Saturday, 09 March 2013 14:08

የዋልያዎቹ የዓለም ዋንጫ ህልም በውዝግቦች ታጅቧል

Written by 
Rate this item
(4 votes)

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በዓለም ዋንጫ የምድብ ማጣርያ ለሚያደርገው ሶስተኛ ጨዋታ ዝግጅቱን በውዝግቦች በመታጀብ ሊጀምር ነው፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ ከቦትስዋና ጋር ከ15 ቀናት በኋላ እዚህ አዲስ አበባ ላይ ይጫወታል፡፡ ይሄው የዋልያዎቹ ወሳኝ ጨዋታ ፌደሬሽኑ እና ክለቦችን ባነካኩ ውዝግቦች ገና ከዝግጅት ምእራፉ የመቃወስ አደጋ ውስጥ ወድቋል፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ ለዓለም ዋንጫው የምድብ ማጣርያው የሶስተኛ ዙር ጨዋታ የሚያደርገውን ዝግጅት ዛሬ እንደሚጀምር ይጠበቃል፡፡ በአፍሪካ ሁለት የክለብ ውድድሮች የሚሳተፉት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ደደቢት ለዋልያዎቹ ተጨዋቾቻውን ለመልቀቅ እንዳመነቱ ናቸው፡፡

በሌላ በኩል በአዲስ አበባ ስታድዬም በተደረገ የሊግ ጨዋታ ላይ የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ፈፅመዋል በተባለው የዲስፕሊን ግድፈት የፌደሬሽኑ ዲስፕሊን ኮሚቴ በክለቦቹ ላይ ያሳለፋቸው የቅጣት ውሳኔዎች በይግባኝ ክርክር ውስጥ ገብተዋል፡፡ ሁለቱ የኢትዮጵያ እግር ኳስ አወዛጋቢ ሁኔታዎች የዋልያዎቹን የተጨዋቾች ስብስብ በማቃወስ እና በክለብ ደጋፊዎች፤ በፌደሬሽኑና በብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች መካከል የተፈጠረው ልዩነት በማካረር ለብሄራዊ ቡድኑ በሚፈልገው ትኩረት እና ሁለገብ ድጋፍ ላይ መቀዛቀዝ እንዳይፈጠር ስጋት ሆኗል፡፡ ለብሄራዊ ቡድን የተጠሩ 22 ተጨዋቾች ስም ዝርዝር ሰሞኑን በእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ይፋ ተደርጓል፡፡ ደደቢት እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ዘጠኝ እና ስምንት ተጨዋቾችን እንደቅደምተከተላቸው በማስመረጥ ከፍተኛ ውክልና አግኝተዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ቡና ሁለት ተጨዋቾች ሲጠሩ ንግድ ባንክ ፤ መብራት ኃይልና ሰበታ ከነማ እያንዳንዳቸው 1 ተጨዋች አስመርጠዋል፡፡ የዋልያዎቹ የዓለም ዋንጫ ህልም ኢትዮጵያ በዓለም ዋንጫ ማጣርያዎች በፈርቀዳጅነት በመሳተፍ ከሚጠቀሱ የአፍሪካ አገራት አንዷ ነበረች፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ የተሳተፈችበት የዓለም ዋንጫ ማጣርያ በ1962 እኤአ ላይ የነበረ ሲሆን ከዚያን ጊዜ ወዲህ በማጣርያው ውድድሮች በየአራት አመቱ በመደበኛነት ተሳታፊ ሆና ቆይታለች፡፡ በ2002 እኤአ ጃፓንና ኮርያ በጣምራ ላዘጋጁት የዓለም ዋንጫ በተደረገው ቅድመ ማጣርያ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በሜዳው የቡርኪናፋሶ አቻውን 2ለ1 ቢያሸንፍም ከሜዳው ውጭ 3ለ0 ተሸንፎ ወደቀ፡፡

