Print this page
Saturday, 16 February 2013 13:23

በ‹‹እማዋዬ ዕንባ›› ወደ ዘመናችን እንመለስ!

Written by  በኃይሉ ከፍያለው
Rate this item
(3 votes)

አንዴ ደመቅ አንዴ ደብዘዝ በሚለው የስነ-ጽሑፍ ጉዟችን ውስጥ የተለያዩ ክስተቶች ይከሰታሉ፡፡ አንዳንድ የሥነ-ጽሑፍ ሰዎች እንደሚከፋፍሉት አምስት የታሪክ ዘመናት ያሉት ዘመናዊ ሥነ-ጽሑፋችን (ከ1900 እስከ ጣሊያን ወረራ፣ የጣሊያን ወረራ፣ ድህረ ጣሊያን ወረራ፣ የአብዮቱ ዘመን እና አሁን ያለንበት የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ዘመን) የተለያዩ ቀለሞችን እየተላበሰ ለተለያየ ሚና ሲጻፍ ኖሯል፡፡ ያለፈውን ዘመን ትተን የአሁኑን ዘመን የሥነ-ጽሑፍ ጉዞ ብናስተውል ከይዘት፣ ከቅርጽና ከጭብጥ አንጻር ወጣ ገባነት በዝቶበት እናያለን፡፡ ይህ ዘመን በተለይ የታሪክ መጻሕፍት የሚበዙበት ሳይሆን አይቀርም፡፡ በእርግጥ የግጥም መጻሕፍት ቁጥር ሊበረክት ይችላል፡፡ የወረቀት ጥራዙን ሁሉ እንደመጽሐፍ መቁጠሩ ሊያዳግት እንደሚችል በማመን ነው፡፡ የታሪክ መጻሕፍትን መብዛት ያስቀደምኩት፡፡
ከእነዚህ ከሚጻፉ የታሪክ መጻሕፍት ደግሞ እንዲሁ በወፍ በረር ቅኝት ሲታይ በዘመነ ደርግ የነበረውን የተለያዩ ጎራዎች ፍትጊያ እና አሁን ስልጣን ላይ ያለውን መንግስት ትግል የሚዘግቡት ይበዛሉ፡፡ ያም ሆነ ይህ ከ1960ዎቹ ወዲህ ያሉ የግብግብ ታሪኮች በብዛት ተዘግበው እናገኛቸዋለን፡፡
የደርግን ዘመን ታሪክ በተቀናበረ መረጃ ከጻፉት ደግሞ ገስጥ ተጫኔ ቀደምቱ ይመስለኛል፡፡ ‹‹ነበር›› በሚል ርእስ ሁለት ቅጽ ያለው መጽሐፍ አሳትሟል፡፡ በተደጋጋሚ ታትሞ በብዙ ቁጥር የተነበበ መጽሐፍ ነው - “ነበር”፡፡ በእነዚህ ሁለት ቅጾች ውስጥ እውነተኛ መረጃዎች እና ተአማኒነት ያለው ታሪክ ማቅረቡን ብዙዎች ሲስማሙበት እንጅ ሲቃወሙት አላስተዋልኩም፡፡ (በዚያ ዘመን ያለውን ታሪክ የሚጽፉ ሰዎች እርስ በእርሳቸው ይሕኛው ልክ ነው አይደለም ከመቆራቆስ አልፈው ምላሽ እስከመጻጻፍ የደረሱ እንዳሉ ልብ ይሏል) ገስጥ ተጫኔ ጠንቃቃ ደራሲ መሆኑን ለህትመት ባበቃቸው መጻሕፍት ውስጥ ማስተዋል ይቻላል፡፡ እያንዳንዷን ሁነትና ክስተት መዝግቦ የመያዝ ልምዱ ‹‹ነበር››ን ለመጻፍ እንዳስቻለው መገመት ከባድ አይደለም፡፡ ዛሬ መዳሰስ የፈለግሁት “ነበር”ን አይደለም፡፡ “ነበር”ን የጻፈው ገስጥ ተጫኔ ከእውነተኛ የታሪክ ክስተት ላይ ተነስቶ በአዲሱ ሥራው ምን መልክ ይዞ መጣ? የሚለውን ነው ማንሳት የምፈልገው፡፡
