Saturday, 23 February 2013 11:25

“የእስራኤል መንግሥት ዘረኛ አይደለም”

Written by 
Rate this item
(4 votes)

“በእስራኤል ቆራጥነትና በምትሰራው ጀብዱ እኮራባታለሁ”
በታዳጊነቱ ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ እውቅ የእስራኤል ጋዜጠኞች ጋር በፈጠረው ትውውቅ ነው ወደ እስራኤል የተጓዘው - ከ45 ዓመት በፊት፡፡ ቤተእስራኤላዊው አላዛር ራህሚም በ1983 ዓ.ም ከኢትዮጵያ 14ሺ 200 ቤተእስራኤላውያን ወደ እስራኤል ያጓጓዘው “ዘመቻ ሰለሞን” ንቁ ተሳታፊ እንደነበር ይናገራል፡፡ ለ30 አመት ገደማ በእስራኤል ብሄራዊ ሬዲዮ በጋዜጠኝነት የሰራው አላዛር፤ የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለሚሰጡት ሹመት ተወዳድሮ አሸንፎ ነበር፤ ሆኖም በራሱ የግል ምክንያት ሹመቱን ሳይቀበለው ቀረ፡፡ ቤተእስራኤላውያን በመፅሃፍ ቅዱስ ላይ “ማርና ወተት የምታፈስ” በሚል የተጠቀሰችውን እስራኤል አልመው ቢጓዙም ምድረበዳና በጦርነት የተከበበች አገር ነው ያገኙት የሚለው አላዛር፤ ቤተእስራኤላውያን የዘር ልዩነት መድልዎ ይደርስባቸዋል የሚለውን ውንጀላ ብዙም አይቀበለውም፡፡

በግለሰብና በቡድን ደረጃ ዘረኝነትን የሚያራምዱ ቢኖሩም የእስራኤል መንግሥት ግን ዘረኛ አይደለም በሚል ሽንጡን ገትሮ ይከራከራል፡፡ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ መልካሙ ተክሌ ጋር የተጨዋወተው ቤተእስራኤላዊው ጋዜጠኛ አላዛር ራህሚም ስለ ቤተእስራኤላውያን የሥራ ዕድሎች፣ ስለሚያደንቃቸው የእስራኤልና የኢትዮጵያ መሪዎች እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮችን አውግቷል፡፡ እነሆ፡-


ራስህን በማስተዋዋቅ ጨዋታችንን ብትጀምረውስ…
አላዛር ራህሚም ነኝ፡፡ የኢትዮጵያ ስሜ አላዛር ምህረቱ ነው፡፡ ራህሚምን ወደ አማርኛ ስትተረጉመው ምህረቱ ማለት ነው፡፡ የእብራይስጡን ስም ወደድኩት፡፡ እብራይስጥ የኦሪት ቅዱስ ቋንቋ ስለሆነ ወድጄ ነው ያደረግሁት፡፡
ከኢትዮጵያ የት አካባቢ ነው ወደ እስራኤል የሄድከው?
