Sunday, 03 March 2013 07:11

የአትሌቶች ስደት በአበባ አልተጀመረም፤ አያበቃም

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(2 votes)

ባለፉት 15 ዓመታት በ3 አህጉራት ወደ የሚገኙ 12 አገራት ከ25 በላይ አትሌቶች ተሰደዋል
አበባ አረጋዊ በቀጣይ ሳምንት በስዊድኗ ሁለተኛ ከተማ ጉተንበርግ በሚጀመረው የ2013 የአውሮፓ የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለሜዳልያ ተስፋ ካላቸው አትሌቶች አንዷ ሆነች፡፡ ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ስዊድንን በመወከል በሻምፒዮናው የምትሳተፈው በ1500 ሜትር ነው፡፡ አትሌት አበባ አረጋዊ የስዊድን ዜግነቷን ከ9 ወራት በፊት እንዳገኘች ዘገባዎች ያመለክታሉ፡፡ ቢጫ እና ሰማያዊውን የስዊድን ማልያ በመታጠቅ ከሳምንት በፊት በስቶክሆልም በተደረገ ውድድር ያሸነፈችው አትሌቷ በወቅታዊ ብቃቷ ከዓለም ምርጦች ተርታ እንደተሰለፈች ናት፡፡ የስዊድኗ ከተማ ጉተንበርግ የአውሮፓ የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮናን ከ29 አመታት በፊት አዘጋጅታ እንደነበር ያወሳው የአይኤኤኤፍ ዘገባ ያኔ ምንም ሜዳልያ ባታገኝም ዘንድሮ ግን በአበባ አረጋዊ እርግጠኛ የሜዳልያ ድል ይኖራል ብሏል፡፡ ባለፈው የውድድር ዘመን ሃመርቢ የተባለውን ክለብ በመወከል በ800 እና በ1500 ሜትር ውድድሮች የስዊድን ሻምፒዮን ለመሆን የበቃችው አትሌት አበባ ከሳምንት በፊት ኤስቪቲ ስፖርት ለተባለ የአገሬው ሚዲያ በሰጠችው ቃለምልልስ በአህጉራዊው ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳልያ ለማግኘት ፍላጎት እንዳላት ተናግራለች፡፡ ከኢትዮጵያዊ ወደ ስዊድናዊ ዜግነቷን በመቀየሯ በአገሯ አትሌቶችና የስፖርቱ አስተዳደር ብዙ ቅሬታ እንዳልተፈጠረ ደግሞ በሃመርቢ የአትሌቲክስ ክለብ ድረገፅ በተመሳሳይ ወቅት በሰጠችው ቃለምልልሷ አስታውቃለች፡፡ 
ከሳምንት በፊት አትሌት አበባ አረጋዊ ስዊድንን በመወከል ብስቶክሆልም ጋለን በተደረገ ውድድር በ1500 ሜትር ማሸነፏ በወቅታዊ ብቃቷ ጥሩ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ
ያስመሰከረችበት ነው፡፡ በወቅቱ ርቀቱን የሸፈነችበት 4 ደቂቃ ከ01. 47 ሰኮንዶች የዓመቱን ፈጣን ሰዓት ከመሆኑም በላይ በአዲሱ አገሯ ስዊድን የቤት ውስጥ እና የትራክ ውድድር ሁለት ሪከርዶች ሆኖ ተመዝግቦላታል፡፡
ከኢትዮጵያዊ ወደ ስዊድናዊ
