Saturday, 16 March 2013 12:05

ቻታኩዋ

Written by  አሸናፊ አሰፋ
Rate this item
(3 votes)

…ጠዋት 2፡10 ላይ ነው፡፡ የዩኒቨርሲቲ class-room ውስጥ ነው፡፡ የማኔጅመንት፣ የሶስተኛ አመት ተማሪዎች Research Methods የተባለውን (ለምን ግን Research ተባለ? Research ማለት ዳግም- ፍለጋ ማለት ነው፡፡ ሰው አንዴ ያገኘውን ነገር ለምን ደግሞ ይፈልጋል?) ኮርስ እየተማሩ ነው፡፡ አስተማሪያቸው በእድሜም በአለባበስም አስተማሪ አይመስልም፤ እንኳንስ የዩኒቨርስቲ አስተማሪ፡፡ እድሜው ሃያ አራት ነው፤ አለባበሱ ግድ የለሽ፡፡ ብሩህ ጠዋት ነው፡፡ አስተማሪው ገፁ ብሩህ ነው፡፡ ድምፁ ከፍተኛ ነው፡፡ የተማሪዎች ፊትም ብሩህ ነው፡፡ ምንም እንኳ አብዛኛዎቹ አምሽተው የተኙ ቢሆንም፡፡ መነቃቃታቸው፤ የፊታቸው ፀዳል ደስ ይላል፡፡ ሌክቸር እየተሰጠ ያለው እንደተለመደው በጉራማይሌ ቋንቋ ነው፤ በአማርኛ እና በእግሊዝኛ፡፡ አስተማሪ፡- የጥናት እና የምርምር ስራ የራሱ የስራ እርከኖች ወይም ደረጃዎች አሉት፡፡

በስራ እርከኖቹ ቅደም ተከተል እና በስራ እርከኖቹ ብዛት ላይ አንድ አይነት ስምምነት የለም፡፡ ያ ብዙ አያስቸግርም፡፡ የመጀመሪያው የስራው መነሻ ግልፅ ይሁን እንጂ ሌላው እዳው ገብስ ነው፡፡ ጉራ አይሁንብኝና ያንድን የጥናት እና የምርምር ስራ መነሻ አይቼ ስለይዘቱ በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ፡፡ ስለዚህ ዛሬ የማወራችሁ ወይም የዛሬው ቻታኩዋ (Chautauqua) ስለ ጥናት እና የምርምር ስራ የመጀመሪያ እርከን ይሆናል፡፡ (የመምህሩ ስም ሀሌታ ነው፤ Chautauqua የምትለውን ቃል ከሁሉም ቃላት አብልጦ ይወዳታል፡፡ Chautauqua ማለት ጨዋታ፣ ዲያሎግ፣ ዲስኮርስ ማለት ነው፡፡) Anyway the process I have here is the most accepted one (እዚህ ጋ ተፅፎ የምታዩት የጥናት ፕሮሰስ ብዙዎች የሚስማሙበት ነው፡፡) ፕሮሰሱ ብላክ ቦርዱ ላይ ተፅፎ ይታያል፤ ስድስት እርከኖች ናቸው ተፅፈው የሚታዩት፤ ለዚህ ፅሁፍ አስፈላጊው ግን የመጀመሪያው እርከን ብቻ ስለሆነ እዚህ የተጠቀሰውም እሱው ነው፡፡

The research process Step 1: Define the Research Problem (የጥናቱን መነሻ ችግር በይን፡፡) Okay what does the first step of undertaking research say? It says ‘define the research problem’. What is the key word here? (ተማሪዎች ወደ ተቀመጡበት እየተራመደ፣ እጁን ወደ አንድ ተማሪ እየጠቆመ) Alazar what is the key word in this statement? (አልአዛር የምርምር እና ጥናቱን መነሻ ችግር በይን የሚለው አረፍተ ነገር ውስጥ ቁልፉ ቃል የትኛው ነው?) አልአዛር፡- Which statement, sir? (የትኛው አረፍተ ነገር?) አስተማሪ፡- You see, I was right. You were not following me. That is why I put the question for you. I am discussing the first step a research work starts with. There it is, written on the board. Read it! (አየህ ልክ ነበርኩ፤ እየተከታተልከኝ አልነበረም፤ ለዛም ነው አንተን የጠየኩት፡፡