ሰቀልት የሚባል የጐንደር አካባቢ ነው የተወለድኩት፡፡ አስራ አንድ ልጆች ላሉት ቤተሰብ ስድስተኛ ልጅ ነኝ፡፡ የሰፈር ረባሽ እና ተደባዳቢ ስለነበርኩ በቦታ ለውጥ ፀባዬ ይለወጣል በሚል አምቦበር የምትባል ቦታ ዘመድ ቤት ወሰዱኝ፡፡ ፈረንጆች ለመጀመርያ ጊዜ ያየሁት እዚያ ነው፡፡ ቤተሰብ አካባቢ “እብራይስጥ የተናገረ ዘመዳችን ነው” ተብያለሁ፡፡ ፈረንጆቹ እብራይስጥ ሲናገሩ ሰማሁና “ሻሎም” አልኳቸው፤ የምችለውን መጠነኛ እብራይስጥ ተጠቅሜ፡፡ ይህ የሆነው ከአርባ አመት በፊት ነው፡፡ ፈረንጅ አይቼ ስለማላውቅ “ምንድነው ነጭ ቆዳ” ብዬ እጠይቅ ነበር፡፡
ግን ጣታቸውን ሳይ እንደኔ በአንድ እጅ አምስት ጣቶች አሉ፡፡ ሁለት ጆሮዎች አሏቸው፡፡ እናም እየተከታተልኳቸው ሆቴል ገቡ፡፡ ፈረንጆቹ ምንድነህ ሲሉኝ፣ ፈላሻ ነኝ አልኳቸው፡፡ በወቅቱ ቤተእስራኤል “ፈላሻ” በሚል የስድብ ቃል ነበር የሚጠሩት፡፡
ስድብ ነው… ወይስ ከሰዎች መፍለስ ጋር ይገናኛል?
በታሪክ ወደኋላ መለስከኝ እንጂ ይሄ ስም የተሰጠው በአስራ ስድስተኛ አስራ ሰባተኛ ክፍለ ዘመን ነው፡፡ የክርስትያኑ ግዛተ አፄ ባልጠነከረበት ጊዜ የይሁዲ ግዛቶችም ነበሩ፡፡ የክርስትያኑ መንግሥት እየጠነከረ ሲሄድ፣ ይሁዳውያን ክርስትና ይነሱ፤ ካልተነሱ ይፍለሱ ተባለ፡፡ ከዛሬ ጀምሮ ፈላሻ ይሁኑ ተባለ፡፡ ፈላሻ ማለት መሬት የሌለው ማለት ነው፡፡
ወደ እስራኤል የሄድክበት ሁኔታስ?
እነዚያ ነጮች ጋዜጠኞች ነበሩ፡፡ አንዱ ለአቭየሽን መፅሔት ይፅፍ ነበር፡፡
ሌላኛው የእስራኤል ወታደራዊ ሬዲዮ ኃላፊ፣ ሦስተኛው በጋዜጠኝነት ከታች እስከ ዋና አዘጋጅነት የደረሰ ነበር፡፡
ውሰዱኝ አልኳቸው፡፡ ልጅነትም ስላለኝ አላወቅሁም፣ “ሻንጣችሁ ውስጥ ከታችሁ ውሰዱኝ” አልኳቸው፡፡ ደነገጡ፡፡
በተለይ አንዱ ሰው በሻንጣ ከቶ መሄድ እንደማይቻል አስረዳኝ፡፡ ፍተሻ ላይ ትያዛለህ አለኝ፡፡ ፍተሻ ምን እንደሆነ አላውቅም፤ ፈረንጅም ለመጀመርያ ጊዜ ነው ያየሁት፡፡ ከተመለስን በኋላ እንሞክርልሃለን ብለው ቃል ገቡ፡፡

ከአንድ ስድሰት ወር በኋላ አንደኛው ተመልሶ መጣ፡፡ እኔ ወደ ቤተሰብ ተመልሻለሁ፤ ትምህርት ቤቴ አጠያይቆ አድራሻ ትቶልኝ ሄደ፡፡ ከሦስት ሳምንት በኋላ ስመለስ ሰምቼ ቆጨኝ ግን ፃፍኩለት፡፡ ከጥቂት መፃፃፍ በኋላ የአየር ትኬት መጣልኝ፡፡ ፓስፖርት ለማውጣት መከራ ነበር፡፡ በኋላ ኤምባሲ ስሄድ ቪዛ ሰጪው “ለምንድነው የምትሄደው? ማነው የሚወስድህ” ብሎ ሲጠይቀኝ፤ ሦስቱን ጋዜጠኞች ጠቀስኩለት፡፡ ሰዎቹ በእስራኤል መገናኛ ብዙሃን በጣም ታዋቂ ናቸው፡፡ ጓደኞቼ ናቸው ስለው ደነገጠ፡፡ አድራሻቸውን ከሰጠሁት በኋላ፣ ቴሌግራም ተላልኮ ተፈቀደልኝ፡፡ አባቴ በሬ ሸጦ ነው ወደ እስራኤል የላከኝ፡፡

በንጉሡ ጊዜ ከሀገር መውጣት አስቸጋሪ ነበር፡፡ በዚያ ላይ ገና ታዳጊ ወጣት ነበርኩ፡፡
የእስራኤል መንግሥት ደግሞ ያኔ ለቤተእስራኤላውያን እውቅና ባለመስጠቱ ይሁዲ ነኝ ብልም አልተቀበሉም፡፡ እሱም አስቸጋሪ ነበር፡፡
ቤተእስራኤላዊነትን ካነሳን አይቀር የብዙ መቶ ዘመን ዘር ቆጥሮ ቤተእስራኤላዊ ነኝ ማለት አያስቸግርም?
