Saturday, 09 March 2013 10:58

እኔ እያለቀስኩ እሸምታለሁ እሷ እየዘፈነች ትፈጫለች

Written by 
Rate this item
(5 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን ሁሉም የስሜት ዓይነቶች ይኖሩበት የነበረ አንድ ደሴት ነበረ ይባላል፡፡ እነዚህም ስሜቶች ደስታ፣ ሐዘን፣ ዕውቀት እንዲሁም ፍቅርን ጨምሮ በርካታ ሌሎች ነበሩ፡፡ አንድ ቀን ያ ደሴት ሊሰምጥ ነው የሚል ማስታወቂያ ተነገረ፡፡ ሁሉም በየፊናቸው ጀልባ እየሰሩ፣ ዘር ማንዘሮቻቸውን ይዘው፤ እግሬ - አውጪኝ እያሉ ከደሴቲቱ ወጡ፡፡ ከፍቅር በስተቀር፡፡ ፍቅር፤ “የመጣው ይምጣ እንጂ ስንት ዘመን የኖርኩበትን ደሴት ጥዬ አልሄድም” አለ፡፡ “የመጨረሻዋ ቅጽበት መጥታ ምርጫ ካላጣሁ በስተቀር ንቅንቅ አልልም” ሲል ወሰነ፡፡ ደሴቱ ሊሰጥም ተቃረበ፡፡ ፍቅር እርዳታ የሚያሻው ሰዓት ደረሰ፡፡

በአንድ ትልቅ ጀልባ ላይ ሆኖ ሀብት እየተኮፈሰ በፍቅር አጠገብ ሲያልፍ ታየ፡፡ ይሄኔ ፍቅር፤ “ሀብት ሆይ! ከአንተ ጋራ ልትወስደኝ ይቻልሃልን” አለና ጠየቀው፡፡ ሃብትም፤ “ወዳጄ ፍቅር! በጀልባዬ ላይ ስፍር ቁጥር የሌለው ብርና ወርቅ፣ ሌላም ጌጣጌጥ ስለከመርኩኝ፤ አንተን የማስቀምጥበት ቦታ የለኝም፡፡ ፍቅርም ሀብት እንደማይወስደው ሲያውቅ፤ ውብ በሆነች ጀልባ ላይ ኮርቶ ተቀምጦ እየፈሰሰ በአጠገቡ እያለፈ ወዳለው ወደ አያ ከንቱነት ሄዶ፤ “ከንቱነት ሆይ እባክህ ከዚህ ከሚሰምጠው ደሴት አውጥተህ ወደ ዳርቻው ውሰደኝ፤ እርዳኝ” አለው፡፡ “አዬ፤ አየህ አቶ ፍቅር አንተ ሁለመናህ እርጥብ ነው፡፡ ውብ ጀልባዬን ታረሰርስና ታቆሽሽብኛለህ፡፡ ስለዚህ አልጭንህም” ሲል ይመልሳል፡፡ ቀጥሎ ፍቅር በአካባቢው ወደነበረው ወደ አቶ ሐዘን ሄደና፤ “አብሬህ እሄድ ዘንድ ፍቀድልኝ” አለና ተማፀነው፡፡

“አይ አቶ ፍቅር፤ በጣም አዝናለሁ፡፡ እኔ አሁን ብቻዬን መሆን ያለብኝ ሰዓት ነው” ቀጥሎ በፍቅር አጠገብ የምናልፈው ደስታ ነበረችና ወደሱዋ ተጣራ፡፡ ደስታ ግን በጣም ፍንድቅድቅ ብላ ስለነበር የፍቅርን ድምጽም ለመስማት ሳትችል አልፋው ሄደች፡፡ በዚህ መካከል አንድ ድንገተኛ ድምጽ ተሰማ፡፡ “ፍቅር ሆይ፤ ና ወደኔ እኔ እወስድሃለሁ” አለ፤ ያ የአንጋፋዋ እመቤት ድምጽ፡፡ ፍቅር ይህን የተባረከ ዕድል በማግኘቱ እጅግ ሀሴት ተሰምቶት ወዴት እንደሚሄዱ እንኳ ለመጠየቅ ጊዜ አልወሰደም፡፡ ወደ አንድ ደረቅ ምድር በደረሱ ጊዜ አንጋፋዋ እመቤት ወደራስዋ አቅጣጫ ተጓዘች፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ፍቅር ወደ አንጋፋው ዕውቀት ሄደና፤ “አሁን እርዳታ ያደረገችልኝ አንጋፋ እመቤት ማን ናት?” ሲል ጠየቀው፡፡ ዕውቀትም፤ “ጊዜ ናት” ሲል መለሰ፡፡