አንድ የምርምር ስራ በምን መጀመር እንዳለበት እያወራኋቸው ነበር፣ ያውልህ ብላክ ቦርድ ላይ ተፅፏል፤ አንብበው እስኪ) ከአፍታ በኋላ አስተማሪ፡- Have you read it, Alazar? (አነበብከው?) (ተማሪው እራሱን ይነቀንቃል፡፡ አስተማሪው ይቀጥላል፡፡…) Please read it for us. It wakes you more, Read it, will you? (እባክህ ለእኛም አንብብልን እስኪ፣ አንተም በዚያው ትነቃለህ፡፡) አልአዛር፡- (ጮክ ብሎ ያነባል፡፡) It says define the research problem (ለጥናቱ መነሻ የሆነው ችግር በይን ነው የሚለው) አስተማሪ፡- Yeah, that is what it says, I was telling the class that this step of the research work is the most crucial one and I want to discuss it in depth. And my question was what the key word in the statement is, Alazar can you tell us that? (ልክ ነህ፤ እንዲያ ነው የሚለው፤ እና ለማንኛውም የምርምር እና ጥናት ሥራ ወሳኙ ይህ መነሻ ነው፤ እና ስለ እሱ በደንብ ማውራት እፈልጋለሁ፡፡ ጥያቄዬም በአረፍተ ነገሩ ውስጥ ቁልፉ ቃል የትኛው ነው የሚል ነው) አልአዛር፡- በአረፍተ ነገሩ ውስጥ ያለው ቁልፍ ቃል አይደል? አዎ፤ አዎ that is what I’m asking (እሱኑ ነው እኔም የጠየኩት) አልአዛር፡- ‘Define’ የሚለው ይመስለኛል፡፡

(“በይን” የሚለውን ማለቱ ነው) አስተማሪ፡- Come on Alazar, you are not yourself today. ምንድነው ደሞ ይመስለኛል ብሎ ነገር? (አልአዛር ዛሬ ምን ሆነሃል?) በዚህ መሃል አንዲት ተማሪ እጇኝ ታወጣለች፤ ጥያቄውን ለመመለስ፡፡ ሀና ናት፤ በጣም ጐበዝ ተማሪ ነች፡፡ በዚህ በሶስት አመት ቆይታዋ ከእነሱ Batch በውጤት የሚበልጣት ተማሪ አንድ ብቻ ነው፡፡ ጌትነት ይባላል፡፡ በቅርብ እርቀት እሷን የሚከተለው አልአዛር ነው፡፡ ሀና ክፍሉ ውስጥ ተሳታፊ ተማሪ ናት፡፡ አሁን ግን ጥያቄ ለመመለስ እጇን ያወጣችው አልአዛርን ለመታደግ ነው፡፡ አልአዛር ለምን ሀሳቡ እንደተሰረቀ ታውቃለች፡፡ ማታ ከእሷ ጋር ነበር፡፡ ሲጨቃጨቁ ነበር፤ አልአዛር በጣም ጐበዝ ተማሪ ነው፡፡ ግን እስከ ዛሬ ማንም ማንንም አፍቅሮ በማያውቀው ልክ ሀናን አፍቅሯታል፡፡ ሀና ጐበዝ ብቻ አይደለችም፤ ዘንድሮ በዩኒቨርስቲው በተካሄደ የቁንጅና ውድድር አንደኛ ወጥታ Miss Bahir Dar University ተብላለች፤ ይገባታል፡፡) Ok Hanna, you want to answer the Question? (ሀና ጥያቄውን ልትመልሺ ነው?) ሀና፡- Yes sir (አዎ፡፡) አስተማሪ፡- Go ahead. (መቀጠል ትችያለሽ፡፡) ሀና፡- The key word in the statement ‘define the research problem’ is problem. (የጥናቱን መነሻ ችግር “በይን” በሚለው አረፍተ ነገር ውስጥ ቁልፉ ቃል “ችግር” የሚለው ነው፡፡)

