Saturday, 23 March 2013 13:58

አክሲዮን - የብልፅግናና የኪሳራ፣ የትብብርና የውዝግብ መናኸሪያ

Written by 
Rate this item
(5 votes)

የአክሲዮን ማህበር፣ ከስልጡን የብልፅግና መንገዶች መካከል አንዱ ቢሆንም በርካታ ችግሮችም ይታዩበታል፡፡ ለአርያነት የሚበቁ የአክሲዮን (ኩባንያዎች) የመኖራቸውን ያህል በውዝግብ የታመሱ የአክሲዮን ማህበራት፣ በምስረታ ላይ አመታትን እያስቆጠሩ ባለ አክሲዮኖችን ተስፋ የሚያስቆርጡ ማህበራት፣ ለብክነትና ለስርቆት የተጋለጡ፣ ለትንሽ ጊዜ ግርግር ፈጥረው እልም የሚሉ የአክሲዮን ሽያጮችም አሉ፡፡ አሰራሩ ለአገራችን አዲስ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፣ ብዙ ሰው በቂ መረጃ የሌለው መሆኑ ለአገራችን አዲስ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፣ ብዙ ሰው በቂ መረጃ የሌለው መሆኑ ደግሞ ችግሮቹ አወሳስቧቸዋል፡፡

ከሁለት አመት በፊት በወጣው ህግ መሰረት፣ በታቀደለት ጊዜ ገንዘብ አሰባስበው ያላጠናቀቁ የአክሲዮን አደራጆች፣ ለባለ አክሲዮን ወለድ ለመክፈል እንደሚገደዱ ያውቃሉ? የአክሲዮን ማህበራት ህግ በጣም ጥብቅ ከመሆኑ የተነሳ፣ የአክሲዮን አደራጆች ተጠያቂ በሚሆኑበት ጊዜ የማስታወቂያ ድርጅቶችም ተጠያቂ እንደሚሆኑ ያውቃሉ? በእነዚህና በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከንግድ ሚኒስቴር የንግድ ምዝገባና ፈቃድ ጊዜያዊ ዳይሬክተር ከአቶ ኑረዲን መሀመድ ጋር ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ያካሄደችውን ቃለ ምልልስ አቅርበናል፡፡ አክሲዮን ማህበር ላይ ብዙ መሟላት ያለባቸው የህግ ግዴታዎች እንዴት ይነገራል? እነዚህን ነጥቦች ቢጠቃቅሱልን፡፡

አክሲዮን ማህበር ከሌሎች ማህበራት የሚለየው፤ ተስማምተው ከፈረሙት አባላት ውስጥ፤ የተከፈለው ካፒታል 1/4ኛ ሲደርስ አክሲዮን ማህበሩ ሕጋዊ ሠውነት ያገኛል፡፡ ይሄ አንደኛው ነው፡፡ ሌላው የአክሲዮን ማህበር አደራጆች መስራቾች አክሲዮኑ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ተሸጦ ማለቁንና ገንዘቡ ተሰብስቦ መግባቱን ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ፡፡ አክሲዮን ማህበሮች በንግድ ህጉ ላይ ከ317 እስከ 322 የተጠቀሱ የህጉ አንቀፆችን ማሟላት አለባቸው፡፡ ዝቅተኛው የአባላት ቁጥር አምስት ነው፡፡ ዝቅተኛው የካፒታል መጠን ደግሞ 50ሺህ ብር፡፡ አክሲዮን ማህበር እንደ ማንኛውም የንግድ ማህበር መመስረቻና መተዳደሪያ ደንብ ማዘጋጀት አለበት፡፡ በአባላት መፈረም አለበት፡፡ በተጨማሪ ሌሎች ነገሮችንም ማሟላት አለበት፡፡

