Saturday, 09 March 2013 11:30

‘ኢንዴንጀርድ ስፒሽስ…’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)

ስሙኝማ…የምር ግን፣ እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ነገረ ሥራችን ሁሉ ወደ ‘ሰርቫይቫል’ እየወረደ ሲሄድ… አለ አይደል… ከእነቤተሰባችን እንዳይርበን፣ እንዳይጠማን መሸሸጊያ መፈለግ እዚች አገር ላይ የተለመደ ነው፡፡ ልጄ…‘ፕሪንሲፕሉ’ ሳይፈርስ ሆድ ባዶ ከሚሆን ‘ፕሪንሲፕሉን’…አለ አይደል… “ውሀ በልቶት…” ሆድ ቢሞላ ይሻላል የሚለው አስተሳሰብ እየበዛ ሲሄድ አብረው ውሀ የሚበላቸው እሴቶች መአት ናቸው፡፡ እንዴት ሰነበታችሁሳ! ስሙኝማ…ከአንጀታቸው “ለሀቅ፣” “ለክሬ…” የሚሉ ሰዎች በሚያስደነግጥ ፍጥነት ‘ኢንዴንጀርድ ስፒሽስ’ እየሆኑ ነው፡፡ ሁሉም ብልጥ፣ ሁሉም ‘ስትሪት ስማርት’ እንደሚባል አይነት እየሆነ ነው፡፡

ግርም የሚላችሁ ነገር ምን መሰላችሁ…ለምንድነው ራሳችንን ብልጥ የምናደርግ ሰዎች ከእኛ በስተቀር ድፍን አገር ሞኝ እንደሆነ ነገር አድርገን የምንቆጥረው! እንዴ እኛ ቤት ብልጥነት ዶፉን ቢለቀው እኮ እዛኛው ቤት ደግሞ ካፊያው አይጠፋም፡፡ “ነጋዴ ነኝ…” የሚለውም፣ “ፖለቲከኛ ነኝ…” የሚለውም፣ “ኢንቴሌክቿል ነኝ…” የሚለውም“ ላይ አካባቢ ሰዎች አሉኝ…” የሚለውም፣ ብቻ ምን አለፋችሁ ሁሉም ብልጥ ሲሆን አሪፍ አይደለም፡፡ አሀ…አገር በብልጦች ብቻ አትገነባማ! ቂ…ቂ…ቂ… ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ይቺን ከሆነ ዌብሳይት ላይ ያገኘኋትን ቀልድ ስሙኝማ…ስኮትላንዳውያን ከጋብሮቮዎች ጋር የሚቀራረብ የ‘ቆንቋናነት’ ባህሪይ አላቸው ይባላል፡፡ እናማ…አንድ ቀን አንድ ስኮትላንዳዊና አንድ የጋብሮቮ ተወላጅ በአንድ ሰብአዊ ጉዳይ ላይ የሚሰጥ ሌክቸር ላይ ይገኛሉ፡፡

ሌክቸሩ እንዳለቀ ከተሳታፊዎቹ ለበጎ አድራጎት ገንዘብ የመሰብሰብ እንቅስቃሴ ይጀመራል፡፡ በዚህ ጊዜ ስኮትላንዳዊው ምን ቢሆን ጥሩ ነው…ራሱን ስቶ ይወድቃል፡፡ ይሄን ጊዜ የጋብሮቮው ተወላጅ ደግሞ ተሸክሞት ወጣ ይላል፡፡ እናላችሁ…አስቸጋሪ ነው፡፡ ‘ኢንዴንጀርድ ስፒሽስ…’ ዝርዝር ውስጥ የሚገቡ እየበዙ ነው፡፡ አሁን ለምሳሌ እንደው የዓለም ነገር አልሆን ሲለን፣ ሁሉ ነገር የእንግድድ ሲሄድብን እንደው ‘ለእግዚአብሔር የቀረቡ’ የምንላቸውን ሰዎች አማክረን ቢያንስ ቢያንስ እውነተኛ ከልብ የመነጨ መጽናኛ ቃላት እናገኛለን፡፡ አሁን ግን ነገር ተገለባበጠና…‘የፌስቡክ ዘመን’ ሆነና፣ ለዘመናት አብረውን የቆዩ እሴቶች ኋላ ቀር ተባሉና፣ ምግባርን በተመለከተ በሰው ልጅና በሌሎች ፍጡራን መካካል ያለው ክፍተት ጠበበና…አለ አይደል…ለጽድቅ ያበቁኛል፣ ይጸልዩልኛል፣ “በሰማይ ቤት ይመሰክሩልኛል…” የምንላቸው የሀይማኖት አባቶች ‘ኢንዴንጀርድ ስፒሽስ…’ እየሆኑ ነው፡

