Saturday, 23 March 2013 13:24

መንግስት፣ የ5 አመቱ እቅድ እንደማይሳካለት የሚነግረን መቼ ነው?

Written by 
Rate this item
(4 votes)

እስካሁን የተሳካው ምንድነው? ገበሬዎችን በ1ለ5 እየሰበሰቡ “የልማት ሠራዊት” ማደራጀት “የተፈጥሮ ሃብት ልማት” እያሉ ገበሬዎችን በዘመቻ መጥመድ ያልተሳካውስ ምንድነው? “ልማት” የሚባለው አልተሳካም። ትልልቅ ፕሮጀክቶች ተጓተዋል የገበሬዎች የእርሻ ምርት፣ የእቅዱን ግማሽ ያህል እንኳ አልተሳካምእንደኔ እንደኔ፣ የእድገትና የትራንስፎርሜሽ እቅዱ የታሰበውን ያህል እየተሳካ እንዳልሆነና፣ በታለመለት መጠን ሊሳካ እንደማይችል፣ ካሁኑ ቢነገር የሚሻል ይመስለኛል። አሁኑ “እቅጩን” ይነገረን የምለው፤ “እርማችንን እንድናወጣ” በሚል አይደለም። በተጨባጭ መረጃ ላይ በመመስረት እቅዱን መከለስና መስራት ይሻላል ለማለት ፈልጌ ነው። እቅዱ እየተሳካ እንዳልሆነና፣ በታቀደው መጠን ተግባራዊ ሊሆን እንደማይችል ብዙም አከራካሪ አይመስለኝም።

ግዙፎቹን ፕሮጀክቶች ተመልከቱ። ከሁሉም በላይ ትልቅ ትኩረት የተሰጠው የህዳሴ ግድብን መጥቀስ ይቻላል። በአምስት አመት ይጠናቀቃል የተባለው የህዳሴ ግድብ፣ አሁን በሚታየው ሁኔታ ከቀጠለ አስር አመት ሊፈጅ ይችላል። በሁለት አመት ውስጥ የተከናወነው ስራ 18 በመቶ ያህል ነውና። ሌሎቹ ትልልቅ ፕሮጀክቶችም ብንመለከት ከዚህ የተሻለ ውጤት አናገኝም። በአምስት አመቱ እቅድ ተገንብተው ስራ ይጀምራሉ የተባሉት 10 የስኳር ፋብሪካዎች፣ ገና በጣም ገና ናቸው። 10 አዳዲስ ፋብሪካዎችን ገንብቶ ለማጠናቀቅ ይቅርና፤ ከሰባትና ከስምንት አመት በፊት እቅድ ወጥቶላቸው ቢበዛ ቢበዛ በሶስት አመት ይጠናቀቃሉ ተብለው የነበሩት የስኳር ፋብሪካ ግንባታዎችና የማስፋፊያ ፕሮጀክቶችም እስካሁን ስራ አልጀመሩም።

በ1997ቱ የአምስት አመት እቅድ ውስጥ የተጀመረው የተንዳሆ ፕሮጀክት፣ የሸንኮራ ልማቱም ሆነ የስኳር ፋብሪካው ግንባታው ይሄው፣ ለ2002ቱ የአምስት አመት እቅድ ተሸጋግሮ አሁንም አልተጠናቀቀም። የመተሃራና የከሰም ፕሮጀክቶችም እንዲሁ እየተጓተቱና እየተሸጋገሩ የመጡ ነባር ፕሮጀክቶች ናቸው - በመጪው አመትም ስራ ይጀምራሉ ተብሎ አይጠበቅም። ሊጠናቀቅ ተቃርቧል የተባለው ነባሩ የወንጂ ስኳር ፋብሪካ ማስፋፊያ ፕሮጀክት እንኳ፤ በሚቀጥለው ወር፣ በሚቀጥለው የመንፈቅ አመት እየተባለ ስንት አመት አስቆጠረ? ይሄው ዘንድሮም፤ በጥቅምት ወር ስራ ይጀምራል ከተባለ በኋላ፤ ስራው ተጓትቶ ለጥር ይደርሳል ተባለ። ከዚያ ወደ መጋቢት ተሸጋገረ።

