Print this page
Saturday, 23 March 2013 14:24

ረዥሙ ባለ5 ኮከብ ሆቴል - በባህርዳር

Written by 
Rate this item
(6 votes)

ባለ 18 ፎቅ ሆቴል በክልል ከተሞች ቀርቶ በአዲስ አበባም አልተለመደም፡፡ ጣና ሐይቅን ከጀርባው አድርጐ የተሠራው ባለ 5 ኮከቡ ሆቴል ለባህርዳር ከተማ ተጨማሪ ውበት ሆኗታል፡፡ የሆቴሉ ባለቤት ትልቅሰው ገዳሙ ወደ ኮንስትራክሽን ቢዝነስ የገቡት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቢሆንም የሆቴሉን ግንባታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ችለዋል - ፈተናዎችን እየተጋፈጡ፡፡ በጐጃም ውስጥ በገጠር አካባቢ የተወለዱት ወ/ሮ ትልቅሰው፤ ከአምስት አመት በላይ በባሌ እና በአዲስ አበባ በአስተማሪነት ከሰሩ በኋላ ነው ወደ ቢዝነስ የገቡት፡፡ ከትንሽ ንግድ ተነስተው፣ አንዱን ቢዝነስ ለሌላ ትልቅ ቢዝነስ መሰላል እያደረጉ ዛሬ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ የፈጀ ሆቴል ሰርተዋል፡፡ ከወ/ሮ ትልቅሰው ጋር ጋዜጠኛ አበባየሁ ገበያው ያደረገችውን ቃለ-ምልልስ እነሆ! የትልቁ ሆቴል ግንባታ እየተጠናቀቀ ነው… ባህርዳር ከተማ ባለ አምስት ኮኮብ ሆቴል “G+18” ፎቅ እየሰራሁ ነው።

በከተማውና በክልሉ ሆቴል ኢንቨስትመንት ትልቁና የመጀመሪያው ይሆናል ብዬ እገምታለሁ። 150 ክፍሎች፣ አምስት ሬስቶራንት፣ መዋኛ፣ ሳውና፣ ስቲም፣ ጃኩዚ... የባለ አምስት ኮኮብ ሆቴል ደረጃዎችን የሚያሟላ ነው። የፊታችን ሐምሌ ወር ላይ በ“ሶፍት ኦፕኒንግ” ስራ ለማስጀመርና በ2006 ዓ.ም. ለማስመረቅ እቅድ አለኝ። 24 ሰዓት እየተሰራ ነው። ዘጠና ፐርሰንት ተጠናቋል። ሻምፑና ኮንድሽነር፣ ሹካና ማንኪያ ካልሆነ በስተቀር... ሁሉም ነገሮች ገብተዋል።

ማኔጅመንቱ ፍሬንቻይዝድ ነው፤ ነጮች ናቸው የሚያስተዳድሩት። እግዚአብሄር ከፈቀደ ብዙ ነው አላማዬ። ሄሊኮፕተር ገዝቼ እንግዶቼን ለማስጎበኝበት ህልም አለኝ። ለምሳሌ ከአዲስ አበባ እንግዶችን ተቀብለናቸው ደብረ ማርቆስ እናሳርፋቸዋለን። ከዛ ባህርዳር እኛ ሆቴል፤ ከዚያም ላሊበላ ጎንደር እያልን ለማስጎብኘት በቅብብሎሽ መስራት ነው ቅድመ ዝግጅታችን። የሄሊኮፕተር ጊዥውን አጥንተን ጨርሰናል። ሆቴሉ ስራ ሲጀምር አስር ማርቼዲስ፤ አራት ላንድ ክሩዘር፤ ሶስት ጀልባዎች ይኖሩታል። ሶስቱ ጀልባዎች ከጀርመን ታዘው እየመጡ ነው። አንደኛው ጀልባ 45 ሰዎችን ማስተናገድ የሚችልና የባህር ላይ እራት የሚዘጋጅበት ነው። ሶስት መኝታ ቤቶችና አንድ ሻወር ያለው ጀልባ ነው። ሁለቱ 25 ሰው የሚጭኑ ትናንሽ ጀት ስክኒች ናቸው። ሆቴሉ የሚከፈተው ይሄ ሁሉ ተሟልቶ ነው። የየት ሀገር ባለሞያዎች ናቸው ሆቴሉን የሚስተዳድሩት? ማኔጅመንቱን እኔ መያዝ አልፈልግም። ከአለም አቀፍ የሆቴል ማኔጅመንት ጋር እየተነጋገርን ነው። ገና አልተፈራረምንም። ግን ፍራንቻይዝ ነው የሚሆነው።