አስተማሪ፡- Good Hanna, the keyword is problem, you’re right. But to continue my question what is a problem? Hanna can you define what problem is? (ጐበዝ ልጅ ሀና፤ ልክ ነሽ፤ ቁልፉ ቃል ችግር የሚለው ነወ፡፡ እና አሁን ጥያቄዬን ልቀጥል፤ ችግር ማለት ምን ማለት ነው? ሀና ልትነግሪን ትተያለሽን?) ሀና፡- What is a problem? A problem is, is is… (ችግር ማለት ምንድነው? ችግር ማለት፣ ችግር ማለት፣ ችግር ማለት… ችግር ማለት) ክላሱ በጉርምርምታ ተሞላ፡፡ መጀመሪያ ጥያቄው እንደተጠየቀ እና ሀና ለመመለስ ስትሞክር ክፍሉ ውስጥ የሚከብድ ፀጥታ ነግሶ ነበር፡፡ ሁሉም ጥያቄው ያልጠበቁት ሆኖባቸው ነበር፡፡ በጣም ቀላል እና ግልፅ በመሆኑ ያልጠበቁት ጥያቄ ነበር፡፡ እናም እራሳቸው ለመመለስ እየሞከሩ ነበር፡፡ አስተማሪው ግርምት የቀላቀለ ፈገግታ ፊቱ ላይ ሰፍቶ ያያቸዋል፤ ይሰማቸዋል፡፡ ጫጫታው ቀስ እያሉ እንደጨመሩት የማጉያ ድምፅ እየጨመረ መጣ፡፡ ክርክር በረከተ፡፡ ተማሪዎቹ አስተማሪው መኖሩን ረስተዋል፡፡ problem ማለት ምን ማለት እንደሆነ እያብራሩ፣ እየመከቱ ነው፡፡ ጫጫታው እየጨመረ ነው፡፡ አስተማሪው መረሳቱ ገብቶታል፤ አስደስቶታል፡፡ እውነተኛ መማር እንዲህ እንደሆነ ያምናል፡፡ ጥቂት ተማሪዎች ጥያቄውን ለብቻቸው በጥሞና ያመነዥጋሉ፤ አይናቸው በግርምት ፈጦ፡፡

የተቀሩት በከፍተኛ ድምፅ ይከራከራሉ፡፡ ጩኸት በረከተ፡፡ ከጩኸቱ ጋር የአስተማሪውም ደስታ አብሮ ይጨምራል፡፡ በዚህ መሃል የክፍሉ በር ተንኳኳ፤ አስተማሪው ከፈተው፡፡ ጫጫታው ካለበት ክፍል ግራና ቀኝ እያስተማሩ የነበሩ ሁለት መምህራን ናቸው፡፡ እንደተለመደው ጫጫታው እንደረበሻቸው ለመናገር ነው የመጡት፡፡ አስተማሪ አንድ፡- (ፈገግ ብሎ በአክብሮት…) ሀይ ሀሌታ ዛሬም አንኳኳሁ አይደል ይቅርታ፡፡ እዚህ ከጐንህ ሆኜ note እየፃፍኩ ነበር፡፡ ትንሽ ጫጫታው እየበረከተ መጥቶ ከልጆቹ ጋር መስማማት አልቻልኩም፤ ለዚያ ነው የረበሽኩህ፤ ይቅርታ፡፡ አስተማሪ፡- እኔ ነኝ ይቅርታ መጠየቅ ያለብኝ፤ ይቅርታ፡፡ የሆነች ጥያቄ ጠይቄያቸው በሷ ላይ እየተወያዩ ነው፡፡ አስተማሪ ሁለት፡-(በንዴት፣ በቅናት…) ይኼ ውይይት አይደለም፤ ጫጫታ ነው፤ ሁከት፡፡ ደሞ ይህ ሲከሰት የመጀመሪያ ጊዜ አይደለም፤ ሁሌ ነው እረብሻው፡፡ አንተ ካለህበት አካባቢ ክላስ እንዳልመደብ በተደጋጋሚ አመልክቻለሁ፡፡ አስተማሪ፡- (ንዴተኛውን አስተማሪ ሳይሆን ቀናውን እና ትሁቱን አስተማሪ እያየ፡፡) ይቅርታ ብያለሁ፡፡ ትንሽ ብቻ ከተወያዩ በኋላ አስቆማቸዋለሁ፡፡ Sorry. You know, I usually forget that there are near by classes, It would not happen again, if I help it actually. (ይቅርታ ብዙ ጊዜ እኔ ያለሁበት ክፍል አካባቢ ሌሎች ክፍሎች እንዳሉ እዘነጋለሁ፡፡