ለምሣሌ የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር ማግኘት ይኖርባቸዋል፡፡ የንግድ አድራሻቸው በትክክል መታወቅና መለየት አለበት፣ የተከፈለው ወይም የተሰበሰበው የገንዘብ መጠንም ከተስማሙበት እቅድ ከአንድ አራተኛ መብለጥ አለበት ይላል ህጉ፡፡ በሀገራችን የአክሲዮን ምስረታና ሽያጭ መቼ ተጀመረ አሁን የሚስተዋሉ ችግሮችስ ከምን የመነጩ ናቸው? እርግጥ በሀይለ ስላሴ ዘመን የተጀመረ ነው፡፡ የንጉሱ ቤተሠቦች ከሌሎች ሠዎች ጋር ገንዘብ አሠባስበው አክሲዮኖችን መስርተው ነበር፡፡ ለምሣሌ ኢትዮ-መተሀራ አክሲዮን ማህበር ተመስርቶ ነበር፡፡ የኢንሹራንስና የባንክ አክሲዮን ማህበሮችም ነበሩ፡፡

የደርግ ሥርዓት መጥቶ አጠፋቸውና ሁሉም ነገር በመንግስት ቁጥጥር ስር ሆነ፡፡ አክሲዮን ማህበር እንደ አዲስ መፍላት የጀመረው ከ1984 ዓ.ም ወዲህ ነው፡፡ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ወደ አክሲዮን ማህበራት በመቀየር ባለሃብቶች እንዲሳተፉ ተደረገ፡፡ የተወሰነ ብር ያላቸው ሠዎች አቅማቸውን እያሰባሰቡ በባንክና በኢንሹራንስ ዘርፎች የአክሲዮን ማህበር በማቋቋም አሁን እያደጉ የምናያቸውን የፋይናንስ ተቋማት እውን አድርገዋል፡፡ ከፋይናንስ ሴክተሩ ውጤታማነት ጋር የአክሲዮን ማህበራት በሌሎች ዘርፎችም መግባት ጀምረዋል - በቢራ፣ በሲሚንቶ፣ በጅምላ ንግድ፣ በአግሮ ኢንዱስትሪ ፕሮሠሲንግ ዘርፍ፣ በኢንተግሬትድ አግሮ ኢንዱስትሪ ፕሮሠሲንግ ዘርፍ ወዘተ፡፡ የአክሲዮን ማህበር፣ ሰዎች አቅማቸውን አሰባስበው በጋራ እንዲሰሩ የሚያደርግ በመሆኑ ሊደገፍ ይገባዋል፡፡ በሌላ በኩልም የባለ አክሲዮኖችን ገንዘብ ለአደጋ የሚያጋልጡ ቀዳዳዎች እንዳይፈጠሩ መጠንቀቅ ስለሚያስፈልግ በ2002 ዓ.ም የህግ ማሻሻያ ተደርጓል በአዋጅ ቁጥር 686/2002፡፡

እስኪ ስለ አዋጁ ትንሽ ያብራሩልኝ… አዋጁ፣ በአክሲዮን ማህበር አደራጆች ላይ ተጠያቂነትን የሚፈጥር፣ ለአክሲዮን ባለድርሻዎች ደግሞ ከለላ የሚሰጥ ነው፡፡ የአክሲዮን ማህበር ከመቋቋሙ በፊት የፅሁፍ ድጋፍ ከመንግስት ማግኘት አለበት፡፡ ለዚህም መሟላት ያለባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ ህዝቡ አክሲዮን ሲገዛ፣ ገንዘቡ እንዳይባክን በዝግ አካውንት መግባቱን ማረጋገጥ፣ የአክሲዮን ማህበሩ አደራጆች እነማን እንደሆኑ ማወቅ፣ በተሠጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ስለተጠራቀመው ገንዘብና ስለ አጠቃላይ እንቅስቃሴው ሪፖርት እንዲያደርጉ ማድረግ … ለአብነስ መጥቀስ ይቻላል፡፡ በአዋጁ መሰረት መመሪያዎች ከመውጣታቸዉ በፊትም ይህንን ድጋፍ መስጠት ጀምረናል፡፡ መንግስት ጉዳዩን በትኩረት ነው የሚመለከተው፡፡

