Sunday, 03 March 2013 08:41

የማረሚያ ቤት ንቅሳቶችና አስከፊ የጤና ገፅታቸው

Written by  መታሰቢያ ካሳዬና ሠላም ገረመው
Rate this item
(1 Vote)

በዳቦ ውስጥ በሚገባ አንድ መርፌ በርካታ ንቅሣት ፈላጊዎች ይስተናገዳሉ
የተነቃሾቹ ደም ያለ ጓንት በሶፍትና በጨርቅ ይጠረጋል
የተቃጠለ ጐማ በንቅሣቱ ላይ ይደረጋል
አንዳንድ ታራሚዎች በማረሚያ ቤት ውስጥ የሚያሳልፉትን ረዥም የእስር ጊዜ የተለያዩ ሥራዎችን በመፍጠር፣ ትምህርታቸውን በመማር አሊያም ደግሞ እዛው ማረሚያ ቤት ውስጥ ላሉ ታራሚዎች አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን (እንደ ሲጃራ፣ ውሃ፣ ማስቲካ የመሣሰሉትን) በመሸጥ ከወህኒ ቤት የሚፈቱበትን ወቅት ይጠባበቃሉ፡፡
ከዚህ በተለየ በማረሚያ ቤቱ ህግና መመሪያ የተከለከሉ ሥራዎች ላይ ተሰማርተው ከማረሚያ ቤቱ ጠባቂዎች ጋር ድብብቆሽ እየተጫወቱ፣ የንቅሣት አገልግሎትን ለታራሚዎች የሚሰጡ ነቃሾችም ማረሚያ ቤት ውስጥ ይገኛሉ፡፡
እነዚህ የንቅሣት ባለሙያዎች የንቅሣት አገልግሎቱን የሚሰጡት በመፀዳጃ ቤት፣ በሻወር ቤቶችና ጭር ባሉ አካባቢዎች ሲሆን ድርጊቱን ሲፈፅሙ የተገኙ ነቃሽም ሆነ ተነቃሽ አመክሮአቸውን ከመከልከል ጀምሮ ከባድ ሥራ እንዲሠሩ የሚደረግበት መመሪያ በወህኒ ቤቱ ውስጥ ተግባራዊ ይደረጋል፡፡
“Dear mama” የሚል ፅሁፍ፣ የእሾህ አክሊል፣ የማርያምና የክርስቶስ ምስል በማረሚያ ቤት ነቃሾች በአብዛኛው የሚሠራ የንቅሣት አይነት ነው፡፡ ነቃሾቹ እነዚህን ንቅሳቶች የሚሠሩት በዘመናዊ መንገድ አይደለም፡፡ በባህላዊና እጅግ አደገኛ በሆነ የንቅሣት ዘዴዎች ነው፡፡ በቃሊቲ ማረሚያ ቤት የሚገኙ ነቃሾች ይህንን የንቅሣት ጥበብ የተማሩት በልምድ ነው፡፡
ነቃሾቹ የንቅሳት አገልግሎቱን ፈልጐ ወደ እነሱ ጋ የሚመጣውን ተነቃሽ የሚነቅሱት ያለጥንቃቄና እጅግ አደገኛ በሆነ ሁኔታ ነው፡፡ ታራሚዎቹ የንቅሳት አገልግሎት ሲፈልጉ የልብስ መስፊያ መርፌ ወደ ማረሚያ ቤቱ በዳቦ ውስጥ ተከቶ እንዲገባላቸው ያደርጋሉ፡፡ የራሱን የመነቀሻ መርፌ ያስገባ ሰው በራሱ መርፌ ሊነቀስ ይችላል፡፡ አሊያም በርካታ ሰዎች የተነቀሱበት መርፌ በእሳት እየተቃጠለ እንዲነቀሱበት ይደረጋል፡፡ ተነቃሹ ንቅሳቱ እንዲሠራለት በሚደረግበት አካባቢ የሚፈልገው ምስል እስከሚወጣ ድረስ በመርፌ በተደጋጋሚ እየተወጋ ንቅሳቱ ስለሚሰራለት በሚነቀስበት