ከ400 በላይ ሰራተኞች ይኖሩታል። የሆቴሉ ስም ምን ተባለ-- በፍራንቻይዝ ስለሚሰራ፣ የሆቴሉን አስተዳደር በሚመራው ኩባንያ የሚወሰን ይሆናል። ምናልባት ከእነሱ ጋር ካልተስማማሁ “ግራንድ ባህርዳር” እለዋለሁ። በባህርዳር ላይ እየተሰራ ያለው ባለ አምስት ኮኮብ ሆቴል መጀመሪያ ላይ ባለ 18 ፎቅ እንዲሆን አልታሰበም ነበር ሲባል ሰምቻለሁ። ደግሞም፤ የህንፃ አርኪቴክቶችና ዲዛይነሮችን እየተከታተልሽ ትፈታተኚያቸዋለሽ ይባላል? እውነት ነው። የሆቴሉ ቁመት ወደ ላይ ረጅም እንዲሆን የፈለኩት እኔ ነኝ፡፡ ክልሉ የሰጠኝ ቦታ ቆንጆ ነው። ታወር ነበር፤ ዲዛይን አቀረብኩላቸውና “አስራ አራት አድርጊው” ሲሉኝ “አስራ አራት ከደረስኩ፤ አስራ ስምንት ለምን አይሆንም” ብዬ አስራ ስምንት አድርጌ ሰራሁት። ከዲዛይነሮች ጋር እኩል ነው የምራመደው። እኩል ነው ቻሌንጅ የማደርጋቸው። ኤክስፓዠሩ አለኛ! ዓለም ላይ ብዙ አገር እዞራለሁ።

ሆን ብዬ ባለ አምስት ኮኮብ ሆቴሎች ነው የማርፈው። ይህቺ ግድግዳ፣ ጣሪያ ምን ትመስላለች? ፍሪጅዋ ምን ላይ ተቀመጠች? እያልኩ የሚሉትን ነገሮች በደንብ እመለከታለሁ። ካሜራዬ ውስጥ ብታይ የሰው ፎቶ አታይም። የመፀዳጃ ቤት፣ የመታጠቢያ ገንዳ፣ የአልጋ ዓይነት፣ የሆቴሉ ክፍሎች፣ የግድግዳና የጣሪያ ቀለማቸው፣ የሬስቶራንት ዕቃ አቀማመጥ ፎቶ ነው የምታይው። አርክቴክቶች ከእኔ ፈቃድ ውጪ አይሰሩም። እያንዳንዱዋን ነገር እኔ ማየት አለብኝ፤ መተማመን አለብን። ለእኔ ሳያሳዩ ያደረጉት ነገር ካለ፣ ቀስ ብለን እናሳምናታለን ብለው ነው የሚሰሩት፡፡ የሚመቸኝንና የሚሆነውን ነው የማሰራቸው።

ከዱባይ ኤሚሬት ኮንኮርድ፣ ግራንድ አይነት ሬስቶራንት እኔ ጋ እንዲደገም አድርጌዋለሁ። ውስጡ ምን ይመስላል? የሚለው በሙሉ የእኔ ምርጫና ፍላጎት ነው፡፡ አልጋ፣ የአልጋው ቀለም፣ የቤቱ ግድግዳ ቀለም “ይሄ የራሴ ስራ መሆን አለበት” ብያቸው ሙሉ በሙሉ የእኔ የእጅ ስራ ውጤት ነው። ከሠራተኞቼ ጋር እኩል ቱታ ለብሼ፣ ኮፍያ አድርጌ አንዱን ሳነሳ አንዱን ስጥል ነው የምውለው። በጣም ደስተኛ ነኝ። ኤስያ፣ ቻይና ሌሎች በሆቴልና ቱሪዝም ትልልቅ ስም ያላቸው አገሮችን ጎብኝቻለሁ። አምስት ኮኮብ ሆቴል አርፌ አይቻቸዋለሁ። ብቻዬን ሳይሆን አርክቴክቸሮቼንም ይዤ፣ በዓለም ላይ ያልተጓዝኩበት አገር የለም። እንግሊዝ አገር ብቻ ነው የሚቀረኝ። ሌላ የት የት ከተማ ነው ሆቴሎች የሠራሽው? ምዕራብና ምስራቅ ጎጃም ፈረስ ቤት፣ ደብረ ማርቆስ፣ አሁን ደግሞ ትልቁና ባለ አምስት ኮኮብ ሆቴሉ የባህር ዳሩ ነው። በሆቴል ኢንዱስትሪ ውስጥ ደግሞ ሰፊ ስራ ጀምሪያለሁ።