ይህ ችግር ሁለተኛ እንዳይፈጠር እጥራለሁ፤ ቃል ግን አልገባም፡፡) በመጨረሻው አረፍተ ነገር ከቀናው አስተማሪ ጋር ተሳሳቁ፤ ተጠቃቀሱ፡፡ … ያኛው በንዴት ጦፎ፤ ይጠፋል፡፡ አስተማሪ፡- Chao, guys. (ቻዎ፡፡) በሩን ዘጋው፤ በሩ ፊታቸው ላይ የተዘጋባቸው አስተማሪዎች ተያዩ፡፡ ንዴተኛው አስተማሪ፡- ይኼ እብድ ሰውዬ ሁሌ እንደረበሸን ነው፡፡ (አለ ፍርጥም ብሎ፡፡ ቀናው አስተማሪ ፊቱ ላይ ሽሸግ አድናቆት እና ደስታ ይዞ በሃሳብ ተሰርቋል፡፡ ንዴተኛው አስተማሪ ላለው ነገር ከቀናው አስተማሪ ስምምነት ጠብቋል፤ በንዴት የታጀበ ስምምነት፡፡ አላገኘም፡፡ ግራ ተጋባ፡፡ በግራ መጋባቱ፣ መልሶ ተናደደ፤ በረባሹ አስተማሪ ተናደደ፤ እንደጠበቀው ወዲያው መልስ ባልሰጠው አስተማሪ ተናደደ፤ ተናደድ ያለው፡፡) ንዴተኛው አስተማሪ፡- ይኼ እብድ ሰውዬ ሁሌ እንደረበሸን ነው፤ አይደል እንዴ? (አለ በድጋሚ) ቀናው አስተማሪ፡- እኔን የሚገርመኝ ምን እያላቸው እርስ በርስ እንደሚንጫጩ ነው፡፡ ምንም ኮርስ ያስተምር ሁሌ ክፍሉ በተማሪዎች ክርክር እንደተሞላ ነው፡፡ እሱ ሲያስተምር ለመታደም ሁሌ እንደፈለግሁ ነው፡፡ አንድ ቀን አደርገዋለሁ፡፡ ንዴተኛው አስተማሪ፡- (በንዴት፣ በግርምት፣ በግራ መጋባት፡፡) ተማሪን ማንጫጫት ቁም ነገር ነው እንዴ? ቀናው አስተማሪ፡- እኔ በበኩሌ በተደጋጋሚ ሞክሬው አቅቶኛል፡፡ ተማሪዎች እንዴት እንደሚያደንቁት እና እንደሚወዱት አትጠይቀኝ፡፡