አያስቸግርም፡፡ የምኒሊክ ዘር ነኝ፣ የካሌብ ዘር ነኝ እንደሚባለው ቤተእስኤላዊነትም በታሪክ የተመሰረተ ነው፡፡ ሐይማኖታችን በራሱ አንድ ማስረጃ ነው፡፡ የብሉይ ኪዳንን ሥርዓት ጠብቀን ቆይተናል፡፡ ቤተእስራኤላውያን ኢትዮጵያ የገቡት ሦስት ጊዜ ነው፡፡ አንደኛው በቀዳማዊ ምኒሊክ ጊዜ ነው፡፡ ሌላው ከየመን በአፄ ካሌብ ጊዜ በስድስተኛው ክፍለ ዘመን ነው፡፡ ሦስተኛው የሰሎሞን ቤተመቅደስ በወራሪዎች በወደመችበት ጊዜ ነው፡፡ ከኢትዮጵያውያን ይሁዲ ነገሥት መካከል ዮዲት እና ጌድዮን ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ብሉይ ኪዳን እስራኤልን “ማርና ወተት የምታፈስ” ሀገር ይላታል፡፡ እዚያ የገቡ ቤተእስራኤላውያን “ማርና ወተት የምታፈስ” እስራኤል አገኙ?
ልክ በመፅሐፍ ቅዱስ እንደተባለው ማርና ወተት የምታፈስ፣ በሽታና ችግር የሌለባት፣ የተረጋጋች፣ ሞት የሌለባት አድርገው የሚቆጥሩ የተሳሳተ እምነት የነበራቸው ቤተእስራኤላውያን ነበሩ፡፡
በሱዳን በረሃ ማንም ሳያስገድዳቸው ተጉዘው እስራኤል ሲደርሱ ዛፍ የማይበዛበት ምድረበዳ፣ በአካባቢዋና በውስጧ ጦርነት ያልተለያት ሀገር ነው ያገኙት፡፡ በዚያ ላይ የቋንቋና የባህል ችግር ይገጥማል፡፡ ያሰቡትን ላያገኙ ይችላሉ፡፡ ለወጣት ቤተእስራኤላውያን ግን ቋንቋና ባህሉን ቶሎ ስለሚለምዱ ሀገሪቷ የተሻለች ነች፡፡
ቤተእስራኤላውያን የነጭ እስራኤላውያን የዘር መድልዎ ተጠቂዎች እንደሆኑ ይነገራል፡፡ የዘረኝነቱ ምንጭ ምንድን ነው?
