Saturday, 23 March 2013 13:44

ኢትዮጵያዊ መልኮች በአሜሪካ

Written by  ጽዮን ግርማ tsiongir@gmail.com
Rate this item
(6 votes)

መልክአ ኢትዮጵያ - ፲

በሬኖ የሚገኘውን የኔቫዳ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኞች ትምህርት ክፍልን ለመጎብኘት በሄድኹበት በአንዱ ቀን ነው፡፡ የዩኒቨርስቲው ግቢ ስፋት ፈረስ ያስጋልባል ከምንለው በላይ መጨረሻውን በዐይን እይታ ለመድረስ እንኳን አዳጋች ነው፡፡ ከመኪና ማቆሚያው በኋላ እያንዳንዱ ትምህርት ክፍል ወደሚገኝበት ሕንጻ ለማምራት የግቢውን አውቶብስ ቆሞ መጠበቅና አውቶቡሱን መጠቀም ግድ ነው፡፡ ከግቢው ዋና ዋና በሮች አስቀድሞ ከሚገኙት ሰፊ የመኪና ማቆሚያዎች በኩል ብቅ ብቅ እያሉ ወደ ውስጥ የሚዘልቁት ተማሪዎች÷ በካምፓሱ የአውቶብስ መጠበቂያ ፌርማታ ላይ ተሰብስበዋል፡፡ በኻያ ደቂቃ ልዩነት የሚመጣውን አውቶብስ ለመጠበቅ እኔም አብሬ ቆሜያለኹ፡፡ ምቹ መቀመጫ ባለው ባለመስተዋቱ ፌርማታ ውስጥ ቦታ አግኝተው የተቀመጡ ተማሪዎች አንገታቸውን ወደ ስልኮቻቸው ዘልሰው ጆሯቸውን በማዳመጫ ደፍነውታል፡፡ አንዱ ሌላውን ለአፍታ ዘወር ብሎ አያይም፡፡ አንዳንዶቹ በመጽሐፎቻቸው ላይ ተተክለዋል፡፡

ወዲያ ወዲህ የሚንቀዠቀዠው የእኔ ዐይን ብቻ ሳይኾን አይቀርም፡፡ በጀርባው ያዘለው ትልቅ ቦርሳ በፈጠረው ክብደት በጥቂቱ ጎንበስ ያለ፣ ሰፊ ካኪቁምጣ የታጠቀ፣በተጫማው ስኒከር ጫማ ነጠር ነጠርእያለ ቀልቡን ጆሮው ላይ ለሰካው ማደመጫ የሰጠ፣ ዕድሜው በኻያዎቹ የሚገመት አንድ መልከ መልካም ወጣት ወደ ፌርማታው አቅጣጫ ሲመጣ በአትኩሮት ተመለከትኹ፡፡ መቼም በዚህች ከተማ የአገር ልጅን እንደልብ ማግኘት እንደሚከብድ አውግቻችኋለኹ፡፡ ወጣቱ እየቀረበኝ ሲመጣ የሐበሻ መልክ እንዳለው በመጠርጠር ትክ ብዬ አየኹት፡፡ስልኩን እየነካካ አጠገቤ መጥቶ ቆመ፡፡አሁን አረጋገጥኹ፡፡

ራሴን ለጥያቄ ሳሰናዳ ወጣቱ ቀና ብሎ ገርመም አደረገኝ፡፡ ለአፍታም ሳይቆይ በደስታና በታፈነ ድምፅ ጣቶቹን አቆላልፎ ‹‹ሐበሻ ነሽ?›› ሲል በተኮላተፈ አማርኛጠየቀኝ፡፡ ‹‹አዎ፣ነኝ፤አንተስ ኢትዮጵያዊ ነህ?›› አልኹት እጄን ለሰላምታ እየዘረጋኹለት፡፡ ‹‹የተወለድኩት እዛ ነው…ያደኩት እዚህ ነው…አሜሪካዊ ነኝ…አማርኛ ግን በደንብ እችላለኹ፤ወንድሜ ስለሚችል እሱ ነው ያስተማረኝ››አለኝ፡፡ሲናገር ይፈጥናል፤ ንግግሩ ጥቂት አማርኛ በብዙው እንግሊዝኛ ነው፡፡ ጎበዝነህ አልኁት፤ በርግጥም ጎበዝ ወጣት ነው፡፡ በዚህች ከተማ አድጎ በአማርኛ መኮላተፍ መቻሉን አደነቅኹለት፡፡ፍልቅልቅነት ተፈጥሮው ሳይኾን አይቀርም ስል ጠረጠርኹ ፡፡ ፈጠን ያለ የመግባባት ችሎታ አለው፡፡ አንዳች የደስታ ስሜት ሰቅዞ እንደያዘው ከገጽታው ያስታውቃል፡፡ ምናልባት በሚማርበት ዩኒቨርስቲ ፌርማታ ላይ ያልጠበቀውን ነገር ማግኘቱ ሊኾን ይችላል -የትውልድ አገሩን ልጅ፡፡

