Saturday, 23 March 2013 13:27

ሰላማዊ ሰልፍ - የተከለከለ መብት!?

Written by 
Rate this item
(0 votes)

‹‹ለእንዲህ ዐይነት ሰው ለምን ይህ ክብር ይሰጣል በሚል ከጣልያን መንግሥት ጋራ ተነጋግረናል›› - አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ‹‹እስር ቤት የገቡትን ሰዎች ያለአግባብ ያንገላቱትን፣ ቶርች ያደረጉትን በግለሰብ ደረጃ በሕግ እንጠይቃለን›› - አቶ ይልቃል ጌትነት በአበባየሁ ገበያው እና ዓለማየሁ አንበሴ ከመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ መብቶች አንዱ የኾነው ሰላማዊ ሰልፍ የማካሄድ መብት ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ቅንጦት ነው›› በተባለበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡ አባባሉ÷ ከተራ ዜጎች ሳይኾን አማራጭ የ[መንግሥታዊ] ሥልጣን/የኀይል ማእከል ከኾኑትና ለዴሞክራሲያዊነትና ሰብአዊ መብቶች መከበር እንቆማለን ከሚሉት የተቃውሞ ፖሊቲካ ፓርቲ አመራሮችና የሲቪክ ማኅበራት ክፍሎች አንደበት ሲደመጥ መስማት÷ የአፈናው የከፋ ገጽታ መልክ አውጥቶ አካል ገዝቶ እንድናየው ያደርጋል፡፡

አመራሮቹ÷ ሰላማዊ ሰልፍ የማካሄድ መብት ጨርሶ መከልከሉ ከቶም ጥያቄ ሊኾንብን፣ ሊያነጋግረንና ሊያስገርመን አይገባም ሲሉን ግን የኹኔታውን ተስፋ አስቆራጭነት በጉልሕ ያረጋግጥልናል፡፡ አቶ ዐሥራት ኣብርሃም የአረና ለዴሞክራሲና ሉዓላዊነት ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊና የመድረክ የሥራ አስፈጻሚ አባል ናቸው፡፡ ሰላማዊ ሰልፍ የማካሄድ መብት ስለሚገኝበት ድቅድቅ ጨለማ አስመልክተው ሲናገሩ÷ ‹‹ሰላማዊ ሰልፍ የማካሄድ መብት ማንም ሊከለክለው የማይችል ሕገ መንግሥታዊ መብት መኾኑን ጠንቅቀን እናውቃለን፡፡ ከ1997 ዓ.ም. ወዲህ ግን ይህ መብት በተግባር የተከለከለ ኾኖ እናገኘዋለን፡፡

በኛ በኩል ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ ይቅርና አባሎቻችን በጽ/ቤት ደረጃ ከሚያካሂዱት ስብሰባ እንኳ ሲወጡ ጠብቀው እያሰሯቸው ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ሰላማዊ ሰልፍ ቅንጦት ነው የሚኾነው፤›› ይላሉ፡፡ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ ሕገ መግሥታዊ መብት መኾኑን ጠንቅቀው ቢያውቁም ይህን መብት የመጠቀም ዕድል ማግኘት ግን አለመቻላቸውን አቶ ዐሥራት ኣብርሃም ይናገራሉ፡፡ መብቱ በሕግ እንጂ በተግባር የተፈቀደ አለመኾኑን ተገንዝቦ አርፎ ከመቀመጥ ውጭ መብቱን ለማስከበር ገፍተው የሄዱበት አጋጣሚ እንደሌለ የሚናገሩት አቶ ዐሥራት÷ ‹‹ሓላፊነት የሚወስድ ፓርቲና አመራር እስካለ ድረስ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብትን መጠቀም ያስፈልጋል፤›› ይላሉ፡፡ ‹‹ክልክላውን የሚያደርገው አካል ርምጃውን ወደ እስር ከፍ ቢያደርገው ሁሉንም አካል ማሰር ስለማይችል በሂደት ሕግን ወደ ማክበር ሊመጣ ይችል ነበር፤›› የሚሉት አቶ ዐሥራት÷ መብት ለማስከበር የሚደረግ ትግል የምር መኾን እንዳለበት ያምናሉ፡፡

