Saturday, 23 February 2013 11:32

ውሃ የተጠማች የውሃ ማማ

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(0 votes)

“በውሃ ምክንያት የጤና ችግር መከሰቱን አልሰማንም” - ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን
በ1979 ዓ.ም በእቴጌ ጣይቱ ለመኖሪያነት የተመረጠችው አዲስ አበባ በምቹ የአየር ፀባይዋና በመልክአምድሯ አቀማመጥ የብዙዎችን ቀልብ መሳብ ጀመረች፡፡ ቀስ በቀስም የነዋሪዎቿ ብዛት እየጨመረ ሄደ፡፡
በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ይገኙ የነበሩት ምንጮች በየጊዜው ቁጥሩ እየጨመረ ለሚሄደው ነዋሪ በቂ ውሃ ማቅረብ ተሳናቸው፡፡ የውሃ እጥረት በከተማዋ እየተስፋፋ ሄደ፡፡ ገንቦውን እየተሸከመ በየወንዙና በየምንጩ የሚንከራተተው የከተማዋ ነዋሪ ተበራከተ፡፡ ሁኔታው በእጅጉ ያሳሰባቸው አፄ ምኒልክ፤ የውጭ አገር አማካሪዎቻቸውን ሰበሰቡ፡፡

በእናንተ አገር የውሃ ነገር እንዴት ነው ሲሉም ጠየቁአቸው፡፡ ፈረንጆቹ በአገራቸው ውሃን ከምንጭ በመጥለፍ በቧንቧ እንዴት ወደተጠቃሚው ቤት እንዲደርስ እንደሚያደርጉ ነገሯቸው፡፡ ንጉሱ በእጅጉ ተገረሙ፡፡ እንዴት እንዲህ ይሆናል ሲሉም አሰቡ፡፡ ይህ የተባለው ነገር በአገራቸው እንዲሰራ ዋና አማካሪያቸው ሙሴ ኢልግን አዘዙት፡፡ ሰባት ሺ ማርትሬዛ ብር ፈጅቶ የቧንቧ መዘርጋቱ ሥራ በጥር ወር 1886 ዓ.ም ተጠናቀቀ፡፡
ኪዳነምህረት ቤተክርስቲያን አካባቢ ከሚገኝ ምንጭ የተጠለፈው ውሃ በቧንቧ ቤተመንግስት ደረሰ፡፡ ይህ ሁኔታ በወቅቱ የከተማዋን ነዋሪዎችና የንጉሱን ባለሟሎች ሁሉ በእጅጉ አስገርሞአቸው ነበር፡፡
እንዲህ ያለ ንጉስ የንጉስ ቂናጣ
ውሃ በመዘውር ሠገነት አወጣ
አሁን ከዚህ ወዲያ ምን ጥበብ ሊመጣ
ሲልም ህዝቡ አድናቆቱን በግጥም ይገልጽ ነበር፡፡
በቤተመንግስቱ የገባው ውሃ ለአዲስ አበባ ከተማ ህዝብ እንዲደርስ ያሰቡት አፄ ምኒልክ፤ የውሃ ቧንቧ ከውጭ አገር እንዲገዛላቸው አደረጉ፡፡
ቧንቧው ተገዝቶ ከጅቡቲ ድሬዳዋ ድረስ በባቡር ከመጣ በኋላ ወደ አዲስ አበባ የሚመጣበት መንገድ ባለመኖሩ፣ በሰው ሸክም ከድሬዳዋ አዲስ አበባ ድረስ እንዲመጣ ምኒልክ ትዕዛዝ አስተላልፈው እንደነበር ጳውሎስ ኞኞ “አጤ ምኒልክ” በተሰኘው መጽሐፉ ላይ አስፍሯል፡፡
በዚህ መንገድ ወደከተማዋ የገቡት የውሃ ቧንቧዎች ጥቂት ሹማምንቶችን እንጂ የከተማዋን ነዋሪ ህዝብ ፍላጐት ለማርካት ባለመቻሉ ከተማዋ ለረዥም ጊዜያት ከውሃ ችግሯ ጋር ቆይታለች፡፡

