Saturday, 23 March 2013 13:42

አቤቱታ ለ‘በላይ አካል’…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)

ግራ የገባው ብሶተኛ፣ የምድሩ ነገር አልሆን ቢለው፣ “እህ…” ብሎ የሚያዳምጥ፣ “አይዞህ…” ብሎ የሚያበረታታ፣ “አትበሳጭ ሁሉም ያልፋል…” ብሎ የሚያጽናና ቢያጣ፣ እንደገና ለአቤቱታ የአንድዬን በር እያንኳኳ ነው፡፡ ብሶተኛ፡— አንድዬ ቢቸግረኝ፣ ግራ ቢገባኝ፣ የምጨብጠው ቢጠፋኝ ተመልሼ መጣሁ፡፡ አንድዬ፡— አላወቀሁህም፡፡ ማን ነህ አንተ? ብሶተኛ፡— እኔው ነኝ’ኮ አንድዬ… አንድዬ፡— እኮ አንተ ማነህ? ብሶተኛ፡— እኔው ነኛ አንድዬ፣ ከዚህ በፊት አንድ ሁለት ጊዜ አናግረኸኝ… ትዝ አይልህም? ከዚህ በፊት ከዚች ከኢትዮዽያ… አንድዬ፡— እህ…አጅሬው ተመልስህ መጣህልኝ! ብሶተኛ፡— አዎ አንድዬ፣ ተመልሼ መጣሁ፡፡ ግራ ሲገባኝ ምን አባቴ ላድርግ ብለህ ነው! እውነቱን ልንገርህ አይደል፣ መኖር ሁሉ እያስጠላኝ ነው አንድዬ፡— እሺ፣ አሁን ደግሞ ምን ሆንን ልትለኝ ነው የመጣኸው? ብሶተኛ፡— ምን ያልሆንነው ነገር አለ፣ አንድዬ! ምን ያልሆንነው ነገር አለ! ይኸውልህ እንደ ሰማንያ ሚሊዮንነታችን ልባችንም ሰማንያ ሚሊዮን ሆኖልሀል፡፡ ተነጋግረን መደማማጥ፣ ተወያይተን መተማመን እያቃተን ነው፡፡

አንድዬ፡— እና ምን ሁን ነው የምትለኝ! የእናንተ ነገር ሰልችቶኛል ብዬህ አልነበር! እውነቱን ልንገርህ አይደል፣ አሁን አሁንማ እናንተን የፈጠርኩበት ምክንያት ሁሉ ምን እንደነበር እንኳን ዘንግቼዋለሁ፡፡ ብሶተኛ፡— አንድዬ እንዲህማ አትጣለን፡፡ …የአንተው የተመረጥነው ህዝቦች አይደለን እንዴ! አንድዬ፡— ጎሽ! እንዴት አምሮባችኋል? ጭራሽ ምርጦቹ ሆናችሁና አረፋችሁት! ደግሞ ማነው የተመረጣቸሁ ህዝቦቼ ናችሁ ያለው? ብሶተኛ፡— እንዴ ራስሀ ነህ አንድዬ፣ ራስህ ነህ! ምነው በታላቁ መጽሐፍህ እንኳን ስማችን ስንትና ስንት ጊዜ ተጠቅሶ… አንድዬ፡— እንደሱ ነው ነገሩ! በል እሱን ተወው ተመልሶ አይጻፍ ነገር ሆኖ ነው አሁንም የምታነበው፡፡ በዛ በደጉ ዘመን፣ ለክራቸውና ለማተባቸው የታመኑ፣ የወደቀን ማንሳት እንጂ የቆመን መጣል የማያውቁ፣ እኔ ዘንድ መጥተው “የእከሌን መጨረሻ ሳታሳየኝማ…” እያሉ ሊያሳስቱኝ እያለቀሱ የማይለማመኑ፣ ኮርተው የሚያኮሩኝ ነበሩ የአገርህ ሰዎች፡፡ በያኔ ዘመን የተጻፈ ነው፡፡ አሁን ላላችሁትማ፣ አይደለም እንደዛ ሊጻፍላችሁ፣ የእኔ ፍጡር መሆናችሁን እየተጠራጠርኩ ነው፡፡