ንዴተኛው አስተማሪ፡- ደሞ የዛሬ ተማሪ የሚደነቅና የሚወደድ የት ያውቃል? ቀናው አስተማሪ፡- (በመገረም እየሳቀ…) የዛሬ ጊዜ ተማሪ… ነው ያልከው--- የሚገርምህ አንድ ቀን ከሱ ጋር ስናወራ “የዛሬ ጊዜ ተማሪ” ብዬ ስጀምር እብድ ነው የሆነው፡፡ (ቀናው አስተማሪ ከአጠገቡ ካለ ሰው ጋር የሚያወራ አይመስልም፤ አልነበረምም፡፡ ከራሱ ጋር ነበር የሚያወራው፡፡ ሁለቱም እያስተማሩ የነበረውን ክፍል አቋርጠው እንደወጡ ረስተዋል፡፡ የት እንዳሉ ረስተዋል፤ ጫጫታ የሞላበት ክፍል በር ጋ ቆመው ነበር የሚያወሩት፡፡ ጫጫታው አሁንም እንደቀጠለ ነው፤ አሁንም ይሰማል፡፡ ሁለቱ ግን ጫጫታው እየተሰማቸው አይደለም፡፡ ቀናው አስተማሪ በአድናቆት ተወስዷል፡፡ ሌላኛው ንዴቱ ወደ ግራ መጋባት ሀገር ወስዶታል፡፡) ንዴተኛው አስተማሪ፡- እንዴት? ቀናው አስተማሪ፡- (እንደመባነን አለ፡፡ አሁን ነው የት እንዳለ እና ከሰው ጋር እንዳለ ያስታወሰው።) ምን አልከኝ? ንዴተኛው አስተማሪ፡- “የዛሬ ጊዜ ተማሪ” ብዬ ስጀምር ይኼ እብድ አበደ ነው ያልከው? (አገጩን ጫጫታ ወደለበት ክፍል እጠየቆመ፡፡) ቀናው አስተማሪ፡- እ…አንዴ በተማሪዎች ተናድጄ የዛሬ ተማሪ ብዬ ስጀምር ተቆጣ፡፡ “የዛሬ ተማሪ ብሎ ነገር የለም፤ ይህ ተማሪዎችን በጅምላ ለመውቀስ ቀሽም አስተማሪዎች የሚጠቀሙበት ዘዴ ነው” አለኝ፡፡ “ወቀሳ፣ ወቀሳ፣ ወቀሳ፡… የዛሬ ተማሪ፣ የዛሬ ተማሪ ብሎ ነገር ምንድነው? እኔ የተቀጠርኩት ተማሪን ለመውቀስ አይደለም፤ ለማስተማር ነው፡፡ የማስተምረው ደግሞ የዛሬን ተማሪዎች ነው፡፡ ወሬ ከማብዛት መማር የሚፈልጉት ተማሪዎች ወዳሉበት መሄድ ነው፤ ወይ ወደ ድሮ፤ ወደ ሙታኑ፤ ወይ ወደ መጪው፤ ገና ወዳልተፈጠሩት” አለኝ፡፡

ከሱ ጋር ማውራት ደስ ይላል፡፡ (የአድናቆት ፈገግታ አሁንም ፊቱ ላይ ተረጭቷል፡፡ ይሄን እየተባባሉ እደጃፉ ቆመውበት ከነበረው ክፍል ውስጥ የነበረው ጫጫታ በድንገት ተቋረጠ፡፡ ድንግጥ አሉ፡፡ በዝንጋታ ተፈጥሮአዊ አድርገው የወሰዱት ጫጫታ ድንገት ሲቋረጥ ፀጥታው ጮኸባቸው፤ አስደነገጣቸው፤ አነቃቸው፡፡ ሁለቱም በመገረም ተያዩ፡1 በዚህ መሃል ከክፍሉ ከፍተኛ ድምፅ ተሰማ፡፡)አስተማሪ፡- ይበቃል፣ ይበቃል፤ በቂ ተወያይታችኋል፡፡ Now is there anyone who could define what a problem is? What is a problem? Tell me. (እስኪ አሁን ከመሃላችሁ ችግር ማለት ምን ማለት እንደሆነ ሊግረኝ የሚችል አለን?)ቀናው እና ንደተኛው አስተማሪ ተያዩ፤ በመገረም፡፡ ከግርምት ድንጋጤያቸው ያይላል፡፡

ጥያቄው ገርሟቸዋል፤ አስደንግጧቸዋል፡፡ የት እንደነበሩ መርሳታቸው፣ ለምን እንደረሱ አለማወቃቸው ገርሟቸዋል፡፡ ቀናው አስተማሪ የተማሪዎቹን ጫጫታ የተካው አስገምጋሚ ድምፅ ያለበትን ክፍል በአድናቆት እያየ አቋርጦት ወደነበረው ክፍል ሄደ፡፡ እራሱን እየነቀነቀ በለሆሳስ ‘what is a problem?’ እያለ፡፡ ንዴተኛው አስተማሪ አሁን በጣም ነቃ፡፡ የት እንዳለ እና ለምን እዚያ እንደሆነ ሲገባው የረሳዋን ንዴት አስታውሶ ተናደደ፤ በደንብ ተናደደ፡፡ ጀርባውን ሰጥቶት ይሄድ የነበረውን ቀና አስተማሪ በንቀት አየ፤ ገላመጠው፡፡ አስገምጋሚው ድምፅ ያለበትን ክፍል በንዴት እያየ በዛቻ እራሱን ነቀነቀ፤ በጣም ነቀነቀ፡፡ እሱም አቋርጦት ወደነበረው ክፍል ተመለሰ፡፡