መሰረቱን ያጠናከረ ዘረኝነት በሀገረ እስራኤል አላየሁም፤ ያ ማለት ዘረኝነት የሚያራምዱ ቡድኖችና ግለሰቦች የሉም ማለት ግን አይደለም፡፡ የእስራኤል መንግስት ዘረኛ መንግስት አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ ለምሳሌ የባርያ ንግድ ሕጋዊ ሆኖ በመንግስት የሚደገፍበት ወቅት ነበር፡፡
ከዚህ የሄዱ መድልዎ እንደሚደርስባቸው እንሰማለን…
ነገርኩህ እኮ፡፡ ከዚህ ሲሄዱ ከነባህላቸው ነው የሚሄዱት፡፡ ባህላቸውን አየር ማረፊያ ወይም ጉምሩክ አያስረክቡም፡፡
እስራኤል ሄደው እንጀራ ሲጋግሩ ጠረኑ ከሩቅ ይሸታል፡፡ ነጮች ጐረቤቶቻቸው የዚያ ባህል የላቸውም፡፡
ወጡ ጨውና ቅመም የበዛበት ስለሆነ እሱም እንደ እንጀራው ነው፡፡ በድግስ፣ በሰርግ ጊዜ አሸሼ ገዳሜውን፣ አሃ ገዳሆውን ያስነኩታል፣ እልልታ ይቀልጣል፡፡
አሸበል ገዳዬ ነው፡፡ የሰአት ገደብ የለም መጨፈር ነው፡፡ ፈረንጅ የሰአት ገደብ አለው፡፡ ሁካታው ሲረብሻቸው ይበሳጫሉ፡፡ ያን ይዘን እኛ ነጮቹን ዘረኛ እንላለን፡፡ መበሳጨት የባህርይ እንጂ የዘር አይደለም፡፡
ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ የበለፀገች አገር ብትሆን ኖሮ ቤተእስራኤላውያን ወደ እስራኤል ይጓዙ ነበር ትላለህ? ምናልባት የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ቢሆንስ…
ወደ እስራኤል የተጓዙት ሃይማኖቱን በደንብ የሚጠብቁበት፣ ይሁዲነታቸውን የሚያጠነክሩበት ሀገራቸው ስለሆነች ነው፡፡ በ1960ዎቹ ከኢራቅ 120ሺህ ይሁዲዎች በ”ዘመቻ እዝራ” ወደ እስራኤል ተጓጉዘዋል፡፡ በ”ዘመቻ የሂን” ከሞሮኮ፣ በ”ዘመቻ ተአምረኛ ምንጣፍ” ከየመን ይሁዲዎች እስራኤል ገብተዋል፡፡ ያለና የነበረ እንጂ እንደተአምር አይቆጠርም፡፡
እስራኤል የዛሬ ስልሳ አምስት አመት ስትመሰረት ምጣኔ ሀብቷ ደቃቃ ነበር፡፡
ያኔም ዜጐቿ ወደ ሀገሪቱ ገብተዋል፡፡ በሕገመንግስቷ ላይ፤ “እስራኤል ሀብታም ድሃ፤ ጥቁር ነጭ ሳትል ልጆቿን ትጠራለች” ይላል፡፡
በ”ዘመቻ ሰሎሞን” ቤተእስራኤላውያንን ከኢትዮጵያ ለማውጣት ዘምተሃል፡፡ ስለዚህ የምታስታውሰውን ብትነግረን…
“ዘመቻ ሙሴ” ቀደም ብሎ በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1977 ተካሄደ፡፡
“ዘመቻ ሰሎሞን” ከስድስት አመት በኋላ በ1983 ተካሄደ፡፡ “ዘመቻ ሙሴ” ዓላማው ሰዎቹን ከየትኛውም የመከራ ቦታ ማውጣት ነበር፡፡
በጀርመን ናዚዎች በይሁዳውያን ላይ ከተደረገው ጭፍጨፋ አንፃር ማንኛውም ሀገር ያለ ይሁዲ መጠጊያ እንድትሆን ነው እስራኤል የተመሰረተችው፡፡ በዚህ ሀሳብ የተነሳ በ”ዘመቻ ሙሴ” በሱዳን አቋርጠው እስራኤል ለመግባት ያሰቡ ብዙ ሰዎች በረሃ ላይ ሞተዋል፡፡
ያኔ የእስራኤል መንግሥት ምን አደረገ?