፡እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… ይሄን ጉዳይ ካነሳን አይቀር፣ ይቺን ስሙኝማ… ቄሱ ይችን ዓለም ሊሰናበቱ አልጋ ላይ እያሉ ሁለት ኮሚኒስቶች እንዲመጡላቸው ዘመዶቻቸውን ጠየቁ፡፡ እንደጠየቁትም ከየትም ከየትም ተፈልገው ሁለት ኮሚኒስቶችም መጡላቸው፡ ኮሚኒስቶቹ ራስጌያቸው ቀኝና ግራ ቆሙና ቄሱ የሁለቱን እጆች ያዙ፡፡ እና…ቄሱ ምንም አይናገሩም ምንም አይሉም፡፡ ኮሚኒስቶቹ ግራ ይገባቸውና “የፈለጉን እንዲህ ግራና ቀኝ ቆመን እጃችንን ለመያዝ ብቻ ነው እንዴ?” ብለው ይጠይቋቸዋል፡፡ ቄሱም “አዎ” ሲሉ ይመልሳሉ፡፡ ኮሚኒስቶቹም ነገሩ አልገባ ብሏቸው እንደዛ ማድረጋቸው ምክንያቱን ሲጠይቋቸው ቄሱ ምን ብለው ቢመልሱ ጥሩ ነው፡፡ “እንደ እየሱስ መሞት ፈልጌ ነው፡ እሱም እንዲሁ በሁለት ሌቦች መካከል ነው የሞተው፡፡” ቄሶቹም ለራሳቸው፣ ምእመናኑም ለራሳቸው ይሏችኋል እንዲህ ነው፡፡ እናላችሁማ…እምነት የሚጣልባቸው ሰዎች ‘ኢንዴንጀርድ ስፒሽስ’ እየሆኑ ነው፡፡ ለአደራ የሚበቃ እየተመናመነ በሄደ ቁጥር መልካም አይደለም፡፡

የግለሰብና የቡድን ብቻ ሳይሆን ለአገር አደራ የሚበቃም ማግኘት አስቸጋሪ ይሆናል፡፡እምነት የሚጣልባቸው (‘ጄኒዊን’ ብትሉትም ያስኬዳል፡፡) ምርቶች “ኢንዴንጀርድ…” እየሆኑ ነው፡፡ (እነ እንትና…እኔ የምለው… ውስኪውም ‘መወጋቱ’ ቀርቶ ልክ ከፋብሪካ እንደወጣ መታሸግ ጀምሯል የሚሉት እውነት ነው እንዴ!) ከአንገት ሳይሆን ከአንጀት…አለ አይደል…“መልካሙን ሁሉ እመኝልሀለሁ…” መባባል ‘ኢንዴንጀርድ…’ እየሆነ ነው፡፡ ሲያደናፍቀን፣ ደንበርበር ሲያደርገን “እኔን ይድፋኝ…” የሚል አባባል ‘ኢንዴንጀርድ…’ እየሆነ ነው፡፡ የምር እኮ የሚያሳዝን ነው…አይደለም “እኔን…” ምናምን መባባል በፊት ለፊት ባይሆንም በሆዳችን “እያየ አይሄድም እንዴ… ደንባራ!” ምናምን የምንል ነን የበዛነው፡፡ ደግሞላችሁ…ተገልጋዩን “የአገሬ ልጅ…” “የብሔረሰቤ አባል…” “የሚስትረሴ ታናሽ ወንድም…” ምናምን ሳይሉ ከልባቸው ያለ አድልዎ የሚያገለግሉ የሥራ ሀላፊዎች ‘ኢንዴንጀርድ ስፒሽስ’ እየሆኑ ነው፡፡ አድልዎ በዝቷል፣ በጣም በዝቷል! በየቦታው የምንሰማው ነገር አስቸጋሪ ነው፡፡

እንዲህ አይነት አስተሳሰብ እየበዛ ሲሄድ ሰዎች በችሎታቸው ማመናቸው እየተመናመነ ይሄድና “የወንዜ ልጅ ሀላፊ የሆነበት መሥሪያ ቤት ወይም ድርጅት…” እያሉ መፈለግ ሊኖርባቸው ነው ማለት ነው፡፡ (ስሙኝማ…የምር ግን፣ እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ነገረ ሥራችን ሁሉ ወደ ‘ሰርቫይቫል’ እየወረደ ሲሄድ… አለ አይደል… ከእነቤተሰባችን እንዳይርበን፣ እንዳይጠማን መሸሸጊያ መፈለግ እዚች አገር ላይ የተለመደ ነው፡፡ ልጄ…‘ፕሪንሲፕሉ’ ሳይፈርስ ሆድ ባዶ ከሚሆን ‘ፕሪንሲፕሉን’…አለ አይደል… “ውሀ በልቶት…” ሆድ ቢሞላ ይሻላል የሚለው አስተሳሰብ እየበዛ ሲሄድ አብረው ውሀ የሚበላቸው እሴቶች መአት ናቸው፡፡ እንዲህ አይነት ነገር እየበዛ አይመስላችሁም! በእርግጥ …በተደላደለ ሁኔታ ላይ እየሆኑ፣ የሌላውን ጓዳ በደንብ ሳያውቁ ሰውን ማውገዝ…አለ አይደል… ትንሽ ያስቸግራል፡፡ ግን በዚህም ሆነ በዛ…ለ‘ፕሪንሲፕላቸው’ ሽንጣቸውን ገትረው “እንዲች ብሎ ነቅነቅ የለም…” የሚሉ ሰዎች ‘ኢንዴንጀርድ ስፒሽስ’ እየሆኑ ነው፡፡ ከተማሪዎቻቸው በፈረንካ መልክ ወይም በ“በደረቁ ሌሊት…” መልክ ‘ኢንሴንቲቭ’ ሳይፈልጉ በማስተማር ላይ ብቻ የሚያተኩሩ አስተማሪዎች እንደ አያያዛችን ከሆነ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ‘ኢንዴንጀርድ ስፒሽስ’ እንዳይሆኑ ያሰጋል፡፡ በአጠቃላይ በትምህርት ቤቶች አካባቢ የምንሰማቸው ነገሮች…አለ አይደል…በአጠቃላይ መማር/ማስተማር በሚባለው ነገር አካባቢ ‘ኢንዴንጀርድ…’ የሚሆኑ እሴቶች እየበዙ እንዳይሄዱ ያስፈራል፡፡ የምናነባቸው፣ ‘ውሀ የሚያነሳ’ ኢንፎርሜሽን የምናገኝባቸው የህትመት ውጤቶች ‘ኢንዴንጀርድ…’ ከመሆንም ያለፉ ይመስላል፡፡

