረሻው ምእራፍ ላይ ደርሷል፡፡

Read 6158 times Last modified on Saturday, 16 February 2013 12:41