አካባቢ ብዙ ደም ይፈሰዋል፡፡ ነቃሹ ይህንን ከተነቃሹ ክንድ፣ ደረት ወይም ጀርባ ላይ የሚፈሰውን ደም ለመጥረግ የሚጠቀምበት መከላከያ (ጓንት) የለም፤ በንፁህ እጁ በሶፍት ወይም በቁራጭ ጨርቅ ደሙን ይጠርገዋል፡፡ በንቅሳቱ ላይ የሚፈሰውን ደም ለማስቆምና የተሠራውን ምስል ለማድመቅም ነቃሹ የተቃጠለ ጐማ በመርፌ በመጠንቆል የተሠራውን ዲዛይን እየወጋ ቅርፅ እንዲይዝ ያደርገዋል፡፡
ከዚያም በመርፌ እየተወጋ በተሠራው ምስል ላይ የተቃጠለውን ጐማ በመደምደም ቅርፁ (ምስሉ) ጐልቶ እንዲወጣ ያደርገዋል፡፡
የተሠራው ምስል በደንብ መያዙና የማይለቅ መሆኑ የሚረጋገጠው በንቅሳቱ ላይ ያለውን ደም በሶፍት በመጥረግ ምስሉ ከደሙ ጋር ተጠርጐ ባለመውጣቱ ንቅሣቱ ይዟል ይባላል፡፡ ካልያዘ ግን በድጋሚ ይሠራል፡፡ ከአምስት ቀን በኋላ ቁስሉ ድኖ ንቅሣቱ ይወጣል፡፡
ነቃሹ ከሰዎች እይታ በተገለሉ ቦታዎች በመፀዳጃ ቤት፣ በሻወር ቤቶች፣ በመኝታ አካባቢዎች ላይ የንቅሳት አገልግሎቱን በሚሰጥበት ጊዜ የማረሚያ ቤቱ ጠባቂዎችና ፖሊሶች እንዳይመጡ የሚጠብቅና አስቀድሞ ምልክት የሚሰጥ ሰው ያቆማል፡፡
ይህ ምልክት ሰጪም ሥነ ስርዓት አስከባሪዎች ወይንም ፖሊሶች ወደ ሥፍራው መምጣታቸውን ካየ “ስድስት” በሚል ቃል ለነቃሹ ምልክት ይሰጠዋል፡፡
ይህ ማለት ፖሊስ መጥቷል ማለት እንደሆነ የሚገባው ነቃሽም ሥራውን በፍጥነት ያቆማል፡፡ በማረሚያ ቤቱ ህግና ደንብ መሠረት ማንኛውም ስለታምና ሹል ነገሮች ወደ ማረሚያ ቤት እንዲገቡ አይፈቀድም፡፡ ይሁን እንጂ ነቃሽም ሆነ ተነቃሽ ይህንን የማረሚያ ቤቱን ጥብቅ መመሪያ በመጣስ ሹል ነገሮችን ሆነ ስለታም ምላጮችን ወደ ውስጥ ለማስገባት መንገድ አላጡም፡፡
ታራሚዎች የተከለከሉ ነገሮችን ወደ ውስጥ ለማስገባት ከሚጠቀሙባቸው ነገሮች አንዱ ዳቦ ነው፡፡ ንቅሳት የሚፈልግ ሰው ቤተሰቦቹ ወይም ጠያቂዎቹ በዳቦ ውስጥ መርፌ ከተው እንዲያስገቡለት ያደርጋል፡፡ በዚህ መንገድ መርፌውን ወደ ማረሚያ ቤቱ ማስገባት እንደልብ ስለማይቻልና ምናልባትም በጥርጣሬ ሊያሲዝ ስለሚችል ታራሚዎች በዳቦ አማካኝነት ወደ ማረሚያ ቤቱ የገባችውን መርፌና ምላጭ በጋራ ይጠቀሙባቸዋል፡፡ ጐይቶም ሀለፎም (ጐቲካ) በቃሊቲ ማረሚያ ቤት በሥርቆት ወንጀል ተከሶ የሰባት ዓመታት እስር የተፈረደበት ታራሚ ነው፡፡ ጐይቶም በማረሚያ ቤቱ ውስጥ የንቅሣት አገልግሎት በመስጠት የሚታወቅ ነቃሽ ነው፡፡ እስከ አሁን ድረስ 48 ለሚደርሱ ሰዎች ንቅሣት ሠርቷል፡፡ ጐይቶም የእስር ጊዜውን ያቀናቀቀ ቢሆንም በንቅሣት ሥራ ላይ ተገኝቶ አመክሮ በመከልከሉ እስከ አሁንም ከእስር አልተፈታም፡፡
