Saturday, 23 February 2013 12:06

ጊዮርጊስና ደደቢት የኳሱን መነቃቃት ቀጥለዋል

Written by 
Rate this item
(3 votes)

ባለፈው ሳምንት በ2013 የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ እና ኮንፌደሬሽን ካፕ ላይ ከሜዳ ውጭ የተጫወቱት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ደደቢት በሰፊ የግብ ልዩነት ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈው ወደ መጀመርያ ዙር ማጣርያ የሚገቡበትን እድል አሰፉ፡፡ በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ቅዱስ ጊዮርጊስ ካዛንዚባሩ ጃምሁሪ ጋር ተገናኝቶ 3ለ0 ሲያሸንፍ ጎሎቹን ፍፁም ገብረማርያም፤ ኡመድ ኡክሪ እና ጆሴፍ ከመረብ አዋህደዋል፡፡ በአፍሪካ ኮንፌደሬሽን ካፕ ደግሞ ደደቢት የሴንትራል አፍሪካውን አንጌስ ዴፋቲማ 4ለ0 ሲረታ ግቦቹን ያስቆጠሩት ጌታነህ ከበደ፤ አዲስ ህንፃ፤ በሃይሉ አሰፋ እና ዳዊት ፍቃደ ናቸው፡፡ በቀጣይ ሳምንት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ደደቢት በቅድመ ማጣርያው የመልስ ጨዋታቸው ተጋጣሚዎቻቸውን በአዲስ አበባ ያስተናግዳሉ፡፡ ሁለቱም ክለቦች በአህጉራዊ ውድድሩ ወደ የሚቀጥለው የመጀመርያ ዙር የማጣርያ ምእራፍ ለመሸጋገር በመልስ ጨዋታቸው በቀላሉ አቻ መውጣት እና ማሸነፍ ይበቃቸዋል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ የዛንዚባሩን ጃምሁሪ በቅድመ ማጣርያው ጥሎ ሲያልፍ በሻምፒዮንስ ሊጉ የመጀመርያ ዙር ማጣርያ ቀጣይ ተጋጣሚው የማሊው ክለብ ዲ ጆሊባ ይሆናል፡፡ ደደቢት ደግሞ አንጌስ ዲ ፋቲማን ጥሎ ካለፈ በኮንፌደሬሽን ካፑ የመጀመርያ ዙር ማጣርያ የሚያገኘው የሱዳኑን ክለብ አሊሂላል ሼንዲ ነው፡፡
በአፍሪካ ሁለት ትልልቅ የክለብ ውድድሮች ቅዱስ ጊዮርጊስና ደደቢት ኢትዮጵያን በመወከል በነበራቸው ተሳትፎ ከሜዳቸው ውጭ ብዙ ጎል አግብቶ በማሸነፍ ያስመዘገቡት ውጤት በአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ በአገሪቱ እግር ኳስ የተፈጠረውን መነቃቃት አስቀጥሏል፡፡ በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለተሳተፈው ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ሁለቱ ክለቦች በጋራ 17 ተጨዋቾችን በማስመረጥ ግንባር ቀደም ነበሩ፡፡ በእነዚህ የብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾቻቸው በአፍሪካ ዋንጫው ያገኙት ልምድ ደግሞ በአህጉራዊው የክለቦች ውድድር ከቀድሞው የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ምክንያት ሆኖላቸዋል፡፡ በሻምፒዮንስ ሊጉ እና ኮንፌደሬሽን ካፑ አጀማመር ላይበሁለቱ ክለቦች ከተመዘገቡት 7 ግቦች አራቱን ለብሄራዊ ቡድን ያስመረጧቸው ተጨዋቾች ከመረብ አዋህደዋል፡፡ በሻምፒዮንስ ሊግ በሚወዳደረው ቅዱስ ጊዮርጊስ ውስጥ የብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች የሆኑት አምበሉ ደጉ ደበበ ፤ ግብ ያስቆጠረው ኡመድ ኡክሪ እና አማካዩ ሽመልስ በቀለ በዛንዚባሩ ጨዋታ ምርጥ ብቃት እንደነበራቸው ተገልጿል፡፡ በኮንፌደሬሽን ካፕ ተሳታፊ የሆነው ደደቢት የሴንተራል አፍሪካውን አንጌስ ዴፋቲማ በሰፊ የግብ ልዩነት ሲያሸንፍ 3 ጎሎችን ያስመዘገቡት የብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾቹ ነበሩ፡፡ ሌሎቹ የብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች አዲስ ህንፃ የጨዋታው ኮከብ እንደነበረና ግብ ጠባቂው ሲሳይ ባጫ በርካታ ግብ ሊሆኑ የሚችሉ ኳሶችን በማዳን ምርጥ ብቃት ማሳየታቸው ታውቋል፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ በሻምፒዮንስ ሊግ
ለዘንድሮው የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ከ1 ወር በላይ የተዘጋጀው የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ከቅድመ ማጣርያው አንስቶ በሶስት ዙር የሚደረጉትን የማጣርያ ምእራፎች በማለፍ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ሻምፒዮንስ ሊጉ የምድብ ድልድል ውስጥ ለመገባት አቅዷል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ዛንዚባር ሲያቀና ወሳኙን የግብ አዳኝ አዳነ ግርማን ከደረሰበት ጉዳት ባለማገገሙ አልያዘም ነበር፡፡ አዳነ በአዲስ አበባ ለሚደረገው የመልስ ጨዋታ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ መሰለፉ ቢጠበቅም ጨዋታው ያን ያህል አስጨናቂ ባለመሆኑ ካለበት ጉዳት በተሟላ ሁኔታ እንዲያገግም ሊደረግ ይችላል፡፡
በኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግን ለ25 ጊዜያት ሻምፒዮን በመሆን ክብረወሰን የያዘው ቅዱስ ጊዮርጊስ የዘንድሮው የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎው ለ10ኛ ጊዜ ሲሆን ውድድሩ አፍሪካን ካፕ ኦፍ ሻምፒዮንስ ክለብስ እየተባለ ደግሞ 10 የውድድር ዘመኖችን ተካፍሎበታል፡፡ ባለፈው የውድድር ዘመን ደግሞ ጊዮርጊስ በካፍ ኮንፌደሬሽን ካፕ ለመጀመርያ ጊዜ መሳተፉ አይዘነጋም፡፡በወቅቱ በቅድመ ማጣርያው የተገናኘው ከኤስ ማንጋ ስፖርት ጋር ነበር፡፡ በዚሁ የደርሶ መልስ ፍልሚያ በመጀመርያው ጨዋታ ከሜዳ ውጭ 1ለ0 አሸንፎ ከተመለሰ በኋላ በመልሱ ጨዋታ እዚህ አዲስ አበባ ላይ ማንጋ ስፖርት 4ለ0 በመርታት ወደ መጀመርያው ዙር ገብቶ ነበር፡፡ በመጀመርያው ዙር የተገናኘው ከቱኒዚያው ክለብ አፍሪካን ነበር፡፡ የመጀመርያውን ጨዋታ በሜዳው ሲያደርግ 1ለ1 ተለያየ ከዚያም በመልስ ጨዋታው በክለብ አፍሪካን 2ለ0 ተሸንፎ ከውድድሩ ውጭ ሆኗል፡፡