ከ4 ዓመታት በኋላ በ2006 እኤአ ላይ ጀርመን ለምታስተናግደው 18ኛው የዓለም ዋንጫ በተደረገው ቅድመ ማጣርያ ደግሞ ኢትዮጵያ በሜዳዋ 3ለ1 በማላዊ ተሸንፋ በመልሱ ጨዋታ 0ለ0 በመለያያት ቅድመ ማጣርያውን ማለፍ ተስኗታል፡፡ ከ3 ዓመት በደግሞ ደቡብ አፍሪካ ለምታስተናግደው 19ኛው የዓለም ዋንጫ በቅድመ ማጣርያው ሞውሪታንያን በደርሶ መልስ ጨዋታ ኢትዮጵያ 6ለ1 ብትረታም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ከፊፋ ውድድሮች ተሳትፎ በመታደጉ ጉዞው በአጭሩ መቅረቱ ይታወሳል፡፡ በ2014 እኤአ ላይ ብራዚል በምታስተናግደው 20ኛው የዓለም ዋንጫ ማጣርያ ላይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ታሪክ በአስደናቂ ስኬት የተለየ ሆኗል፡፡ ከ31 ዓመታት በኋላ ወደራቀበት የአፍሪካ ዋንጫ ተመልሶ መግባት የቻለው ብሄራዊ ቡድኑ በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ሲሳተፍ ለብራዚሉ የዓለም ዋንጫ በሚደረገው የምድብ ማጣርያ በምድብ 1 መሪነቱን እንደያዘ ነበር፡፡

በዓለም ዋንጫው የምድብ ማጣርያ ላይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በምድብ 1 ከደቡብ አፍሪካ፤ ቦትስዋና እና መካከለኛው አፍሪካ ጋር ተደልድሏል፡፡ በምድብ ማጣርያው የመጀመርያ ጨዋታ ላይ ዋልያዎቹ ከሜዳቸው ውጭ ከደቡብ አፍሪካ ጋር ተጫውተው 1 እኩል አቻ ተለያዩ፡፡ በሁለተኛው ጨዋታ ደግሞ በሜዳቸው አዲስ አበባ ላይ መካከለኛው አፍሪካን 2ለ0 አሸንፈዋል፡፡ዋልያዎቹ ከእነዚህ ሁለት ጨዋታዎች በሰበሰቡት አራት ነጥብ ሁለት የግብ ክፍያ የምድቡን መሪነት ጨብጠዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በዓለም ዋንጫ ማጣርያው እዚህ አዲስ አበባ ላይ ከቦትስዋና አቻው ጋር የሚገናኝበት ግጥሚያ 3ኛው የምድብ ጨዋታ ነው፡፡ አራተኛው የምድቡን ጨዋታ ይህን ጨዋታ ካደረገ ከ10 ሳምንታት በኋላ ከሜዳው ውጭ በጋብሮኒ ቦትስዋናን መልሶ የሚገጥምበት ነው፡፡ ከዚሁ የቦትስዋና ጨዋታ በኋላ በሳምንቱ ደግሞ በምድቡ አምስተኛ የዓለም ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታ ደቡብ አፍሪካን በሜዳው አስተናግዶ ይቀጥላል፡፡

በዚህ መሰረት ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የዓለም ዋንጫ የምድብ ማጣርያው ሂደት የሚያበቃው ከ6 ወራት በኋላ ከመካከለኛው አፍሪካ ጋር በሚያደርገው ስድስተኛው የምድብ ጨዋታ ይሆናል፡፡ የጊዮርጊስ ፤ የደደቢት እና የዋልያዎቹ የጨዋታ ጭንቅንቅ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ደደቢት ለብሄራዊ ቡድን ያስመርጧቸውን ተጨዋቾች በመልቀቅ ዙርያ ከፌደሬሽኑ ጋር መወዛገብ የጀመሩት ከሳምንት በፊት ነው፡፡ ሁለቱ ክለቦች ባለፈው ሰሞን በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ እና ኮንፌደሬሽን ካፕ በቅድመ ማጣርያ የመልስ ጨዋታዎቻቸው የዛንዚባር እና የመካከለኛው አፍሪካ ክለቦችን ጥለው በማለፍ ወደ የመጀመርያው ዙር የማጣርያ ምዕራፍ ተሸጋግረዋል፡፡