ተማሪዎች የእስረኛ በመሰለ ፊት ተቀበሉት፡፡ ፍርሃት፣ ጥላቻ፣ ንዴት፣ ንቀት፤ መሰላቸት… የሞላበት ብዙ ፊት ያለበት ክፍል፤ ብዙ ጫጫታ የነበረበት ክፍል፡፡) አስተማሪ፡- ሀና፤ አሁን problem ምንድነው ትያለሽ? ሀና፡- For me problem is an obstacle. (ችግር ማለት እንቅፋት ነው) አስተማሪ፡- No, no. no (እየሳቀ) እስኪ አልአዛር አንተ problem ምንድነው ትላለህ? አልአዛር፡- Problem is any unwanted thing. (ማንኛውም የማይፈለግ ነገር ችግር ነው) አስተማሪ፡- No, no, no (እየሳቀ) Come on guys you have made a discussion, a longer and a louder one. I want you to give me a simple definition (አይደለም፤ አይደለም፤ አይደለም፡፡ ምን ሆናችኋል ልጆች? ከዛ ሁሉ ረዥም ክርክር በኂላ ችግር ማለት ምን ማለት እንደሆነ ቅልብጭ ያለች መልስ እንድትነግሩኝ እፈልጋለሁ) ሮዛ፡- ለኔ እንደገባኝ ከሆነ ማንኛውም መጥፎ ነገር problem ሊባል ይችላል፡፡ አስተማሪ፡- There you go. (ይኸውላችሁ እንግዲህ) አሁን እንደመናደድ እንደመቆጣት ብሏል፤ ንዴት አይደለም፤ ቁጣም አይደለም፡፡ እንዲህ አይነት ስሜት አለው፤ ለመግለፅ አስቸጋሪ የሆነ፡፡ ግን ብዙ ሰዎች በተለይ ተማሪዎች እዚያ ስሜት ውስጥ ሆኖ ሲያዩት ደስ ይላቸዋል፡፡

ከፍተኛው የተመስጦ ስሜት ውስጥ መግባቱን ያኔ ያውቃሉ፡፡ ያኔ ነው ብዙ ነገር የሚነግራቸው፡፡ እሱም ማስተማር የሚፈልገውን ነገር ለማስተላለፍ ሁሌ እዚህ ስሜት ውስጥ እስኪገባ ራሱን ይጠብቃል፡፡ እስኪ ሌላ የሚሞክር---- (የተወሰኑ ተማሪዎች እጃቸውን አወጡ፡፡) አስተማሪ፡- ግን Problem ማለት ሀና obstacle አልአዛር unwantred thing … ያሉትን እንዳትሉኝ፡ (ይህን ሲል ጥያቄውን ለመመለስ ተመዘው የነበሩ እጆች ሁሉ ወደ ቦታቸው ተመለሱ፡፡) ችግር ማለት እንቅፋት፣ ችግር ማለት ያልተፈለገ ነገር፣ ችግር ማለት መጥፎ ነገር ነው ካላችሁ፤ እሺ እንቅፋት ምንድነው? ያልተፈለገ ነገር ምንድነው? መጥፎ ነገር ምንድነው? (ክፍሉ በሳቅ ተሞላ፡፡ አስተማሪውም አብሯቸው ይስቃል፡፡) አስተማሪ፡- You see that is a poor definition. Now let me go for my last chance. You know whom I risk my last chance with. (አያችሁ እስካሁን የተባለው ሁሉ ቀሽም ብያኔ ነበር፡፡ አሁን እንግዲህ እንደተለመደው መልስ ፍለጋ ወደ መጨረሻወ ተጠያቂያችን እንሄዳለን፡፡) እንዳለውም ሁሉም የመጨረሻው ተጠያቂ ማን እንደሆነ ያውቃል፡፡ ፊቶች ሁሉ ጌትነት ወደ ተቀመጠበት ተጠመዘዙ፡፡ ጌትነት መጨረሻ ነው የሚቀመጠው፤ genius ነው፡፡