አሁን ደግሞ ወደ ሰኔ ወይም ወደ ሃምሌ። መንግስት እነዚህ ነባር ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ ሳይችል፤ ተጨማሪ 10 አዳዲስ የስኳር ፋብሪካዎችን መገንባት ይችላል ብላችሁ የምታስቡ ከሆነ፤ “ተአምር” የማየት ረሃብ ይዟችኋል ማለት ነው። ሌላኛው ትልቅ ፕሮጀክት የባቡር ሃዲድ ግንባታ ነው። ይሄኛውም ፈቅ አላለም። ከሁሉም በላይ፣ በጣም ተስፋ አስቆራጭ የሆነው ደግሞ የእርሻ ምርት ብዙም ሲያድግ አለመታየቱ ነው። በአማካይ በነፍስ ወከፍ ሲሰላ፣ የእርሻ ምርት በየአመቱ በ6% እንዲያድግ ነበር የታቀደው - በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ። የአምናው እድገት ግን፤ 2.5% ገደማ ብቻ ነው። የእቅዱ ግማሽ ያህል እንኳ አልተሳካም። መንግስትና ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ፣ ይህንን ያውቃሉ። በአምስት አመት ውስጥ ይተገበራል ተብሎ የወጣው “የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ”፣ የታሰበውን ያህል እየተሳካ እንዳልሆነ ኢህአደግ በግልፅ ባይናገርም፣ የገበሬዎች ምርት የታሰበውን ያህል እያደገ እንዳልሆነ የሚክደው አይመስለኝም።

እንዲያውም፤ የኢህአዴግ ድርጅቶች ሰሞኑን ባካሄዷቸው ጉባኤዎች ጉዳዩ ተነስቷል። የእርሻ ምርት ላይ የሚታየው እድገት ዝቅተኛ እንደሆነ በኢህአዴግ ጉባኤዎች በየጣልቃው ጠቀስቀስ ተደርጎ ሲታለፍ ታዝባችሁ ይሆናል። ለምሳሌ ብአዴን በባህርዳር ባካሄደው ጉባኤ ላይ፤ “የአምናው የእርሻ ምርት እንደተጠበቀው አይደለም” ተብሏል። በሃዋሳው ጉባኤ ደግሞ፣ “የሰብል ምርት ላይ ድክመት አለ” ተብሏል። አሳሳቢነቱ፣ የአምና ምርት ከጠበቀው በታች መሆኑ ብቻ አይደለም። የዘንድሮው የመኸር ምርትም እንደተጠበቀው እንዳልሆነ የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ጥናት ያረጋግጣል።

እናም፣ በነፍስ ወከፍ ሲሰላ፣ የዘንድሮ የግብርና ምርት እድገትም እንደአምናው 2.5 በመቶ ገደማ ብቻ እንደሚሆን ይገመታል። ምን ለማለት ፈልጌ ነው? እንደሌሎቹ ዋና ዋና የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅዶች ሁሉ፣ የእርሻ ምርትም የታቀደለትን ያህል እያደገ እንዳልሆነ ሊካድ አይችልም ለማለት ነው። በእርግጥ፣ ታዲያ በኢህአዴግ ጉባኤዎች ላይ ለምን በጨረፍታ ብቻ ተጠቅሶ ታለፈ? “አልተሳካልኝም” ብሎ መናገር አስጠልቶት ሊሆን ይችላል። በአራቱም ጉባኤዎች ላይ እጅግ ሲበዛ ተደጋግሞ የተነገረውስ ምንድነው? የኢህአዴግ ድርጅቶች በሙሉ በየፊናቸው ባካሄዱት ጉባኤ፤ በገጠርና በገበሬዎች ላይ ስኬታማ ውጤት እንዳስመዘገቡ ደጋግመው ገልፀዋል። የተመዘገበው ውጤት ግን የምርት እድገት አይደለም። እናስ ምንድነው? “በልማት ሠራዊት ግንባታ” እና “በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ” ዙሪያ እጅግ “አስደናቂ ውጤት” መመዝገቡን ነዋ የገለፁት።