ለምን ቢባል፣ ጥቂት ገንዘብ ያላቸው ሠዎች በጋራ ትልቅ ሥራ በመስራት ውጤታማ ይሆናሉ ብሎ ያምናልና፡፡ የአክሲዮን ባለ ድርሻ የሆኑ በርካታ ሰዎች የሚያነሱት ቅሬታ አለ፡፡ አንዳንድ አክሲዮን አደራጆች በቃላቸው መሰረት ስራውን አያከናውኑም፡፡ ለምሳሌ በዚህ አመት አስፈላጊውን የአክሲዮን መጠን ሸጠን ወደ ስራ እንገባለን ይላሉ፡፡ ነገር ግን ጊዜ ይፈጅባቸዋል፡፡ የአክሲዮን ማህበሩን ሳይቋቋም ይዳከማል፡፡ የአክሲዮን ማህበራት ያቀዱትን ያህል ገንዘብ ስላልሠበሠቡ አይቋቋሙም የሚል ህግ የለም፤ ይፍረሱ የሚል ህግም የለም፡፡ አባላት ከፈለጉ በሠበሠቡት ብር ተቋቁመው፣ ስራ መጀመርና ጎን ለጎን ተጨማሪ ገንዘብ እየሠበሠቡ መሄድ ይችላሉ፡፡

ካልፈለጉ ግን አለማቋቋም ይችላሉ፡፡ የአክሲዮን ገንዘብ ከሠበሠበ በኋላ በተለያየ ምክንያት ሳይቋቋም ቢቀር፣ በዝግ አካውንት የተቀመጠው ገንዘብ ለባለቤቶች ያለ ብዙ ጣጣ ይመለስላቸዋል? በባለ አክሲዮኖች ላይ የሚደርስ የገንዘብም ሆነ የሞራል ጉዳትስ እንዴት ይካካሳል? ሁለት ነገሮችን ለይተን እናስቀምጥ! አንደኛው ነጥብ፣ አክሲዮን መግዛት በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ስለዚህ ሠዎች አክሲዮን ለመግዛት ሲወስኑ፣ የማመዛዘን ሃላፊነት አለባቸው፡፡ አክሲዮኑ አዋጭ ነው? ህገ-ደንብ አለው? ባይሳካስ ምን መፍትሄ አለው? የሚሉ ጥያቄዎችን ማገናዘብና መወሰን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለምሣሌ ቀደም ሲል የተቋቋሙ የባንክ አክሲዮኖች ወዲያውኑ ውጤታማ ሆነዋል፡፡ አሁን እየተቋቋሙ ያሉ አክሲዮኖች ግን የስራ ዘርፋቸው ከባንክ ይለያል፡፡

ጥረትንና ትጋትን የሚጠይቁ፣ ውጤታማ ለመሆን ረጅም ጊዜ የሚያስፈልጋቸው ናቸው፡፡ ሲሚንቶ የሚያመርት ኩባንያ በአንድ ወር ውስጥ የሚቋቋም አይደለም፡፡ ከሶስት ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ሊያስፈልገው ይችላል፡፡ ገንዘቡን መሰብሰብ ምን ያህል ትጋትና ልፋት እንደሚጠይቅ መገመት የግድ ነው፡፡ የተወሠነውን ገንዘብ ከህዝብ ከሠበሠበ፣ ሌላውን ከልማት ባንክ ብድር፣ ቀሪውን ደግሞ ከውጭ ኩባንያ ጋር በመጣመር አሳካለሁ ብሎ ከተቋቋመ፣ እንደ ስራ ዘርፉ ባህርይ ውጤታማ ለመሆን ረዥም ጊዜ ሊወስድ ይችላል፡፡ ሌላው ቀርቶ፣ ግንባታው ራሱ አምስትና ስድስት አመት ሊፈጅ ይችላል፡፡ አንድ ባለአክሲዮን ከዚህ ዘርፍ በአጭር ጊዜ ውጤት ከጠበቀ ገና ከጅምሩ ተሳስቷል፡፡ ከረዥም ጊዜ በኋላ ከፍተኛ ትርፍ እንደሚያገኝ አረጋግጦ ነው መግባት ያለበት፡፡ ፈጣን የሆነ ትርፍና ውጤት የሚፈልግ ሰው፣ ምናልባት እንደ ባንክ ወደ መሳሰሉ ዘርፎች ማተኮር አለበት፡፡ ስለዚህ አክሲዮን የሚገዙ ሰዎች በመጀመሪያ የስራውን ባህርይ፣ የአጭርና የረዥም ጊዜ አዋጭነትና ትርፍ ማገናዘብ የባለአክሲዮኖች ሃላፊነት ነው፡፡