ጊዜና ዘመን እየተለወጠ መጥቶ የውሃ አቅርቦቱ በዘመናዊ መልክ እንዲሆን ከተደረገና በርካታ የምንጭ ማጐልበት፣ የጉድጓድ ቁፋሮና የግድብ ሥራዎች ከተሰሩላት በኋላም ከተማዋ ከውሃ ችግሯ ልትላቀቅ አልቻለችም፡፡ ከለገዳዲና ገፈርሣ ግድቦችና የማጣሪያ ሥፍራዎች እንዲሁም ከአንድ መቶ አስር በላይ ከሚሆኑ ጉድጓዶች በቀን 374 ሺ ሜ.ኩ ውሃ በማምረት ለከተማዋ ነዋሪ ህዝብ እንዲዳረስ እየተደረገ ቢሆንም የአዲስ አበባ አንዳንድ አካባቢዎች ዛሬም ድረስ ቧንቧቸው ጠብታ ውሃን ናፍቆ ውሃ እንደተጠሙ ናቸው፡፡

በከፍተኛ መጠን እያደገ የመጣውን የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ህዝብ ፍላጐትና የውሃ አቅርቦቱን ለማመጣጠን የከተማዋ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን መ/ቤት የተለያዩ የማስፋፊያ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ ከእነዚህ የማስፋፊያ ሥራዎች መካከልም የድሬ ግድብን ውሃ የመያዝ አቅም በ11 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ የማሳደግ፣ የለገዳዲን የማጣሪያ ፕሮጀክት በ30ሺ ሜ.ኪዩብ ከፍ የማድረግና ሌሎች ፕሮጀክቶችን አጠናቆ ወደ ሲስተም የማስገባት ሥራዎች ይገኙበታል፡፡ ሰሞኑን ባለስልጣን መ/ቤቱ በድሬ ግድብና በለገዳዲ ውሃ ማጣሪያ ሥፍራ እያከናወናቸው የሚገኙትን የማስፋፊያ ሥራዎች ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች አስጐብኝቶ ነበር፡፡
በዚህ የጉብኝት ፕሮግራም ላይም መ/ቤቱ የነዋሪውን የመጠጥ ውሃ ፍላጐት ለማሟላት እያደረገ ስለአለው ጥረትም ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡
368ሺ ቆጣሪ ያላቸው ደንበኞች እንዳሉት የሚነገረው የአዲስ አበባ ከተማ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን፤ ከአለም ባንክ ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ በርካታ የማስፋፊያ ሥራዎችን፣ ተጨማሪ የማጣሪያ ፕላንቶችንና የመሥመር ዝርጋታ ሥራን እያከናወነ ይገኛል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከተለያዩ የአውሮፓና የአሜሪካ አገራት የሚያስመጣውን የውሃ ማከሚያ ክሎሪን እዚሁ በአገር ውስጥ ለማምረት የሚያስችለው ፋብሪካ ለማቋቋም ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ ፕሮጀክቶቹ ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት እስከሚጀምሩ ድረስ የህብረተሰቡን የንፁህ መጠጥ ውሃ ፍላጐት በጊዜያዊነት ለማርካት ጥረት እየተደረገ እንደሆነም በጉብኝቱ ወቅት ተገልፆልናል፡፡
የፕሮጀክቶቹ መጠናቀቅ በአሁኑ ወቅት በከተማዋ የሚታየውን ከፍተኛ የውሃ እጥረት በማስወገድ ረገድ የሚኖረው ጠቀሜታ ምን እንደሆነና ሌሎች ጥያቄዎች የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን መ/ቤት የፕሮጀክቶች ልማትና ማስፋፊያ ጽ/ቤት ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ሥዩም ብርሃኑ ምላሽ ሰጥተውናል፡፡
የውሃ አቅርቦቱን ለማሳደግ ከፍተኛ ሥራ እየተከናወነ እንደሆነ ቢነገርም በአሁኑ ወቅት በአብዛኛው የከተማዋ አካባቢዎች ከፍተኛ የውሃ እጥረት ይታያል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ምንድነው?
የውሃ እጥረቱ ከከተማዋ ዕድገትና ከኮንስትራክሽን ሥራዎች መስፋፋት ጋር ተያይዞ የሚከሰት ጉዳይ ነው፡፡ እንደሚታወቀው የአዲስ አበባ ከተማ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ዕድገት እያሳየች በመሄድ ላይ ያለች ስትሆን የነዋሪዎቿም ቁጥር ከቀን ወደቀን በከፍተኛ መጠን እየጨመረ ነው፡፡ የከተማዋ ዕድገት ከሚገለጽባቸው ጉዳዮች አንዱ የኮንስትራክሽን ሥራዎች መስፋፋት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ለኮንስትራክሽን ሥራዎች ደግሞ ውሃ እጅግ አስፈላጊና ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡

እነዚህ በከተማዋ ውስጥ በስፋት ለሚታየው የኮንስትራክሽን ግንባታ የምንጠቀመው ደግሞ ለመጠጥ አገልግሎት የሚውለውን የታከመ ውሃ ነው፡፡ የውሃ አቅርቦቱን ለማሳደግ እየተከናወኑ ካሉት ተግባራት መካከል የማስፋፊያ ሥራዎች፣ የአቃቂ ከርሰ ምድር ውሃ ሥራዎች፣ ቀደም ሲል ተጀምረው የነበሩ ፕሮጀክቶችን የማጠናቀቅና ወደሥራ የማስገባት ሥራዎችና የጥልቅ ጉድጓድ ቁፋሮ ሥራዎችን እያከወናንን እንገኛለን፡፡ እነዚህን ትንሽ ለማብራራት ያህል ቀደም ሲል በዓመት 42 ሜ. ኪዩብ ውሃ የመያዝ አቅም የነበረውን የድሬ ግድብ በ11 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ በማሳደግ 53 ሚሊዮን ሜ. ኪዩብ ውሃ በዓመት እንዲይዝ ማድረግ፣ የለገዳዲ ማጣሪያን የማጣራት አቅም ደግሞ በ30ሺ ሜ. ኪዩብ በቀን በማሳደግ 195 ኪ ሜ ኪዩብ ውሃ በቀን እያጣራ ለህብረተሰቡ ለማዳረስ የሚያስችል ሥራ እየሰራን ነው፡፡

