Saturday, 09 March 2013 12:28

ፍለጋ

Written by  ዘሪሁን ብርሃኑ
Rate this item
(1 Vote)

እሷ እንዳይክደኝ ውል ነበረን፡፡ እንዳልከደው ውል ነበረን፡፡ ቀኔን በቀኑ አሰርኩት፡፡ እድሜዬን በዕድሜው ጐዳና ቀላቅዬ አብሬው ተጓዝኩ፡፡ ዛሬ ለምን እንደሆነ በማይገባኝ ሁኔታ ህይወቴን ሁሉ ሰጠሁት፡፡ ልዩ ሆኖብኝ ነበር፡፡ ያለፉት አምስት ዓመታት ስጋዬ እንጂ ነብሴ እኔ ጋ አልነበረችም፡፡ ስጋዬም ቢሆን ከእሱ ጋር ስትሆን እና ብቻዬን ስሆን ልታስቡት ከምትችሉት በላይ ልዩነት አለው፡፡ እሱ ዋሽታኛለች፡፡ ለምን አመንኳት? ለምን ነብስ እና ስጋዬን ሰጠኋት? ዛሬ ከአምስት አመት በኋላ እንዴት እንደኖርኩ ሳስበው ይገርመኛል፡፡ በሷ ትንፋሽ ስተነፍስ ነበር፤ በሷ የልብ ትርታ ገላዬ ሲንቀሳቀስ ነበር፡፡ እኔ አልነበርኩም፡፡

እኔ አልኖርኩም፡፡ እሷ ኖሯል፡፡ ሰውነቱን ለኔ ሰጥቶኝ ነብሱን ደብቆኛል፡፡ ካለሁበት እንዳልንቀሳቀስ ገትሮኝ እሱ ዓለምን ዞሯል፡፡ በድን ነበርኩ፡፡ ለእሱ ዓለም ብቻ ታዝዤ ኖርኩ፡፡ እሱ አልኖርኩም፡፡ ገላዬንም ነብሴንም ለሷ አስገዝቼ ኖርኩ፡፡ እሷ ግን እኔን አንድ ቦታ ገትራኝ ዓለምን ትዞራለች፡፡ እኔ አልኖርኩም፡፡ እሷ ግን ዓለምን ገዛች፡፡

ደስታዋን አሳደደች፡፡ እሷ የተገናኘነው ድንገት ነበር፡፡ ትዝ ይለኛል፡፡ ስድስት ኪሎ ጋ ቆሜ ባስ እጠብቃለሁ፡፡ የምጠብቃት ባስ 31 ቁጥር ነበረች፡፡ ወደ ለገሃር ሄጄ እህቴን ልጠይቃት፡፡ እህቴ ጨርቆስ ነው የምትኖረው፡፡ ሽቅብ ወደ ሽሮ ሜዳ አንጋጥጬ ባሷን በጉጉት ስጠብቅ ድንገት መጥቶ ከፊቴ ቆመ፡፡ “ምን እየጠበቅሽ ነው?” “እዚህ ተቁሞ ምን ይጠበቃል?” “ምናልባት እኔን!” “ሆሆ! አንተ ደግሞ ማነህ?” “መኮንን እባላለሁ፡፡” እውነትም መኮንን ነበር፡፡ የመኳንንት ዘር!! ነገሩ ሁሉ እንደዛ ነው፡፡ ውሸታም ነው፡፡ ይዋሸኛል፡፡ ለግሉ ዓለሙን እያጣጣመ እኔን ግን “ካንቺ ጋር ነኝ” እያለ ይዋሸኛል፡፡ ከተዋወቅን በኋላ አንሶላ ለመጋፈፍ ብዙ ጊዜ አልወሰደብንም፡፡ በጣም ተዋድደን ነበር፡፡ አቤት ፍቅር!! መኮንን ውሸቷን ነው፡፡ አላፈቀረችኝም፡፡ እኔ ነብስና ስጋዬን ጥዬ አበድኩላት፡፡