ሁለተኛው ነጥብ፣ አክሲዮን የሚያደራጁ ሰዎች በንግድ ህጉ ውስጥ በግልፅ የተቀመጠ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ አክሲዮን ማህበሩ ሳይቋቋም ቢቀር፣ አደራጆቹ ለእያንዳንዱ ባለ አክሲዮን ድርሻውን የመመለስ ግዴት አለባቸው፡፡ ገንዘቡ በተሰበሰበ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ አክሲዮን ማህበሩ ካልተቋቋመ፣ አደራጆች ወለድ የመክፈል ግዴታ አለባቸው፡፡ ነገር ግን ህጉ ከአደራጆቹ ውጭ ለአክሲዮኑ አለመቋቋም ተጠያቂ የሚያደርጋቸው ሌሎች አካላት አሉ … አዎ፤ ለምሳሌ ማስታወቂያ ያወጡ ሚዲያዎች፣ ያሻሻጡ አካላት፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ድጋፍ ያደረጉ በሙሉ ተጠያቂ ናቸው፡፡ ህጉ የማስታወቂያ ድርጅቶችን ተጠያቂ ያደርጋል፡፡ ሌላው ቀርቶ ማስታወቂያ ያስተናገዱ ሚዲያዎችም ይጠየቃሉ፡፡ ለምን? ለምሳሌ አክሲዮን የሚያደራጁ ሰዎች መጥተው ማስታወቂያ ስራልኝ ይላሉ፡፡ የማስታወቂያ ድርጅቱ ይሰራላቸዋል፡፡ በቃ ይለያያሉ፡፡

ታዲያ በምን ሂሳብ ነው፣ የማስታወቂያ ድርጅት ተጠያቂ የሚሆነው? በጣም ጥሩ! አንድ አክሲዮን አደራጅ ማስታወቂያ ሊያስነግር ሲመጣ ከንግድ ሚኒስቴር ወይም ከመዝጋቢው አካል የተሰጠውን የፈቃድ ደብዳቤ ማየትና ማረጋገጥ፣ የሚዲያው ወይም የማስታወቂያ ድርጅቱ ድርሻ ነው፡፡ ይህን ሳያደርግ ዝም ብሎ የመጣለትን ሁሉ ተቀብሎ ማስታወቂያ ከሰራና ካሰራጨ ተጠያቂ ይሆናል፡፡ ይሄ ህጉ ነው፡፡ ደብዳቤውን ቢያይም ማስታወቂያው ተአማኒ መሆን አለመሆኑን ማረጋገጥ አለበት፡፡ ያለበለዚያ ማስታወቂያ ድርጅቱ ተጠያቂ ይሆናል፡፡ ህጉ ይህን ያህል በጣም የጠበቀ ነው፡፡ ነገር ግን በአደራጆች ዘንድ ይህንን ህጉን ያለመገንዘብ እጥረት አለ፡፡ ለምሳሌ የአንድ ሺ ብር አክሰዮን ለመግዛት ከ5 እስከ 9% የአገልግሎት ክፍያ ይጠይቃሉ፡፡ ታዲያ ይህ የአገልግሎት ክፍያ በምን ተግባር ላይ እንደዋለ በግልፅ የማስረዳት ሃላፊነት እንዳለባቸው አይገነዘቡትም፡፡ ኦዲት የማድረግ ግዴታዎች አሉ፡፡ በስፋት ከማይታወቁት የህጉ ነጥቦች መካከል አንዳንዶቹን ቢጠቅሱልኝ… ከአክሲዮን ማህበሩ አባላት አስር በመቶ የሚሆኑት ቅሬታ ካላቸው፣ ለመዝጋቢው አካል ቅሬታቸውን ያቀርቡና ንግድ ሚኒስቴር አሊያም ንግድ ቢሮ ኦዲተር ይሠየምላቸዋል፡፡