ተማሪዎችም አስተማሪዎችም እኩል የሚያደንቁት፣ የሚያከብሩት፣ የሚፈሩት፣ አእምሮ አለው፡፡ አሁን የክፍሉ ተማሪ አይኖች በመሉ ጌትነት ላይ ናቸው፡፡ እሱ ግን አያይም፡፡ እጆቹን አጣምሮ አይኖቹን የክፍሉ ኮርኒስ ላይ ተክሎ በሃሳብ ተወስዷል፡፡ ተማሪዎች እያፈራረቁ አንዴ መምህሩን፣ አንዴ ጌትነትን ያያሉ፡፡) አስተማሪ፡- (አስተማሪው ጌትነት ወደ ተቀመጠበት የመጨረሻ ወንበር ሄዶ አጠገቡ ቆመ፡፡ ጌትነት አያይም፡፡) ጌ-ት-ነ-ት! (ብሎ አጠገቡ ሆኖ በቀልድ ጮኸ፡፡ ጌትነት ደንግጦ ባነነ፡፡ ክፍሉ በሳቅ ተሞላ፡፡ ጌትነት ምን እንደተፈጠረ አልገባውም፡፡ ነገሩን ሲረዳ ከክፍሉ ጋር አብሮ መሳቅ ያዘ፡፡ አስተማሪው ተመልሶ ብላክ ቦርዱ ፊት ቆመ፡፡) አስተማሪ፡- ምነዉ እባክህ ጌትነት ለምን በግልፅ አትነግረኝም፤ ቀሽም አስተማሪ መሆኔን፡፡ ይሄን ያህል ጥለኸን ትጠፋለህ? ይኼን ሁሉ ስለፈልፍ አንተ ጥለኸን ጠፍተኸል፡፡ ያን ያህል ቀሽም አስተማሪ መሆኔን አላውቅም ነበር፤ የተማሪን ሃሳብ ክፍሉ ወስጥ ይዞ ማቆየት የማልችል፡፡

(ሳቅ፤ ጌትነት ይስቃል፤ አስተማሪውም ይስቃል፡፡) ጌትነት፡- እያሰብኩ ነበር፡፡ አስተማሪ፡- እኔ ደግሞ እዚህ ያለህ መስሎኝ ጥያቄ ልጠይቅህ ነበር፡፡ እስኪ ስለምን ነው ስታስብ የነበረው ጌትነት፡- What is a problem? የሚለውን ጥያቄ ሳስብ ነበር፡፡ (ችግር ምንድነው? የሚለውን) አሁንም ክፍሉ በሳቅ ተሞላ፡፡ እንዲህ ነው ጌትነት፤ እልኸኛ ነው፡፡ ከጥያቄዎች ጋር እልህ ይጋባል፡፡ አስተማሪ፡- እድለኛ ነኝ፤ ልጠይቅህ የፈለኩትን ነው ስታስብ የነበረው፡፡ (ሳቅ) እሺ ጌትነት What is a problem? Share with us the answer you have come up with after all that deep thinking. Tell us. (ችግር ምንድነው? እስኪ እባክህ ከዚህ ሁሉ ተመስጦ በኂላ የደረስክበትን መልስ ንገረን) ጌትነት፡- Okay, sir. What is a problem? (መልካም፣ እውነት ግን ችግር ምንድነው?) (ሳቅ) (ጌትነት ጥያቄውን የማሰላሰያ አፍታ ወሰደ፡፡ ክፍሉ ወስጥ ከባድ ፀጥታ ወድቋል፡፡