በተለያዩ ክልሎች ስራዬን ማስፋፋት እፈልጋለሁ። በርግጥ ደክሞኛል.. ግን ባለኝ የተፈጥሮ ባህሪ ከስራ ርቄ መኖር አልችልም። ቱሪዝሙን ተከትዬ የምሰራ ይመስለኛል። በደብረማርቆስ ከተማ በጥሩ መስተንግዶ የሚታወቀው “ትልቅ ሆቴል” የሚባል ባለ ሶስት ኮኮብ ሆቴል አለኝ። 50 የመኝታ ክፍሎች፣ ሳውና፣ ስቲም፣ መጠነኛ የስብሰባ አዳራሽ አለው። አምስት ሺ ካሬ ሜትር ማስፋፊያ ቦታ ሰጥተውኛል። አሁን ደግሞ አስፋፍቼ የተለያዩ ነገሮችን ለመስራት ዲዛይኑ ተሰርቶ ግንባታ ላይ ነው። በማህበረሰባችንም በቤተሰብም ሴት ልጁ በተለያየ ስኬትና ኃላፊነት ለማጨት ያለው ውስንነት ደፍሮ ለመውጣት ፈተናዎችንና ችግሮችን ለመጋፈጥ ያለውን አስተሳሰብ በመስበር ምን ሰራሁ ትያለሽ--- “ሴት” የሚለው ቋንቋ እኔን አይገልፀኝም።

ወንድ ሊያደርግ የሚችለውን ነገር ሁሉ ማድረግ እችላለሁ። መማታት ቢኖርብኝ፤ እማታለሁ(ሳቅ)። ግፍና በደል እንኳን የደረሰብኝ የለም። በእምነት በኩል ያጎደልኩት ነገር የለም። ባንኩም ሰዉም “ትልቅሰው ትሰራለች፣ ተበድራ ትከፍላለች” ይላል እንጂ፣ በጥርጣሬም ሆነ በሌላ ስሜት የሚያየኝ የለም። ስራዎቼን አይተው አድንቀው ከጨረሱ በኋላ፣ “አይገርምም ሴት አኮ ናት” ብለው የሚናገሩ አሉ። ይኼ በጣም የሚያናድደኝ ቋንቋ ነው፡፡ “እና ሴት ብሆንስ ማድረግ አልችልም?” ነው የእኔ ጥያቄ። ወንድ ከእኔ የተሻለ አእምሮ አለው? እሱ ሊያስብ የሚችለውን ያህል እኔም አስባለሁ። እንዲያውም ከወንዱ የተሻለ ዲሲፕሊን የሚታየው በሴቶች ላይ ነው። ለ”ኮሚትመንት” ተገዢ በመሆንም ሴቶች ይበልጣሉ። በቃላችን ለመገኘት እንበረታለን።

ገንዘብ አናባክንም፣ ሴቶች ጥንቁቅ ነን። ዕዳና ብድር ብዙ አንደፍርም። ብዙ መስራትና መሄድ እችል ነበር። ወደ ጠንቃቃነት እናደላለን ብዬ አምናለሁ። ቤተሰብም ላልሽው የሰጡኝ ነገር ሲኖር ገንዘባቸውን እንዳላባክንባቸው ሊሆን ይችላል። እኔ ጥሬ ግሬ ያመጣሁት ገንዘብ ነው። ማንም በእኔ ህይወት ጣልቃ ሊገባ የሚፈልግ የለም። የምፈልገውን እሸጣለሁ፤ የምፈልገውን አጠፋለሁ። ይሄ መንገድ ልክ አይደለም የሚለኝ ሰው የለም። በርግጥ ቤተሰቦቼ የገጠር ሰው ናቸው። አስተማሪነትን ስለቅ በጣም ተሰምቷቸዋል። ኑሮዬን ያበላሸሁ መስሎ ስለታያቸው። ኑሮዬ በየጊዜው እየተቀየረ ሲያዩ ግን በጣም ያደንቁኝ ጀመር።