አትሌት አበባ አረጋዊ በኦፊሴላዊ ድረገጿ ስለሩጫ ታሪኳ ባስቀመጠችው መረጃ ሩጫን በ16 ዓመቷ ተወልዳ ባደገችበት አዲግራት መጀመሯን ገልፃለች፡፡ ህልሟ በኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያ ማግኘት እንደሆነም ታስታውቃለች፡፡ ገና በታዳጊነቷ በአዲግራት በ800 ሜትር ስትወዳደር ቆይታ ወደ አዲስ አበባ ከተማ በመምጣት ስፖርቱን እንደቀጠለች የሚያወሳው የአትሌቷ ግለ ታሪክ፤ በዚሁ ጊዜ ከስዊድን ልምምድ ለመስራት ከመጣ አትሌት ጋር ተዋወቀች፡፡ አትሌቱ የስዊድን ዜግነት ያለው ሄኖክ ወልደገብሬል ሲሆን ከእሱ ጋር የፈጠረችው ግንኙነት ወደ ስዊድን ለመሰደድ ምክንያት እንደሆናትም ገልፃለች፡፡
አበባ በስዊድን ስቶክሆልም የነዋሪነት ፈቃድ በማግኘት ከ2009 እኤአ ወዲህ በዚያው አገር መኖር ጀምራለች፡፡ በአሁኑ ጊዜ በስዊድን ሃመርቢ ለተባለ የአትሌቲክስ ክለብ ተቀጥራ እየሰራች እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡
በመካከለኛ ርቀት ከዓለማችን ምርጥ አትሌቶች አንዷ የሆነችው አበባ አረጋዊ ወደ ስዊድን ሳትሰደድ ከ15 አመታት በፊት በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ800 ሜትር ሻምፒዮን ለመሆን በቅታ ነበር፡፡ በተመሳሳይ ወቅት በመጀመርያው አህጉራዊ ውድድር ኢትዮጵያን ወክላ በመሳተፍ በአፍሪካ ሻምፒዮና በ800 ሜትር የነሃስ ሜዳልያ አግኝታለች፡፡ ከ2010 አኤአ ወዲህ ደግሞ በ1500 ሜትር መሮጥ ቀጠለች፡፡
በ1500 ሜትር በኢትዮጵያዊነት ስዊድን ውስጥ እየኖረች መወዳደደር ከጀመረች ከዓመት በኋላ በተለያዩ የአውሮፓ አገራት በተካሄዱ የቤት ውስጥ እና የትራክ ላይ የአትሌቲክስ ውድድሮች ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብምን ብቃቷን እያሻሻለች እስከ 2012 እኤአ ቆይታለች፡፡ በ2012 እኤአ ላይ በአይኤኤኤፍ የዳይመንድ ሊግ ውድደሮች በመሳተፍ በአውሮፓ ሶስት ከተሞች አሸንፋ የአመቱ የዳይመንድ ሊግ ሻምፒዮን ለመሆን ችላለች፡፡ ከአምናው የዳይመንድ ሊግ ውድድር በለንደን የተካሄደው 29ኛው ኦሎምፒያድ ሊጀመር ከወር ያነሰ እድሜ ሲቀረው አትሌት አበባ ለኢትዮጵያ ወይንስ ለስዊድን ትሮጣለች በሚለው ጉዳይ ሁለቱ አገራት ውዝግብ ገቡ፡፡
አበባ አረጋዊ በ2009 እኤአ ላይ ዜግነት ይሰጠኝ ብላ ለስዊድን መንግስት ያስገባችው ማመልከቻ ኦሎምፒኩ ከመጀመሩ አንድ ወር ቀደም ብሎ ምላሽ አግኝቶ ነበር፡፡ ከዚሁ በኋላም የስዊድን ኦሎምፒክ ኮሚቴ በ29ኛው የለንደን ኦሎምፒያድ ስዊድንን ወክላ እንድተሳተፍ በደብዳቤ ለአለም አቀፉ አማተር አትሌቲስ ፌደሬሽን ደብዳቤ በማስገባት ሙከራ አድርጎ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ይህንኑ ሁኔታ ተቃወመ፡፡ የስዊድን መንግስት ለአይኤኤኤፍ ያቀረበው ጥያቄ ውድቅ እንዲሆን ፌደሬሽኑ ሲያመለክት አትሌቷ በኦሎምፒኩ ለኢትዮጵያ ለመወዳደር መመረጧን ከማሳወቁም በላይ በዓለም አቀፍ ውድድሮች ከአገር አገር በመዘዋወር ስትወዳደር የቆየችው በኢትዮጵያ ፓስፖርት መሆኑን ማስረጃ በማቅረብ ተከራክሮ ሊያሸንፍ ችሎ ነበር፡፡