አማርኛ መቻሉን ደጋግሞ ቢነግረኝም፡፡ አጋጣሚው ይበልጥ ‹እንዳንተባተበው› ገባኝ፡፡ በስፍራው የመከሠቴን ምስጢር ለማወቅ በጥያቄ አዋከበኝ፤ ስለመጣኹበት ጉዳይ እየነገርኹት አብረውኝ ካሉት ሰዎች ጋራ አስተዋወቅኹት፡፡ ለሌሎቹ ብዙም ቦታ ሳይሰጥ እኔኑ ብቻ በጥያቄ ያጣድፈኝ ጀመር፡፡ በመሀል መልከኛው የግቢው አውቶብስ ደርሶ ተሳፈርን፡፡ ከፊል ተሳፋሪው በስልኩና በሚያነበው ነገር ላይ ተኩሯል፡፡ ወጣቱ ግን በተኮላተፈ አማርኛው እየተቻኮለ ማውራቱን ቀጥሏል፡፡ መውረጃው ደረሰበት፤ ግን ደግሞ መልሶ ሊያገኘኝ ፈልጓል፡፡ ስልክ ቁጥሬን ወስዶ እኔ ወደምጎበኘው ትምህርት ክፍል መጥቶ እንደሚያገኘኝ ነግሮኝ ተሰናብቶኝ ወረደ፡፡የደስታው ምንጭ ሐበሻ በአገሩ ብርቅ መኾኑ ብቻ አልመሰለኝም ፡፡ በርካታ ጥያቄዎች ቢኖሩኝም እንደማገኘው ተስፋ አድርጌ እጄን አወዛውዤ ተሰናበትኹት፡፡

************* ከምሳ በኋላ እኔና ወጣቱ ልጅ ኄኖክ በዩኒቨርስቲው ግቢ ውስጥ በሚገኘው መናፈሻ ውስጥ በተሠራ መቀመጫ ላይ ቁጭ ብለን ወግ ይዘናል፡፡ የግቢው ውበት ማራኪ ነው፡፡ተማሪዎቹ በመናፈሻው ውስጥ ተቀምጠው በላፕቶፕ ኮምፒዩተሮቻቸው፣አይፖድና ስልኮቻቸውን እየተጠቀሙ የራሳቸውን ሥራ ይሠራሉ፡፡ ቦርሳቸውን በጀርባቸው አዝለው ከወዲያ ወዲህ ይላሉ፡፡ምናለ የዚህ ግቢ ተማሪ በኾንኁ ብዬ መመኘቴ አልቀረም፡፡ ኄኖክ ስለተወለደባት ኢትዮጵያ የምትባል አገር እንጂ ስለወላጆቹ አንድም የሚያውቀው ነገር የለም፡፡ ስለ እርሷም ቢኾን ከድረ ገጽ ላይ በየቀኑ ከሚጎለጉለው መረጃ በቀር ከአገሩ ሲወጣ በነበረው የሦስት ዓመት ዕድሜ በአእምሮው ቀርፆ ያስቀረው አንዳችም ትዝታ የለውም፡፡ ሁሌም የሚናፍቀው የማያውቃትን ኢትዮጵያ ነው፡፡

‹‹የማላውቃት አገር ለምን እንደምትናፍቀኝ አላውቅም፤ ግን በቃ ሁሌም አስባታለኹ፤ትናፍቀኛለች፤ ምን ትመስል ይኾን? ሕዝቡ እንዴት ይኾን የሚኖረው? በቃ የወለዱኝ ሰዎች ምን እንደሚመስሉ ማየት እናፍቃለኹ፤ በአማርኛ በደንብ ለማውራት እጓጓለኹ…፡፡›› ኄኖክ ከተወለደባት አገር በጣም ርቆ ሬኖ የተገኘው በማደጎ ተወስዶ ነው፡፡እናት አባቴ የሚላቸው አሳዳጊዎቹን ነው፤ እርሱን ከወሰዱት በኋላ ሌላ ወንድምና እኅት ጨምረውለታል፡፡ ወንድምና እኅቱ ከኢትዮጵያ በማደጎ የመጡ ይኹኑ እንጂ ከተለያየ ቦታ የተወለዱ ናቸው፡፡ እነሱም እንደሱ በማሳደጊያ በኩል የመጡ፣ የወለዷቸው ሰዎች የማይታወቁ ናቸው፡፡