ትግሉ ደግሞ የኢሕአዴግን ባሕርይ ጠንቅቆ ከመረዳት በሚቀየስ ጠንካራና ሰላማዊ የመታገያ ስልት በማስቀመጥ እስከ መጨረሻው መሄድ ነው፡፡ የኢሕአዴግን አረንጓዴ መብራት እየተጠበቁ ብቻ በመንቀሳቀስ በተግባር ክልከላ የተደረገበትን የሰላማዊ ሰልፍ መብት ማስከበር እንደማይቻል የፓርቲው አመራር ያስረዳሉ፡፡ በሚልዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን በግፍ ላስጨፈጨፈው ዓለም አቀፍ ወንጀለኛ ማርሻል ሩዶልፍ ግራዚያኒ መታሰቢያ በስሙ ሐውልትና መናፈሻ መሥራት÷ ‹‹የአባቶቻችንን መሥዋዕትነት የሚያራክስ ነው›› በማለት የተቃውሞ ድምፃቸውን ባሰሙ ዜጎች ላይ የደረሰውን እናውቃለን፡፡ የኢትዮጵያ ተቆርቋሪ የግል ተነሣሽነት ማኅበር፤ ሰማያዊ ፓርቲና ባለራእይ ወጣቶች ማኅበር በጋራ በመኾን በሕጋዊ መንገድ አሳውቀው ለማካሄድ ባቀዱት ሰላማዊ ሰልፍ ላይ የወጡ ዜጎች ታስረዋል፡፡ ‹‹ይህ የአፈናው ዐይነተኛ ገጽታ ነው፤›› ይላሉ አቶ ዐሥራት፡፡ ‹‹የሰላማዊ ሰልፉ ሐሳብ የአገር ጉዳይ እንጂ የፖሊቲካ አጀንዳ እንደሌለው ግልጽ ነው፡፡ ሕዝብን የጨፈጨፉ ሰዎች ፍርድ ማግኘት ሲገባቸው ይባስ ብሎ መታሰቢያ ሊቆምላቸው አይገባም የሚለው ጉዳይ በሕግም በሞራልም የሚያስጠይቅ በመኾኑ አጀንዳነቱ የመንግሥት መኾን ነበረበት፡፡

አሁን ያለው መንግሥት የኢትዮጵያ መንግሥት ነኝ ብሎ ሃገር እያስተዳደረ ነው፡፡ ኢትዮጵያን የሚመለከት አጀንዳ እንደ አጀንዳ መደገፍ ነበረበት እንጂ በዚህ ጉዳይ ሰልፍ መከልከሉ፣ ከልክሎም የወጡትን ሰዎች ማሰሩ የሚገርም ነገር ነው፡፡›› በአቶ ዐሥራት እምነት÷ ኢሕአዴግ በሰላማዊ መንገድ ለሃገሪቱ ዲሞክራሲያዊነት ይጠቅማል በሚል እሳቤ የሕዝብን ጥያቄ አይቀበልም፡፡ ሰልፍ የሚያስወጡ በርካታ ጉዳዮች ቢኖሩም በተለይ ከ1997 ዓ.ም ወዲህ ሰልፍ ለማድረግ የሚያስችል አበረታች ነገር የለም፡፡ ስለዚህም ፖሊቲካዊ በኾኑ ጉዳዮች ላይ ሰልፍ የማድረግ መብትን እስከ መጨረሻው አሟጦ ከመጠቀም አንጻር ፓርቲዎች ብዙ መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ‹‹መብቱ የሚፈቅድለትን ያህል ለመጠቀም ታግሎ ለመታሰር ዝግጁ የኾነ የፖለቲካ አመራርና አባል መኖር አለበት፤›› የሚሉት አቶ ዐሥራት÷ ‹‹ማንም የራሱን መብት ማስከበር ካልቻለ ሌላ አካል መጥቶ መብቴን ያስከብርልኛል ማለት አይችልም፤›› ይላሉ፡፡ አሁን ያለው የዜጎች መብት ፅልመታዊ የኾነው በአደባባይ በሚታየው ሰላማዊ ሰልፍ የማካሄድ ችሎታ አንጻር ብቻ ሳይኾን፣ ‹‹ፍርድ ቤት ሄጄ መብቴን አስከብራለኹ ማለትም ተስፋ አስቆራጭ ነው፡፡ ፍርድ ቤት አቤቱታ የማቅረብ መብት አለኝ በሚል ለመከራከር ቢሞከር ማስረጃ የለውም ተብሎ አቤቱታው ውድቅ ይኾናል፤›› ይላሉ አቶ ዐሥራት፡፡