እውነቱን ለመናገር የገስጥ ዘመነኞች ጸጥታን መርጠዋል፡፡ አዳዲስ ሥራዎችንም ለንባብ ሲያበቁ እያስተዋልን አይደለም፡፡ አሁን የመጽሐፉን ገበያ የወጣቶች ሥራዎች ይበልጥ ተቆጣጥረውታል፡፡ ይህ መሆኑ ምንም ክፋት የለውም፡፡ ክፋቱ ቀደምቶቹ ጸጥ ረጭ ማለታቸው ብቻ ነው፡፡
በዚህ ጸጥታ መኻል ነው ገስጥ ተጫኔ አዲሱን መጽሐፉን ይዞልን ብቅ ያለው፡፡ ‹‹የእማዋዬ ዕንባ›› ይሰኛል፡፡ 278 ገጾች አሉት፡፡ የታሪኩ መሠረት የ1977 ዓ.ም ድርቅ ይሆንና እስከ 1983 ዓ.ም የዘለቀውን የእርስ በእርስ ጦርነት ይተርካል፡፡ የታሪኩ ሥፍራ ደግሞ ወሎ ነው፡፡ ቋንቋውም የወሎ አማርኛ፡፡
ይህ መጽሐፍ ልቦለድ ነው፡፡ ልብወለድነቱ ግን የባለታሪኮቹ አሳሳል እንጅ የባለታሪኮቹ ሃቅና ኑሮ ግን ልብወለድ እንዳይደለ አንባቢ በቀላሉ ይረዳዋል፡፡ ከብርሃኑ ዘሪሁን ‹‹ማዕበሎች›› ቀጥሎ ርሃብና ጦርነት ላይ የተጻፈ የወሎ ታሪክ የሆነው “የእማዋዬ ዕንባ” ብዙዎቻችን የምንናፍቀውን የኢትዮጵያ ሥነ-ጽሑፍ ስልት እናስተውልበታለን፡፡ ባለታሪኩ አንድ ቤተሰብ ነው፡፡ ሲነሳ ሲወድቅ የሚስተዋል ግዙፍ ቤተሰብ፡፡ የቤቱ መሠረት ደግሞ ውባየሁ(እማዋዬ) ናት፡፡ ይህ መጽሐፍ ምን አዲስ ነገር ይዞ መጣ? ሲባል ብዙ ነገር ማንሳት የሚቻል ቢሆንም በዚህ ዳሰሳ ግን ተምሳሌታዊ የገጸ-ባህሪይ አሳሳል ስኬቱንና የወሎ ዘዬ አማርኛ አጠቃቀም እምርታውን ብቻ ማንሳት በቂ ይሆናል፡፡
ውብአየሁ ማን ናት? ስለምንስ ነው ይህች ሴት እንደቆዳ ግራና ቀኝ የምትወጠረው? ምንስ ቢፈጠር ነው የዚህች ሴት ሁለት ወንድ ልጆች እርስ በእርስ የሚጋደሉት? ስለምንስ ይሆን እርሷን ንቆ ለግል ሆዱ ቀን ከሌሊት በአጭበርባሪነት የሚዳፋ ልጅ ያጎለመሰችው? ለምንስ ነው አሉባልተኞችና ሸረኞች ታጥቀው የተነሱባት? ቀጣዩን አንቀጽ እንውሰድ፡፡ ከገጽ 81