“ጊዜ? ጊዜ ለምን ትረዳኛለች” አለና በአግራሞት ጠየቀ፡፡ ዕውቀትም ጥልቅ ጥበባዊ ፈገግታ ፈገግ ብሎ፤ “ፍቅር ምን ያህል ዋጋ እንዳለው የሚያውቅ ዕውቀት ብቻ ነው” ሲል መለሰ፡፡ *** በወርሃ የካቲት ፍቅር፣ ዕውቀትና ጊዜ አይንሳን፡፡ ለውጥ ምን ጊዜም አይቀሬ ነው፡፡ ከሚሰምጥ ደሴት ግን ያውጣን፡፡ ዱሮ ስናውቀው በ60ዎቹ የየካቲት ወር ብዙ ነገር አርግዞ ነበር፡፡ የዛሬ አርባ ዓመት ግድም የለውጥ ንፋስ በየአቅጣጫው ወጀቡን ይዞ መምጣቱ ይታወሰናል፡፡ የሁሉም መሽከርክሪት የሥርዓት ለውጥ ነበር፡፡ የቤንዚን ዋጋ መናር፣ ከዚያ የተያያዘው የታክሲዎች ሥራ ማቆም፣ የወሎ ረሃብ፣ የተማሪዎች እንቅስቃሴ የመምህራን ሥራ ማቆም፣ የወታደሮች የደሞዝ ጭማሪ ጥያቄ፣ የሙስሊሙ ህብረተሰብ የሃይማኖት እኩልነት ጥያቄ፣ ወዘተ ብርቱ የለውጥ ጥንስስ ሆነው ከተፍ ያሉት በወርሃ የካቲት ነበር፡፡ ጠቅለል አድርገን ስናነጥራቸው የኢኮኖሚ ጥያቄና የፖለቲካዊ አስተዳደር በደል ጥያቄዎችና የሃይማኖት እኩልነት ጥያቄዎች ግዘፍ - ነስተው እናገኛቸዋለን፡፡ ያኔ የአለም አቀፉ ፖለቲካ ባጠቃላይ ሲታይ ሁለት ጐራዎች ነበሩት፡፡

ስለሆነም ማናቸውም አገር የውስጥ ችግሩን ለመፍታት የውጪ እጅ ካስፈለገው ወደነዚህ ሁለት ጐራዎች ያንጋጥጣል፡፡ ያኔ ያላደጉት አገሮች ቻይና፣ ህንድ፣ አፍሪካ እና ላቲን አሜሪካ ነበሩ፡፡ አንጋፎቹ ጐራዎችም ቋታቸውን የሚሞሉት የነዚህኑ ያላደጉ አገሮች ድንግል አንጡራ ሀብት በመቦጥቦጥ ነበር፡፡ ዘመን ተሻረ፤ ሁኔታዎች ተለዋወጡ፡፡ የምዕራቡ ኃይል ብቸኛ ጐራ ሲሆን ሌሎቹ ምዕራብ ያልሆነው ክፍል ተቃራኒ ጐራ ናቸው፡፡ እነቻይናና ህንድ ወደላይ ወጡ፤ ያደጉ አገሮች ሆኑ፡፡ ላቲኖችም ወደላይ ተጓዙ፡፡ ባለበት የሚረግጡትና ቆሞ ቀር የሆኑት ከሞላ ጐደል የአፍሪካ አገሮች ናቸው፡፡ ስለዚህ ዛሬም ለውጥ ለማምጣት ጠረጴዛ ዙሪያና ምርጫን ለመንተራስ ቢፍጨረጨሩም ገና ከጫካ አልወጡም፡፡ ጠመንጃ ከመንከስ አልተላለቁም፡፡ ከጐሣ ግጭት አልወጡም፡፡

የበሽታ መናኸሪያ የጉስቁልና መፈልፈያ ከመሆን ገና አልዳኑም፡፡ የዱሮዎቹ ትውልዶች ጭቆናን ለመቃወም፣ ግፍን ለመጋፋትና የውስጥ ታጋዮቹ ብዝበዛን ለመታገል ቆርጠው ይነሱ ነበር፡፡ ለውስጥ ታጋዮቹ ዓለም አቀፋዊ ኃይሎችም ያግዟቸው ነበር፡፡ ዛሬ ያ የለም፡፡ ሆኖም የማይለወጥ ነገር የለም፡፡ ሁሉም ነገር ይለወጣል፤ ከለውጥ ህግ በስተቀር (Everything changes except the law of change እንዲል ፈረንጅ) ሀገራችንም ከለውጡ ሽታ መጋራቷ አይቀሬ ነው፡፡ ቢያንስ “የመሬት ላራሹ” ጥያቄን ምላሽ ማግኘት ማስታወስ ከቻልን ወርሃ የካቲትን ልናሰምርበት እንችላለን፡፡ ያልተመለሱ ጥያቄዎችን ዛሬም አጽንኦት መስጠት አስፈላጊ ነው - ዲሞክራሲው ሀቀኛ መሆን አለበት፡፡ የኢኮኖሚ ብዝበዛ ተቋማዊም ሆነ ድርጅታዊ፤ አሊያም ግለሰባዊ ዛሬም በፅኑ ልንዋጋው ይገባናል፡፡

ከውጪ ኃይሎች በማናቸውም መልክ የሚመጣውን አሉታዊ ተጽእኖ ዐይናችንን ከፍተን ወገባችንን አጥብቀን መቋቋም አለብን፡፡ የሃይማኖት ችግር የራሳችን ይሁን የውጪ ኃይሎች ፍላጐት ብለን አጥርተን ማሰብ አለብን፡፡ የፍትሕና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ በተግባር መመለስ አለበት፡፡ ህዝብ እየለፋ እየታተረ የሚገነባውን ኢኮኖሚ የባለጊዜ ልጅ ልጆች የሚንዱ ከሆነ “እኔ እያለቀስኩ እሸምታለሁ፣ እሷ እየዘፈነች ትፈጫለች” ይሆናል፡፡

Read 5907 times