አስደናቂውን ውጤት የሚያብራሩ “ድንቅ” መረጃዎችና ሪፖርቶችም ቀርበዋል። በመቶ ሺ እና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ገበሬዎችን በ1ለ5 አደራጅተን ሰፊ “የልማት ሠራዊት” ገንብተናል ብለዋል የኢህአዴግ ድርጅቶች። በመቶ ሺ እና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ገበሬዎችን ለ”ተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ” በዘመቻ አሰልፈናል ተብሏል። በእርግጥም “የልማት ሠራዊት” ተገንብቶ፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ገበሬዎች “ለተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ” ለበርካታ ቀናት በዘመቻ ሲሰማሩና በየእለቱ እየጨፈሩ ሲመለሱ የሚያሳዩ የኢቲቪ ዘገባዎችን ተመልክተናል። ግን ምን ዋጋ አለው? የ“ልማት” እና የ“ሃብት” ውጤት አልተመዘገበም። የኢህአዴግ ድርጅቶች የሚያቀርቡት፣ ያ ሁሉ አስደናቂ ውጤትና ሪፖርት፤ በገበሬዎች የእርሻ ወይም የሰብል ምርት ላይ ከወትሮው የተለየ ቅንጣት ለውጥ አላመጣም።

ምን አስታወስኩ መሰላችሁ? ከአምስት አመት በፊት ነጋ ጠባ እንሰማው የነበር የ“ውሃ ማቆር” መፈክር። በ“ውሃ ማቆር” ምን ያህል አስደናቂ ውጤት እንደተመዘገ ለማስረዳት ይቀርቡ የነበሩ ድንቅ ሪፖርቶችን አታስታውሱም? በየክልሉ ምን ያህል እልፍ አእላፍ ገበሬዎች፣ ውሃ ማቆሪያ ጉድጓድ እንደቆፈሩ፣ በላስቲክና በሲሚንቶ ጉድጉዱን እያበጃጁ እንደሆነ በዝርዝር የሚተነትኑ እልፍ ዘገባዎችና ሪፖርቶች ቀርበዋል - ያኔ ከአምስት አመት በፊት። ለውሃ ማቆር ዘመቻ ስንትና ስንት ሚሊዮን ብር እንደተመደበ፣ በመቶ ሺ እና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ገበሬዎችም በዘመቻው እንደተሳተፉ… የሚያብራሩና የሚዘረዝሩ ሪፖርቶች ትዝ አይሏችሁም? ምን ያደርጋል! አገሪቱ በ’ውሃ ማቆር’ ዘመቻ እንደምትለወጥ የሚያበስሩ ድንቅ ሪፖርቶች ሲቀርቡና ሲደመጡ ከርመው፣ ወራት አልፈው አመታት ተተክተው… መጨረሻ ላይ ሲታይ፤ ምንም ጠብ የሚል ውጤት ጠፋ።

በቃ፤ በገበሬዎች ምርት ላይ ምንም የመጣ ለውጥ የለም ተባለ። የኋላ ኋላ፣ የፌደራል ባለስልጣናትና ከየክልሉ የመጡ ርዕሰ መስተዳድሮችና ከፍተኛ መሪዎች በተሰበሰቡበት ነው ፍርጥርጡ የወጣው። በእርግጥ በስብሰባው ላይ፣ እንደወትሮው ድንቅ የውሃ ማቆር ሪፖርቶችና ማብራሪያዎች ቀርበዋል። በዚህ መሃል ነው፣ አንድ ቀላል ጥያቄ ዱብ ያለው… “ግን በገበሬዎች ምርት ላይ ያመጣው ለውጥ ምንድነው?” የሚል ጥያቄ። ጥያቄውን ለፌደራልና ለክልል ከፍተኛ መሪዎችና ባለስልጣናት በአፅንኦት ያቀረቡት ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ነበሩ። ከመነሻው “ውሃ ማቆር” የሚለው ሃሳብ የመጣው፤ የገበሬዎችን ምርት የማሳደግ አላማን ለማሳካት ነበር።