ከአባላት መካከል ሁለት ሶስተኛው፣ ጠቅላላ ጉባኤ ማስጠራት ይችላሉ፡፡ ነገር ግን በርካታ ባለአክሲዮኖች ህጉን ባለማወቅና የተቀመጡትን የቦርድ ዳይሬክተሮች እንደ ንጉስ በመቁጠር ችግራቸውን በሚዲያ፣ በግልና በሌላ መንገድ ነው ሲናገሩ የሚሠማው፡፡ ምን ያህል የአክሲዮን ማህበራት እንደተቋቋሙ፣ ስንቶቹስ እንደተሳካላቸው ወይም እንደፈረሱ ይታወቃል? በእኛ የመረጃ አውታር ውስጥ ከ762 በላይ አክሲዮን ማህበራት አሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ባንኮችን ጨምሮ ከአራት መቶ በላይ ማህበራት የማቋቋሚያ ፎርም ተሞልተዋል፡፡ የማቋቋሚያ ፎርም ተሞልቷል ሲባል፤ ተቋቁመዋል ማለት ነው? ተቋቁመዋል ማለት አንችልም፡፡ የንግድ ስም አጣርተው በምስረታ ላይ የሚገኙም አሉ፡፡ የተቋቋሙም አሉ፡፡ ተቋቁመው ስራ ጀምረው ዓመታዊ ሪፖርት እያቀረቡ የሚሄዱም አሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ምን ያህሉ ውጤታማ ናቸው የሚለውን ነገር ለማወቅ ገና ሥራው አልተሠራም፡፡

ግን እነዚህን ድርጅቶች ኦዲት እንድናደርግ በህግ ስልጣን ተሠጥቶናል፡፡ እርግጥ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ገና ራሱን እያደራጀ ስለሆነ አክሲዮን ማህበራትን ኦዲት ማድረግ አልጀመረም፡፡ እና ምን የተሰራ ነገር አለ? ችግሮች በተከሰቱባቸው ማህበራት ዙሪያስ መረጃቸው ምን ያህል ነው? ንግድ ሚኒስቴር ራሱን ችሎ ከተቋቋመ ገና ሁለት አመቱ ቢሆንም፤ የተጀመሩ ስራዎችና ጥረቶች የሉም ማለት አይደለም፡፡ የአክሲዮን ጉዳይ ትኩረት የሚሠጠው ጉዳይ መሆኑን እናውቃለን፡፡ ችግር ያጋጠማቸው ማህበራትን በተመለከተ የቀረበው ጥያቄ ላይ … ጉዳዩ ለህግ የተተወ ነው ብዬ በደፈናው አለፍኩት እንጂ ከዚያ ውጭ የሆኑ መረጃዎች ላይ መነጋገር እንችላለን፡፡ ለምሣሌ፤ “ሀገሬ ኮንስትራክሽን” … ለመፍረስ ጉዳዩ በፍርድ ቤት እንዳለ እናውቃለን፡፡ ሙሉ መሶብ ፉድስ አክሲዮን ማህበር … በባለአክሲዮኖቹ መካከል ችግር ተፈጥሮ ነበር፡፡ ነገር ግን እኛ ለማግባባት ጥረን ሥራቸውን እንደቀጠሉ እናምናለን፡፡ ጃካራንዳ የተባለው አክሲዮን ማህበር፣ በባለአክሲዮኖቹ መካከል ትልቅ ረብሻ ቢኖርም ማህበሩ ግን ውጤታማ ነው፡፡