በ2013 የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ የኢትዮጵያው ቅዱስ ጊዮርጊስ ተጋጣሚ የሆነው የዛንዚባሩ ክለብ ጃምሁሪ በአፍሪካ ክለቦች ውድድር ብዙም ልምድ የለውም፡፡ ጃምሁሪ አምና በኮንፌደሬሽን ካፕ ለመጀመርያ ጊዜ የተሳተፈ ሲሆን በዛንዚባር ሊግ ሻምፒዮን ሆኖ የሚያውቀው አንዴ ብቻ ነው፡፡ የ2013 የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ በታሪኩ ለ47ኛ ጊዜ በአዲስ የውድድር ስርዓት መካሄድ ከጀመረ ደግሞ ለ17ኛ ጊዜ የሚከናወን ነው፡፡ በዘንድሮው ውድድር ከ45 የእግር ኳስ ፌደሬሽኖች የተወከሉ 56 ክለቦች ይሳተፉበታል፡፡
ደደቢት በኮንፌደሬሽን ካፕ
ላይ ደደቢት በአፍሪካ የክለቦች ውድድር ካለው የአጭር ጊዜ ልምድ የተሻለ ታሪክ ለማስመዝገብ የሚያስችለውን የአሸናፊነት ስነልቦና መያዙን ወደ መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ ሲጓዝ በተደረገለት ሽኝት እንደተገለፀ የሚታወስ ነው፡፡ በቅድመ ማጣርያው ከሜዳው ውጭ 4ለ0 በማሸነፍ የተመዘገበው ውጤት ይህን ያረጋገጠ ነበር፡፡ ደደቢት ከሁለት የውድድር ዘመን በፊት በኮንፌደሬሽን ካፕ ተሳታፊ ነበር፡፡በቅድመ ማጣርያው ከታንዛኒያው ያንግ አፍሪካንስ ጋር ተገናኝቶ በመጀመርያው ጨዋታ ከሜዳው ውጭ 4ለ4 ተለያይቶ በመመለስ በመልሱ ጨዋታ እዚህ አዲስ አበባ ላይ 2ለ0 አሸንፎ ጥሎ ማለፍ ችሏል፡፡ ከዚያይ በመጀምርያ ዙር ማጣርያ ከግብፁ ሃራስ ኤልሁዳድ ጋር ነበር የተገናኘው፡፡ በመጀመርያ ዙር ከሜዳው ውጭ በሃራስ ኤልሁዳድ 4ለ0 ተሸንፎ በመልሱ ጨዋታ አዲስ አበባ ላይ አንድ እኩል አቻ በመውጣት ከውድድሩ ተሰናብቷል፡፡
በ2013 የአፍሪካ ክለቦች ኮንፌደሬሽን ካፕ የደደቢት ተጋጣሚ የሆነው የመካከለኛው አፍሪካ ክለብ አንጌስ ዴፋቲማ በአገሩ የሊግ ውድድር 5 ጊዜ ሻምፒዮን ለመሆን የበቃ ሲሆን ስታድዬሙ በዋና ከተማው ባንጉዊ የሚገኝ ነው፡፡ በአፍሪካ ሻምፒዮን ክለቦች ውድድር 5 ጊዜ፤ በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ 2 ጊዜ፤ እንዲሁም በካፍ ኮንፌደሬሽን ካፕ 1 ጊዜ ተሳትፎ ከመጀመርያ ዙር አላለፈም፡፡ በታሪኩ ለ10ኛ ጊዜ በሚደረገው የ2013 የአፍሪካ ክለቦች ኮንፌደሬሽን ካፕ ከ41 ፌደሬሽኖች የተውጣጡ በአጠቃላይ 59 ክለቦችን ያሳትፋል፡፡
የሁለቱ ክለቦች አርዓያነት
ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ደደቢት በኢትዮጵያ የክለብ እግር ኳስ በአርዓያነት ሊወሰድ የሚገባ አስተዳደርን ይከተላሉ፡፡ ሁለቱ ክለቦች ለዋና ቡድኖቻቸው መሰረት የሆኑ የቢ እና የሲ ቡድኖችን በመያዝ፤ ለተጨዋቾች ጠቀም ያለ የፊርማ ክፍያ በመስጠት እና ከፍተኛ ደሞዝ በመክፈል፤ ከተለያዩ የውጭ አገራት ተጨዋቾችን በመቅጠር፤ ስለክለባቸው የተሟላ መረጃ ማግኘት የሚቻልባቸውን ድረገፆች በማንቀሳቀስ፤ የሴት እግር ኳስ ክለቦችን በመዋቅራቸው በማካተት ይሰራሉ፡፡ ሁለቱም ክለቦች በዙርያቸው ድጋፍ ሰጭ ስፖንሰሮችን በማሰባሰብም ብዙ ርቀት ተጉዘዋል፡፡