ካልሽስ፣ አንድ ጊዜ ወደ ባህርዳር በአውሮፕላን እየተጓዝኩ ሳለ ከአንዲት የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዓመት ተማሪ ጋር እያወራን ነበር፡፡ እኔን አታውቀኝም። ስለ እኔ እያደነቀች ለኔ ታወራለች። “አንድ ሴት ጀግና፤ በጣም ጎበዝ…” እያለች ስታወራልኝ፣ ዝም ብዬ አዳምጣታለሁ። መጨረሻ ላይ፤ እኔ መሆኔን ስነግራት፣ ተነስታ ተጠመጠመችብኝ። በክልሌ እንደብርቅ ነው የሚያዩኝ። በጣም ያከብሩኛል። ህዝቡ የባህርዳሩን አዲሱን ሆቴሌን ወደ ላይ ቆሞ ሲቆጥር፣ ሲያደንቅ፣ መተዋወቅ ሲፈልግ ነው የማየው። የልጅነት ህልምሽ ምን ነበር? ነጋዴ፣ የቢዝነስ ሰው የመሆን ምኞት ነበረሽ? በእንጨት የተሰራ ትንሽ ሳጥን “ባንክ” እያልሽ ሳንቲም ማስቀመጥ… “የእንቁጣጣሽ” ሳንቲም ማጠራቀም… የገጠር ልጆች ነኝ።

ሳንቲም አላውቅም ነበር ንግድ ምን እንደሆነ አላውቅም። የአካባቢዬ ልጆችና ወንድሞቼ እንዳጋጣሚ ወደ ቢዝነስ ገብተው ውጤታማ የሆኑበት ጊዜ ነበር። እነሱን ተከትዬ ነው የገባሁት እንጂ ቢዝነስ ምን እንደሆነ እንኳን አላውቅም ነበር። የት ነው የተወለድሽው፣ ያደግሽው? ጎጃም ቆላ/ደጋ ዳሞት የሚባል አውራጃ ደጋዳሞት ውስጥ አሁን ምዕራብ ጎጃም ፈረስ ቤት ነው የተወለድኩት። ትምህርቴንም ያጠናቀቁት እዛው ፈረስ ቤት ነው። ከዛም መምህራን ማሰልጠኛ ባሌ ገባሁ። ሁለት ዓመት ሰርቻለሁ። አዲስ አበባ አምስት ዓመት ሰርቻለሁ። ከባሌ ወደ አዲስ አበባ ስቀየር ያኔ አዲስ አበባ ክልል አልነበረም። በጊዜው ዝውውር የለም። አዲስ አበባ እየሰራሁ ደሞወዛችንን ክልል ይከፍለን ነበር። ባሌ ክ/ሀገር ማለት ነው።

በኋላ ክልል ሲመደብ “ይሄንን ዓይነት ዝውውር አናስተናግድም” ብሎ አዲስ አበባ ላይ ማስታወቂያ ሲያወጣ፤ ወደ ባሌ ተመለሽ ተባልኩኝ.. ከ5ዓመት በኋላ ማለት ነው። አንድ ጓደኛዬ “አትሄጅም፤ እኛ ጋ ትሰሪያለሽ” አለኝ። ያኔ ነው አሰተማሪነቱን የተውኩት። መጀመሪያ ወደ ንግዱ ስትገቢ ገንዘብ ከየት አመጣሽ? ሰው ብር ሰጥቶኝ በብድር? እረ! ስጦታ ነው። ምን ያህል ገንዘብ--- 18 ሺህ ብር የመጀመሪያው የንግድ ስራሽ ምን ነበር? በጣም ትንሽ የሸቀጣሸቀጥ ሱቅ ነው የከፈትኩት። ትንሽ ዓመት ሰራሁና ወደ ግሮሰሪ አሳደኩት። ከትንሽ ተነስቶ የማደግ ምሳሌ ነኝ። እንደ ጓደኞቼ ማደግ፤ ሰው መርዳት፣ አገሬ ላይ መስራት እፈልግ ነበር። እግዚአብሄር ይመስገን የተመኘሁትን ሁሉ አድርጌያለሁ።