ሱዳን የእስራኤል ወዳጅ አይደለችም ሆኖም እስራኤል ሱዳን የሰፈሩ ዜጐቿን ለማሸሽ ተግታለች፡፡ በሰላሳ ሁለት በረራዎች ሰባት ሺህ ስምንት መቶ ሰው አውጥተናል፡፡ በግምት ሦስት ሺህ ሰዎች ሞተዋል ይባላል፡፡ ሰሞኑን ጥናታዊ ምዝገባ እየተካሄደ ነው፤ ምን ያህል ሰዎች እንደሞቱ ለማወቅና ለመዘከር፡፡
“ዘመቻ ሰሎሞንስ?”
በዚያ ዘመቻ በንቃት ተሳትፌአለሁ፡፡ በግንቦት 1983 የተካሄደ ነው፡፡
ወደ ሱዳን ያልሄዱት አዲስ አበባ መጥተው ተሰባሰቡ፡፡ እስራኤልና የደርግ መንግሥት ግንኙነት አሻሽለው የእስራኤል ኤምባሲ ከተከፈተ ሁለት አመቱ ነበር፡፡ በወቅቱ አቶ ካሳ ከበደ ዋነኛ ተዋናይ ነበሩ በጉዳዩ፡፡ ከመንግሥት ጋር እየተደራደርን ተቃዋሚዎች እየገሰገሱ መጡ፡፡ ዘመቻው ሊካሄድ ጫፍ ላይ ሲደርስ ነው ይኼ መንግሥት የመጣው፡፡ ሲአይኤም መጣ፤ ያኔ ወያኔ ይባሉ የነበሩት ታጋዮች “ቆዩን፣ አዲስ አበባ አትግቡ” ተባሉ፡፡ ቤተእስራኤሎች በኬንያ ወጡ፡፡
ኢትዮጵያ ለሃያ አራት ሰዓት ያለምንም መንግሥት ቆየች፡፡ ከአርብ ጠዋት እስከ ቅዳሜ ከሰአት አስራ አራት ሺህ ሁለት መቶ ሰዎች ቦሌ ላይ ሲጫኑ ነበርኩ፡፡ እስራኤል ተአምር ሰራች፡፡ የዚያን ቀን ቦሌ ያለ አውሮፕላን ሁሉ የእስራኤል ነበር፡፡ የማንም የሌላ አልነበረም፡፡
ሰዎች በወቅቱ እንደ ካርጐ ተጭነው ነው የሄዱት…
አዎ፡፡
በጉዞ ወቅት ችግር አልገጠመም?
የአውሮፕላን ወንበሮች ተነስተው እንደ ባዶ አዳራሽ ነው የገቡበት፤ ባንዴ ብዙ ሰው ማሳፈር እንዲቻል፡፡ አንድም ችግር አልገጠመንም፡፡ ባይደንቅህ ሰባት ሕፃናት አውሮፕላን ላይ ተወልደዋል፡፡
ስለ ጋዜጠኝነትህ ደግሞ ንገረኝ…
በእስራኤል ብሔራዊ ሬዲዮ ለ28 አመት ሰርቻለሁ፡፡ አሁንም እሰራለሁ፡፡ በህትመት ሚዲያ ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ነው የሰራሁት፡፡ ሁለት መፃህፍት ፅፌአለሁ፡፡
አንድ የአማርኛ እብራይስጥ መዝገበ ቃላትም አዘጋጅቼአለሁ፡፡ ሦስት ፊልሞች ሠርቻለሁ፡፡ ከዚያ በፊት ተማሪ ሳለሁ “ቤተሰቦቻችን ይምጡልን” ከሚሉ አድማ መቺዎች ቅድሚያ ተሰላፊ ነበርኩ፤ የአድማ መሪም ነበርኩ፡፡
ከአዲሷ በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር ጋር ለመሾም እንዴት ተወዳደርክ?