ሁሉም በጉጉት የጌትነትን አፍ ያያል፤ አስተማሪውን ጨምሮ፡፡) እውነቱን ለመናገር ቲቸር፣ I am still thinking about it. (እውነቱን ለመናገር አሁንም እያሰብኩበት ነው) (ሳቅ) አስተማሪ፡- (እየሳቀ…) Take your time & think እንጠብቅሃለን፡፡ (ጊዜ ውሰድና አስብ፤ እንጠብቅሃለን) (ሳቅ፡፡) ጌትነት፡- No, sir. I’m afraid I will make you wait too long before I answer the question. (ይቅርታ፤ ጥያቄውን ከመመለሴ በፊት ብዙ እንዳላስጠብቃችሁ እሰጋለሁ፤ ብዙ ጊዜ ይወስድብኛል ብዬ እፈራለሁ፡፡) አስተማሪ፡- (እየሳቀ…) How long will it take you? (ምን ያህል ጊዜ ይወስድብሃል?) ጌትነት፡- A year, at the minimum. (በትንሹ አንድ ዓመት) (አሁንም ተማሪው ሁሉ ሳቀ፡፡) አስተማሪ፡- እንደዛ ከሆነ ብዙ ታስጠብቀናለህ፡፡ አኔው ልመልሰው እንግዲያው problem is any gap between what we are and what we want to be. Or problem is any gap between what is or what ought to be. (ችግር ማለት በሆነው እና መሆን በምንፈልገው ነገር መሃል ያለ ክፍተት ነው፡፡ ወይም ደግሞ በሆነው እና መሆን ባለበት ነገር መሃል ያለ ክፍተት ነው፡፡) እንዲህ እያለ የክፍሉ በር ተንኳኳ፡፡ ሰዓቱ አልቆ ነበር፡ የቀጣዩ ክፍለ ጊዜ አስተማሪ ነበር ያንኳኳው። ክፍሉ በቅሬታ ተንጫጨ፡፡ ለመስማት የጓጉት መልስ ሲጀምር ለክፍለ ጊዜው የተመደበው ሰዓት በማለቁ ሁሉም ተከፍተው ነበር፡፡ አስተማሪው ሲጋራውን እያጨሰ ወደ ቢሮ ሄደ፡፡) በቀጣዩ ጊዜ ሁሉም ችግር ምንድነው? እያሉ ሲያስቡ ሰነበቱ በቀጣዩ ጊዜም እንዲህ ተከሰተ፡፡ ክስተት አንድ፡- መምህር ሀሌታ በተደጋጋሚ ጫጫታ በመፍጠር ችግር ከስራ ተባረረ፡፡

ክስተት ሁለት፡- ንዴተኛው እና ቀናተኛው መምህር እራሱን ሰቅሎ ተገኘ፡፡ ‘My problem is life’ የሚል ማስታወሻ ትቷል፡፡ ክስተት ሶስት፡- ብታምኑም ባታምኑም፤ የቀናው መምህር ክፍል በጫጫታ መታጀብ ይዟል፡፡ ክስተት አራት፡- አልአዛር እና ሀና አሁን ችግራቸው ገብቷቸዋል፤ ይፋቀራሉ፤ ግን አብረው አልነበሩም፤ ሀና ስታንገራግር ቆይታ ነበር፤ አሁን አብራው ሆነች፡፡ ክስተት አምስት፡- ጌትነት የኔ ችግር ምንድነው እያለ ሲጨነቅ ሰነበተ፤ ችግሩ ጊዜ እንደሆነ ከስንት እንቅልፍ ማጣት በኋላ ተከሰተለት፤ የጊዜ እስረኛ መሆኑን ጠላው፤ እና በጊዜ ከመታሰር ለመውጣት ወሰነ፤ በጊዜ ውስጥ ወደ ፊትም ወደ ኋላም ሊያመላልሰው የሚችል የጊዜ መኪና (Time Machine) ለመፈልሰፍ ቆረጠ፡፡ እንደሚሳካለት እርግጠኛ ነበር፡፡ የግርጌ ማስታወሻ፡- Robert M.Pirsig, “Zen and the Art of Motorcycle Maintenance” በሚለው ድንቅ መፅሐፉ Chautauqua እንዲህ ይገልፀዋል፤ Chautauqua is an old time series of popular talks intended to edify and entertain, improve the mind and bring culture & enlightenment to the ears and thoughts of the hearer.

Read 3753 times Last modified on Saturday, 16 March 2013 12:30
More in this category: « ፍለጋ ኮፍያው »