ይቺን አሪፍ ቀልድ ስሙኝማ…ታላቁ አሌክሳንደር፣ ጁሊየስ ሴዛርና ናፖሊዮን በሞስኮ ቀዩ አደባባይ ይደረግ በነበረ ወታደራዊ የሰልፍ ስነ ስርአት ላይ ይገናኛሉ፡፡ ታላቁ አሌክሳንደር… “እንዴት አሪፍ ነገር ነው! እነዚህ አይነት ታንኮች ቢኖሩኝ ኖሮ ማንም ሊያሸንፈኝ አይችልም ነበር፣” ይላል፡፡ ሴዛር በበኩሉ፣ “እንዴት አሪፍ ነገር ነው! እነዚህ አይነት አውሮፕላኖች ቢኖሩኝ ኖሮ ዓለምን መቆጣጠር እችል ነበር፣” ይላል፡፡ ናፖሊዮን በበኩሉ ምን ቢል ጥሩ ነው… “እኔ ደግሞ የፕራቭዳ አይነት ጋዜጣ ቢኖረኝ ኖሮ ወተርሉ ላይ የደረሰብኝን ማንም አያውቅም ነበር፡፡” እናላችሁ… “ማንም አያውቅብኝም…” እንደሚባሉት ሳይሆን አሪፍ የህትመት ሚዲያ ውጤቶች ‘ኢንዴንጀርድ…’ እየሆኑ ነው፡፡ የምር’ኮ በመቶ ምናምን ጋዜጣና መጽሔቶች ተጥለቅልቀንና ምርጫዎቻችን ሰፊ የነበሩባቸው ዓመታት…አለ አይደል… “ከዕለታት አንድ ቀን…” ወደሚባል ደረጃ ደርሰናል፡፡

እናላቸሁ…ኤንዴንጀርድ…የሆኑ ነገሮች እየበረከቱ በሄዱ ቁጥር ችግሮቻችን እየበዙ…አለ አይደል…ደስ ባይለን፣ ምቾት ባይሰማን ምን ይገርማል! የችግርን ነገር ካነሳን ይቺን ስሙኝማ…ሚስት ሁልጊዜ በቦርሳዋ ውስጥ የባሏን ፎቶ እየያዘች ነው የምትሄደው፡፡ ባል ሆዬም… “ሁልጊዜ ፎቶዬን በቦርሳሽ ይዘሽ የምትሄጂው ለምንድነው?” ሲል ይጠይቃታል፡፡ ሚስትም እንዲህ ስትል ትመልስለታለች… “ምንም አይነት አስቸጋሪ ቢሆንም አንድ ችግር በደረሰብኝ ጊዜ ፎቶውን አይና ችግሩ ወዲያው ይጠፋልኛል፡፡” ባል ሆዬም ደስ ይለውና…“እኔ ለአንቺ ምን ያህል ተአምረኛ የሆንኩ ጠቃሚ ሰው እንደሆንኩ አየሽ አይደል!” ይላታል፡፡ ሚስት ምን ብላ ብትመልስለት ጥሩ ነው…“ልክ ነህ፡፡ የሆነ ችግር ሲገጥመኝ የአንተን ፎቶ አውጥቼ እያየሁ ለራሴ ‘እዚህ ፎቶ ላይ ከማየው የበለጠ ምን ችግር ሊደርስብኝ ይችላል?’ እልና ትልቅ የመሰለኝ ችግር ወዲያው ይጠፋልኛል፡፡” ‘ኢንዴንጀርድ…’ የሚሆኑ ነገሮችን ይቀንስልንማ! ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 4359 times