ጐይቶም ማረሚያ ቤቱ የንቅሳት ሥራውን ህገወጥ ነው ማለቱን አይስማማም፤ ይልቁንም ሥራው እንደሌሎቹ የማረሚያ ቤት ውስጥ ሥራዎች ታይቶና ቦታ ተሰጥቶት መደበኛ ሥራው አድርጐ መሥራት ቢችል ጥሩ እንደሆነ ይነገራል፡፡ “ይህ እንደውም ሥራዬን በኃላፊነትና በጥንቃቄ ለመሥራት ያስችለኛል” ይላል፡፡ ሥራው መደበኛ ሥራው ሆኖ ያለመሳቀቅ ቢሠራ በቀን 20 እና 30 ሰዎችን ለመንቀስ እንደሚችልም ይገልፃል፡፡ ከሦስት ዓመታት በፊት ሰው በመደብደብ ወንጀል ተከሶ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት የገባው ሙሉጌታ አየነው፤ በማረሚያ ቤቱ የምግብ ኮሚቴ አባል ሆኖ የታራሚዎችን የምግብ ሁኔታ ይከታተላል፡፡
የሙሉጌታን ፈርጣማና ሞላ ያለ ሰውነት ይበልጥ ያሣመረው የተለያዩ ምስሎችንና ፅሁፎችን የያዘው ንቅሣቱ ነው፡፡ “Dear mama” ከሚለው ፅሁፍ አንስቶ የጌታ ምስልና የማርያም ምስል ያሉባቸው ንቅሣቶች ሰውነቱ ላይ ተነቅሷል፡፡ የስዕሎቹ ማማርና የንቅሳቱ ውበት ብዙዎችን ያስገርማል፡፡ የገደሉትን ሰው ስም፣ ሃይማኖታዊ ነገሮችን፣ የሚያፈቅሩትን ሰው ስም በክንዶቻቸው፣ በጀርባቸውና በደረታቸው ላይ የሚነቀሱ በርካታ ታራሚዎች መኖራቸውን የማረሚያ ቤቱ ነቃሽ ጐይቶም ይነገራል፡፡
በተነቀሰው ንቅሳት ሣቢያ ታሞ ሆስፒታል የሚገኘው ደረሰ ግርማ የተባለው ሌላው ታራሚ በደረቱ ላይ የሚወዳት ፍቅረኛውን ስም ተነቅሷል፡፡
“ፍቅረኛዬ ከዳችኝ ከሌላ ወንድ ጋር ተቃቅፋ ስትሄድ አይቼአት በጣም ስለተናደድኩ በጩቤ ወጋኋት፤ ድርጊቱን ከፈፀምኩ በኋላ ግን በጣም ተፀፀትኩ፡፡
ስለዚህም ህመሟ እንዲሰማኝ ስሟን ደረሴ ላይ ተነቀስኩ” ብሏል፡፡ ይህ በማረሚያ ቤቱ ውስጥ እየተካሄደ ያለው የንቅሳት ሥራ ከጤና አኳያ እጅግ አደገኛ የሆኑ ችግሮችን ሊያስከትል እንደሚችል የጤና ባለሙያዎች ይነገራሉ በኤችአይቪ ኤድስ ላይ ለበርካታ ዓመታት በመሥራት የሚታወቁት ዶ/ር አርሴዶ ሌንዴቦ እንደሚናገሩት፤ ድርጊቱ በደም ንክኪ ሊተላለፉ የሚችሉ በሽታዎችን በቀላሉ ከአንዱ ወደ አንዱ ሊያስተላልፍ ይችላል፡፡ ለንቅሳት አገልግሎት የሚውለው መርፌ ኤችአይቪ ኤድስን፣ የመተላለፍ ዕድሉ እጅግ ከፍተኛ የሆነውንና በአሁኑ ወቅት በአገራችን ከፍተኛ ስርጭት ያለውን Heptites B