ከሳቸው ጋር አይደለም የተወዳደርኩት፡፡

ወይዘሮ በላይነሽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባልደረባ ናቸው፡፡ እኔ አይደለሁም፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አስራ አንድ አምባሳደር መሾም ስለሚችሉ አንድ የመ/ቤታቸው ባልደረባ የሆነ ትውልደ ሩስያዊውን በሞስኮ አምባሳደርነት ሾሙ፡፡ ይሄኔ ለአማካሪያቸው “ኢትዮጵያዊ አምባሳደር በኢትዮጵያ ቢሾሙ ታሪክ ነው” ብዬ እንደቀልድ ተናገርኩ፡፡ ቆይቶ ከሌሎች ባለሙያዎች ጋር ተወዳደርኩ፤ ተመርጠሃል ተብዬ ለሹመቱ ታጨሁ፡፡ ግን በተለያየ የግል ምክንያት አምባሳደር ሳልሆን ቀረሁ፡፡
ከዚህ የሚሄዱ ቤተእስራኤላውያን “ዝቅተኛ” ሥራ ላይ ነው የሚመደቡት ይባላል፡፡ እውነት ነው?
ችግሩ አለ፡፡ አንደኛ ከመነሻው ትምህርታቸው ዝቅተኛ ነው፡፡ ከዜሮ ነው በብዛት የሚጀምሩት፡፡ ሌሎች በጨረሱት ትምህርት ልክ ስራ ያላገኙም አሉ፡፡ ይኼ በነጮቹ ላይም የሚታይ ቢሆንም ከዚህ የሄዱት ሥራ አጦች ቁጥር ይበዛል፡፡ ጠንካራ ሰው ብዙ አላፈራንም፡፡ በውትድርናም ከፍተኛ ደረጃ የደረሱ የመኖራቸውን ያህል በራሳቸው ላይ አደጋ ያደረሱም አሉ፤ ተስፋ ቆርጠው፡፡

ለምሳሌ ታሚር አላዛር የሚባል የወንድሜ ልጅ ሌተና ጀነራል ሆኗል፡፡ የታናሽ እህቴ ልጅ ሻለቃነት ደርሳለች፡፡ ሌላውም ዘመዴ ሻለቃ ነው፡፡ ብዙ ጠንካራና ታማኝ ወታደሮች አሉን፡፡ ስራ የሚያፈላልግላቸው በማጣት ነው ብዙዎቹ ዝቅተኛ ሥራ የሚሰሩት፡፡ የዘር መድልዎ የሚመስል ነገር አለ፡፡ የለየለት የዘር ጭቆና አለ ብሎ መደምደም ባይቻልም፡፡
ጋዜጠኛ ከመሆንህ በፊት ምን ሰርተሃል?
የኢትዮጵያ ይሁዳውያን ማህበር ሊቀመንበር ነበርኩ፡፡ ማህበሩ ስሙን ቢቀያይርም አሁንም አለ፡፡
ከሁለቱ ትልልቅ የእስራኤል የፖለቲካ ፓርቲዎች (ሌበር እና ሊኪውድ) ቤተእስራኤላውያን ለየቱ ያደላሉ?
አብዛኞቹ ለሊኪውድ ፓርቲ ያደላሉ፡፡ ሌበር ፓርቲ ሰላም ፈላጊ ነው፡፡ ሰላም በእስራኤል የመጣው ግን በሊኪውድ ጊዜ ነው፡፡ ከግብፅ ጋር ተደራድሮ፤ በሜናሂም ቤጊን አማካይነት፡፡
በጋዜጠኝነትህ ያነጋገርካቸው መሪዎች አሉ?
