Sunday, 03 March 2013 07:08

ቅ/ጊዮርጊስ እና ደደቢት በአፍሪካ ደረጃ የመልስ ጨዋታ አላቸው

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ እና ኮንፌደሬሽን ካፕ በቅድመ ማጣርያ የመልስ ጨዋታዎቻቸውን በአዲስ አበባ የሚያደርጉት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ደደቢት ወደ የመጀመርያ ዙር የማጣርያ ምእራፍ ለመግባት ሰፊ እድል አላቸው፡፡ ሁለቱ ክለቦች በቅድመ ማጣርያው የመልስ ጨዋታዎቻቸው ተጋጣሚዎቻቸውን በማንኛውም ውጤት መርታት ወይንም በአቻ ውጤት መለያየታቸው ወደ የመጀመርያው ዙር የማጣርያ ምእራፍ ያስገባቸዋል፡፡ በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ከሜዳው ውጭ በመጀመርያው ጨዋታ የዛንዚባሩን ጃምሁሪ 3ለ0 ያሸነፈው ቅዱስ ጊዮርጊስ በመልሱ ጨዋታ ጥሎ ካለፈ ከአስራምስት ቀናት በኋላ የመጀመርያ ዙር የማጣርያ ግጥሚያውን ከሜዳው ውጭ የሚያደርገው ከማሊው ክለብ ዲጆሊባ ጋር ነው፡፡ በአፍሪካ ክለቦች ኮንፌደሬሽን ካፕ የሚሳተፈው ደደቢት በበኩሉ የመካከለኛው አፍሪካውን ክለብ አንጌስ ዲፋቲማ ከሜዳው ውጭ 4ለ0 እንደረታ የሚታወስ ሲሆን በመልስ ጨዋታው ጥሎ ካለፈ በመጀመርያ ዙር ማጣርያ በሜዳው ከሱዳኑ ክለብ አልሃሊ ኤልሻንዲ ጋር ይገናኛል፡፡ በመጀመርያ እና በሁለተኛ ዙር የደርሶ መልስ ማጣርያዎች በሻምፒዮንስ ሊጉ የመጀመርያ ዙር ማጣርያ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጋጣሚ ሊሆን የሚችለው ዲጆሊባ ከተመሰረተ ከ50 ዓመታት በላይ ይሆነዋል፡፡ ከማሊ ስኬታማ ሁለት ክለቦች አንዱ የሆነው ዲጆሊባ በአገሪቱ የክለቦች ሊግ ውድድር ለ22 ጊዚያት ሻምፒዮን ከመሆኑም በላይ በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ 8 ጊዜ ተሳትፎ አስከ ሁለተኛ ዙር መግባት ችሏል፡፡ ዲጆሊባ በኮንፌደሬሽን ካፑ ላይ ከሶስት የውድድር ዘመናት በፊት ለሩብ ፍፃሜ ባለፈው የውድድር ዘመን ደግሞ ለደረጃ በመጫወት ከጊዮርጊስ የተሻለ ልምድ ያለው ነው፡፡ በኮንፌደሬሽን ካፑ የደደቢት ተጋጣሚ የሚሆነው አልሃሊ ሻንዲ ደግሞ ከተመሰረተ ከ65 አመታት በላይ የሆነው አንጋፋ የሱዳን ክለብ ነው፡፡አልሃሊ ሻንዲ ባለፈው የውድድር ዘመን ለኮንፌደሬሽን ካፕ የምድብ ድልድል በመብቃት ጠንካራ አቋሙን አሳይቷል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ደደቢት በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግና ኮንፌደሬሽን ካፕ ላይ እንደቅደምተከተላቸው የመጀመርያ ዙር ማጣርያ ተጋጣሚዎቻቸው የሆኑትን የማሊውን ዲጆሊባ እና የሱዳኑን ክለብ አልሃሊሻንዲ በደርሶ መልስ ጨዋታዎች ጥለው ካለፉ በሁለተኛው ዙር የማጣርያ ምእራፍ ከሃያላኖቹ የግብፅ ክለቦች ጋር የመገናኘታቸው እድል ሰፊ ነው፡፡ በሻምፒዮንስ ሊጉ ቅድመ ማጣርያ የቻዱን ጋዜቤ 7ለ0 ያሸነፈው የግብፁ ክለብ ዛማሌክ እና በተመሳሳይ ምእራፍ የቶጎውን ዳይናሚክ 3ለ0 ያሸነፈው የዲሞክራቲክ ሪፖብሊክ ኮንጎውን ክለብ ቼቼስ ቪታ በመልስ ጨዋታቸው ውጤታቸውን ካሳመሩ በመጀመርያ ዙር የማጣርያ ምእራፍ መገናኘታቸው አይቀርም፡፡ በዚህ መሰረት ቅዱስ ጊዮርጊስ በመጀመርያው ዙር የማሊውን ክለብ ዲጆሊባ ጥሎ ካለደፈ በተመሳሳይ ምእራፍ ሊገናኙ ከሚችሉት የግብፁ ዛማሌክ እና የዲሞክራቲክ ሪፖብሊክ ኮንጎው ኤኤስ ቪታ አሸናፊ ጋር በሁለተኛ ዙር ማጣርያው ይገናኛል፡፡ በኮንፌደሬሽን ካፕ በቅድመ ማጣርያው የማዳጋስካሩ ቲቦ ቦኒ ከስዋዚላንዱ ማባኔ ሃይላንደርስ በመገናኘት 2ለ1 ያሸነፈ ሲሆን በመልሱ ጨዋታ ከሁለቱ ክለቦች ያሸነፈው በመጀመርያ ዙር የሚጠብቀው ተጋጣሚ የግብፁ ኢስማሊያ ይሆናል፡፡ በዚህ መሰረት ደደቢት በመጀመርያ ዙር የኮንፌደሬሽን ካፕ የደርሶ መልስ ማጣርያው የሱዳኑን ክለብ አልሃሊ ሻንዲ ከረታ የሁለተኛ ዙር ማጣርያ ተጋጣሚው የግብፁ ክለብ ኢስማሊያ የመሆኑ እድል ያመዝናል፡፡

Read 2666 times