የተባለውን በሽታና ሌሎች በደም ንኪኪ ሊተላለፉ የሚችሉ በሽታዎችን በቀላል መንገድ እንዲሰራጩ ማድረግ እንደሚችልም ዶ/ር አርሴዶ ይገልፃሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሹልና ስለታም ነገሮቹ የሚያዙበት ሁኔታ ለዝገትና ለመበከል የሚዳርጋቸው ከሆነ የቁስል ኢንፌክሽን እንዲፈጠርና ተነቃሹን ለከፍተኛ የጤና ችግር እንዲዳረግ የሚያደርጉበት ሁኔታም እንዳለ ባለሙያው ይናገራሉ፡፡
ስለታም ነገሮች ወደማረሚያ ቤቶች እንዳይገቡ የሚደረግበት ምክንያት መኖሩን የጠቀሱት ዶክተሩ፤ እነዚህ አሁን ለንቅሳት አገልግሎት ዋሉ የተባሉት ስለታምና ሹል ነገሮች በማረሚያ ቤቱ ውስጥ የሚገኙ ታራሚዎች በደል ሊካካሱበት፣ ዓይን ሊያጠፉበት፣ ደም ሥር ሊቆርጡበትና በታራሚው ላይ አደጋ እንዲደርስ ሊያደርጉበት ይችላሉ ብለዋል፡፡ በእነዚህ ነገሮች ላይ ጥብቅ ክትትል መደረግ እንዳለበትና እጅግ አደገኛ በመሆናቸውም ማስቆም እንደሚገባ ዶክተሩ ተናግረዋል፡፡
በማረሚያ ቤት ውስጥ የሚሰጡ የንቅሳት አገልግሎቶችን መከልከልና ማገድ ተጠቃሚዎቹ ድርጊቱን ይበልጥ በሚስጢር እንዲፈጽሙ ስለሚያደርጋቸውና በዚህም የተነሣ ችግር ቢያጋጥማቸውም የሚደርስባቸውን ቅጣት ፈርተው ከመናገር ስለሚቆጠቡ እጅግ የከፋ የጤና ችግር ሊያስከትልባቸው ይችላል ያሉት ሐኪሙ፤ ክልከላው አማራጭ ያስቀመጠና መፍትሔ ያለው ሊሆንም ይገባዋል ብለዋል፡፡ ፍላጐት እስካለ ድረስ ክልከላ ውጤት አያስገኝም የሚሉት ዶክተሩ፤ የማረሚያ ቤት አስተዳደሩ የንቅሳት ሙያና ዕውቀት ያላቸው ታራሚዎች አገልግሎት ለሚፈልጉ ሰዎች አገልግሎታቸውን በንጽህናና ደረጃውን በጠበቀ መንገድ በህጋዊ ሁኔታ እንዲሰጡ የሚያስችል አሠራር ቢኖረው መልካም መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡
ታራሚው በንቅሳት ሙያ ያለውን ዕውቀት አዳብሮ በዘመናዊ መንገድ አገልግሎቱን ለሚፈልጉ ሰዎች እየሰጠ ራሱንም ሆነ ማረሚያ ቤቱን በገንዘብ ሊደጉም የሚችልበት አሠራር እንዲኖር ማድረግ እንደሚቻልም ዶ/ሩ ይገልፃሉ፡፡
ማረሚያ ቤቱ ለዘመናት በልምድና በዘፈቀደ የሚካሄደው የንቅሳት አገልግሎት ቀን ወጥቶለት የነቃሹንም ሆነ የተነቃሹን ጤና በማይጐዳና ለከፍተኛ ችግር በማይዳርግ መልኩ እንዲካሄድ ማድረጉ ትልቁ መፍትሔ መሆኑ እሙን ነው፡፡ ዶክተሩ እንዳሉት ፍላጐት እስካለ ድረስ ክልከላው ውጤት አያመጣምና፡፡

Read 4593 times