አሁን ግን፣ የተነሳንበት አላማ እየተረሳ፣ የውሃ ማቆሪያ ጉድጓዶችን የመቁጠርና የመደመር ነገር… ራሱን የቻለ አላማ እየሆነ መጥቷል ያሉት አቶ መለስ፤ ሥራው የገበሬዎችን ምርት ለማሳደግ በሚጠቅም መንገድ እየተሰራ ነው ወይ? የውሃ ማቆር ዘመቻው ወደ ገበሬው ኪስ ተጨማሪ ገቢ በሚያመጣ መንገድ እየተሰራ ነው ወይ? በማለት አጥብቀው ጠይቀዋል። በእርግጥ፤ የውሃ ማቆር ዘመቻውን በቀዳሚነት ያቀነቀኑት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሊሆኑ እንደሚችሉ የሚገምቱ ሰዎች አሉ። ነገር ግን፤ እዚህ ላይ ዋናው ቁምነገር፣ የሆነ እቅድ የታሰበለትን ውጤት እያስገኘ እንዳልሆነ በተግባር ሲታይ፣ ሳይረፍድበት ቆም ብሎ ማሰብ ማስፈለጉ ነው።

አለበለዚያ፣ ያሸበረቀ ሪፖርት ማዘጋጀትና የተንቆጠቆጠ መግለጫ ማቅረብ፤ በአንዳች ተአምር ወደ ምርት እድገትና ወደ ኢኮኖሚ እድገት እንዲቀየር እየተቁለጨለጩ መጠበቅ ይሆናል። የሆነ ሆኖ፤ “የውሃ ማቆር ዘመቻው ምን አይነት ተጨባጭ ውጤት አስገኘ?” በሚለው ጥያቄ አማካኝነት ነገሩ መቋጫ አገኘ። ከዚያ በኋላማ በየእለቱና በየሰዓቱ በሬድዮና በቲቪ ሲያሰለቸን የነበረው የውሃ ማቆር ነገር ድምፁ ጠፋ። በውሃ ማቆር ፋንታ፤ ባለፉት ሁለት አመታት በመንግስት ሚዲያ የሚቀርብልን የዘወትር ቁርስና እራት፤ “የልማት ሠራዊት ግንባታ” እና “የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ” በሚሉ ሃረጎች የተጥለቀለቁ “ድንቅ ሪፖርቶችና መግለጫዎች” ናቸው - የገበሬዎችን ምርት ለማሳደግ ይጠቅማሉ እየተባለ። ነገር ግን፣ የአምናውና የዘንድሮው ተጨባጭ የምርት መጠን ሲታይ፣ እነዚያ ድንቅ ሪፖርቶች፣ የገበሬዎችን ምርት ለማሳደግ እየጠቀሙ አለመሆናቸውን መገንዘብ ይቻላል።

በ1ለ5 የተደራጀ ገበሬና በየቀበሌው ለስራ ዘመቻ የተጠራ ገበሬ ምን ያህል እንደሆነ እየቆጠሩ “ድንቅ ሪፖርት” ማቅረብ… ራሱን የቻለ ትልቅ አላማ እየሆነ መጥቷል። ይሄ ግን አያዛልቅም። ገበሬዎችን በተፅእኖ አደራጅቶ በዘመቻ እንዲሰሩ ማድረግ፤ ወደ ገበሬዎቹ ኪስ ተጨማሪ ገቢ አያመጣም። እፍኝ የእህል ምርት ለማሳደግም አይጠቅምም፤ ገበሬዎችን ከእውነተኛው የምርት ስራ ከማስተጓጎል ያለፈ ጥቅም አያስገኝም። አሁን ያለው አንዱ አማራጭ፤ “የሠራዊት ግንባታ” እና “የሥራ ዘመቻ” ሪፖርቶችን እያሳመሩ በመጓዝ ያለመፍትሄ ውድቀትን መደገስ ነው። ሌላኛው አማራጭ ደግሞ፤ የአምስት አመቱ እቅድ እየተሳካ እንዳልሆነ በግልፅ ተናግሮ፤ በሌሎች የኢኮኖሚ መስኮች ላይ እንደሚታየው የመንግስት ገናናነት መልካም ውጤት እንደማያስገኝ ተገንዝቦ መፍትሄ መፈለግ ነው። ኢህአዴግ የትኛውን አቅጣጫ እንደሚመርጥ እስካሁን በግልፅ አይታወቅም።

Read 3504 times