‹‹እቴነሽ አገር ጥላ መጥፋቷን በተመለከተ ጭራና ቀንድ እያወጣ በመንደሩ የተዛመተው ወሬ የውባየሁን ቅስም በሀዘን ሰበረው፡፡ በተለይ አቶ ዳውድ ‹‹ ይች ወልዶ የማባረር ሾተለይ የታጋኛት የእባብ ዘር ይህም የተረፋት አንዱ ትቷት እብስ ይልና ታርፈዋለች፡፡ የእባብ ልጆች ከእናታቸው አጠገብ እንዳያድጉ የአላህ እርግማን አለባቸው›› እያለ ሲናገር በመስማቷ ምርር ብሏት ‹‹አንተ ሰውዬ ምነው ተኔ ራስ አልወርድ አልህ? ልጆቼ ተኔ በመለየታቸው የእባብ ልጆች ተሆኑ አንተ እዚህ የተገኘኸው የማን ልጅ ሆነህ ነው?›› ብላ ወላጅ አባቱ እንጀራ ፍለጋ ከአረብ ተሰደው የመጡ መሆናቸውን እያስታወሰች ጎሸመችው፡፡
በንዴት ሳቅ እየተንፈቀፈቀ ‹‹ የትናንቱን ሳይሆን የዛሬውን ያንችን እናውራ፡፡ ያንች ልጆች ወደ አባቴ አገር አልኮበለሉ፤ እንደሁ ዋል አደር ብለሸ ስደቢኝ›› አላት ስንት እውነት ማግኘት እንደምንችል መርማሪና አንባቢ ሊመልሰው ይችላል፡፡ ይህ ተምሳሌታዊነት የመጽሐፉ መገለጫ ነው፡፡ እማዋዬ መከረኛዋ ውብአየሁ ሀገሪቱ ናት፡፡ እሻላለሁ ተብሎ ሳይሆን ይገባኛል ተብሎ ለወንበር ግብግብ የሚገጠምባት ሀገር፡፡ ርሃብተኛ በየመንገዱ እየወደቀ በሚሞትባት ሀገር፣ የእርዳታ መኪና እንደ ሸቀጣሸቀጥ ሱቅ የሚያገለግልበት እርዳታ እየታፈሰ የሚሸጥበት ዘመን እና ሀገር!
ለመሆኑ እማዋዬ ምን ያስነባታል? ስለምንስ በሰቀቀን መዓት ታነባለች? ጤናዋንስ ስለምን ታጣለች? ቀጣዩን አንቀጽ እንመልከት፡፡ ከገጽ 188
‹‹ እቤትዎ ወንበዴ አስተናግደዋል ይባላል እውነት ነው?››
ድንጋጤዋ መለስ አለላት ‹‹ ወንበዴ አላስተናገድኩም፤ ያስተናገድኩት ልጄን ነው›› ብላ መለሰች፡፡
‹‹ እኮ ወንበዴ ልጅዎን?››
‹‹አዎ ወንበዴ ልጄን ብቻ ሳይሆን ወታደር ልጄንም አስተናግጃለሁ፡፡
‹‹ እየቀለዱብን ነው እንዴ ሴትዮ›› አላት በቁጣ ድምጸት‹‹ አልቀለድኩም ጌታዬ ፣ሁለቱም ልጆቼ ናቸው፡፡ ›› አለች ፍርጥም ብላ፡፡ ቀጥላም ‹‹ ወንበዴ በምትሉት ውስጥ ይመር ክንዴ እሚባል ልጅ አለኝ፡፡ እናንተ ካቢን ስትለቁ ይመጣና አይቶኝ ይሄዳል ፡፡ እናንተ ውስጥ ደግሞ ሻምበል አንተነህ ክንዴ እሚባል ልጅ አለኝ፡፡ እሱም እንዲሁ እናንት ካቢን መልሳችሁ ስትይዙ ላንዳፍታ ብቅ ብሎ አይቶኝ ይሄዳል ፡፡ ታዲያ ልጆቼን እቤታችሁ አትግቡ ማለት ይቻለኛል? እናት ነኝኮ፡፡ በኔ ስፍራ ሆናችሁ ማየት ብትችሉ የተሸከምኩት የመከራ ቀንበር የቱን ያህል ከባድ እንደሆነ ትመዝኑ ነበር›› አለቻቸው፡፡ ……..