ለብሄራዊ ቡድኑ ዝግጅት ሲባል የመለስ ካፕ የሊግ ውድድር ለሶስት ሳምንት እንደሚቋረጥ ፌዴሬሽኑ እንዳሳወቀ ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው የሚፈልጓቸውን ተጨዋቾች ከየክለቡ አሰባስበው ዝግጅታቸውን በያዙት እቅድ ለመስራት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ደደቢት በብሄራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ጥሪ የሚቀርብላቸውን ተጨዋቾቻቸውን ላለመልቀቅ ሲያመነቱ፤ በአፍሪካ ሁለት የክለብ ውድደሮች ከሚያደርጉት የመጀመርያ ዙር የመጀመርያ ጨዋታዎች በኋላ ለመልቀቅ እንደሚፈልጉ በመግለፅ ነው፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽኑ በበኩሉ ክለቦቹ በብሄራዊ ቡድኑ እጅግ ወሳኝ ሚና ያላቸውን የሁለቱን ክለብ ተጨዋቾች ለመልቀቅ እንዲችሉ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን የክለቦቹን የጨዋታ ፕሮግራም እንዲያሸገሽግላቸው እጠይቃለሁ እያለ ነው፡፡

በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ከሜዳው ውጭ በመጀመርያው ጨዋታ የዛንዚባሩን ጃምሁሪ በአጠቃላይ የደርሶ መልስ ውጤት 8ለ0 በማስመዝገብ ወደ የመጀመርያ ዙር ማጣርያው ገብቷል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ15 ቀናት በኋላ የመጀመርያ ዙር የማጣርያ ግጥሚያውን ከሜዳው ውጭ ከማሊው ክለብ ዲጆሊባ ጋር በማድረግ ይጀምራል፡፡ በአፍሪካ ክለቦች ኮንፌደሬሽን ካፕ የሚሳተፈው ደደቢት በበኩሉ የመካከለኛው አፍሪካውን ክለብ አንጌስ ዲፋቲማ ከሜዳው ውጭ 4ለ0 እንደረታ የሚታወስ ሲሆን ምንም እንኳን በመልስ ጨዋታው 2ለ1 ቢሸነፍም በደርሶ መልስ ውጤት 5ለ3 በማስመዝገቡ ሊያልፍ ችሏል፡፡

ደደቢት በኮንፌደሬሽን ካፑ የመጀመርያ ዙር ማጣርያ በሜዳው ከሱዳኑ ክለብ አልሃሊ ኤልሻንዲ ጋር በመገናኘት ይቀጥላል፡፡ የፌደሬሽኑ ዲስፕሊን ኮሚቴና የቅጣት ውሳኔዎቹ ሰሞኑን ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የደረሰን መረጃ ጉዳዩ የውድድር ፕሮግራምን ለማሳወቅ፤ በብሄራዊ ቡድኑ የዓለም ዋንጫ ማጣርያ ዝግጅት ዙርያ ወይንም በአጠቃላይ ስለ ኢትዮጵያ እግር ኳስ በጎ እንቅስቃሴን የተመለከተ አይደለም፡፡ ጉዳዩ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ ስለተከሰተ የስርዓት አልበኛነት ተግባር እና ይህንኑ ተከትሎ በፌደሬሽኑ የዲስፒሊን ኮሚቴ የቅጣት ውሳኔ ያትታል፡፡ መለስ ካፕ ተብሎ በተጠራው የዘንድሮ የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ 10ኛ ሳምንት በአዲስ አበባ ስታድዬም ላይ ቡና ከደደቢት ባደረጉት ጨዋታ ላይ ተፈፅሟል ባለው የዲስፕሊን ግድፈት ላይ የዲስፕሊን ኮሚቴው በቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር እና በኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ላይ ያሳለፈውን ባለ ሁለት አባሪ ገፅ የቅጣት ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የዲስፕሊን ኮሚቴ በሁለቱ ክለቦች ላይ የቅጣት ውሳኔውን ለማስተላለፍ የጨዋታ አመራሮችን ሪፖርት መመርመሩንና ማጣራቱን ገልጿል፡፡ የዲስፕሊን ኮሚቴው የመጀመርያ ውሳኔ በኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ላይ የተላለፈ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ስታድዬም ቡና ከደደቢት አድርገውት በነበረው ጨዋታ ላይ በቀኝ ጥላፎቅ የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ አርማና ማልያ የለበሱ ደጋፊዎች የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አባላት የሆኑትን እነ ደጉ ደበበ፤ አሉላ ግርማና አበባው ቡጣቆ የተባሉ ተጨዋቾችን ሞራል የሚነካ ቃላት በመወርወር እና አስፀያፊ ስድቦችን በመሳደብ ጥፋተኛ ሆነው መገኘታቸውን ዲስፕሊን ኮሚቴው ይገልፃል፡፡ የቡና ደጋፊዎች ተመሳሳይ የዲስፕሊን ግድፈት በፌደሬሽኑ ላይ መፈፀማቸውን ያሳወቀው ኮሚቴው፤ ይህ ሳይበቃቸው በእለቱ በሚያሟሙቁ የተቃራኒ ቡድን ተጨዋቾች ላይ የውሃ ላስቲክና ድንጋይ በመወርወር ስርዓት መጣሳቸውን ዘርዝሯል፡፡ በመሆኑም በእግር ኳስ ፌደሬሽኑ የዲስፕሊን መመርያ ክፍል 9 አንቀፅ አምስት ንዑስ አንቀፅ ሁለት በፊደል ኸ በተቀመጠው መሰረት የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ በደጋፊዎች ለተፈጠረው የዲስፕሊን ግድፈት ተጠያቂ ተደርጓል፡፡