በጣም የሚገርመው ስራ ገብቼ የምወጣበት ጊዜ እንኳ አቤት ርቀቱ፡፡ እየቆየሁ ስራዬን ትቼ ከሷ ጋር ቤት ውስጥ ተቃቅፌ መዋል ተመኘሁ፡፡ አንዳንድ ቀናት አለቃዬን አሞኛል ብዬ እየዋሸሁ አደረግሁት፡፡ ከእሷ ጋር ውዬ አደርኩ፡፡ ራሴን ሰጠኋት፡፡ እሷ ከጓደኞቼ ሁሉ ራቅሁ፡፡ ከመኮንን ውጪ ሁሉም ጣዕም አጡብኝ፡፡ እንዲሁ ሰው ብቻ ሆኑብኝ፡፡ እሱ የሰው ልክ ነበር፡፡ አንዳንዴ ከቢሮ አመመኝ እያልኩ ከእሱ ጋር እውላለሁ፡፡ አቤት ጫ-ወ-ታ ሲችልበት፡፡ ንጉስ ነው፡፡ መኮንን እንደ ንግስት ነበር የምንከባከባት፡፡ እኔ ካልተንከባከብኳት አንድ ነገር የምትሆን ይመስለኝ ነበር፡፡ ካላጐረስኳት የማትጠግብ፣ ካላቀፍኳት የማይሞቃት ይመስለኝ ነበር፡፡ ተሳሳትኩ፡፡ እሷ ስህተቱ የኔ ነው፡፡ ያን ሁሉ ማመን አልነበረብኝም፡፡ አምስት ዓመት ሙሉ፣ ዕድሜዬ እንደ ጉም በነነች፡፡ የእሱ ግን እየፈካና እየደመቀ ይሄዳል፡፡ የእኔ ግን እንዲሁ ቀረ፡፡ ተስፋ የለኝም፡፡ እሱ እናቴ የሁልጊዜ ምኞቷ እኔ አግብቼ ልጅ ወልጄ እሷን አያት አድርጌአት እንድኖር ነበር፡፡

ግን አልሆነም፡፡ ከሰርኩ፡፡ ከዚህ በኋላ ሴት አምኜ የምኖር አይመስለኝም፡፡ ልቤ ተሰብሯል፡፡ እሷ የዛሬ ዓመት ገደማ ነው ክህደቱን የጀመረው፡፡ አስታውሳለሁ፡፡ እሁድ እለት ነበር፡፡ ለአራት ዓመት ያህል ሲናገር ሰምቼው የማላውቃትን አክስቱን ለመጠየቅ በሚል ወደ ቦሌ እሄዳለሁ አለ፡፡ “እንዴ የምን አክስት አመጣህ? እስከ ዛሬ የማላውቃት አክስትህ ከየት መጣች?” ስለው “ከሰማይ” ብሎ አሾፈብኝ፡፡ የመጀመሪያውን የክህደት ደውል ያኔ ደውሎ ሄደ፡፡ ያን ቀን ቀኑን ሙሉ አክስቱ ቤት ዋለ፡፡ እኔም ቤት ዋልኩ፡፡ አመሻሹን ሳንገናኝ ነጋ፡፡ መኮንን የዚያን ቀን አክስቴ ከረዥም ጊዜ በኋላ ደውላ ልታናግረኝ እንደምትፈልግ ነግራኝ ወደ ቤቷ ሄድኩ፡፡ ነገር ግን ለሷ ስነግራት አዲስ አክስት ያመጣሁ ይመስል እጅግ ተገረመች፡፡ በእርግጥ ስለ አክስቴ ነግሬአት አላውቅም፡፡ ነገር ግን አዲስ አክስት አልፈጠርኩም ነበር፡፡