‹‹ፍርድ ቤትን ብቸኛ አማራጭ አድርጐ መጠቀም የሚቻለው ነፃና ገለልተኛ መኾኑ የታመነበት የፍርድ ተቋም ሲኖር ነው፡፡ በኛ አገር እንደዚህ ዐይነቱ የፍርድ ቤት ተቋም እንደሌለ ደግሞ ይታወቃል፡፡›› አቶ ዐሥራት በመደራጀት፣ ሐሳብን በነጻነት መግለጽና ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ መብቶች መረጋገጥ ተስፋ የቆረጡ ይመስላሉ፡፡ መብትን ለማስከበር ጠንካራ ተፎካካሪ ፓርቲና ለመታገል የቆረጠ አመራር፣ አባላትና ሕዝብ ያስፈልጋል ባይ ናቸው፡፡ አለበለዚያ በተቃዋሚው በኩል÷ በየጊዜው መታፈንን ከማስተጋባት የዘለለ ፋይዳ የሌለው መብት የማስከበር ሥራ ሊሠራ እንደማይችል፣ ገዢው ፓርቲም የራሱን መቀመጫ ለማደላደል ሌት ተቀን ከመትጋት ውጪ ለሕዝብ መብት ደንታ ያለው ፓርቲ ሊኾን እንደማይችል የፓርቲው አመራር አረጋግጠው ይናገራሉ፡፡

የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀ መንበር አቶ ይልቃል ጌትነት÷ ‹‹የታላቋን ሃገር ኢትዮጵያ ታሪክ እየዘነጋን፣ በቀድሞ አባቶቻችን ደም ላይ እንደቆምን እየረሳን፣ ብሔራዊ ስሜት ከልጆቻችን ከትውልዶችም እየጠፋ ውሎ አድሮ አንድ ያደረገን ክር ሁሉ እየላላ ገመናችንን ለጠላቶቻችን እያጋለጥን ነው፡፡ አልፎ ተርፎ ደግሞ የእኛ ገዳዮች ብሔራዊ ጀግና ተብለው ሐውልት እየተሠራላቸው እኛ ምን ያህል ቁልቁል እየሄድን መኾኑን የሚያመለክት ነበርና ይህን መቃወም፣ አባቶቻችንን ማሰብ ስለነበረብን ይህን ለማስታወስ በሕገ መንግሥቱ ሰላማዊ ሰልፍ ስለማድረግ የሰፈረውን ተጠቅመን ለሚመለከተው አካል አሳውቀን ነበር ሰልፉን የጠራነው፡፡›› ይላሉ፡፡ ‹‹የ30 ሺሕ ሰዎች ደም ሳይገድበው መብታችንን የሚገፍ አካል ካለ፤ ይግፈፉን፤ ለዚያ ግን እኛ የመጨረሻውን ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ ነን፤›› የሚሉት አቶ ይልቃል ቀጣይ አካሄዶቻቸውን ያመለክታሉ÷ ‹‹እስሩም ኾነ የሰላማዊ ሰልፍ ክልከላው በጉልበት የተደረገ ነው፡፡ እኛ ግን እስር ቤት የገቡትን ሰዎች ያለአግባብ ያንገላቱትን. ቶርች ያደረጉትን በግለሰብ ደረጃ በሕግ እንጠይቃለን፡፡