ስለሆነም የኢትዮጵያ ቡና የስፖርት ክለብ በዲስፕሊን መመርያው ክፍል 6 አንቀፅ 35 በንዑስ አንቀፅ አራት መሰረት 50ሺ ብር በቅጣት እንዲከፍል እና በፕሪሚዬር ሊጉ ባለሜዳ ሆኖ የሚያደርጋቸውን ሁለት ጨዋታዎች ያለተመልካች በዝግ ስታድዬም እንዲጫወት በዲስፕሊን ኮሚቴው ተወስኖበታል፡፡ የዲስፕሊን ኮሚቴው ሁለተኛ የቅጣት ውሳኔ ደግሞ የቅዱስ ጊዮርጊስና የብሄራዊ ቡድን ተጨዋች በሆነው አበባው ቡጣቆ ላይ የተሰጠ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ደጋፊዎች ስድብና ዘለፋ የደረሰበት አበባው የኢትዮጵያ ባህል ባልሆነ መልኩ በሰውነት ምልክት ተሳድቦ ተመልካቹን እንዳስቆጣና ረብሻው እንዲባባስ ምክንያት ሆኗል ብላል፡፡ ስለሆነም በዲስፕሊን መመርያው ክፍል ስድስት አንቀፅ 38 መሰረት አአባው ቡጣቆ ለክለቡ በ5 ጨዋታዎች እንዳይሰለፍ እና 5ሺ ብር መቀጮ እንዲከፍል በዲስፕሊን ኮሚቴው ተወስኖበታል፡፡

የዲስፕሊን ኮሚቴው የቅጣት ውሳኔ ክፍል ሶስት የሚመለከተው የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበርን ነው፡፡ በቡና ደደቢት የፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታ በግራ ጥላ ፎቅ የጊዮርጊስን አርማና መለያ የለበሱ ደጋፊዎች መሳደባቸውን የገለፀው ዲስፕሊን ኮሚቴው፤ በተጨማሪም የዚሁ ክለብ ደጋፊዎች የካቲት 15 ቀን በሴቶች የሊግ ውድድር የደደቢት እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ሴት እግር ኳስ ቡድኖችን ባጫወቱ ዳኞች ላይ አስነዋሪ ተግባር መፈፀማቸውን ጨምሮ ለሁለቱም የደጋፊዎች የዲስፕሊን ግድፈቶች የስፖርት ማህበሩ ተጠያቂ ሆኖ እንዲቀጣ መወሰኑን አሳውቋል፡፡ ስለሆነም በእግር ኳስ ፌደሬሽኑ የዲስፕሊን መመርያ ክፍል 6 አንቀፅ 35 በቁጥር 4 በተቀመጠው ድንጋጌ መሰረት የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር 40ሺ ብር መቀጮ እንዲከፍልና በወንዶች ዋናው ቡድኑ በሜዳው የሚያደርገውን አንድ ጨዋታ በዝግ ስታድዬም እንዲያደርግ መወሰኑን ዲስፕሊን ኮሚቴው አመልክቷል፡፡

Read 5878 times