ብሶተኛ፡— አንድዬ እኛም እኮ ግራ ገብቶን ነው! ከዛሬ ነገ ይሻላል ስንል ይኸው ስንቧጨቅ፣ ስንናከስ፣ የምንጠፋፋበትን መንገድ ስናሰላስል… ብቻ አንድዬ የእኛ ነገር እንዲህ በአጭር ተወርቶ አያልቅም፡፡ አንድዬ፡— ጉድ እኮ ነው፣ የሚገርመኝ ምን እንደሆነ ልንገርህ፣ እርስ በእርሳችሁ መአት ክፍልፍል ስትፈጠሩ እያየሁ ሲገርመኝ … “እነሱ ከተመቻቸው እንደ ፍጥርጥራቸው” ብዬ ብተዋችሁ… በገዛ ቤቴ! በገዛ ቤቴ! ብሶተኛ፡— ምን አደረግን አንድዬ…ኧረ እንዲህ አትማረርብን፡፡ አንድዬ፡— ደግሞ ምን አደረግን ትለኛለህ! ሌላውን ብተዋችሁ፣ “ልብ ሲገዙ ዓይናቸው ይከፈትላቸዋል” ብዬ እንዳላየ ባልፍ፣ በገዛ ቤቴ ዘር ትቆጣጠራላችሁ? እኔ የፈጠርኳችሁ ሰው አድርጌ፣ ጭራሽ በወንዝ ልጅ፣ በአገር ልጅ እየተቧደናችሁ ቤቴን ልታበላሹ! ብሶተኛ፡— ምን መሰለህ… አንድዬ፡— በቃ! በቃ! የእናንተን ምክንያት መስማት ነው የሰለቸኝ፡፡ ደግሞስ ትንሽ ሆዳችሁ ሲሞላ እኔን የለም እስከ ማለት እየደረሳቸሁ፣ ሆዳችሁ ሲጎድል ደግሞ መጥታችሁ ታለቅሳላችሁ፡፡ ብሶተኛ፡— አንድዬ፣ ሉሲፈር እኮ ነው እንዲህ የሚያደርገን… አንተን ረስተን የት እንደርሳለን! አንድዬ፡— እና አሁን ምን አድርግ ነው የምትለኝ? ብሶተኛ፡— አንድዬ፣ መኖር አቃተን፡፡

በቀን አንድ ጊዜ መብላት ራሱ ቅንጦት እየሆነብን ነው፡፡ ሰዉ ከፋ፡፡ አንድዬ፣ ሰዉ በጣም ከፋ! አላስቆም፣ አላስቀምጥ፣ አላራምድ፣ አላሠራ እያለን ነው፡፡ አንድዬ፡— ማን ነው ይሄን የሚሠራው? እኔ ሌላ፣ ሌላ ቦታ ስመለከት አምልጦኝ እንደሆነ …ባዕድ ገባባችሁ እንዴ! ብሶተኛ፡— አንድዬ፣ እሱማ መግባታቸው የት ይቀራል? እንደ ድሮ ታንክና መድፍ ደርድረው በድንበር ሳይሆን፣ ሰተት ብለው በአውሮፕላን ጣቢያ ነው የሚገቡት! ግን አንድዬ፣ የእነሱ እንዳለ ሆኖ አሁን የቸገረን የራሳችን ጉዳይ ነው ባዕድም እኮ እኛ በቆፈረነው ቀዳዳ እየገባ ነው የሚጫወትብን፡፡ አንድዬ፡— ታዲያ ራሳችሁን አስተካክሉ እንጂ፣ ለትንሹም ለትልቁም እኔ መጠራት አለብኝ እንዴ! እንደ እናንተ በአቤቱታ የሚጨቀጭቁኝ ሳይሆኑ፣ “እኛ ተባብረን በመስራታችን እዚህ ደረጃ ደርሰናል፣ አንተ ደግሞ ትንሽ አግዘን” የሚሉ ሰዎችን ፈቃድ ልሙላ ወይስ ዓመት ወደፊት እየቆጠራችሁ ነገረ ሥራችሁ ሁሉ ወደ ኋላ የሚንሸራተተውን የእናንተን የማያልቅ አቤቱታ ልስማ! ብሶተኛ፡— ምናለ እንድንደማመጥ ብታደርገን አንድዬ! አንድዬ፡— እንግዲህ ሦስተኛና አራተኛ ጆሮ አልፈጥርላችሁ! ሁለተኛና ሦስተኛ ልብ አልጨምርላችሁ! ሌላውም የሰው ልጅ አፈጣጠሩ እንደ እናንተ ነው፡፡ ብሶተኛ፡— አቃተና! አቃተን፡፡

አንድዬ፡— እኔም የእናንተ ነገር እያቃተኝ ነው አልኩህ እኮ! ለሙሴ አሥር ህግ ብሰጠው፣ እናንተ ሀጢአቱን አንድ ሺህ አሥር አደረጋችሁልኝ፡፡ እና ምን አድርግ ነው የምትለኝ! ብሶተኛ፡— ቸገረና አንድዬ! ቸገረን… አንድዬ፡— ምን ይቸገራችኋል? የእናንተም አእምሮ ያው እንደ ሌላው ነው፡፡ ወይስ አዳልተህ ለእኛ የተዛባ አእምሮ ሰጠኸን እያለከኝ ነው? ብሶተኛ፡— ኧረ በጭራሽ! አንድዬ፡— እኮ የሰጠኋችሁን አእምሮ ለበጐ ተጠቀሙበታ፡፡ ሌላኛውን ሰው እንዴት እንደምታጠፉ ነገር ስትጎነጉኑበት ከምታድሩ ችግርን እንዴት እንደምታጠፉበት ዘዴ አትፈጥሩበትም? ብሶተኛ፡— ለዚህስ ቢሆን እረፍት ቢኖረን አይደል! ብቻ፣ ሁሉም ነገር አልሆን አለን… አንድዬ፡— እኮ፣ ይህንኑ አይደል የምልህ፡፡ አልሆን ያላችሁ አምሯችሁን እኔ ላልፈጠርኩት ምክንያት እየተጠቀማችሁበት ነው አልኩህ፡፡ ይኸው ባል አልረጋ እንዳላት ዕድለ ቢስ ሴት አንዴ አንዱን አገር መወዳጀት፣ ደግሞ እሱን ትቶ ሌላውን ጠጋ ማለት የለመደባችሁ እኮ አምሯችሁን ለበጎ ተግባር መጠቀም ስላቃታችሁ ነው፡፡