›› ‹‹የግራዚያኒ ሐውልት መቆሙ፣ መናፈሻ መሠየሙ አግባብ አይደለም›› የሚሉት ደግሞ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የውጭ ግንኙነት መምሪያ መምህር ሰሎሞን ቶልቻ ናቸው፡፡ በጉዳዩ ላይ የግል አስተያየታቸውን የሰጡን መምህሩ፤ ‹‹ታሪኩን የሚያውቅና ኢትዮጵያዊነቱ የሚቆረቁረው እያንዳንዱ ዜጋ በዋዛ የሚያየው ጉዳይ አይደለም፡፡ በሃገር ደረጃ የየትኛውም እምነት ተከታይ ይኹን ኢትዮጵያዊ ሁሉ ትላንት አባቶቻችንን፣ በምን ዐይነት ኹኔታ እንደጨረሰ፣ በቁም እንደቀበረ፣ ባካፋ ከርጉዝ ሴት ሆድ ፅንስዋን እያወጣ በአደባባይ የንጹሐንን ደም ያፈሰሰበት ነው፡፡ በሃገር ደረጃ ሁሉም ረጋ ባለ መልክ መክረው አንድ ውሳኔ ማስተላለፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡›› ይላሉ፡፡ ‹‹ትላንት ባሳለፍነው የብፁዓን አባቶቻችን÷ አቡነ ጴጥሮስ እና አቡነ ሚካኤል÷ ደምና ሕይወት አንደራደርም፡፡ እንዲህ ዐይነት ሰው ለጣልያን ሕዝብና መንግሥት ሞዴል የሚኾነው ከምን አኳያ ነው፡፡

መልእክቱስ ምንድን ነው? እንደምንስ ዛሬ ሊነሣ ቻለ? መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው ብንልም በልማት፣ በሰላምና በጸጥታ፣ የሰው ልጆች በፍቅር ተከባብረው እንዲኖሩ፣ በመልካም አስተዳደር ዙሪያ ቤተ ክርስቲያናችን ከመንግሥት ጋራ በአጋርነት ትሰራለች፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን የአገሪቱን ታሪክ በአደራ ተቀብላ አቆይታለች፡፡ በዩኔስኮ ደረጃ የተመዘገቡ የሦስት ሺሕ ዘመን መንፈሳዊና ቁሳዊ ቅርሶች ባሏት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነው ያሉት፡፡ ጉዳዩ በቤተ ክርስቲያኒቱ ብቻ የሚወሰን ሳይኾን መንግሥትንም ይመለከተዋል፡፡ ሲቪክ ማኅበራት፣ አባት አርበኞች፣ ተመራማሪዎችም ይኹኑ የሃገር መልካም ገጽታ ግንባታ የሚቆረቁራቸው ሁሉ አብረው ሊሰለፉበት ይገባል - እንደ መ/ር ሰሎሞን ቶልቻ፡፡ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ጉዳዩን የሚለከቱት ለየት ባለ መንገድ ነው፡፡ የግራዚያኒን ሐውልት ለመትከል የተንቀሳቀሰው የኅብረተሰብ ክፍል/ግለሰቦች÷ በጣሊያን መንግሥት ደረጃ ሳይኾን ከጣልያን ማእከላዊ መንግሥት ፍላጎትና ዕውቅና ውጭ በጣሊያን አንድ ግዛት ውስጥ የራሱ አስተዳደር ባለው አንድ አካባቢ የሚገኝ ነው፡፡ ይህ እንቅስቃሴ እንደተሰማ ከጣልያን መንግሥት ጋራ በዲፕሎማሲ ቻናል ተነጋግረናል፡፡ የፋሺዝም ታሪክ ያጠላበት የኢትዮ - ጣልያን ግንኙነት ሳንካ ሊገጥመው ይችላል፤ ፋሽዝም ደግሞ የኢትዮጵያም ብቻ ሳይኾን የጣልያን ሕዝብ ጠላት ነው፤ ለእንዲህ ዐይነት ሰው ለምን ይህ ክብር ይሰጣል በሚል ከጣልያን መንግሥት ጋራ ተነጋግረናል፡፡