‹‹ በሉ ደህና ይዋሉ ጥናቱን ይስጥሁ ›› ብሎ አለቅየው ባልደረቦቹን አስከትሎ ሄደ፡፡
ይህ ተአምረኛ መጽሐፍ ምስያው ተዋጥቶለታል፡፡ ይህችን መከረኛ እናት በብዙ ገጽታዋ ያሳያታል፡፡ ለኢህአዴግ የሚዋጋ ልጅ አለሽ፤ ስለዚህም ወንጀለኛ ነሽ ብለው ደርጎች ጠይቀዋት በኢህአዴግ ብቻ አይደለም በደርግም በኩል አንዱ ልጄ እየታገለ ነው ስትላቸው የእናትነት ሰቀቀኑዋ ገብቷቸው እግዚያብሄር ያጥናሽ ብለዋት መከራዋን ተካፍለው ይሄዳሉ፡፡ በሌላ አጋጣሚ ኢህአዴጎች ለደርግ የሚዋጋ ልጅ ነበረሽ ብለው ወንጀለኛ እንደሆነች ይናገሯታል፡፡ ከላይ ያለውን ሐሳብ ለእነዚህም ትነግራቸዋለች፡፡ ይሁንና እንደነዚያኞቹ እግዚአብሔር ያጥናሽ ማለት ሳይሆን እስር ቤት ወስዶ መወርወር ቀናቸው፡፡
መጽሐፉ የእውነት መጽሐፍ ነው፡፡ እንደልቦለድ ብቻ ሳይሆን እንደታሪክ ማጣቀሻ ሊያነቡት የሚቻል አይነት፡፡ የሰዎች ባህርይ የሀገርን እና የሀገሬውን ባህርይ ሲገልጽ የሰው ልጅ የደስታ እና የመከራ ጫፍ ሲተረክ ብሎም እንደ ፊልም ሲታይ ….
ወደ ሁለተኛው ቅኝት እንለፍ ፡፡ ወደ ቋንቋ አጠቃቀሙ፡፡ ብዙ ደራሲዎች እምብዛም ስለጽሑፍ ቋንቋ አይጨነቁም የሚለው የሃሲያን እይታ ልክ መሆኑን ለማስተዋል እጃችን ላይ ያለውን አንድ የዘመኑ መጽሐፍ ማስተዋል በቂ ነው፡፡ እንግዲህ በዚህ መካከል ነው የገስጥ “የእማዋዬ እንባ” የተገኘው፡፡ ከፍ ሲል እንደተገለጸው መጽሐፉ የተጻፈው በወሎ አማርኛ ነው፡፡
የቋንቋ አጠቃቀም ስኬቱን ለመገምገም ሙሉ መጽሐፉን ማንበቡ ይበልጥ ለፈራጅነት ቅርብ ያደርጋል ፡፡ እኔ ማሳያዎችን ብቻ እጠቅሳለሁ፡፡ በነገራችን ላይ ደራሲው በዘዬ አጠቃቀም ረገድ ለጻፈበት ዘዬ ተጋላጭ ሆኖ አለማደጉን በተለያየ ጊዜ በተለያዩ ሚዲያዎች ከሰጠው ቃለምልልስ መረዳት ይቻላል፡፡ (ምንም እንኳ ደራሲ የሚለካው ባደገበት ሳይሆን በጻፈበት ቋንቋ ቢሆንም)፡፡
ሽማግሌው የውባየሁ ጭንቀት ገብቷቸው ‹‹ ዋ እኔን… በየህ የመከራ ዘመን የሰው ማጀት ባዶ መሆኑን ማን ያጣዋል? ቢጨንቀንና መድረሻ ብናጣ ነውይ…›› ብለው ወደ መጡበት ሊመለሱ ራመድ ሲሉ አብራቸው ያለችው ሴት ልጅ ‹‹ ተየህ ወዲያ ዌየትም አልሄድ›› አለችና እደፉ ላይ እንዘጭ ብላ ተቀመጠች፡፡
የእማዋዬ እንባ ሊነበብ የሚገባው መጽሐፍ ነው፡፡ በሰፊ ዳሰሳም ሊታይ፣ በዚህ ዘመን ካሉትም ልብወለዶች ሊጠቀሥ የሚችል ነው፡፡ የስነ-ጽሑፍ መምህራን እጅግ ወደኋላ እየተመለሱ የሚጠቅሱበትን ምክንያት በዚህ ልብወለድ ውስጥ ያገኙታልና ከዚህ ወዲያ ወደዚህኛው ዘመን ይመለሳሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

Read 3883 times