ነገ ደግሞ የተሻለ ሰው እንደምሆን አውቃለሁ። የሸቀጣሸቀጥ ሱቁና ግሮሰሪው አሁንም አሉ? አይ የሉም። ወደያው የውጭ ንግድ ጀመርኩ። ከዛ ደግሞ አድጌ ወደ ትራንስፓርት ንግድ ገባሁ። ትራንስፓርቱ ስራ አሁንም ድረስ አለ። የውጭ ንግድ ስትይ ---? የዛሬ 16 ዓመት ወደ ቻይና፣ ወደ ዱባይ አገር ሄጄ ጨርቃጨርቅና ኮርያ ብርድ ልብስ አመጣ ነበር። በጅምላ ልብስ አከፋፍል ነበር። ስራው ደስ ስላላለኝ ነው እንጂ አድካሚ ነበረ፡፡ ጉምሩክ ላይ ያለው ጣጣ “ኤስ ጂ ኤስ” የሚባል መስሪያ ቤት ነበር። እዚያ ሄዶ መዞሩና መግዛቱ ፈተናውና ድካሙ ከባድ ነው። ብዙ ስላልወደድኩት ወደ ትራንስፖርት ገባሁ። በተፈጥሮዬ አንድ ስራ ላይ ሙጭጭ ብዬ መቆየት አልወድም። የተወሰነ ነገር በተወሰነ ጊዜ ነው በፍቅር የምሰራው።

ከዚያ በኋላ መገልበጥ ወደ ሌላ ነገር መሄድ እፈልጋለሁ። ለሆነ ጊዜ ያህል ከሰራሁ በኋላ ቁጭ ብዬ ገንዘብ መቁጠር አይደለም። ለምሳሌ ሆቴል ሰርቼ ገንዘብ መሰብሰቡ ላይ አይደለም የማተኩረው። ደብረ ማርቆስ ያለውን ንግዴን ትንሽ ወንድሜ ነው የሚሰራበት። ፈረስ ቤት ያለውን ሆቴል፤ ትልቅ ወንድሜ ማኔጅ እንዲያደርገው ሰጥቸዋለሁ። የትራንስፓርት ስራውስ? አገር አቋራጭ ሦስት የህዝብ አውቶብሶች ገዛሁ። ከዛ ደግሞ ሶስት ቦቴዎችን። ስሰራ ቆይቼ፤ እንደገና ሶስት ቦቴዎች ጨመርኩ። ወደ ደረቅ ጭነት ትራንስፖርትም ገባሁበት፣ 27 የደረቅ ጭነት መኪኖች ነበሩኝ። ከዚያ ደግሞ፤ አርባ ገልባጭ መኪኖችን በአንድ ጊዜ አስገባሁ። ከባድ ስራ ነው፡፡ ሾፌር፣ ረዳት፣ ጥገና... ከባድ ነው። ከጊዜ በኋላ ወደ ግንባታው አዘነበልኩ።

አሁን የተወሰኑት መኪኖች ተሸጥዋል። የተወሰኑት አሉ፤ የትራንስፓርት ድርጅቱ እየሰራ ነው። የትራንስፓርት ድርጅትሽ ስም ምን ይባላል? “ቻኩ ትራንስፓርት” ይባላል። የደረቅ ጭነትና የፈሳሽ ጭነት መኪኖች፣ ገልባጮችና ሌሎች የኮንስትራክሽን መሳሪያዎችን እያሰማራ ሲሰራ ነው የቆየው። ገልባጮቹን ቀስ በቀስ ሸጥኳቸው። አሁን ደረቅ ጭነቱ ይሰራል። ለንግድ ስኬታማነትሽ አይነተኛ ሰው ለአንቺ ማን ነው? ወንድሞቼንና የአካባቢ ልጆቼን አይቼ ነው ወደ ንግድ የገባሁት ብየሽ የለ? በጣም የምወደው ወንድሜና ጓደኛዬ፣ እንደ ራሴ የማየው፣ ‹‹ጥላሁን ደስታ›› ይባላል። ዛሬ ለእኔ ብር ማግኘት ቀላል ነው። 4 እና 5 ሚሊዮን ብር መበደር እችላለሁ። ከሆነ ሰው ሄጄ መቀበል እችላለሁ። ያን ጊዜ ማንም በማያውቀኝ ሰዓት፤ ማንም በማይሰጠኝ ሰዓት ”አበድረኝ” ብዬ አይደለም የምጠይቀው። “ብር እፈልጋለሁ” ብዬ ነው የምጠይቀው። በተለይ የማልረሳው አንድ ጊዜ 425 ሺ ብር ነበር እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ የመኖሪያ ቤቴን የገዛሁት። እኔ የነበረኝ 300 ሺ ብር ብቻ ነበር። ቀብድ ከፈልኩና በቀጥታ ደውዬ፣ “125 ሺህ ብር እፈልጋለሁ” አልኩት።