ዩኒቨርስቲው ከሚገኝበት ከተማ ወጣ ብለው የሚኖሩት አሳዳጊ አባትና እናቱ ሦስቱንም በክብካቤ ነው ያሳደጓቸው፤ ወንድምና እኅቱም ጎበዝ ተማሪዎች መኾናቸውን ነግሮኛል፡፡ በሚቀጥለው ዓመት ወንድሙ ዩኒቨርስቲውን ይቀላቀላል ብሎ ተስፋ ያደርጋል፡፡ ኄኖክ በአስተዳደግ በኩል ምንም የጎደለበት ነገር እንደሌለ አጫወተኝ፡፡ቤተሰቡ በፍቅር የተሞላ ነው፡፡ ለኄኖክ ግን አካላዊ ምቾት ብቻ በውስጡ የሚላወሰውን ጥያቄ ሊያሥታግስለት አልቻለም፡፡ ሁሌም በአንድ ጥያቄ ራሱን ያስጨንቃል÷‹‹ወላጅ እናት አባቴ ምን ይመስላሉ? ዘመዶቻቸውስ? ኢትዮጵያስ?›› ኢትዮጵያ ለእርሱ ሩቅ ኾናበታለች፡፡አንድ ቀን ሔጄ አያታለኹ ብሎም ስለሚያቅድ ከተወለደባት አገር ሕዝብ ጋራ እንዲያግባባው አሜሪካዊ ዜግነት ይዞ አማርኛን ለመለማመድ ይታትራል፡፡

ከርሱ በኋላ በሰባት ዓመቱ አማርኛ እየተናገረ የመጣ ‹ታናሽ ወንድሙ› አሁን የሚኮለተፍባትን አማርኛ ለማቃናት እገዛ አድርጎለታል፡፡ ‹‹ወንድሜ [የማደጎ] ሲመጣ አማርኛ ብቻ ነበር የሚችለው፤ በኋላ እየረሳው እንዳይመጣ ብዬ ቤትውስጥ በአማርኛ አወራቸዋለኹ፤ እኅቴ ግን በጣም ያስቸግራታል፤›› አለኝ፡፡በተለይ ታናሽ ወንድሙ ወደ ዩኒቨርስቲ ሲገባ እኅቱ አማርኛውን ሙሉ ለሙሉ ልትረሳው ትችላለች የሚል ስጋት አለው፡፡ ከአለባበሱ ጀምሮ ነገረ ሥራው ኹሉ አሜሪካዊ የኾነው ኄኖክ በአገርኛ ቋንቋ ለመግባባት የሚያደርገውን ትንቅንቅ ማየት የምር ስሜትን ይነካል፡፡ ምናልባት ይህን ወጣት ያገኘኹት እንደ ዋሽንግተን ዲሲ ባለከተማ ቢኾን እንዲህ ያለው ስሜት ላይሰማኝ ይችል ነበር፡፡

ኄኖክ ትምህርቱን ከሁለት ዓመት በኋላ ሲያጠናቅቅ ኢትዮጵያን የማየት ፍላጎት አለው፡፡ ‹‹ግን የት? ማን ጋራ እንደምሄድ አላውቅም፤ ምናልባት ወደ ሕፃናት ማሳደጊያ. . . እዛስ ማን ያውቀኛል? ግን በኾነ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ መሄድ ኢትዮጵያን ማየት እፈልጋለኹ፤››አለኝ፡፡ የኄኖክ ፍላጎት ኢትዮጵያን ማየት ብቻ አይደለም፡፡ሕፃናት በማደጎ ለሌሎች ሰዎች ‹የሚሸጡበትን› ምክንያት ማጥናት ይፈልጋል፡፡ የድኻ አገር ልጆችን መርዳት የፈለጉ ባለጸጎች ሕፃናቱን እትብታቸው ከተቀበረበት ነጥለው ከመውሰድ ይልቅ በተወለዱበት አገራቸው መርዳት የተሻለ አማራጭ መኾኑን በማመን ድርጅት ማቋቋም ይፈልጋል፡፡ ባለጸጎቹ ሕፃናቱን በማደጎነት ለመውሰድ የሚከፍሉት ክፍያ ለኄኖክ ከባሪያ ንግድ ለይቶ አያየውም፡፡ ኄኖክ ወደ ዩኒቨርስቲ ሲገባ ለመማር የመረጠው ትምህርት ይህን ዓላማውን ለማሳካት የሚረዳው ነው፡፡