አክስቴ ቤት ስሄድ የአንድ የቅርብ ዘመዳችን ልጅ ከሀገር ቤት “ትምህርትሽን አቋርጠሽ ማግባት አለብሽ” ብለዋት እምቢ ብላ ሸሽታ የመጣችን ልጅ ታሪክ ነግራኝ ከሷ ጋር አስተዋወቀችኝ፡፡ ልጅቱ እጅግ ታሳዝን ነበር፡፡ ትምህርቷን መቀጠል ስለምትፈልግ አክስቴ እንድረዳት ነበር የፈለገችው፡፡ እሷ ጋር ተቀምጣ እንድትማር ፈቅዳላታለች፡፡ እሷ ይሄን ታሪክ ሲነግረኝ በጣም ነበር የሳቅሁት፡፡ የውሸት ታሪኩን ከዓይኑ ውስጥ ማንበብ ችዬ ነበር፡፡ እርግጠኛ ነኝ ዋሽቶኛል፡፡ የሆነ ነገር ሲከዳኝ ይታወቀኛል፡፡ መኮንን አላመነችኝም፡፡ በጣም ነው የገረመኝ፡፡ ከዓይኗ ስር ግልጽ የሆነ ዓለማመን አንብቤአለሁ፡፡ መጀመሪያ ስትቀልድ መስሎኝ ነበር፡፡ ጊዜ እየገፋ ሲሄድ ግን ነገሩ እየከረረ መጣ፡፡ እሷ መጀመሪያ ያን ታሪክ ሲያወራ ቀልድ መስሎኝ ነበር፡፡ ኋላ ግን እየከረረ መጣ፡፡ እንደገና በሌላ ጊዜ ይህችው አክስቴ የሚላት ሴትዮ ቤት እየሄደ የሆነ የሆነ ነገር እያደረገ ይመጣና የማይሆን የፈጠራ ታሪኩን ይዘረዝርልኛል፡፡ በጣም እበሽቃለሁ፡፡ ሳውቀው የዋህና ምንም የማይደብቀኝ ነበር፡፡ አክስቱ መጥፎ ነገር ታስተምረው ጀመረች መሰለኝ መዋሸት ጀመረ፡፡ መኮንን እየዋሸኝ ይሁን አይሁን የዓይኑ ቅንድብ ሲነቃነቅ አውቀዋለሁ፡፡ እየዋሸኝ ነበር፡፡ መኮንን አክስቴ በተደጋጋሚ እየጠራችኝ በልጅቷ መሸሽ ምክንያት ገጠር የተፈጠሩ ችግሮችን ትነግረኛለች፡፡ ልጅቷን በህግ ለመከላከል እንዲያመች ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ይዘን እንድንሄድ ሀሳብ አቅርቤላት እሷም ተስማምታ ከልጅቷ ጋር ቁጭ ብዬ ስለጉዳዩ በዝርዝር ነገሮችን እየጠየቅሁ ለፍርድ ቤት በሚመች መልኩ እጽፈዋለሁ እና የማደርገውን ደግሞ መጥቼ በዝርዝር ለሷ እነግራታለሁ፡፡

ልጅቱ ትምህርቷን ማቋረጥ አትፈልግም፡፡ ተምራ መምህርት የመሆን ጠንካራ ፍላጐት አላት፡፡ ልትረዳ እና ልትታግዝ የሚገባት ልጅ ናት፡፡ አክስቴ ያን ያህል ገንዘብ ስለሌላት እኔ እረዳት ጀመርኩ፡፡ በተለይ የመጀመሪያ ሰሞን ለልብስ እና ለልዩ ልዩ ነገሮች መግዣ እያልኩ ብዙ ብር አወጣሁ፡፡ እሷ መሄዱ እና አምሽቶ መምጣቱ ሳያንሰው ገንዘቡንም ይረጨው ጀመር፡፡ ጭራሽ ልብስ ልገዛላት ነው፣ አክስቴ ገንዘብ የላትም ምናምን የሚሉ ወሬዎችን ጀመረ፡፡ ያኔ መሸነፌ እየታወቀኝ መጣ፡፡ ያኔ የፍቅር ሃይሌ በእሱ ዘንድ ዋጋ እያጣ መምጣቱ ታወቀኝ፡፡ እሱ ግን ያን የማይረባ ታሪኩን እንደ ህፃን ልጅ እየመጣ ይተርክልኛል፡፡ ከልቤ ስለማፈቅረው ምንም እንደማይገባኝ ገምቷል፡፡ እኔ ግን ጠረጠርኩ፡፡ ጠረጠርኩና አንድ መላ ዘየድኩ፡፡ መኮንን ከጊዜ ወደ ጊዜ የልጅቱ እና የአክስቴ ጉዳይ በእሷ ዘንድ አበሳጭ እየሆነ መምጣት ጀመረ፡፡ ስለዚህ ነገር ሳወራት ትበሳጫለች፡፡ በፍፁም ሊገባኝ አልቻለም፡፡