እርግጥ ባለአክሲዮኖች ተጨቃጭቀዋል፣ ፍርድ ቤት ድረስ ሄደዋል፡፡ እኛም የራሣችንን አስተያየት ሠጥተናል - ፍርድ ቤትም የራሱን ውሳኔ ወስኗል፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ ድርጅቱ በሥራው ውጤታማ ነው፡፡ ብዙ የተለያየ ባህሪና ባህል ያላቸው ሠዎች አንድ ላይ በሚሠሩበት ጊዜ ውዝግብ ሊያጋጥም የሚችል ነው እንላለን፡፡ ውጤታማ አልሆንም ብለው በግልፅ የፈረሱ ማህበራት የሉም፤ ሪፖርት የተደረገልንም የለም፡፡ ምክንያቱም መዝጋቢው አካል አውቋቸው የተቋቁሙና የፈረሱ እስካሁን አላጋጠሙም፡፡ አንድ አክሲዮን ማህበር ለመፍረስ ምን ምን ሂደቶችን ማለፍ ይጠበቅበታል? ለዚህም ግልፅ ህግ ተቀምጦለታል፡፡ በመጀመሪያ አባላት ተሠብስበው ቃለ-ጉባኤ ማፅደቅና የሠነዶች ማረጋገጫ ሄደው መፈረም አለባቸው፡፡ ከዚያም ለመፍረስ ስለመወሠናቸው ቢያንስ ሶስት ጊዜ በጋዜጣ ላይ ማስታወቂያ ማውጣት ይኖርባቸዋል፡፡ ይህ የሚሆንበት ምክንያት እንዳይፈርስ ፍላጐት ያለው አካል ካለ አቤቱታ የማቅረብ እድል እንዲያገኝ ነው፡፡ ይህን ህግ ተከትለው በእኛ በኩል ፈርሠዋል የምንላቸው የሉም፡፡

ነገር ግን በህጋዊ መንገድም ባይሆን የፈረሱ ይኖራሉ፡፡ ለምሣሌ ቦርዱ ስራውን የማያከናውን፣ አባላቱ በስብሠባ የማይገናኙና በአክሲዮናቸው ላይ የማይመክሩ እንዲሁም ዓመታዊ ሪፖርት የማያቀርቡም ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ግን አቶ ኑረዲን፣ የበርካታ ማህበራት ምስረታ እየተጀመረ ሳይቋጭ ይቀራል፤ በአንድ ሠሞን ግርግር ተፈጥረው ደብዛቸው የጠፋ በርካቶች ናቸው፡፡ የፈረሠ የለም ካሉኝ ጋር አልጣጣም ስላለኝ ነው … ቅድም እንዳልኩት፣ በራሣቸው መንገድ ችግሮች ተፈጥረው ሥራ ያቆሙ፣ እርስ በእርስ የሚነታረኩ፣ ብር ሠብስበው ወዳልተፈለገ አቅጣጫ በመዞር ባለአክሲዮኖችን የሚያማርሩ የሉም አይደለም፡፡ በህጉ መሠረት ሲፈርሱ ነው ፈረሱ የምንለው፡፡ ባለ አክሲዮኖችም ችግር ሲፈጠር ለመዝጋቢው አካል አሣውቀው ኦዲተር እንዲሰየምላቸው፣ ጠቅላላ ጉባኤ አስጠርተው መቀጠልም መፍረስም ይፈልጉ እንደሆን የመወሠን መብት እንዳላቸው አያውቁም፡፡

ይሄ ህጉን ያለመረዳት ችግር ነው በየቦታው የሚያማርራቸው፡፡ እስካሁን ውጤታማ ሆነዋል የሚሏቸው የአክሲዮን ማህበራት እንደ ምሣሌ የሚያነሷቸው ካሉ … በርካቶች ናቸው፡፡ ለምሣሌ 18 ያህል ውጤታማ ባንኮችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ የአክሲዮን ማህበር ባንኮች ናቸው፡፡ የባንኮቹ እህት ሆነው የሚመሠረቱ ኢንሹራንስ ኩባንያዎችም ውጤታማ ናቸው፡፡ በአግሮ ኢንዱስትሪም ጃካራንዳን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ኢሌምቱን ስንመለከትም በውጤታማ ስራ ምርቶቻቸውን ለገበያ እያቀረቡ ነው፡፡ በመኖሪያ ቤት ግንባታ በርካታ አክሲዮን ማህበራትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ እነዚህን እንደ ምሣሌ ስናስቀምጥ አንዳቸው ከአንዳቸው በልጠው አይደለም፡፡ ሁሉም አክሲዮን ማህበራት ህጉን ጠብቀው እየሄዱ ነው የሚል እምነት ስላለን ነው፡፡

Read 9143 times