በዚህ መሰረት ከ9 ወራት በፊት በተካሄደው 29ኛው የለንደን ኦሎምፒያድ አትሌት አበባ አረጋዊ በኢትዮጵያ ባንዲራ ተወዳደረች፡፡
በ1500 ሜትር ለፍፃሜ በመድረስም 5ኛ ደረጃ አገኘች፡፡ ከለንደን ኦሎምፒክ በኋላ አትሌት አበባ አረጋዊ ለአራት ወራት ያህል በኢትዮጵያ ልምምዷን ስተሰራ ቆይታለች፡፡ ከ ወር በፊት ደግሞ በስዊድን ዜግነት እንድትወዳደር ከአይኤኤፍ ፈቃድ አግኝታ ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ መራቋ ተረጋግጧል፡፡
ከአበባ በፊት የነበረው ስደት በኋላም ቀጥሏል
ከ9 ወራት በፊት በተደረገው የለንደን ኦሎምፒክ በ1500 ሜትር ለኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ቡድን በመሰለፍ ለፍፃሜ ደርሳ 5ኛ ደረጃ ያገኘችው አትሌት አበባ አረጋዊ በተያዘው የውድድር ዘመን ለስዊድን መሮጥ መጀመሯ ያስቆጫል፡፡ አበባ አረጋዊ በመካከለኛ ርቀት ከዓለማችን ምርጥ አትሌቶች አንዷ ነበረች፡፡ በኦል አትሌቲክስ ድረገፅ ስለአበባ አረጋዊ በሰፈረ አሃዛዊ የውጤት መረጃ ለመረዳት እንደሚቻለው አትሌቷ በዓለም አቀፍ ደረጃ በ1355 ነጥብ በ1500 ሜትር የአትሌቲክስ ውድድር አንደኛ እንዲሁም በሁሉም የአትሌቲክስ የውድድር መደቦች በ33ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡
ይህች ምርጥ አትሌት ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ መራቋ የሚያስደነግጥ ሲሆን የአትሌቶቹ ስደት በእሷ እንዳልተጀመረ እና በሷም እንደማያበቃ ከአይኤኤኤፍ ድረገፅ ኦፊሴላዊ ድረገፅ የተገኙ ሰነዶች ያረጋግጣሉ፡፡ ይህም በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ላይ የተጋረጠውን ስጋት ያባብሰዋል፡፡
ከ15 ዓመታት በፊት ወደ ተለያዩ አገራት ዜግነት በመቀየር የተጀመረው የኢትዮጵያ አትሌቶች ስደት ባለፈው የውድድር ዘመን በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩን ከአይኤኤኤፍ ድረገፅ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
ከ1998 እኤአ ጀምሮ በየዓመቱ አንድ እና ሁለት አትሌት ኢትዮጵያዊ ዜግነትን በመቀየር ለሌሎች አገራት በመሮጥ የተጀመረው ስደት በባለፈው የውድድር ዘመን እስከ 5 ደርሷል፡፡
ከዓለም አቀፉ የአማተር አትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር (አይ.ኤ.ኤ.ኤፍ) ድረገፅ የተገኙ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ባለፉት 15 አመታት በኤሽያ፤አውሮፓ፤ አሜሪካ እና ኦሺንያ ወደ የሚገኙ ከ12 በላይ አገራት ከ25 በላይ አትሌቶች ኢትዮጵያዊ ዜግነታቸውን በመቀየር በሌላ አገር ማልያ እና ባንዲራ ስር የሚወዳደሩበትን ፍቃድ እንዳገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በአይ.