ይህ የማስፋፊያ ሥራ ከዓለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የሚሰራ ሲሆን ሥራው ባለፈው ጥር ወር ላይ ተጀምሯል፡፡ በ16 ወራትም ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ሌላው ከዚሁ የማስፋፊያ ሥራዎች ጐን ለጐን የክሎሪን ማምረቻ ፋብሪካ ለመሥራት እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እንገኛለን፡፡ የማስፋፊያና የማጣሪያውን እንዲሁም የኬሚካል ማምረቻ ሥራውን የሚሰሩት የቻይና እና የፈረንሳይ ሁለት ታላላቅ ኩባንያዎች ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ለእነዚህ ሥራዎች 450 ሚሊዮን ብር በጀት ተመድቦለታል፡፡
ሌላው የአቃቂ ከርሰ ምድር ውሃ ሥራዎችን በከፍተኛ ሁኔታ ትኩረት ሰጥተን እየሰራንበት እንገኛለን፡፡ ይህ ፕሮጀክት በሦስት ዋና ዋና ደረጃዎች ተከፍሎ የሚሰራ ሲሆን በቀን 73ሺ ሜ. ኪዩብ ውሃ ለተጠቃሚው የምናደርስበት አንደኛው ደረጃ ባለፈው ዓመት ተጠናቋል፡፡ ሌሎቹ ሁለቱ ማለትም እያንዳንዳቸው 70ሺ ሜ.ኩ ውሃ የሚያመርቱት ፕሮጀክቶች በመጠናቀቅ ላይ ይገኛሉ፡፡
ሌላው በተለይ ምዕራብና ሰሜን ምዕራብ አዲስ አበባን የማዳረስ ተስፋ የተጣለበት የገርቢ ውሃ ፕሮጀክት ትልቅ ትኩረት ሰጥተን እየሰራንበት እንገኛለን፡፡ በቀጣዩ ዓመት ወደ ግንባታ ሥራ እንገባለን ብለን እናስባለን፡፡
ከቻይና መንግስት በተገኘ የረጅም ጊዜ የብድር ገንዘብ ወደ ሥራ የገባንበት ሌላው ፕሮጀክት የ18 ጉድጓዶች ቁፋሮ ነው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አሁን ሰባት የሚደርሱት ተቆፍረዋል፡፡
ከዋና ዋና የግንባታ ሥራዎች በተጨማሪ የውሃ እጥረቱ በከፍተኛ ሁኔታ በሚታይባቸው አካባቢዎች፣ የውሃ ጉድጓዶችን በመቆፈር ውሃ ለህብረተሰቡ ለማዳረስ ጥረት እያደረግን ነው፡፡ ይህ ለውሃ እጥረቱ ጊዜያዊ መፍትሔ ይሆናል ብለን የምናስበው ሥራ ነው፡፡
በተለይ በተለይ በሰሜንና ሰሜን ምዕራብ አዲስ አበባ፣ በጉለሌ፣ አስኮ፣ ሽሮሜዳ፣ ሰሜን ሆቴል ውሃ ለማዳረስ ጨረታ አውጥተን ሥራው እየተሰራ ነው፡፡ ዋናው ችግራችን ቦታ የማግኘቱን ጉዳይ ነበር፡፡ አሁን በስምንት የተመረጡ ቦታዎች ላይ ፕሮጀክቱን ጀምረናል፡፡
የስድስቱ ጉድጓድ ቁፋሮ ሥራ ተጠናቋል፡፡ ከእነዚህ መካከል የተወሰኑትን በጥቂት ቀናት ውስጥ ወደሥራ እናስገባቸዋለን፡፡ እነዚህ ሥራዎች ትላልቆቹ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት እስከሚጀምሩ ድረስ የህብረተሰቡን ፍላጐት ለማሟሟላት ይረዳሉ ተብሎ ይታሰባል፡፡
በከተማዋ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ከቧንቧ የሚወርደው ውሃ ንፁህ ያልሆነ፣ ድፍርስና ቆሻሻ ነው ሲባል ይሰማል፡፡ ይህ ደግሞ በህብረተሰቡ ጤና ላይ ችግር ያስከትላል የሚል ሥጋት አለ፡፡
ውሃው ለህብረተሰቡ ከመድረሱ በፊት በሚገባ መጣራቱና ንፁህ መሆኑን የምትቆጣጠሩበት መንገድ የለም? በጤና ላይ ስላስከተለው ችግርስ ሪፖርት የተደረገላችሁ ነገር አለ?
በመሠረቱ ውሃው ለህብረተሰቡ ከመድረሱ በፊት በተለያዩ ዘመናዊ የውሃ ማጣሪያ መንገዶች ተጣርቶና በአስተማማኝ ሁኔታ ተዘጋጅቶ ነው፡፡ ውሃው በርካታ የማጣራት ሂደቶችን አልፎ ንፁህ ከሆነ በኋላ፣ ክሎሪን በተባለው ኬሚካል እንዲታከም ያደርጋል፡፡ በዚህ መንገድ ያላለፈ ውሃ ለህብረተሰቡ እንዲደርስ የሚደረግበት ሁኔታ የለም፡፡ ሆኖም አንዳንድ ጊዜ የውሃ ማስተላለፊያ ቧንቧዎች ሊሰበሩ ወይም ጉዳት ሊደርስባቸው ይችላል፡፡ በዚህ ወቅት ደግሞ የደፈረሰ ውሃ በቧንቧ ሊሄድ የሚችልበት ሁኔታ ይኖር ይሆናል፡፡
ከዚህ ውጪ ግን ከማጣሪያ ጣቢያው ሣይጣራ ወደ ህብረተሰቡ የሚደርስ ውሃ የለም፡፡ በቧንቧ ውሃ ምክንያት የተከሰተ የጤና ችግር ስለመኖሩ ግን ለእኛ የደረሰን ሪፖርት የለም፤ በውሃ ምክንያት የጤና ችግር ተከሰተ ሲባልም አልሰማንም፡፡

Read 3317 times