‹‹የምማረው ከኮሙኒኬሽንና ከንግግር ጋራ የተያያዘ ትምህርት ነው፤ ሰዎችን በንግግር ማግባባትና ማሳመን፡፡ እንዳልኩሽ ትምህርቴን ስጨርስ ኢትዮጵያ ሄጄ ሕፃናት በአገራቸው በመረጡት አካባቢ የሚረዱበትን ተቋም ለማቋቋም እፈልጋለኹ›› አለኝ፡፡ ለዚህ ዓላማው ባለጸጎችን ለማሳመን ይረዳው ዘንድ ዕውቀት እና ክህሎቱን የሚያዳብርበትን ትምሕርት እየተማረ ነው፡፡ ኄኖክ ሌሎች ሕፃናት ለርሱ የሚሰማው ስሜት እንዲሰማቸው አይፈልግም፡፡ ሕፃናት በጉዲፈቻ አማካይነት ከአገራቸው የሚወጡት በሽያጭ መልክ መኾኑ ዘወትር ያሳስበዋል፡፡ ይህን አስመልክቶ የሚጻፉትን ያነባል፡፡ በአንድ ወቅት ‹‹ዎል ስትሪት ጆርናል›› በተባለ ድረ ገጽ ላይ በደቡብ ክልል የሚኖሩ ሕፃናትን ቤተሰቦቻቻው በሕይወት እያሉ በማደጎ እንደሚሰጧቸውና ÷ ‹‹ኢትዮጵያ ሕፃናትን በጉዲፈቻ በመስጠት ገበያውን ከቻይና ጋር ትመራለች፤›› በሚል የተጻፈውን አንብቦ መቆጨቱን ያስታውሳል፡፡

በዚያ ጽሑፍ የአሜሪካ ባለጸጎች ልጅ በጉዲፈቻ ለማሳደግ በፈለጉ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ሄደው ገንዘብ ከፍለው እንደሚያመጡ፣ የሚከፍሉት የገንዘብ መጠንም ምን ያህል እንደኾነ በዝርዝር ተጽፎ ማንበቡን ፡፡ በተለይ ቤተሰብ ያላቸው ወላጆች ከልጆቻቸው አንዱን በጉዲፈቻ ሲሰጡ ኹኔታው ከሕፃናት ንግድ ጋራእንደሚያያዝበት በግልጽ ነገረኝ፡፡ ልጆች በወላጆቻቸው ሥር ማደግ እንደሚገባቸው፣ አሳዳጊ አልባ ከኾኑ ደግሞ የወጡበት ማኅበረሰብ ባለበት አቅራቢያ በአሳዳጊ ተቋም ክብካቤ እንዲያድጉ መደረግ እንዳለበት፣ ከአገር የሚወጡም ከኾነ ቋንቋቸውንና ጠቅላላ ማንነታቸውን በሚገባ ከለዩ በኋላ ራሳቸውን ለማሻሻል የሚያስችላቸው የከፍተኛ ትምህርት ዕድል መኾንእንዳለበት የነገረኝ በብስጭት ነው፡፡

የኄኖክ ጥያቄዎች ማብቂያ ባይኖራቸውም እኔም ማዳመጡን ባልጠላም የተገናኘነው ሬኖ የምትባለዋን አገር ለቅቄ ለመውጣት የአንድ ቀን ዕድሜ ብቻ ሲቀረኝ በመኾኑ ከዚህ በላይ ሐሳብ ለመለዋወጥ አልቻልኹም፡፡ መሄድነበረብኝ፡፡አድራሻ ተለዋውጠን ቅር እያለው ሸኘኝ፡፡ መለስ አለና ‹‹ይቅርታ አንድ ጥያቄ. . . ኢትዮጵያ ምን ትመስላለች?›› ብሎ ጠየቀኝ፡፡ ምን ትመስላለች ልበለው÷ የኄኖክ ጥያቄ ‹‹አገራችን እንዴት ነው፤ አድጋለች?›› ከሚለው የብዙኀኑ ጥያቄ ተለየብኝ፤ ‹‹ስትመጣ በደንብ እናስጎበኝኻለን” ብዬ ተሰናበትኹት፡፡ ወደ ማደሪያዬ እየሄድኹ አዲስ አበባን አሰብኋት፡፡ ለአሜሪካ ጉዞ ቪዛ ለመውሰድ ሽሮ ሜዳ ወደሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በሄድኩበት አቅጣጫ በሐሳብ ነጎድኹ፡፡