ኤ.ኤ.ኤፍ ድረገፅ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በ2012 እኤአ ብቻ ወደ አሜሪካ ሁለት፤ እንዲሁም ወደ ሁለቱ የአውሮፓ አገራት ስዊዘርላንድ እና ቤልጅዬም የኢትዮጵያ አትሌቶች ዜግነታቸው በመቀየር በዓለም አቀፍ ውድደሮች የመሳተፍ ፍቃድ አግኝተዋል፡፡
ዜግነታቸውን በመቀየር ለሌሎች አገራት የሚሮጡ ስደተኛ ትውልደ ኢትዮጵያዊ አትሌቶችን በመካከለኛው ምስራቅ ሁለት አገራት ባህሬንና ኳታር በብዛት ማግኘት ቢቻልም በቱርክና ሌሎች የአውሮፓ አገራት ስደተኛ አትሌቶቹ ብዛታቸው ጨምሯል፡፡ በባህሬን ከ8 በላይ ትውልደ ኢትዮጵያዊ አትሌቶች ዜግነታቸውን በመቀየር እየተወዳደሩ ናቸው፡፡
በቱርክ፤ በታላቋ ብሪታኒያ፤ በአሜሪካ በኳታር ከአንድ በላይ ትውልደ ኢትዮጵያዊ አትሌቶች እንደሚገኙም ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡
ስደተኛ የኢትዮጵያ አትሌቶችን ዜግነት በማስቀየር ከሚያወዳደሩ አገራት መካከል በአውሮፓ ስዊድን፤ ስዊዘርላንድ፤ ቤልጅዬም፤ፖላንድ፤ ስፔንና ኔዘርላንድ ሲጠቀሱ እስራኤልና አውስትራሊያም ሌሎቹ ናቸው
አትሌቶች ዜግነታቸውን በመቀየር ለሌሎች አገራት የሚወዳደሩበት ሁኔታ በዓለም አቀፍ የስፖርት ኤክስፐርቶች በሰፊው እየተተቸ ቢሆንም የአትሌቶቹን ስደት ለመግታት ማዳገቱን የተለያዩ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
በተለይ በመካከለኛ እና ረጅም ርቀት የአትሌቲክስ ውድድሮች ከፍተኛ ብቃት ያላቸው የኢትዮጵያ እና የኬንያ አትሌቶች በመካከለኛው ምስራቅ እና በአውሮፓ በሚገኙ አገራት ተፈላጊነታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡ ይሄው ሁኔታም የምስራቅ አፍሪካዎቹን የአትሌቲክስ ጀግና አገራት ውጤታማነት እያደበዘዘው እንዳይሄድ ተሰግቷል፡፡
የመካከለኛው ምሰራቅ እና የአውሮፓ አንዳንድ አገራት ዜግነታቸውን እያስቀየሩ በሚያወዳድሯቸው አትሌቶች በዓለም አቀፍ ውድድሮች በሜዳልያ ውጤት ስኬታማ ለመሆን አነጣጥረው ቢሆንም ስፖርት ከብሄራዊ ኩራት እና ማንነት ጋር የነበረውን ታሪካዊ ትስስር በማደብዘዝ ለጥቅም ብቻ እንዲካሄድ ምክንያት እየሆኑ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቶች ስደት በአገሪቱ የስፖርቱ መሰረተ ልማቶች ባለመስፋፋታቸው፤ በአስተዳደር ችግሮች እና ህይወትን የሚለውጥ ጥቅም ለማግኘት ስደቱ እየተባባሰ መጥቷል፡፡ ሊተኩ የማይችሉ ምርጥ አትሌቶችን በየጊዜው ማጣት ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያሳስባል፡፡

 

Read 5435 times Last modified on Sunday, 03 March 2013 07:19