ፈረሰኞቹ በሚል ቅፅል ስሙ የሚታወቀው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሁለት ዓመት በፊት የተመሰረተበትን 75ኛ ዓመቱን ሲያከብር በኦፊሴላዊ ድረገፅ የክለቡ ፕሬዝዳንት አቶ አብነት ገብረመስቀል ባሰፈሩት መልእክት ክለባቸው ለኢትዮጵያ እግር ኳስ በሚጫወተው ፈርቀዳጅ ሚና እንደሚቀጥል ገልፀው ነበር፡፡ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ደጋፊዎቹን በአባልነት በመመዝገብ እና ባለድርሻ አካል እንዲሆኑ በማድረግ ፤ የውጭ አገር ተጨዋቾችን በመቅጠር እንዲሁም የውጭ አገር አሰልጣኝ በሃላፊነት በማሰራት ቅዱስ ጊዮርጊስ አርዓያ መሆኑን ፕሬዝዳንቱ በኩራት ይገልፃሉ፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ከ20 ዓመታት በፊት የራሱ ቢሮ እንዳልነበረው በመልእክታቸው የጠቀሱት አቶ አብነት አሁን ክለቡ የራሱን ስታድዬም በመገንባት ላይ እንደሚገኝ፤ የወጣቶች አካዳሚ ገንብቶ ስራ እንደጀመረ ገልፀው ክለቡን በአውሮፓ ሞዴል ለማስተዳደር በተቃና መንገድ እየሰራን ነው ብለዋል፡፡ የአርሰናል ክለብ እና የአሰልጣኝ አርሰን ቬንገር አድናቂ መሆናቸውን በዚሁ መልእክታቸው የገለፁት አቶ አብነት ክለባቸው ቅዱስ ጊዮርጊስ በሁሉም ረገድ እንደአርሰናል ቢሆን ፍላጎቴ ነው ይላሉ፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ የራሱን ስታድዬም በመገንባት የያዘው ጅምር ለሁሉም የኢትዮጵያ ክለቦች አርዓያነቱን ያጎላዋል፡፡ ክለቡ ለስታድዬም ግንባታው የሚኖረውን ወጭ 80 በመቶ ከክቡር ሼህ መሃመድ አላሙዲ ያገኛል፡፡ የክለቡን ደጋፊዎች ባለድርሻ አካል ያደረገውና የአባልነት መታወቂያ ይዘው ክለቡን በወርሃዊ መዋጮ እንዲደግፉ በማድረግ የተሳካለት የቅዱስ ጊዮርጊስ አስተዳደር ትልልቅ ኩባንያዎችን በስፖንሰርሺፕ አብረውት እንዲሰሩ በማድረግም አርዓያ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ የስፖንሰርሺፕ ድጋፉን ከቢጂአይ፤ ከዳሸን ባንክ እና ከፔፕሲ ኢትዮጵያም ይሰበስባል፡፡
በቅፅል ስሙ ሰማያዊው ጦር የሚባለው ደደቢት ከተመሰረተ 15 ዓመት ሲሆነው የእግር ኳስ ክለቡ ፕሬዝዳንት ኮለኔል አዎል አብድራሂም ናቸው፡፡ ‹‹ህልማችን እውን ይሆናል›› የሚለውን ያነገበው ክለቡ የልምምድ ሜዳውን በአበበ ቢቂላ ስታድዬም ያደረገ ሲሆን ሳርቤት አካባቢ በተሟላ የመዝናኛ አገልግሎት የሚሰጥበት የተጨዋቾች ካምፕን ይጠቀማል፡፡ የደደቢት እግር ኳስ ክለብ ስፖንሰሮችን በማስተባበር ይሰራል፡፡ ለክለቡ በመጀመርያ ደረጃ ስፖንሰርነት ድጋፍ የሚያደርገው የብረታብረት እና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ሲሆን፤ በ2ኛ ደረጃ ስፖንሰር የሚያደርገው ደግሞ የመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ ነው፡፡ በ3ኛ ደረጃ ስፖንሰርነት የመከላከያ የኮንስትራክሽን ግብዓቶች ማምረቻ ኢንተርፕራይዝ እንዲሁም በ4ኛ ደረጃ ስፖንሰርነት የአርሚ ፋውንዴሽን ክለቡን እየደገፉ እንደሆነ ከድረገፁ የተገኘ መረጃ ይገልፃል፡፡ የክለቡ የማልያ ስፖንሰር ደግሞ ሳምሰንግ ነው፡፡

Read 6145 times