Saturday, 16 March 2013 13:45

የኳታሩ ‹ድሪም ፉትቦል ሊግ› አልተረጋገጠም

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

በኳታር ንጉሳዊያን ቤተሰብ ስፖንሰርነት የአውሮፓ 24 ምርጥ ክለቦችን የሚያሳትፍ ‹ድሪም ፉትቦል ሊግ› ስለመታቀዱ በለንደኑ ታይምስ ጋዜጣ የቀረበ ልዩ ዘገባ እውነታ አልተረጋገጠም፡፡ ኳታር በ2022 እኤአ ላይ በመካከለኛው ምስራቅ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ እንዲካሄድ የተፈቀደውን 22ኛው የዓለም ዋንጫ የምታዘጋጀው ናት፡፡ በሃሳቡ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር እና ፊፋ እንዳይቀየሙ ተሰግቷል፡፡ የለንደኑ ታይምስ ጋዜጣ የኳታር ንጉሳዊያን ቤተሰብ ትልልቅ የአውሮፓ ክለቦች በ‹ድሪም ፉትቦል ሊግ› እንዲሳተፉ በማግባባት ላይ መሆናቸውን ሲዘግብ እስከ 175 ሚሊዮን ፓውንድ ለተሳትፏቸው ብቻ ለመክፈል ጥሪ አድርገጎላቸዋል ብሏል፡፡ ድሪም ፉትቦል ሊጉን በኳታር፤ በዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ፤ በሳውዲ አረቢያ እና በባህሬን በሚገኙ 6 ከተሞች በማዘዋወር በየሁለት ዓመቱ ለማካሄድ መታቀዱን የገለፀው ታይምስ አራቱ የእንግሊዝ ክለቦች ማን ዩናይትድ፤ ማን ሲቲ፤ አርሰናልና ቼልሲ እንዲሁም የስፔኖቹ ሪያል ማድሪድና ባርሴሎና በቀጥታ የተሳትፎ ግብዣ እንደቀረበላቸውም አውስቷል፡፡

በ‹ድሪም ፉትቦል ሊግ› መጀመር ዙርያ ጥሪ ቀርቦላቸዋል የተባሉት እነዚህ ክለቦች በጉዳዩ ላይ እስካሁን የሰጡት መግለጫ የለም፡፡ የኳታር እግር ኳስ ፌደሬሽን በኦፊሴላዊ ድረገፁ ስለ ድሪም ፉትቦል ሊጉ የሚወራውን ሲያስተባብል ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር እና ፊፋ እስካሁን በጉዳዩ ላይ ይፋ መግለጫ ከማውጣት እንደተቆጠቡ ናቸው፡፡ የኳታር ባለሃብቶች በ‹ድሪም ፉትቦል ሊግ› ከ9 አመታት በኋላ አገሪቱ ለምታዘጋጀው 22ኛው ዓለም ዋንጫ ለማሟሟቅ ብለው ውድድሩን ያዘጋጁታል ያሉ ዘገባዎችም ወጥተዋል፡፡ ሌስ ካህሬስ ዴፉትቦል የተባለ የፈረንሳይ ሚዲያ በበኩሉ የለንደኑ ታይምስ ዘገባውን ከማሰራጨቱ አንድ ቀን ቀደም ብሎ የድሪም ፉትቦል ሊግ ጅማሮን በአዝናኝ ሃሳብነት ማቅረቡን ገልጿል፡፡

የአውሮፓ እግር ኳስ በድሪም ፉትቦል ሊግ መጀመር ዙርያ የወጡ መረጃዎችን ለማጣራት እንደሚፈልግ የገለፁ አንዳንድ ዘገባዎች ከሻምፒዮንስ ሊግ እና በፊፋ ከሚዘጋጀው የዓለም ክለቦች ዋንጫ ጋር የሚመሳሰለው ውድድሩ እንዲካሄድ በምንም አይነት ፈቃድ እንደማይሰጥ አብራርተዋል፡፡ በአውሮፓ እግር ኳስ የኳታር ንጉሳዊያን ቤተሰብ የገንዘብ ተፅእኖ እየጨመረ መጥቷል፡፡ በ2010 እኤአ ላይ ከኳታር የንጉሳውያን ቤተሰብ አንዱ የስፔኑን ክለብ ማላጋ በባለቤትነት ተያዘ፡፡ በ2011 እኤአ ላይ ሌሎች የንጉሳውያን ቤተሰብ አባላት የፈረንሳዩን ፓሪስ ሴንትዠርመን በባለቤትነት ገዙ፡፡ ኳታር ፋውንዴሽን ደግሞ የታላቁ የስፔን ክለብ ባርሴሎና ማልያ በታሪክ የመጀመርያው ስፖንሰር መሆን እንደቻለ ይታወቃል፡፡

Read 4205 times