ሚናሂም ቤጊን አነጋግሬአለሁ፡፡ ኢዛቅ ሻሚርን፣ ሺሞን ፔሬዝን አነጋግሬአለሁ፡፡ በቃለምልልስ አይሁን እንጂ ኢዛቅ ራቢንን ብዙ ጊዜ አግኝቻለሁ፡፡
ከመሪዎች ማንን ታደንቃለህ?
ሜናሂም ቤጊን በጣም ትሁት ናቸው፤ በዚህ አደንቃቸዋለሁ፡፡ ራሳቸውን ከፍ ከፍ ሳያደርጉ በትንሽ ቤት የኖሩ ናቸው፡፡ ሃብት ያላካበቱ ለደካማ ህዝብ አሳቢ ነበሩ፡፡ እስራኤልን የመሰረቱት ከአውሮፓ የሄዱ ይሁዳውያን እና በአካባቢው አረብ ሀገራት የነበሩ ዜጐች ነው፡፡ ከአውሮፓ የሄዱት እነዚያን ዝቅ አድርጐ የማየት አዝማሚያ ነበር፤ አሁንም አለ፡፡ ከኢትዮጵያ የሄድነውን በሦስተኛ ደረጃ የሚያዩን ነበሩ፡፡ ቤጊን ይሄ እንዲቀር ጥረዋል፡፡ ሌላው ሻሚር ናቸው፡፡ እሳቸውን የማደንቀው ላመኑበት ቁርጠኛ ስለሆኑ ነበር፡፡

በአቋማቸው እገሌ ምን ይለኛል አይሉም፡፡ የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ናታንያሆ የታይታ ሰው ናቸው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ራቢን የሰላም ሰው በመሆናቸው አደንቃቸዋለሁ፤ ለሀገራቸው መስዋእት ሆነዋል፡፡ በእርግጥ ሻሚርም መስዋእት ሆነዋል፡፡ ኤርያል ሻሮንን በወታደራዊ መስክ አደንቃለሁ፤ በፖለቲከኛነታቸው አላደንታቸውም፤ ብዙ ነገር አበለሻሽተዋል፡፡ ሞሼ ዳያንን በአርበኝነቱና በወንዳወንድነቱ አደንቀዋለሁ፤ ግን ማን አለብኝነት ያጠቃው ነበር፡፡
ከኢትዮጵያስ መሪዎች?
አስቸጋሪ ጥያቄ አመጣህ፡፡ እዚህ ሀገር ተወልጄ እትብቴ ቢቀበርም የመምረጥ የመመረጥ መብት የለኝም፡፡ ለሕዝባቸው ተቆርቋሪ ስለነበሩ የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊን አደንቃለሁ፡፡ ልጅነታቸውንና ጐልማሳነታቸውን ያሳለፉት ለኢትዮጵያ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ከሁለት ሦስት ሺህ አመት እንቅልፏ ያነቋት መለስ ናቸው፡፡ ሰው ሲሞት ያን ያህል አላለቅስም፤ መለስ ሞቱ ሲባል ግን እንባዬን ጠብ አድርጌ አልቅሻለሁ፡፡ ሰው በመሆኔ አልቅሼላቸዋለሁ፤ ኢትዮጵያዊ መሆን አይጠበቅብህም፡፡
ወደ ኢትዮጵያ አመጣጥህ እንዴት ነው? በሥራ ነው ወይስ…
ሀገር ለማየት ወዳጅ ዘመድ ለመጠየቅና እንዳንተ ያለ ጓደኛ ለማፍራት ነው የመጣሁት፡፡ መሬት በሊዝ ተመርቻለሁ፤ እስራኤል ያለው የኢትዮጵያ ኤምባሲ አደራጅቶን ነው ለመኖርያ ቤት የተመራነው፡፡
እስራኤል ሲባል ፊትህ ድቅን የሚልብህ ምንድነው?
ቆራጥነቷና በምትሰራው ጀብዱ የምታስገኘው አመርቂ ውጤት!

Read 6456 times