አልፎ አልፎም ከአክስቴ ቤት ስመለስ ቤቴ እንድንገናኝ ስቀጥራት ፈቃደኛ ሆና እንደ ድሮው ተደስታ መምጣት አቆመች፡፡ እወዳታለሁ፡፡ አምናታለሁ፡፡ እሷም ታምነኛለች፡፡ ግን ለምን የአክስቴ ጉዳይ እንዲህ እንዳስመረራት ግን ሊገባኝ አልቻለም፡፡ ነገሩ በመሃላችን ንፋስ እያስገባ መጣ፡፡ ግን አንድ ነገር ጠረጠርኩ፡፡ የአክስቴ ጉዳይ ብቻ እንዲህ አላበሳጫትም፡፡ እሷ የአክስቱ ጉዳይ ብቻ አልነበረም ያበሳጨኝ፡፡ ከጀርባው የያዘው መዓት ጭምር እንጂ፡፡ ለማን ነው ጊዜውን የሚፈጀው? ለማን ነው ገንዘቡን የሚያወጣው? ማን ናት የበለጠችኝ? ማን ናት ያሸነፈችኝ? ማነች አክስቱ? ማወቅ ፈለግሁ፡፡ በጣም ጓጓሁ፡፡ አራት አመት ሙሉ አቅፌ ያኖርኩትን ፍቅር በአንድ ጊዜ መበተን አልቻልኩም፡፡ አልሆነልኝም፡፡ ስለዚህ ማን እንደሆነች፣ አክስቱስ ቤት እየሄደ ምን እንደሚሰራ ማወቅ ፈለግሁ፡፡ ስለዚህ ቀስ እያልኩ እከታተለው ጀመር፡፡ ለዚህ ጉዳይ እንዲረዳኝ ተስፋነህን አማከርኩት፡፡ ተስፋነህ የፎቶግራፍ ባለሙያ ነው፡፡ እርዳኝ አልኩት፡፡ ተስማማ፡፡

መኮንን አንዳንድ ሰዎች የራሳቸው ተራራ የሚያህል ስህተት እንዳይታወቅባቸው ሲሉ የሌሎችን ጥቂት እንቅፋት አጋንነው ማቅረብ ይቀናቸዋል፡፡ እሷም እንደዛው ነበረች፡፡ ሆን ብላ እኔን ባላደረኩትና ባልሆንኩት ነገር እየወቀሰችኝ የራሷን ህይወት ትኖር ነበር፡፡ ስለዚህ ልከታተላት ጓጓሁ፡፡ ለምንድነው የአክስቴን ጉዳይ ያለ ምክንያት እንዲህ ያጋነነችው እና ትልቅ ጉዳይ አድርጋ ያወራችው? በርግጠኝነት ልትሸፍነው የፈለገችው ጉዳይ አለ፡፡ በጤናዋ እንዲህ አልሆነችም፡፡ ስለዚህ መርምሬ ጉዳዩን ማወቅ አለብኝ፡፡ ስንት ከባድ ርዕሰ ጉዳይ በኩርፍያ ሲያልፈን ከርሞ፣ ዛሬ በዚህ ጉዳይ እንዲህ ያለምክንያት ማምረሯን ማጣራት አለብኝ፡፡ ስለዚህ በራሴ መንገድ አንድ በአንድ ውሎዋን ማጣራት እና መከታተል ጀመርኩ፡፡ እሷ ለተስፋነህ ሁሉንም ነገር አጫወትኩት፡፡