“ቢያንስ ተዘጋጅ እንኳን አትይኝም ወይ?” ሲለኝ፤ “በቃ፤ እፈልጋለሁ፣ እፈልጋለሁ” አልኩት። እንዳለውና እንደሚሰጠኝ አውቃለሁ። እቁብ ብንገባ ቅድሚያ የሚሰጠኝ ለእኔ ነው። ጓደኞቹን ይሰበስብና ተጣጥለው ለእኔ ነው የሚሰጠኝ። ጠንካራ እንድሆን ነው የሚለፋው። ችግር እንኳን ቢኖርብሽ፣ “ሰው አለኝ፤ እገሌ አለኝ” የምትይው አለኝታ ሲኖር፤ ጠንካራና ደፋር ትሆኛለሽ። ለዚህ ሁሉ ስኬት ያበቃኝ፣ ጥላሁን ደስታ ይባላል። እሱ ነው ለእኔ አይነተኛው ሰው። እኔም የወሰድኩትን ያህል ገንዘብ ብወስድ፣ ባልኩት ሰዓትና ጊዜ ሳላዛንፍ ነው የምመልሰው። ከትራንስፓርቱ ቀጥሎ ንግድሽ ወደ ምን አደገ? ኤምባሲ የተከራያቸው ቤቶች አሉኝ። ነዳጅ ማደያ አለኝ። ኧረ ተይኝ፣ መዘርዘሩ ሳይሆን መስራት ደስታን ይሰጠኛል። ዕድሜሽ ስንት ነው? ለቤተሰብሽ ስንተኛ ልጅ ነሽ? መስከረም 21 ቀን 2005 ዓ.ም. 40 አመቴን አክብሬአለሁ፡፡

አምስተኛ ልጅ ነኝ። ከእኔ ላይ አራት፣ ከእኔ ታች አራት አሉ ዘጠኝ ነን። አንድ እህቴ አለች፤ እኔ ነኝ አሳድጌ የዳርኳት፤ ጥሩ ህይወት አላት ባሏም ጎበዝ ነው፡፡ ሌሎችም አሉ ጥሩ የሚያግዙኝ - እግዚአብሄር ይመስገን። አባቴ በህይወት የለም፤ እናቴ አለች። በሆቴልና ቱሪዝም ኢንዱስትሪው በስፋት ለመስራት ስትነሳሺ ወደ ፊት እንደ ዕቅድ የያዝሻቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? ክልሎች ላይ ለመስራት እፈልጋለሁ። በቅርብ እንኳን የማስበው አዋሳ፣ ላሊበላ፣ ጎንደር መስራት እፈልጋለሁ። በምን ያህል ካፒታል ተገነባ የደብረ ማርቆሱም፣ የባህር ዳሩም? የደብረ ማርቆሱን ስሰራ ሁሉም ነገር ርካሽ ነበር። ምን ያህል እንዳወጣሁ አሁን በትክክል አላስተውሰውም። ምናልባት ከ16 እስከ 20 ሚሊዮን ብር ይሆናል። የባህርዳሩ ግን ተይው። በጣም ሁሉ ነገር ያበደበት ጊዜ ነው። ግን አንድም ቀን ስራውን ለማቆም አልፈለግኩም። አንድም ቀን አንድም ሰዓት ስራው አልቆመም። ከተጀመረ ሦስት ዓመቱ ነው። በ2,540 ካሬ ላይ ነው ያረፈው። 350 ሚሊዬን ብር ድረስ ይጨርሳል ተብሎ ይገመታል። ከባንክ ተበደርሽ? ወይም ዛሬም ጓደኛሽን አስቸገርሽ? ኖኖ ዛሬስ አላስቸገርኩትም። 58 ፐርሰንት ከራሴ 42 ፐርሰንት ከባንክ ተበድሬ ነው።

Read 9002 times
Administrator

Latest from Administrator