በጥቁርና ነጭ አሜሪካውያን አሳዳጊዎች እቅፍ ውስጥ ኾነውወደማያውቁት አገር ለመሄድ ቪዛ ሲጠባበቁ ያየኋቸውን ሕፃናት በዐይነ ኅሊናዬ ሣልኋቸው፡፡የድህነት ክፋቱ በዛብኝ፡፡ የኢትዮጵያ ደግሞ ባሰብኝ፡፡ ከኢትዮጵያ ወደ አውሮፓ በጉዲፈቻ በተወሰዱ በሁለተኛ ቀናቸው የተደፈሩትን ሁለት ሕጻናት፣ለኔዘርላንዳውያን በጉዲፈቻ ከተሰጠች በኋላ ስለደረሰባት ድብደባ የተናገረችው ሕጻን፣ አሜሪካ ውስጥ በምግብ ዕጦት በ13 ዓመቷ ሕይወቷ ያለፈው በጉዲፈቻ የተሸጠችው ታዳጊ …..ሁሉም በየተራ ትዝ አሉኝ፡፡ ሕፃናቱን ከኢትዮጵያበጉዲፈቻ ከሚወስዱ የውጭ ዜጎች ውስጥ፤ከወሰዷቸውበኋላግብረሰዶም በመፈጸምለወሲባዊ ጥቃት እንደሚያጋልጧቸው የሰማኋቸውን አስከፊ ወሬዎች ተራ በተራ እያስታወስኹ ከኄኖክ ጋራ አነፃፀርኳቸው፡፡ ኄኖክ ቢያንስ ጥሩ ቤተሰብ ገጥሞት በሚገባ ተምሯል፡፡የሌሎቹ ዕጣ ፈንታስ ምን ይኾን? ጭንቀቱና፣ መቃተቱ ተጋባብኝ፡፡

*************** በአሜሪካና አውሮፓ ላሉ አሳዳጊዎች በማደጎ የሚሰጡ ሕፃናት ቁጥር ዕለት በዕለት እየጨመረ ነው፡፡ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ ሆሳዕና አካባቢ በዘመቻ የተሠራ እስኪመስል ድረስ ወላጅ ያላቸውን ሕፃናት በመመልመልና ቤተሰቦቻቸውን በማያውቁት ቋንቋ በተዘጋጀ ሰነድ ልጆቻቸውን መልሶ መጠየቅ የሚከለክል አንቀጽ አስፍሮ በማስፈረም የተከናወነ የተጭበረበረ ድርጊት ነበር፤ሕፃናትበጉዲፈቻ ለውጭ አገር ሰዎች ሲሰጡሂደቱን የሚያመቻቹት ኤጀንሲዎች ከፍ ያለ የገንዘብ ጥቅም ያገኛሉ፡፡ ከሁለት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ በጉዲፈቻ ስም ሲከናወን የነበረው የሕፃናት ሽያጭ ንግድ መኾኑ መጋለጥ ሲጀምር አገልግሎቱን ከሚሰጡት በርካታ ኤጀንሲዎች መካከል ከዐሥር በላይ የሚኾኑት እንዲዘጉ ተወስኖ ነበር፡፡

አገልግሎቱና የማጣራት ሥራው በሴቶችና ሕፃናት ሚኒስቴር በኩል እንዲሰጥ ቢወሰንም፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሕፃናቱ ከሄዱ በኋላ ያሉበትን የኑሮ ኹኔታ የሚከታተልበት አሠራር እስከሌለው ድረስ የሚለወጥ ነገር አይኖርም፡፡ ሕፃናት በጉዲፈቻ ለውጭ አገር ዜጋ እንዲሰጡ የሚያስወስኑ ምክንያቶች የመጨረሻ አማራጮች ሊኾኑ ይገባል፡፡ሕፃናቱን ከትውልድ ቀያቸው አፈናቅሎ መሸጥ አንድም ለከፋ የመብት ጥሰት ያጋልጣቸዋል ወይም ከማንነት ጥያቄ ጋራ አፋጥጦ መድረስ ከሚገባቸው ቦታ ሳይደርሱ ጎትቶ ያስቀራቸዋል፤ አልያም እንደ ኄኖክ ሁሌም በስም ብቻ የሚያውቋትን በመልክ ያለዩዋትን አገር ሲናፍቁ ውለው ያድራሉ፡፡ (ይቀጥላል)

Read 4352 times Last modified on Monday, 25 March 2013 10:48