Sunday, 03 March 2013 08:44

እሳት ደጉ እሳት ክፉ!

Written by  ከትርጉም ሚካኤል pinumed@gmail.com
Rate this item
(0 votes)

(እውነተኛ ታሪክ ላይ የተመረኮዘ ወግ)
ውድ አንባብያን፤ መቼም ርእሱኑ ስታነቡ ለሚፈጠረው ብዥታ እኔ ይቅርታ ልጠይቅና መድረሻው ላይ ሳትደርሱ ግን እውነቱ አይገለጥምና የጽሞና ንባብ ሲታከልበት እውነትም አሪፍ ርእስ እንደምትሉ ይሰማኛል፡፡ 

ጨዋታው ወግ ቢጤ ነው፡፡ ከአንድ ወዳጄ ጋር ወግ ስንጠርቅ ወጉ ከማስደመም አልፎ አዝናናኝና፤ ከዚያስ አትሉም? ከዚያማ ጻፍኩታ፡፡
አቶ እሳቱ ፈቀደ የሚባል ሰው (ለዚህ ጽሁፍ ሲባል ስሙ የተቀየረ) በአዲስ አበባ ተ/ሐይማኖት አካባቢ በተለምዶ በርበሬ ተራ፤ ጎማ ተራ፤ ምን አለሽ ተራ የሚባል አካባቢ የሚኖር ግለሰብ ሲሆን በሆነ የፖለቲካ ክፍተት የራሱ ያደረጋት ከአስፋልት ዳር የምትገኝ ሁለት ክፍል የቀበሌ መኖሪያ ቤት ያለውና የፊት ለፊቱን ክፍል ለጎማ ነጋዴ 280 ብር እያከራየ፤እርሱ ከኋላ ካለችው ክፍል ውስጥ ከእጅ ወደ አፍ የሚባል ኑሮውን የሚገፋ ብላቴና ነበር፡፡
በአንድ ጊዜና አጋጣሚ ታዲያ በድቅድቅ ጨለማ የእሳት ቃጠሎ ይነሳና ቤቱ መንደድ ሲጀምር ወደ አስፋልት ዘሎ ወጥቶ እሪታውን ያቀልጠዋል፡፡ እሪ…እሪ…እሪ…
የአካባቢው ሰው የድረሱልኝ ጥሪውን ሰምቶ በመውጣት፤እሳቱ አንዲት በእድሜ የገፉ አሮጊት ቤት ከመድረሱ በፊት ተረባርቦ ያጠፋዋል፡፡ (ይህቺን አሮጊት ልብ ይሏል)
ፖሊስ በቦታው ይደርስና የእሳቱ መነሻ የሆነውን ምክንያት ለመመርመር ለአቶ እሳቱ ጥያቄ ያቀርባል፡፡
ፖሊስ - አቶ እሳቱ፤ ቃጠሎው ስንት ሰአት ተነሳ? ለቃጠሎው መነሻ የሚሏቸው ነገሮች ይኖሩ ይሆን?
አቶ እሳቱ - እሳቱ በግምት ከሌሊቱ 9 ሰአት አካባቢ የተነሳ ይመስለኛል፡፡ ነገር ግን ፖሊስ እንዲያውቅልኝ የምፈልገው ነገር ከቃጠሎው በፊት ከባድ ፍንዳታ ሰምቻለሁ፡፡
ፖሊስ - ምን ማለት ነው?
አቶ እሳቱ - እውነት ለመናገር በ1997 ምርጫ ወቅት እከሌ የተባለ የፖለቲካ ፓርቲ የቅስቀሳና ፕሮጋንዳ ሐላፊ ሆኜ እሰራ ስለነበረ ከእርሱ ጋር በተያያዘ ቂም የቋጠሩ ሰዎች እንደማይጠፉ ይሰማኛል፡፡
ፖሊስ - ጉዳዩ ፖለቲካዊ ነው እያሉ በመሆኑ ጉዳዩን አጣርተን ስንፈልግዎት
እንጠራዎታለን ---- ብሎ አሰናበታቸው፡፡
በማግስቱ ታዲያ የመርካቶ ነጋዴ በአቶ እሳቱ ላይ የደረሰውን የእሳት ቃጠሎ ምክንያት በማድረግ የወደመባቸውን ንብረት ለመተካት ብርድ ልብስ አንጥፎ ብር ይለምንና በሳምንት ጊዜ ውስጥ በጠቅላላው 80.000 ብር አሰባስቦ ምስክር ባለበት ለቀበሌው አስተዳደር ያስረክባል፡፡
በዚሁ ብርም የአካባቢው ነጋዴና ቀበሌው በተቃጠለው ቤት ምትክ ሰፊ መጋዘን በብሎኬት ገንብቶ ያስረክባቸዋል፡፡ አቶ እሳቱ ይህንኑ መጋዘን በወር 15.000 ብር እያከራዩ አያት አካባቢ መኖሪያ ቤት ተከራይተው የተንደላቀቀ ኑሯቸውን ይጀምራሉ፡፡ አዲዮስ ድህነት!
በአንድ አጋጣሚ ታዲያ አቶ እሳቱ በአንድ የከተማችን “ዊንተር ፓላስ” የተባለ እውቅ ውስኪ ቤት የሩሲያ ቮድካቸውን ከወዳጃቸው ጋር እያጣጣሙ ሲጨዋወቱ ወዳጅ እንዲህ ይላል፤
“በእውነት ለመርካቶ ነጋዴ ምስጋና ልታቀርብለት ይገባል፤ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከጐንህ ሆኖ አስፈላጊውን ድጋፍ አድርጐልሃል?”
“ለእኔ የደረሰልኝ መች የመርካቶ ነጋዴ ሆነ፡፡” አሉ አቶ እሳቱ፡፡ “ለእኔ የደረሰው እሳት ደጉ ነው፡፡ እኔ እሳት ነው ዘዴ፡፡
የመርካቶ ነጋዴማ ስንት ዘመን ሙሉ ተቸግሬ መች ዞር ብሎ አይቶኝ ያውቃል? ዛሬ እሳት ቤቴን ቢያነደው ላግዝህ አለኝ እንጅ፡፡
ያቺ የእኔ አሮጊት ጐረቤት እሳቱ የኔን ቤት አቃጥሎ እርሷ ቤት ጋ ሲደርስ መቆሙ አናዷት ምን እንዳለች አልሰማህም?” ወዳጅም “ምን አለች?” ሲል ጠየቀ
“አሁን ይሄን እሳት ምን አድርጌው ነው፡፡ የእርሱን ቤት አቃጥሎ እኔ ጋር ሲደርስ የሚቆመው? ክፉ እሳት፤ ምቀኛ እሳት፤ አበሻ እሳት፤ ነገረኛ እሳት” አለች አሉ፡፡
ድኅረ ወግ- አንድ ወዳጄ ይሄን ጨዋታ ባጫውተው በጣም ተገርሞ፤“ለዚህ ሰውማ ምን እሳት ብቻ--- “ኢሳትም” ዘመዱ ነው” ብሎ እርፍ፡፡ ቸር ሰንብቱ፡፡

 

Read 2934 times