የጣልያን መንግሥት እንደሚለው÷ ይህን ነገር ለማሠራት የተንቀሳቀሰው የኅብረተሰብ ክፍል በማእከላዊው መንግሥት አይታወቅም፤ እንቅስቃሴው የማእከላዊ መንግሥት አቋም አይደለም የሚል ምላሽ ነው ያገኘነው፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ መንግሥት ጉዳዩን በዝምታ አልተመለከተውም፡፡ በሁለት አገሮች መካከል እንዲህ ዐይነት ነገር ሲፈጠር ‹‹ሌጋሲዎን ዲፕሎማሲ›› የሚባል ነገር አለ፡፡ ዝም ብሎ አይነገርም፡፡ መጀመሪያ ውይይት ይደረጋል፡፡ ንግግርና መግባባት ይደረጋል፤ በሂደት ነው፡፡ ጉዳዩ የኢትጵያን ሕዝብ እንደሚያስቆጣ፣ የሁለትዮሽ ግንኙነቱንም እንደሚጎዳ በእኛ ኤምባሲ በኩል ለጣልያን መንግሥት ተገልጾልታል፡፡

አምባሳደር ዲና በመጨረሻም ‹‹ኅብረተሰቡ እንደ ኅብረተሰብ በተለያዩ መንገዶች የሚያደርጋቸው ሰላማዊ ሰልፎች፣ ፒቲሽኖችና ሌሎች የተቃውሞ ተጽዕኖዎች በመጨረሻ ወደምንፈልገው ውጤት ሊያመሩ ይችላሉ፤›› ካሉ በኋላ እንቅስቃሴውን እስከ መጨረሻው ድረስ ተከታትሎ የማስቆም ጥረቱ÷ የሁለቱን ሃገሮች የቆየ ጤናማ ግንኙነት በማይጎዳና ያለፈውን ጠባሳ በማይቀሰቅስ መልኩ እንደሚቀጥል አመልክተዋል፡፡ ከዲፕሎማሲያዊ ጥረቱ ውጭ በኅብረተሰቡ ደረጃ ተጋግሎ ስለቀጠለው የተቃውሞ እንቅስቃሴ የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባዩ እንዲህ ይበሉ እንጂ ሕዝባዊውን ዲፕሎማሲ አስመልክቶ በተጨባጭ የታየው ግን ሰላማዊ ሰልፍ የማካሄድ ሕገ መንግሥታዊ መብትን በተግባር የሚከለክል ርምጃ ነው፡፡ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የሕግ ባለሞያ እንዳሉት÷ ከምርጫ 97 ወዲህ የአንድ ዴሞክራሲያዊ አገር መለኪያዎች የኾኑት የመደራጀት፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግና ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት መጀመሪያ ተራ በተራ በወጡት ሕጎችና ዐዋጆች ገደብ ተጣለባቸው፡፡

አሁን በመጨረሻ÷ ሰላማዊ ሰልፍ የማካሄድ ሕገ መንግሥታዊ መብት ለገዢው ፓርቲ አጀንዳዎች ማስተጋቢያ ብቻ የተሰጠ እስከ መምሰል ደርሷል፡፡ ይህም በተቃውሞው ሰፈር ያሉት አካላት ‹‹የመተንፈስ መብት ተከለከልን›› እስከማለት ደርሰው ሲያሰሙት የነበረው ምሬት የተቀላቀለበት አቤቱታ መደምደሚያ ማረጋገጫ ኾኗል፡፡ የተከለከለው ሕገ መንግሥታዊ መብት - ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ዴሞክራዊ መብት - ለኢትዮጵያውያን ቅንጦት ነው መባሉ እውነት ሳይኾን አይቀርም፡፡

Read 2950 times