በጣም አዘነ፡፡ ሊረዳኝ ሙሉ በሙሉ ተስማማ፡፡ ከዚያ በድብቅ እየከታተልነው አክስቴ የሚላት ሴት ቤት ሲገባና እና ሲወጣ መመርመር ያዝን፡፡ አመሻሹን ከስራ ስወጣ ምንም እንዳልተፈጠረ እደውልለታለሁ፡፡ ቀለል አድርጌ፡፡ እንደለመደው አክስቱ ጋ ሊሄድ እንደሆነ ይነግረኛል፡፡ ወድያው ተስፋነህ ጋ እደውላለሁ፡፡ ከኋላው ተከትሎት ሄዶ ፎቶ ያነሳልኛል፡፡ በነጋታው ያነሳውን በሙሉ እንገናኝና ይሰጠኛል፡፡ ልቤ ነግሮኝ ነበር፡፡ መኮንን ተከታተልኳት፡፡ ከቢሮዬ ቀደም ብዬ እወጣና አክስቴ ጋ የማልሄድ ቀን ከቢሮዋ ስትወጣ እከታተላታለሁ፡፡ በቀጥታ ከቢሮዋ ትወጣና ወደ ጉደኛዋ ሰው ትሄዳለች፡፡ ደስ ይላል፡፡ የጠረጠሩትን ሲያገኙ ደስ አይልም? ደስ ይላል፡፡ ቁጭ ብላ ፖስት ካርድ ይሁን ፎቶ ስትለዋወጥ አያታለሁ፡፡ በግንኙነቷ ደስተኛ ትመስለኛለች፡፡ ግን ትንሽ ሚስጥር ብታደርገው ጥሩ ነበር ባይ ነኝ፡፡

እሷ የገረመኝ ሚስጥር ለማድረግ መሞከሩ ነበር፡፡ በእሱ ቤት እኔን ሸውዶ ሞቷል፡፡ አክስቴ ብሎ በሚሄድበት ቤት ተከታትለነው እንሄዳለን፡፡ ፎቶ እናነሳለን፡፡ አንድ ቀን ተስፋነህ ውስጥ ድረስ ለማንሳት ሞከረ፡፡ አጥሩን ተደብቆ እስከ ሳሎን በመስኮት በኩል ሊያነሳ ገባ፡፡ እሱ ግን ሳሎን ውስጥ አልነበረም፡፡ የሩጫዬ መቋጫ ሆነ፡፡ ስለዚህ ለአራት ዓመት የካብኩትን ፍቅሬን በወራት ውስጥ ናደው፡፡ ፍቅሬን ያለ ስስት ሰጥቼዋለሁ፡፡ ምንም አይፀጽተኝም፡፡ መጥኔ ለእሱ እንጂ እንደ ሰው ያሰበ እለት ህሊናው ለሚወቅሰው፡፡ መኮንን ከልጁ ጋር የነበራቸውን ግንኙነት እየተከታተልኩ በሞባይሌ እቀርጽ ነበር፡፡ በጣም አስከፍታኛለች፡፡ በጣም ጐድታኛለች፡፡ ህይወቴን ሁሉ ሳልሰስት ነበር የሰጠኋት፡፡ እሷ ግን ካደችኝ፡፡ እሷ ግን ሸወደችኝ፡፡ ስለዚህ ልለያት ነው፡፡ የማስቀምጥላት እነዚህ ፎቶዎች በቂ ምስክር ናቸው፡፡ ተመልክታ ትማርባቸው ይሆናል፡፡ አልያም እንዳሻት፡፡ እኔ ግን መጓዝ አለብኝ፡፡ እሷ አንጀቴ እያረረ እለየዋለሁ፡፡ ከዚህ በላይ ህይወቴን ማበላሸት አልፈልግም፡፡ ለሰራው ስራ እነዚህ ፎቶዎች ምስክር ይሆናሉ፡፡ አስቀምጬለት እሄዳለሁ፡፡ ምናልባት ተመልክቶ ይማርባቸው ይሆናል፡፡ አሊያም እንዳሻው፡፡ እኔ ግን መሄድ አለብኝ፡፡

Read 7980 times Last modified on Saturday, 09 March 2013 14:27