ብሶተኛ፡— ታዲያ አንድዬ አንተስ በየዘመኑ ለምን ክፉ ክፉ ሰዎች ትፈጥርብናለህ? አንድዬ፡— ጭራሸ እኔኑ ትከሰኝ! ይኸው ነበር የቀራችሁ… ብሶተኛ፡— አንድዬ፣ መክሰሴ ሳይሆን ለሌላው አገር አልበርት አንስታይን፣ አይዛክ ኒውተን፣ ሼክስፒር እያልክ ምርጥ ምርጡን አእምሮ ስትፈጥር እኛ እነ… አንድዬ፡— ተው! እኔ ዘንድ የሌላ ሰው ስም አትጥራ… ብሶተኛ፡— እንዴ አንድዬ፣ አንተም ትፈራለህ እንዴ! አንድዬ፡— እኔንም የእናንተ የመጠላላት አዙሪት ውስጥ እንዳትከተኝ ብዬ ነዋ… ብሶተኛ፡— ቢሆንም ከበፊት ጀምሮ የአንዳንዶቹን ስማቸውን ልንገርህና… አንድዬ፡— አትንገረኝ አልኩህ እኮ! እንደውም እነሱ ከምትላቸው ሰዎች አንዱ በቀደም መጥቶ ከአንተ እንድገላግለው ሲለምነኝ ነበር፡፡ ብሶተኛ፡— እኔን አንድዬ፣ እኔን! አንድዬ፡— አዎ አንተን… ብሶተኛ፡— ደግሞ ምን አደረገ አለ? አንድዬ፡— አጭበርባሪ ነው፤ አፈ ጮሌ ነው፤ በአደባባይ ንጹህ ሰው እየመሰለ ውስጥ ውስጡን ሰዉን አባልቶ ጨረሰው ሲልህ ነበር ብሶተኛ፡— አንድዬ ውሸታቸውን ነው፡ ይኸው የዛሬዋ ቀን… አንድዬ፡— እንዳትምል… ብሶተኛ፡— እየው አንድዬ፣ እንደዚህ እንጨት… አንድዬ፡— አትማል አለኩህ እኮ፡፡ እንኳን አንተ ቀርቶ በእኔ ስም ቤቴ ገብተው የተንሰራፉት በእኔ ስም የሚምሉትን ሁሉ ማመን ትቻለሁ፡፡ ብሶተኛ፡— ብቻ ጌታዬ፣ እኔ ሰው አይወጣልኝም፡፡

በየሄደኩበት ምቀኛ ይከተለኛል፡፡ አንድዬ፡— ሁላችሁም እንዲሁ ነው የምትሉት፡፡ እናንተ ንጹህ፣ እናንተ አዋቂ፣ እናንተ አሳቢ፣ የሁሉም ነገር አልፋና ኦሜጋ እናንተ… ሌላው ደግሞ ምንም የማያውቅ፣ ምቀኛ፣ እናንተን ለመጣል የሚተጋ… ብቻ ምናችሁንም መጨበጥ አልቻልኩም፡ ብሶተኛ፡— እና ምን ይሻላል ትላለህ፣ አንድዬ! አንድዬ፡— የሚሻለውማ… አሁን ጊዜ የለኝም፡፡ እዚች ቦትስዋና የሚሏት ትንሽ አገር ስለሚፈልጉኝ ምን እንዳግዛቸው እንደፈለጉ ልስማቸው፡፡ ትርፍ ጊዜ ሲኖረኝ ግን አሁን ያልነገርከኝ ብሶቶችህንና እስከዛ ድረስ የምታጠራቅማቸውን ሌሎች ብሶቶች አንድ ላይ አድርገህ ትነግረኛለህ፡፡ ለ‘በላይ አካል ያቀረበው አቤቱታ ለጊዜው ፍሬ ያላስገኘለት ብሶተኛ ባንኮኒ ተደገፈ፤ አረቄውን ያዘ፤ ጥርሱን ነከሰ… “እሷንማ… የተወለደችበትን ቀን እንድትረግም ባላደርጋት!” ብሎ ዛተና አረቄውን በነገር የሞላው ሆዱ ውስጥ ቸለሰው፡፡

Read 2934 times